Friday, June 3, 2016

በዚህች ቤተ ክርስቲያን ላይ እጁን ያነሣ አካል እርስዎን ሾመብን - እውን ይህች ቃል ከሲኖዶስ ተሰማችን?

ዲ/ን አባይነህ ካሴ

የቅዱስ ሲኖዶሱን ጉባኤ ገባ ወጣ እያሉ ብቻቸውን የተሰበሰቡ ይመስል የብቻቸውን ሀሳብ ለማስወሰን በከፍተኝ ትጋት የምልዐተ ጉባኤውን ሀሳብ እየጨፈለቁ ወደ ራሳቸው ብቻ እንዳጋደሉ የጸኑት፣ ከቆሙበት ሳይነቃነቁ በየ አጀንዳው ገትረው የያዙት አባ ማትያስ በተግሣጽ ቃል እንደተሸነቆጡ ተሰማ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር የሚገባ ነውና ለምን ኾነ በለን አንደነቅም፡፡ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ዛሬ የተሰማው ብዙ ሽፍንፍን ሲበጅለት የነበረው ነገር ግን አነጋጋሪ ነው፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከተላለፉት ቃላተ ተግሣጻት መካከል አንዱየሚያሳዝነው በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ላይ እጁን ያነሣ አካል አኹንም እርስዎን ሾመብን፤ አኹንም ከጀርባ ኾኖ ያበጣብጠናል፤ ወደ ሰላም፣ ወደ ልማት፣ ወደ ዕድገት እንዳትሔድ፤ ዘወትር የብጥብጥ ዐውድማ እንድትኾን እየሠራ ያለ አካል መኖሩን እኛም እናውቃለን፣ ሕዝቡም ያውቃል፡፡የሚለው ነው፡፡


እዚህ ውስጥ ብዙ እምቅ መልእክታት አሉበት፡፡ አጅግ ጎልተው የሚወጠት ግን ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው በቤተክርስቲያን ላይ እጁን ያነሣ አካል የሚለው ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ሾመብን የሚለው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ቤቱም የእውነት ዓምድ ነው በማለት ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተናገረው ቃል ትዝ አለኝ፡፡ ቤቱ ቤት የሚኾነው እንዲህ የእውነት ዓምድ ከኾነ ብቻ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ እጁን ያነሣ ማለት የሠነዘረ ማለት ነው፡፡ በዓላማ የተነሣ አካል መኾኑን ያሳያል፡፡ ቁም ነገሩም እዚህ ላይ ነው፡፡ ጠላትን ማወቅ ለመከላከልም ኾነ ለማጥቃት ወሳኝ ጉዳይ እና ግዴታም ነው፡፡ ለምን እጁን አነሣ? ከመቼ ጀምሮ? ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች ካሉ በሂደት የሚታዩ ናቸው፡፡ እውነታው የተነሣ እጅ መኖሩ፣ የተቃጣውም እንበለው የተሠነዘረው ደግሞ ለማጥቃት እንጂ ለምሕረት፣ ለትብብር፣ አለመኾኑ ከባለጉዳዩ ሲኖዶስ መገለጡ ብዙ መልእክት አለው፡፡
 
እንደዚህ የኾነባችሁን ስተነግሩን እኛም አይደለም ከጎናችሁ ከጉልበታችሁ ሥር እንገኛለን፡፡ የተሠነዘረው እጅ መሰብሰብ አለበት፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነፃ ኾና ሥራዋን መሥራት ይገባታል፡፡ ባለ ሙሉ መብት፣ ለሁሉም ቤተ እምነት ባለ ውለታ፣ ልትከበር እንጂ ልትገፋ የማይገባት እናት ናት፡፡ የተቃጣ እጅ ወደ ቦታው እንዲመለስ ማድረግ የመጀመሪው ተልእኮ ካልኾነ አሁንም ሰላም እንዳጣች ትቀጥል ዘንድ መፍረድ ይኾናል፡፡

ሁለተኛው ዋና ቃልሾመብንየሚለወ ነው፡፡ አሁን ሲኖዶሱ እኒህን አባት እንዳልሾመ ተናገረ ማለት ነው፡፡ ይህም ዓለም ሊሰማው ሲገባ የዘገየው ድምጽ ነው፡፡ መንበሩ እንደተደፈረ በግልጥ የተነገረበት ቃል በመኾኑ እየመረረንም ቢኾን የምንጋተው ሐቅ ኾነ፡፡ ከዚህ የታሪክ በር ላይ ቆመን ወዴት እና እንዴት መሄድ እንዳለብን መወሠን ይገባናል፡፡ ሊቁ በመክፈቻው ጸሎት ላይ ባስተማሩት ትምህርትፖለቲካ ይውጣ እውነት ይገለጥብለው ነበር፡፡
 
የታያቸው ቢኖር እንጂ እንዲህ እውነት ግልጥልጥ እያለ ጥብዐት ወደቤቱ ገብቶ ከአበው ለዘመናት ልንሰማቸው የምንናፍቃቸውን የእምነት ቃላት እየተምዘገዘጉ ከደጃችን የደረሱት፡፡ እንዴት በቤታችን የሚሾም እየተስተናገደ እንዲቀጥል ዕድል እንሰጣለን? ለወንጌለ መንግሥቱ እንቅፋት፣ ለእርቀ ሰላሙ እንቅፋት፣ ሐራጥቃ ተሐድሶን ለማስወጣት እንቅፋት፣ አማሳኞችን እና የመልክም አስተዳደር ጠምዛዦችን ለመዋጋት እንቅፋት፣ አበው በሀሳብ ልዕልና እንዳይሞግቱ እንቅፋት . . . ስንቱን እንሸከም ዘንድ እንችላለን

እነዚህ ሁለት መልእክታት እግዚአብሔር ባወቀ የተላለፉ ናቸውና ከአንግዲህ ከብፁዓን አበው ጎን ቆመን እናት ቤተ ክርስቲያናችንን ከማንኛውም አጽራረ ሃይማኖት የመጠበቅ አደራ አለብን፡፡ ትናንት የመንግሥት ባለሥልጣናትን አግዙን ብለው ከመንፈስ ቅዱስ ዘወር ብለው ለምን ጠሩ ብለን አዝነን ነበረ፡፡ የጎሸ ውኃ እየቆየ አንደሚጠራው እንዲህ እንዲጠራ ከነበረ ያንን መቀበል አይከብደንም፡፡ ግን አሁንም ወደህ እና ወዲያ የሚል ከኾነ ማጣፊያው ያጥርብናል፡፡ በቆምንበት እንገኝ፡፡ እርዳታው የሚመጣው በዚያ በኩል ነውና! ፈቀቅ ባልን ቁጥር እየራቀን ይሄዳልና!

3 comments:

  1. እውነት ነው ቅድስት ቤ/ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ላይ ናት።

    ReplyDelete
  2. የአባቶቻችን አምላክ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ከፈተና ይጠብቅልን ። የውስጥ ሴረኞችንና የተሀድሶ መናፍቃን ተላላኪዎች በድንቅ ጥበቡ ያጋልጥልን።
    አሜን ይሁንልን ይደረግልን !!!!!

    ReplyDelete