Tuesday, February 11, 2020

ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ጥቃት ላይ መኾኗን ያውጅ !

ዲያቆን አባይነህ ካሴ
(አንድ አድርገን 02/6 2012 ዓ.ም):-  ለየካቲት ቀን ፳፻፲፪ .. አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጥሪ መቅረቡን ከሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ከአቡነ ዮሴፍ ከተሰጠው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አስቸኳይ ጉዳይ ሲገጥም እንዲህ መፋጠን ይገባልና በአክብሮት ተቀብለነዋል፡፡ ጉባኤው ከመሰብሰብ ባሻገር ጠልቆ ይመለከታል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስን በተመለከተ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ የሚግባባበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይወሥናል አፈጻጸሙን ግን አይመረምርም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እና መፍትሔው ምን እንደኾነ ብዙ ጊዜ ስንወተውት ቆይተናል፡፡ አሁንም የአስቸኳይ እና የመደበኛ ስብሰባ ሸብረብ እንጅ የወሠናቸው ጉዳዮች ከምን እንደደረሱ፣ ምን እንቅፋት እንደገጠማቸው፣ ምን ዓይነት ማረሚያ እንደሚሹ በጥሞና ለመመልከት ትዕግስቱ ሊኖረው ካልቻለ ከጉባኤው ማግሥት ታላላቆቹ አጀንዳዎቹ ሁሉ ውኃ ይበላቸዋል፡፡


በመደበኛም ኾነ (በአስቸኳይ) በኢ-መደበኛ ጉባኤው የሚወሥናቸውን ውሣኔዎች አፈጻጸም የሚከታተል አካል መሰየም ካልተቻለ የተመሰቃቀለ የሥልጣን ተዋረድ ይዞ ይህንን ከባድ ጊዜ ማለፍ አይቻልም፡፡ በጥቂቱ እንኳ በኦሮሚያ የካህናት እና የምእመናን ማኅበር ዕውቅና ተሰጠው እንጅ ምን የሥራ ሁኔታ ተመቻቸለት? የሚለውን ማየት ይበቃል፡፡ በዚህ ደካማ ክትትል የተነሣ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን ችላ እንዳለችው መስሎ መታየቱ አነጋጋሪ ከመኾኑ ባሻገር እና ለወቅቱ የሴራ ፖለቲካ ፍጆታነት ተዳርጓል፡፡
ለመሰብሰብ በቂ ምክንያቶች አሉ፡-
·        በምሥራቅ፣ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ስንሰማው የነበረው የክርስቲያኖች ሞት አዲስ አበባ ጠቅልሎ ገባ፡፡
·        ጥምቀትን ያኽል የአደባባይ በዓል ማክበር፣ ታቦት ይዞ ማለፍ የማይቻልበት ዘመን ላይ ተደረሰ፡፡ ፀጥታ አስከባሪውን እና ነውጠኛውን መለየት አልተቻለም፡፡ ኹለቱም እኩል በታቦታተ ሕጉ በካህናቱ እና በሕዝቡ ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ፡፡
·        ሕገ ወጡ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ቡድን ፖለቲካን እና ሃይማኖትን እያደበላለቀ የጥፋት ሰይፉን አነሣ፡፡
·        ምርጫ ይካሔዳል ተብሎ የሚወሠነው በኦርቶዶክሳውያን ታላቅ የሱባኤ ወቅት ኾነ፡፡
·        የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሐረሪ ክልል እስከ ኦሮሚያ ክልል ታጥቀው ቤተ ክርስቲያንንእንሰብራታለንእያሉ ያገሳሉ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግልጽ ፀረ ኦርቶዶክስ መኾናቸውን ከማለዳው ማሳየት ጀምረዋል፡፡
·        ብለው ብለው ደግሞ በዐውደ ምሕረታችን ላይ ቆሞ የሚሰብከውን ሊመድቡልን ብቻ ሳይኾን የትምህርቱን ርዕስ ሊበይኑ ቋምጠዋል፡፡ ሰሞኑን በወንድማችን በመምህር ምሕረተ አብ ላይ የደረሰው ወከባ እና ትንኮሳ ጉልበት እንፈታተሽ የሚል ጎረምሳ እንጅ የመንግሥት ፖሊስ የሚያደርገው አልነበረም ግን በመንግሥት ፖሊስ ኾኗል፡፡ ፖሊስ ታዝዣለሁ ካለ ሠንሰለቱ ሲመዘዝ የት እንደሚደርስ የሚለካ ይለካው፡፡
·        በአጭሩ የምንሞትም የምንታሠርም እኛ ብቻ ኾነናል፡፡ ገደሉን ስንላቸው እስራትም ስደትም መፈናቀልም ይጨምሩልናል፡፡ ገድለናል የሚሉትን ደግሞ ዜግነታቸውን ለማስተካከል ደፋ ቀና ይባላል፡፡ ኢትዮጵያን ለመካድ ለሣልሲት ያላመነታ የኢትዮጵያ ዜግነት በክብር እንደሚመለስለት አታሞ ያስደልቃል፡፡ . . . እኛ ግን ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፡፡
ሕግ አስከባሪው ሕገወጥነቱን የሚለማመደው በእኛ ሜዳ ኾኗል፡፡ በባዶ መሬት ላይ መስጊድ ሲሠራ እንጨት እያቀበለ የዋለ ፖሊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በውድቅት ሌሊት የጥይት ዝናብ ለማውረድ ትጋቱ ይህ ነው አይባልም፡፡ በጥይት አረር ክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት ቀጥፎ ሲንደላቀቅ ማየት አጥንት ዘልቆ ያምማል፡፡


አዎ በዚህ ጊዜ አበው መሰባሰባቸው ይገባል፡፡ ግን ተሰብስበው ምን ሊያደርጉ ነው? የሚለው ያስጨንቃል፡፡ መግለጫ ማውጣት፣ ወይም ጠቅላይ ሚንስትሩን ወይም ሌላ ባለሥልጣን ማነጋገር? እዚህ ውስጥ ምንም ዓይነት መፍትሔ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለደንቡ መደረጉ ክፋት የለው ይኾናል፡፡ እርሱ ላይ ከቆመ ግን አለመሰብሰብ ይሻላል፡፡
የታየኝን ልጠቁም፡-
. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተወሠኑ አካባቢዎች ጥቃት ላይ መኾኗን ማወጅ (Declare The Church is Under State of Attack)


. በቤተ ክርስቲያን ላይ ለተቃጡ ጥቃቶች መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ የጉዳት ካሣን ጨምሮ የማስተካከያ ርምጃ ወስዶ እንዲያሳውቅ የጊዜ ገደብ መስጠት፡፡
.. በምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ በዶዶላ፣ በአቦምሳ፣ በላሃ ሚካኤል ጋሞጎፋ፣ በሐረር እና ድሬዳዋ ከተማ
.. በአዲስ አበባ ከተማ በ፳፬ ቀበሌ የተፈጸመው የሰሞኑን ጥቃት
.. ምርጫ ተካሔደም አልተካሔደም ቢያንስ የጊዜ ሰሌዳው ግን ከሱባኤው ውጭ እንዲኾን ማድረግ፡፡ አሁን ፖለቲካዊ መብታችንን ነአግባቡ የምንጠቀምበት ጊዜ ላይ መኾናችን አይረሳ፡፡


በተዘጋጀለት የጊዜ ገደብ ውስጥ መንግሥት ምላሽ ካልሠጠ ቤተ ክርስቲያን የምትወስደው ርምጃ ምን ሊኾን ይችላል? የሚለውን ዝርዝር ከዚህ ቀደም የተቋቋመው የሰላም እና እርቅ ጉባኤ ሠርቶ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ ማዘዝ፡፡


. በቤተ ክርስቲያን ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ እንዲደረግ የሚያበረታቱ እና የሚያሠራጩ ሚድያዎች አስተዳደራዊ ርምጃ እስከ ፈቃድ ክልከላ እንዲደረግ ከመንግሥት ጋር መደራደር፣


. ውስጥን ማጥራት፡፡ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጃለሁ የሚለው ሕገ ወጥ ቡድን መጠጊያዬ ናቸው እያለ የሚመካባቸው አንዳንድ አባቶች የጉባኤው አባላት መኾናቸው ታውቆ በጉዳዩ ላይ እምነት ክህደታቸውን ተጠይቀው ቁርጥ ያለ ነገር ማሳወቅ፡፡ አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ አዎስጣቴዎስ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘባሌ፣ ሌላም አንድ አባት (ለጊዜው ስማቸውን ከመጥቀስ እታቀባለሁ) በተለይ ስማቸው ይነሣል፡፡ በሽፍንፍን ሳይኾን በጽሑፍ ወይም በተቀረጸ ቪድዮ ቃለ ውግዘታቸውን እንዲያሰሙ ማበረታታት፡፡ ከስም አጠራር ጀምሮ የምናየው ነገር አንጀታችንን አሳርሮታል፡፡ የቀን ሳይኾን የማታ እረኛ አለን እያሉ ሕዝቡን እያደናገሩ መኾኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ኾኗልና፡፡


. የቅዱስ ሲኖዶስን ውሣኔ የሚከታተል ልዩ አካል በቋሚነት መሰየም፡፡ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሊኾን ይገባል፡፡


. ሕገ ወጡን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ቡድን አውግዞ መለየት፡፡ በስም የታወቁትን የቡድኑ አባላትም ስማቸው ተጠቅሶ፣
.

.
.

የቀረውን እናንተ አባቶች እና መንፈስ ቅዱስ ሙሉበት !!!

No comments:

Post a Comment