Wednesday, June 1, 2016

ዛሬ ካሳ ተክለ ብርሃንን የመሰሉ ገብረ ጉንዳኖች ለአባቶች ይዘውላቸው ከሚመጡት መፍትሄ ይልቅ ነገ የሚያመጡባቸው ችግርና ቀዳዳ ገዝፎ ይታያል


(አንድ አድርገን ግንቦት 24 2008 .)- በዓለማየሁ ገላጋይለውድቀት እንደግስ?” የሚለው ጽሑፉ ላይ መንግሥት በየጊዜው በሰበብ አስባቡ ለሚያከናውናቸው ሥርዓትን ያልተከተሉ ነገሮችን በመተቸት በስተመጨረሻ ይኽችን ሀረግ አስቀምጧል ‹‹ ትላልቅ ጉንዳኖች የአይጥ መንጋዎች ብዙ እህል ፈጁ …. ከዚህ ሁሉ መቅሰፍት የባሰው ግን መጥፎ መንግሥትና አስተዳደር ነው፡፡ መጥፎ መንግሥት ሕዝቡ ከተፈጥሮ   ከተመክሮ ያገኝውን ንብረቱንና ማንነቱን ከመቀጽበት ያወድምበታል፡፡›› (Travel to discover the source of Nile).

ለዘመናት የገነባነውን ማንነት የተላበስነውን ስብዕና ያቆየነውን ግብረ ገብነት ያቆዩልንን ሀገር የኖርንበትን ሃይማኖት የተረከብነውን ትውፊት እና በአል ከዘመኑ ጉንዳኖችና የአይጥ መንጋዎች መጠበቅ የሁላችንም ግዴታ መሆን መቻል አለበት፡፡ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ አሁን ለእኔ እና ለእናንተ ቋንቋ ዜማ ሥርዓት ትውፊትና እምነትን አስተላልፋልናለች ፡፡ እኛም ይህን የተረከብነውን ላለማስተላለፍ እንቅፋት የሚሆኑብንን ከበላያችን ያሉ ገብረ ጉንዳኖችና በውስጣችን ያሉ የአይጥ መንጋዎችን ሳንፈራ ለልጆቻችን ማውረስ ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ ግዴታ አለብን፡፡ ትላንት ቤተ ክርስቲያን ህልውናዋን በሚያናጋ መልኩ በብርቱ ፈተና አልፋለች፡፡ ዛሬም እንደ ቀድሞ ያህል ባይሆን እንኳን የዛሬ ከርሳቸው እንጂ የነገ ክስረታቸው ባልታያቸው ዙሪያዋን በከበቧት የአይጥ መንጋዎች በጎውን በማይመኙላት ገብረ ጉንዳኖች ዘንድም እየተፈተነች ትገኛለች፡፡ ነገም ይባስ ወይም ይቅለል አሁን ላይ በማናውቀው ፈተና ውስጥ ቤተክርስቲያኒቱ ታልፋለች፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ከአንድ ኦርቶዶክሳዊ አማኝ የሚጠበቀው የራሱን ክርስቲያናዊ ሃላፊነት መወጣት ብቻ ነው፡፡ የዛኔ ፈተናውን ማስቀረት ባንችል እንኳን ፈተናውን የምንቋቋምበትን ትከሻ እንገነባለን፡፡ 



ዛሬ ላይ ሳንስማማ የጠራናቸው ገብረ ጉንዳኖቹም ሆኑ የአይጥ መንጋዎች ነገ ላይ ተስማምተን ውጡልን ለማለት አቅም ላይኖረን ይችላል……ዛሬ ላይ በሩን ወለል አድርገን ያስገባናቸው ሰዎች ነገ ላይ ብንገፈትራቸውም ላይወጡልን ይችላሉ ፤ ለዛሬ አንዲት ችግር ጉባኤው ይዞት የቆየውን ሕልውና ማናጋት ተገቢ አይደለም ፤ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› በምትል አንዲት አረፍተ ነገር ውስጥ የቅዱስ ሲኖዶስ ክብርንና ስርዓተ ቤተክርስቲያንን በሚጻረር መልኩ ሳይስማሙ መጥራትም ሆነ ዘው ብሎ መግባት አግባብ ነው አንልም፡፡ 


በአምስተኛው ፓትርያርክ  ወቅት በቅዱስ ሲኖዶስ የሚደረጉ ጉባኤዎች ውስጥ መንግሥት በጉባኤያት ላይ እጁን እንዲያነሳ ነበር ብርቱ ትግል ሲደረግ የነበረው፡፡ በ2001 ዓ.ም በአባቶቻችን ላይ የደረሰው የጨለማ ድብደባ እና ማስፈራራት የተከሰተው መንግሥትና ቤተክህነቱ እጅና ጓንት ሆነው በላኳቸው ከለላ በተሰጣቸው ሰዎች አማካኝነት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ስርዓተ ቤተክርስቲያ በ6ተኛው ፓትርያርክ አማካኝነት እየተጣሰ ፤ ቤተክርስቲያቱን የማይመጥኗት ደብዳቤዎች ከቅዱስነታቸው ሲወጡ የተመለከቱት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ይህ ነገር እንዲቆምና በቋሚነት መፍትሄ ለመስጠት ያቀረቡት ሃሳብ መንፈስ ቅዱስ ይመራዋል በሚባልበት ጉባኤ ለጉባኤው የማይመጥን ሰው በመጥራት ‹‹የዛሬን›› ብቻ በሚል መፍትሄ ለማግኝት ተሞክሯል፡፡ ቀድሞ ‹‹መንግሥት ጣልቃ አይግባ›› እየተባለ ሲጮህ የነበረው ዛሬ ላይ ባለመስማማት ላይ የመንግሥት ባለስልጣናት እጃቸውን እንዲያስገቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ዛሬ ላይ ካሳ ተክለ ብርሃን የፌደራል አርብቶ አደር ጉዳዮች  ሚኒስትር ተጠርተው መንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ጉባኤ ተቀላቅለው ለሀገር እና ለሕዝብ የሚሻለውን ለአባቶች አመላክተዋል፡፡ ነገ ደግሞ የፕሮቴስታን እምነት ተከታዩ ዶ/ር ሽፈራው  ተክለማርያም ፤ የእስልምና እምነት ተከታዮቹ ሬድዋን ሁሴንና ሲራጅ ፈጌሳ ይህን ጉባኤ ለታዛቢነትና ለምክር ሰጪነት እንደማይቀላቀሉ እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም፡፡ ዛሬ ካሳ ተክለ ብርሃንን የመሰሉ ትላልቅ ጉንዳኖችና የአይጥ መንጋዎች  ለአባቶች ይዘውላቸው ከሚመጡት መፍትሄ ይልቅ ነገ የሚያመጡባቸው ችግር ቀዳዳ ገዝፎ ይታየናል ፤ ነገ ስምምነት ላይ ባልተደረሰ ቁጥር ወደ እግዚአብሔር ከመጮህ ይልቅ ወደ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የሚጮሁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡


ታዛቢ ይግባ በሚለውን አቋም ላይ ዲ/ን ታደሰ ወርቁ እንዲህ ብሏል

‹‹ይኽ ውሳኔ የቤተ ርስቲያኒቱን ተቋማዊ ነጻነት ለመንግሥታዊው ኀይል አሳልፎ የሰጠ፤የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን የገፈፈ ፤ አስኬማዊ ክብርንና ልዕልናን ያሳጣ ነው፡፡ ከዚሁ በትይዩ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ የደነገገውን ድንጋጌ የጣሰ፤ መንግሥትም ‹‹ተጋብዣለሁ›› በሚል ግብዣውን ተቀብሎ በታዛቢነት የሚገኝ ከሆነ ‹‹ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም›› የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መጣሱ አይቀሬ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሰንበትበት ብሎ ዋጋ ከሚያስከፍላቸው ጋባዥነት መቆጠብ አለባቸው፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዐይነቱን ሕገ መንግሥትን የሚያስጥስ ግብዣ ተቀብሎ ከመግባት መታቀብ ይኖርበታል፡፡  ለሕግ ተገዢ መሆን የሚገባው እረኛ ራሱ ሕግ ጣሽ ከሆነና፤ ሕግ እንዲጣስም የሚጋብዝና የሚያበረታታ ከሆነ፤ ክብረ ክህነቱ ምኑ ላይ ነው? በሕግ አግባብ ለብዙኃኑ ውሳኔ ተገዢ መሆን የሚገባው እረኛ እምቢተኛ ከሆነ፣ ‹‹እናንተ ያላችሁት ሳይሆን እኔ ያልሁት ብቻ ነው መፈጸም ያለበት›› የሚል ከሆነ፣ ከሥርዐት ውጪ ‹‹የእኔ ቡራኬ ያላረፈበት ውሳኔ ሁሉ ውድቅ ነው›› የሚል እብሪተኛ ከሆነ፣ በመንጋው ላይ ፈተናን ከመጋበዝ አልፎ መንጋውን ለከፋ ቅርምት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለውድቀት ይዳርጋል፡፡


No comments:

Post a Comment