(አንድ አድርገን ሰኔ 23 2008 ዓ.ም )፡- የጵጵስና ማዕረግ በቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው የሥልጣንና የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ አመራረጡም ሆነ ሹመት አሰጣጡ በጥንቃቄ የሚካሔድ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአስመራጭ ኮሚቴነት ከመረጣቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ፤ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፤ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፤ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ፤ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ይገኙበታል፡፡ ለዚህ ማዕረግ የሚታጭ አባት ቢቻል በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ዕውቀት የበለፀገ፣ ቅዳሴውን፣ ቅኔውን፣ ትርጓሜውን፣ አቋቋሙን የዘለቀ ፤ ተርጉሞ አመስጥሮ ምዕመናንን የሚያስተምር፣ የሚመክር ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ደግሞ በምግባር የተመሰከረለት ፣ ምዕመናንን በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር እንዲበረቱ በጎ ጎዳናን የሚመራ ሊሆን ይገባዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ለአስመራጭ ኮሚቴው እየተጠቆሙ ያሉት እጅግ ከዚህ መስፈርት የራቁ አባቶች ይገኙበታል፡፡ ቀድሞ አባቶቻችን ከባድ ኃላፊነትን ለመሸከም ብቁ ሆነው ሳሉ ቤተ ክርስቲያን ለትልቅ ማዕረግ ስታጫቸው ‹‹አይገባኝም›› ይሉ ነበር፡፡ አሁን ባለንበት ጊዜ ግን አንዳንዶች እንደ አለማዊ ምርጫ ቀድሞ የምርጫ ቅስቀሳ የሚሰሩ ፤ አንዳንዶች ከመንግሥት ጋር ያላቸውን መልካም ወዳጅነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ምርጫው ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ የተዘጋጁ ፤ አንዳንዶች ሹመቱን አብዝቶ በመመኝት በመማለጃ ያቀኑ ፤ አንዳንዶች ራሳቸውን ደብዳቤ እየጻፉ በክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ፊርማና ማህተም የሹሙኝ መልዕክቱን ለቅዱስ ሲኖዶስ ከማስፈራሪያ ጋር የሚልኩ እና ሌሎች በርካቶች እዚህ ምርጫ ላይ በእጩነት ቀርበዋል፡፡
በሕገ ቤተክርስቲያን በጵጵስና መዓርግ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ አባቶች ድንግላውያን እንዲኾኑ ይወስናል ፤ አሁን ድረስ በተለያዩ መንገዶች የተጠቆሙ እና አስመራጭ ኮሚቴው እንደተቀበላቸው ከተገለጹት እጩዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ሁለቱ አይደለም ለዚህ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕረግ ይቅርና አሁን ላይ የያዙት ማዕረግ ከቀድሞ ስራቸው እና ምግባራቸው አንጻር የሚገባቸው ሆነው የተገኙ አይመስሉም፡፡ ‹‹አንድ አድርገን›› የእነዚህን ሰዎች ስም ዝርዝር አደባባይ ላይ በማውጣት በቀጣይ የሚደርስባቸውን ተጽህኖ በማሰብ የቀድሞ ስራቸው እና አሁን ላይ እያከናወኑ የሚገኙትን ሥራ ብቻ ላይ አንድ ሁለቱን ብቻ አቅርባለች፡፡ የሰዎቹን ስም እና ዝርዝር መረጃ ግን ዝርዝር ማጣራት እንዲያካሂድበት ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰየመው የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ትልካለች፡፡
የመጀመሪያው አባት ‹‹አባ›› ቤተ ክርስቲያቱ በጣሊያን ለአገልግሎት በላከችው ጊዜ ከአንድ አባት የማይጠበቅ ለምዕመናን መጥፎ አርአያ በሚሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ስም በሚያጎድፍ ተግባር ላይ እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሲሆን በወቅቱ በፈጸመው ድርጊት ስልጣነ ክህነቱ የተነሳ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በአንዱ ደብር የአስተዳዳሪነት ሚናውን በመወጣት ላይ ሲገኝ ኮንዶሚኒየም በመከራየት ባለ ባለትዳር በመሆኑ ኑሮውን እንደሚገፋ ይታወቃል፡፡ ይህ ሰው ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ዛሬ ለቅድስት ቤተክርስቲያን የበጎች እረኛ ለመሆን ከፍተኛውን ሥልጣንና የኃላፊነት ደረጃ በመመኝት ስሙ ከእጩዎች ውስጥ ይገኛል፡፡
ሁለተኛው አባት ‹‹አባ›› በአዲስ አበባ የአንዱ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ ደብር አስተዳዳሪ ሲሆኑ በላፍቶ አካባቢ በሰሩት ቤት ውስጥ ከገጠር የቀድሞ ሚስታቸውን በማምጣት በማኖር ላይ የሚገኙ ፤ በፍቅረ ንዋይ ፤ በስልጣን ምኞት መንገድ ላይ በመገኝት የጵጵስናን ማዕረግ ለማግኝት ከእጮዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሰው ናቸው፡፡
ሦስተኛው አባት አባ ዕንቁ ሥላሴ ተረፈ የመዝገበ ምሕረት ካራ ቆሬ ፋኑኤል አስተዳዳሪ የተሀድሶያውያን ተባባሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከድለላ አንስቶ በተለያዩ ለአንድ አስተዳዳሪ የማይመጥኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰው ናቸው፡፡ ምዕመኑን ሕገ እግዚአብሔር በማስተማር ክሩን እንዲጠብቅ ከማድረግ ይልቅ ባልተገባና የቤተክርስቲያኒቱን ክብር እና ስም በሚያጠፉ ስራዎች የተሰማሩ አባት ናቸው፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ምዕመን የተጠቆሙትን አባቶች የቀድሞ ታሪካቸውን ለአስመራጭ ኮሚቴው የማድረስ ሃይማኖታዊ ግዴታ አለበት ፤ ስለ እጩዎቹ ያላችሁን መረጃ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያላችሁ የቤተክርስቲያን ልጆች በ‹‹አንድ አድርገን›› የፌስ ቡክ አድራሻ ታደርሱን ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ለነገ ሰላማዊ አውድ ዛሬ ትብብራችንን እናጠንክር፡፡
No comments:
Post a Comment