(በዲ/ን ታደሰ ወርቁ)
(አንድ አድርገን ጥር 29 2012 ዓ.ም) ፡- ትናንት ዳር ዳሩን ሲገድሉን የነበሩት ዛሬ ደግሞ መሐል ከተማ ገብተው ይገድሉን ጀምረዋል፡፡ ትናትም ሆነ ዛሬ እየተገደልን ያለነው በገዳዮቻችን ጥንካሬ ሳይሆን÷በእኛ ልፍስፍስነት፤በአባቶቻችን ጥብዓት አልባነት፤በመንግሥት ይሁንታነት ነው፡፡ ትዕግስታችንን እንደልምጥምጥነት፤ ጨዋነታችንን እንደፍርሐት፤የሀገራዊ አንድነትና ሰላም ጠባቂነታችንን እንደባለዕዳ እየተቆጠረብን ነው፡፡
የትናት ሌሊቱ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ግድያ÷የግድያችን ሁሉ ማብቂያ ልናደርገው ይገባል፡፡ ለገዳዮቻችን ንብ በሕይወት የምትቆየው እስከትነድፍና መርዟን እስክትጨርስ ብቻ መሆኑን በተግባር ልናሰተምራቸው ይገባል፡፡ ይኼን ምዕራፍ ዘግተን ወደሌላኛው ምዕራፍ ልንሸጋገር ይገባል፡፡ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በተግባር የምንፈተንበት ጊዜና ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዓተ ጉባዔ ተጠርቶ አፋጣኝ ተግባራዊ ውሳኔዎችን በመወሰን÷ቀጣይ እርምጃዎችን በመሪነት ሊያመላክት ይገባል፡፡ እኛም ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ ይኼን የቅዱስ ሲኖዶስን ተግባራዊ ውሳኔ ለመተግበር ራሳችንን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡
መፍትሔው ይኼው ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ከጥቃት ሊጠብቀን እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ጊዜ በአሳየው ቸለተኝነት ተረጋግጧል፡፡ ጭራሽ ወታደሮቹ እንደቅጥር ነፍስ ገዳዮች (mercenary) ኦርቶዶክሳውያንን እያደኑ ወደመግደል ተሸጋግረዋል፡፡ ፍቶ ግራፉ ላይ እንደተመለከተው÷የመንግሥት ወታደሮች የጥቃት ኢላማ በተደጋጋሚ ጊዜ ተደርገናል፡፡
ከዚህ መንግሥት ምንም መጠበቅ የለብንም፡፡ እንደውም በስጋትነት በዐይነ ልቡናችን መዝግበነው አማራጭ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርብናል፡፡ እነርሱ እየገደሉን እኛ አስክሬን ልንቆጥር አይገባም፡፡ እነርሱ እያፈረሱብን እኛ ልንገነባ አይገባም፡፡እነርሱ ዘውትር እየነጠቁን እኛ ሰናስመልስ መኖር አይኖርብንም፡፡አሁንስ በቃችሁ ልንላቸው ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment