የሀገራችን ሕገ መንግሥት መሠረታዊ መርኾች ከሚባሉት መካከል አንዱ አንቀጽ ፲፩ ነው፡፡ መሠረታዊ መርሕ ማለት ሕገ መንግሥቱ ራሱን ያዋቀረበት አስኳል ፍሬ ነገር ማለት ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ ሕገ መንግሥቱ የሃይማኖት እና የመንግሥትን መለያየት በተመለከተ የደነገገ ሲኾን በተለይም አንቀጹ ከያዛቸው ሦስት ንዑሳን አናቅጽ መካከል የመጀመሪያው እና ሦስተኛው እንዲህ ይነበበባሉ፡፡
- መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡
- መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡
የመጀመሪያው ንዑስ አንቀጽ እንደሚያመለክተው መንግሥት ሃይማኖታዊ ቁመና ተላብሶ ወይም ሃይማኖት መንግሥታዊ ቁመና ተላብሶ የሚገኝበት ወይም የሚመሠረትበት አመክንዮ እንደሌለ ያሳያል፡፡ ስለኾነም እነዚህ ሁለት አካለት ተጠባብቀው እና ተናብበው እንዲሄዱ የሚያደርግ ሁኔታ እንዲመቻች ሕገ መንግሥቱ የሰጠው መፍትሔ የለም፡፡ ተገነዛዝበው መሥራት የሚኖርባቸው እጅግ በርካታ የጋራ አጀንዳዎች በመካከላቸው እንደሚኖሩ ስለሚገመት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሃይማኖታዊ ቅርስ እንዴት ሊተዳደር ይችላል? የሚለውን ብናነሣ የሁለቱን መገነዛዘብ ግድ የሚል ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ በአንድ አቅጣጫ ያ ቅርስ የሀገር ሀብት ነውና መንግሥት ያገባኛል ሊል ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ የእምነት ተቋሙ ያፈራው ወይም ያካበተው ቅርስ በመኾኑ ይህኛውም ያገባኛል የማለት መብት አለው፡፡
በእርግጥ በአንዳንድ ደንቦች እና መመሪያዎች እንደዚህ ዓይነት ሀሳቦችን ያካተቱ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ደንቦች እና መመሪዎች የመንግሥትን ጥቅም በሚያስከብሩ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ወይንም ሌሎች አካላት ታስበው የሚከናወኑ እንደመኾናቸው መገነዛዘቡን ከአድልዎ አያጸዱትም፡፡ ሃይማኖት በራሱ ሉዐላዊነቱ ሊጠበቅለት የሚችለው ጥንቱንም በጋራ መሥራት ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ መገነዛዘብ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ እንደእነዚህ ዓይነት ሌሎችም ጉዳዮች ቢኖሩ በሁለቱ አካለት መካከል መገነዛዘብ የሚፈጠርበት መንገድ ያስፈልጋል፡፡
ሕገ መንግሥቱ የሁለቱንም ሉዐላዊ ሥልጣን ዕውቅና ሲሠጥ አንዱ በሌላው ላይ ሊኖረው የሚችለውን ጣልቃ ገብነትም በግልጽ ከመገደብ ጋር ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ የተነሣ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ተልእኮ ለመፈጸም የሚችልበት መንገድ የለውም፡፡ ሃይማኖትም እንዲሁ፡፡ ሃይማኖት የመንግሥትን ምርጫ ልደግፍ እገሌን ምረጡ እገሌን እንዳትመርጡ ማለት እንደማይችለው ሁሉ መንግሥትም በሃይማኖት ውስጥ ገብቶ እገሌ ይምራ እገሌ ይውረድ ሊል አይችልም፡፡ ይህን ሀሳብ ተከተሉ ያንን ተውት እያሉ አንዱ ለሌላው አሳቢ፣ መካሪ፣ ዘካሪ የሚኾንበት ዕድል ፈጽሞ የለም፡፡
ሕገ መንግሥቱ እነዚህን ውድ ዋጋ ያላቸው ሀሳቦች ካሰፈረ በኋላ ይህ መብት ሊገደብ የሚችልበትን ሕግ ሲያስቀምጥ “ሃይማኖትንና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የህዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶች እና መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መኾኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይኾናል፡፡” ይላል፡፡ አንቀጽ ፳፯(፭) ከዚህ አንቀጽ ማንም ሰው ሊረዳ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ይህንን በመጥቀስ በማንኛውም ሰዓት አስፈጽማለሁ የሚል አካል ሊኖር እንደማይችል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህንን መሠረት ያደረጉ ሌሎች ሕጎች እስካልወጡ ድረስ ተፈጻሚነት የለውምና፡፡ ጽንፈኝነትን እና አሸባሪነትን የተመለከቱ የወጡ ሕጎች ይህንን መነሻ ያደረጉ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዚህ አንቀጽ መሠረት ምን ይታገዳል የሚለውን ምላሽም እናገኝበታለን፡፡ የሚታገደው ሃይማኖትንና እምነትን የመግለጽ መብት” ብቻ ነው፡፡ እርሱን መሠረት አድርገው ለሚወጡ ሕጎች ከማገድ ያለፈ ሥልጣን አልሰጠም፡፡
እንደ ውቅያኖስ ስፉህ የኾነውን የመንግሥትንና የሃይማኖትን ግንኙነት እንዲህ በአጭሩ ቀንጭቦ ማሳየት ዳገት ላይ እንደመሮጥ ቢኾንም ወደ ርእሰ ጉዳያችን ለመንደርደር ግን አያንስም ብየ አሰብሁ፡፡ ቅድሰት ቤተ ክርስቲን በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተሰቃየቸው ስቃይ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ተጠቃሚ ናት ብሎ መደምደም ለአፍ እንደሚናገሩት ቀላል አይደለም፡፡ ከዘመነ ሄሮድስ ጀምራ በአወዛጋቢ እና ጨካኝ መንግሥታት ብዙ ግፍ ተቀብላለች፡፡
በእነ ዲዮቅልጥኖስ ዘመን የተጋተችው የመከራ መርዝ ስንት ምርጥ ልጆቿን ዋጋ እንዳስከፈለ ታሪክ አይዋሸውም፡፡ በእነ ንግሥት ብርክልያ ሊቃውንቱ የደረሰባቸውን ስደት ማን ይዘነጋው ዘንድ ይችላል? በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየገቡ የግል ፍላጎታቸውን ለማሣካት ሲጣጣሩ አልበገር ያሉትን አበው ቅዱሳን ደም እንደ ጥገት ወተት የጠጡትን ግፈኞች እንዴት ልንረሳቸው እንችላለን? የሕመሙን ዓይነት አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ከዚያ ታሪካችን መማር የእኛ በቁም ያለነው ሙሉ ኃላፊነት ነው፡፡
አሁን በግንቦቱ ርክበ ካህናት እየተካሄደ ባለው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የምንሰማው ነገር ከእውነትነት ወደ ሃሜትነት በወረደልን ጥሩ ነበር፡፡ ገና በመክፈቻው ጸሎት ጥብዐት የተሞላበት ትምህርት ሲሰጥ ውስጡ ብዙ መልእክትም ነበረው፡፡ ሊቁ “ፖለቲካ ይውጣ እውነት ይገለጥ” ያሉት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ፖለቲካው ተጠርቶ የመጣ ነው ወይስ ራሱን ጋብዞ ነው የሚለው ለጊዜው ይታለፍና እውነታው ግን የፖለቲካው ሽታ በቤተ ክህነቱ ከሚገባው በላይ ማንጸባረቁ ነው፡፡
ጭራሽ እንዲህ ዓይነት ስሜት ባለበት ጊዜ እኛ አልተግባበንም እና ታዛቢ ባለበት እንነጋገር ማለት ጉዳዩን ከሚገባው በላይ ማወሳሰቡ አይቀርም፡፡ በዚህም ላይ ታዛቢ ማለት ምን ማለት ነው? ድርሻቸው ምን ማድረግ ነው? ሀሳብ ሊሰጡ ይችላሉን? ከሰጡስ እስከምን ድረስ ሊሰጡ ይችላሉ? የታዘቡትን ነገር በመጠበቃቸው እና ባለመጠበቃቸው መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? በእርግጥ የተፈለገው ታዛቢ ነው ወይስ አሸማጋይ? ታዛቢም ኾነ አሸማጋይ ከየት ከየት የተውጣጣ ሊኾን ይገባዋል? ሥልጣኑ እና ድርሻው ወሰኑ ምንድን ነው? ከታላላቅ ገዳማት፣ ከሊቃውንት፣ ከምእመናን ወይስ ከመንግሥት? ገለልተኝታቸው እስከምን ድረስ ነው? ተጽእኖ አሳዳሪነታቸውስ? እነዚህ እና ሌሎችም ጉዳዮች በውል ሳይጠኑ ማንንም መጋበዝ የቤተ ክርስቲያንን ሉዐላዊነት አሳልፎ መስጠት ይኾናል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ሉዐላዊ ሥልጣን ያለው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በታች የመጨረሻው ውሣኔ ሰጪ አካል ነው፡፡ በራሱ ምሉዕ የኾነ አካል ነው፡፡ የጎደለውም ቢኖር መንፈስ ቅዱስ ርእሰ መንበር ነውና እርሱ ይሞላዋል፡፡ ስለኾነም ጋባዥ ተጋባዥ ሳያስፈልግ በራሱ ብቻውን መሄድ ወዳለበት አቅጣጫ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እውነት የእነርሱ ሀሳብ ከኾነ እንደገና ቢመለከቱቱ መልካም ነው፡፡ በኋላ ማጣፊያ ያጣረው እንዳይኾን ሥጋት አለኝ፡፡ እኔ ማንም ይጋበዝ ማን አድብቶ ዕድሉን ለመጠቀም እየጠበቀ ያለን ኃይል ይባዕ ንጉሠ ስብሐት ብሎ አርኅው ኆኀተ እያሉ እንደመጋበዝ ይሰማኛል፡፡ አክብሮ የጠሩትን እንግዳ ላለማሰፈር ሲባል በሚመጣ ይሉኝታ ካሰቡት ፈቀቅ ብሎ ለመወሰን መገደድም ይኖራል፡፡ ሰሞኑን አንዳንድ መንፈሳዊ አመራሮች ነን ባዮች ያሳዩት መፍረክረክ በሌላ መንገድ ተቀጣጥሎ እንዳይቀጥል ሥጋት አለኝ፡፡
በሌላ በኩልም የሦስተኛ ወገን ጥሪው በተለይ መንግሥትን የሚመለከት ከኾነ ሕገ መንግሥቱን ማንሸዋረር ይኾናል፡፡ እውን እንዲህ ያለ ግብዣ ቀርቦለት ከኾነም መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል እላለሁ፡፡ ጉዳዩ ጣልቃ ወደ መግባት ሄዶ ላይተረጎምበት የሚችል ምንም ዓይነት አመክንዮ ስሌለ፡፡ የልዩነት ሀሳብ ሲኖር በምን መንገድ እንደሚስተናገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ በቂ መፍትሔ እንዳለው ይታወቃል፡፡ አሁንም በተለመደው ቀኖናዊ ሥርዓት ለማስኬድ ከፍተኛ የመንፈሳዊ ልዕልና እንደያዘ ቢቀጥል ይመረጣል፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ወደኾነ አካል እጆቻችን የሚጠቁሙ ከኾነ የራስን ችግር በራስ የመፍታት አቅማችንን ያዳክመዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ያልተላኩ ሁሉ ተልከናል እያሉ ገብተው እንደለመዱት ማወጫበር ይቀጥላሉ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ምንም የሚጎድለው ነገር የለም፡፡ አሁንም በተያዘው መንገድ በሰከነ ሁኔታ ጊዜ እየገዙ አቋምን ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ጋር እያስማሙ መሄድ ይቻላል፡፡ ኃይል አለኝ የሚሉ አካላትም ያለቸውን ኃይል ተማምነው ከሚቆሙ ቤቱ ባለቤት አለውና በእግዚአብሔር እንዲታመኑ የሚያደርጋቸው የሌሎች አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጥብዐት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እየወሰዱ በአናብስት መንጋጋ የሚጥሉ ሁሉ ሊያርፉ ይገባል፡፡ አረረም መረረም አባቶቻችን ተነጋግራችሁ የምትወስኑት ይበልጥብናል፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያንን ከአናብስት መንጋጋ ትታደጓት ዘንድ አጽመ አበው አደራ ይላችኋል፡፡
By : D/n Abayneh Kassie
ተጋባዡ እንግዳ የምሚመጡት የፓትርያርኩን ሀሳብ ለማስፈፀም ነው።ምክንያቱም እሳቸው ስዩመ መንግስት እንጅ ,,.....
ReplyDeleteውድ ወንድማችን !!! ያልኸው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ መሆኑ እየታወቀ 'አባቶቻችን መክረው ዘክረው ችግሩን የሚፈቱበት ዘዴ እያላቸው ሌላ አካል መጋበዝ ለምን አስፈለገ? ቅዱስ አባታችንስ ኃይል አለኝ ማለትዎ ለምን ነው ? ኃይል የኃያሉ እግዚአብሔር መሆኑን ዘነጉትን? እኔስ የቆሙለትም ዓላማ ያጠራጥረኛል፡፡ ይህን መንጋ እንድትጠብቁ የመረጠዎ እግዚአብሔር በጎቹን በማይቀረው የፍርድ ቀን ከእጆችዎ እንደሚሻ ረሱትን ? መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሆይ በደምህ የዋጀሀትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቸርነትህ ጠብቅልን አሜን !!!
ReplyDeleteሥምረተ ማርያም
ውድ ወንድማችን !!! ያልኸው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ መሆኑ እየታወቀ 'አባቶቻችን መክረው ዘክረው ችግሩን የሚፈቱበት ዘዴ እያላቸው ሌላ አካል መጋበዝ ለምን አስፈለገ? ቅዱስ አባታችንስ ኃይል አለኝ ማለትዎ ለምን ነው ? ኃይል የኃያሉ እግዚአብሔር መሆኑን ዘነጉትን? እኔስ የቆሙለትም ዓላማ ያጠራጥረኛል፡፡ ይህን መንጋ እንድትጠብቁ የመረጠዎ እግዚአብሔር በጎቹን በማይቀረው የፍርድ ቀን ከእጆችዎ እንደሚሻ ረሱትን ? መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሆይ በደምህ የዋጀሀትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቸርነትህ ጠብቅልን አሜን !!!
ሥምረተ ማርያም
ውድ ወንድማችን !!! ያልኸው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ መሆኑ እየታወቀ 'አባቶቻችን መክረው ዘክረው ችግሩን የሚፈቱበት ዘዴ እያላቸው ሌላ አካል መጋበዝ ለምን አስፈለገ? ቅዱስ አባታችንስ ኃይል አለኝ ማለትዎ ለምን ነው ? ኃይል የኃያሉ እግዚአብሔር መሆኑን ዘነጉትን? እኔስ የቆሙለትም ዓላማ ያጠራጥረኛል፡፡ ይህን መንጋ እንድትጠብቁ የመረጠዎ እግዚአብሔር በጎቹን በማይቀረው የፍርድ ቀን ከእጆችዎ እንደሚሻ ረሱትን ? መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሆይ በደምህ የዋጀሀትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቸርነትህ ጠብቅልን አሜን !!!
ReplyDeleteሥምረተ ማርያም
ውድ ወንድማችን !!! ያልኸው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ መሆኑ እየታወቀ 'አባቶቻችን መክረው ዘክረው ችግሩን የሚፈቱበት ዘዴ እያላቸው ሌላ አካል መጋበዝ ለምን አስፈለገ? ቅዱስ አባታችንስ ኃይል አለኝ ማለትዎ ለምን ነው ? ኃይል የኃያሉ እግዚአብሔር መሆኑን ዘነጉትን? እኔስ የቆሙለትም ዓላማ ያጠራጥረኛል፡፡ ይህን መንጋ እንድትጠብቁ የመረጠዎ እግዚአብሔር በጎቹን በማይቀረው የፍርድ ቀን ከእጆችዎ እንደሚሻ ረሱትን ? መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሆይ በደምህ የዋጀሀትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቸርነትህ ጠብቅልን አሜን !!!
ሥምረተ ማርያም