Friday, October 9, 2015

እያንዳችን እራሳችንን በማየት ሁላችንንም እናድን፡፡


በካሌብ ብርሃኑ
(አንድ አድርገን መስከረም 29 2008 ዓ.ም)፡- የተሐድሶ እንቅስቃሴን ብዙዎች እንደሚያስቡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ላይ ብቻ የመጣ እንቅስቃሴ አይደለም በግብፅ ኮፕቲክ ቸርች ላይ በአርመን የአርመን ኦርቶዶክስ ላይ ህንድ (በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰበት ሙሉ አማኙን ለሁለት የከፈለበት) የማርቶማ የማላንካራ መከፋፈል በኤርትራ ሰንበት /ቤቶችን ያዳከመበት …. ጊዜያት ነበር፤ አንዳንዶቹ እንደ ሰንኮፍ አውጥተው ሲጥሉት ሌሎቹ እንደተሸከሙት እዚህ ተደርሷል፡፡ አሁን ተራው የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ነው፡፡ ተሃድሶን እነ መሰረት ስብሃት ለአብ ኤንጂኦ ዎች (በተለይም ለሙሉ ወንጌልቤተ-ክርስቲያ”) ተቀጥረው መስበክ (መፃፍ) ከጀመሩበት 1990ዎቹ / ቶች ጀምሮ ሲዳፋ ሲነሳ አሁን ያለንበት ሰዓት ላይ አድርሶናል፡፡ ታዲያ ከዚህ ካንሰራዊ እንቅስቃሴ እንዴት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ እንችላለን ካልን መልሱ አንድ እና አንድ ነው፡፡


እራስን መመልከት እራስን ማደስ
ብዙዎቻችን ኦርቶዶክስ ነን (በአማኝነት ደረጃ) ጠለቅ ተደርገን ብንታይ ግን ለሃይማኖታችን ከመቅናት እና ከመቆርቆር የዘለለ ልናደርገው ምንፈልገው ነገር በጣም ጥቂቱን እና ተራውን ጉዳይ ነው፡፡ ተሐድሶ በነመሰረት ስብሃትለአብ ጊዜ ሲጀመር የነበሩት እንቅስቃሴዎች ተግተው የቤተ-ክርስቲያንን ትምህርት በሚማሩ የሰንበት /ቤት ተማሪዎች ባይገታ ኖሮ አሁን ላይ የሚኖረን አስተምህሮ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የወደቀ ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህ ከቀደሙት ወገኖቻችን እና ፈተናው ከደረሰባቸው አሃት ቤተ ክርስቲያናት መማር ያለብን ትልቅ ነገር ቢኖር ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ተመለሰን ከመቆርቆር የዘለለ ስራ እራሳችን ላይ መስራት ነው እሱም መማር መማር መማርበቅድስና ህይወት በፆም በፀሎት በምክረ ካህን እና በስጋ ወደሙ እራሳችንን ማደስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምንም መልኩ አትታደስም ሰርክ ሀዲስ የሆነች ናትና ሀዲሱን ኪዳን ሊያድስ የሚችል አንዳች ሃይል አይኖርም ፤ በመሆኑም በዚህ ቅሰጣ ተጎጂ የምንሆነው በመጀመሪያ ሰልፉ ላይ የምንገኝ ምዕመናን ነን ፤ ስለዚህ ደከመን ሰለችን ሳንል ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት በክርስትና ህይወት እጅበን እራሳችንን እናድስ፡፡ አለበለዚያ የሶስት ሰዓት ጉባኤ በመሳተፍ ተሀድሶ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ስለተባለ ብቻ ከቤተ ክርስቲያናችን ማስወገድ አንችልም፡፡

ያለመማራችን እና ያለ ማወቃችን ወደ ራሳችንም ያለመመልከታችን ማሳያ በተገኘው አጋጣሚ ያለ ምንም ማመዛዘን የምንፈፅመው አጉል ጀብደኝነት -ክርስቲያናዊ ልፈፋ፤ በተለይም አዋቂነት የጎደለው ስድብ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ተሐድሶ ለቤተክርስቲያን ፈተና ነው ስለ ተሳደብንስለፎከርንምንም ሀዲስ ነገር አይመጣም፡፡ ስለዚህ ባለ መማር እና ከቅድስናው ህይወት በመራቅ ያዛግነውን ማንነታችንን እናጥፋ መታደስ ካለብን እኛ እንታደስ ፡፡ የተወለወለ የእግዚአብሔር ጦር እቃ እንሁንውጊያችን ከደምና ከስጋ አይደለም፡፡
ዋናው የትግል ሜዳ ያለው ፌስ-ቡክ ላይ አይደለም፤ በየአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያኖቻችን ነው፡፡ ስለዚህ ከሳይበሩ(Cyber) አለም ወረድ ብለን አካባያችንን መመልከት ፤ ወገኖቻችንን መጠበቅ እና ማስጠበቅ ፤ ያለብንን ማስመከር ይኖርብናል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ግን ዋናው ቁም ነገር ሁሉ ሙሉ ከሆነው የቤተ-ክርስቲያናችን የትምህርት ቡፌ ላይ እንዳሻን እየተመላለስን በመመገብ ነው፡፡ አብዛኛው የተሃድሶ ፍደሳ ወደቀደመው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንመለስ የሚል ነው፡፡ እንደዚህ ደፍረው እንዲሉ ያደረጋቸው ደሞ እኛ የቀደሙት አባቶቻችን ልጆች መሆን ስለተሳነን በእውቀትም በመንፈስም የዛግን ስለሆንን አባቶቻችንን እስከ ማስደፈር ደረስን፤ ሚገርመው ግን ይህን ማለት የነበረብን እኛው ነን፤ እናም እላለሁ ወደ ቀደመው የአባቶቻችን አስተምህሮ እንመለስከዛ 16ኛው መቶ ክፍለዘመን የወደቀ አስተምህሮ እንዴት እንደመጣ እንመርምር፡፡ ያኔ የትኛው አስተምህሮ በእውነት መንገድ በጌታም ብርሃን እንደሚመራ እናያለን፡፡

እያንዳችን ….እራሳችንን ….. በማየት ….. ሁላችንንም እናድን፡፡


3 comments:

  1. ......ያኔ የትኛው አስተምህሮ በእውነት መንገድ በጌታ ብርሃን እንደምመራ እናያለን የሚለው አባባልህ ብዙም ምቾት አልሰጠኝም ።መማር ተገቢ ነው። ነገር ግን ተሃድሶን ለመለየት የግድ የተለዬ ትምህርት መጠበቅ የለብንም። ዘምኑ ባመጣው ቴክኖሎጂ መረጃ ልውውጡስ ክፋቱ ምንድን ነው። አጥቢያ አካባቢ ያለውን አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ በለሎች መንገዶች ድርሻቸውን እየተወጡ ያሉትን ማዳከም ተገቢ አይመስለኝም።

    ReplyDelete
  2. ቤተክርስቲያንን ለዚህ ፈተና ያደረጋት የወንጌል ትምህርት አሰራጫጨቱ ላይ ችግር ስለአለ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ምእመኑ በአሁኑ ሰዓት ጊዜ የለውም ቀንም ማታም ነው የሚሰራው፡፡ ቤተክርስቲያን የሚሄድ ብዙ አይኖርም ስለዚህ ትምህርቱ በበራሪ ወረቀቶች እየተበተኑ ቢሰበኩ፡፡ የተለያዩ ርእሶች ላይ እየተነሱ ወንጌል ለማስተማር እንትጋ አስጣቱ ከጊዜው ጋር ቢሆን መልካም ነው፡፡ ተኩላው እየተንቀሳቀሰ ያለው ከጊዜው ጋር ነው፡፡ ሐዋርያት እኮ ወንጌልን ሲያስተምሩ በቃል ብቻ አልነበረም በጽሁፍም ነበር ያውም በዚያ ዘመን፡፡ እነ አቡነ ተክለሀይማኖት ሌሎችም የቤተክርስቲያን ብርቅዬ ልጆች አንድ ቦታ ላይ ብቻም አልነበረም ወንጌል ሲያስተምሩ የነበረው ገድሎቻቸው እንደሚነግረን ከሀገር ሀገር እየተዘዋወሩ ነበር፡፡ ከአባቶቻችን ቅዱሳን እኮ የምንማረው ይህንን ነው እኛ ከየት ያመጣነው አካሄድ እንደሆነ አላውቅም፡፡ የስንፍና ስራ የምንሰራው ደክሞን ነው? ኧረ ገድሎቻችንን አቅፈን አንያዛቸው እናንባቸው እናስተውላቸው እንተግብራቸው፡፡ ዛሬ ተኩላው እያነበበ በራሱ እየለወጠው ነው፡፡ ተኩላው ተግቶ ይሰራል እኛ ተኝተናል፡፡ አሁን እኮ ተኩላው ገድሎቻችን አንብቦ የማይሆን ነገር እየጨመረ ነው እየተሳደበ ያለው፡፡ እኛም ስለማናነባቸው እውነት ነው እንዴ እያለ ስንቱ ወድቋል፡፡ ስለዚህ እኛም ተኩላው በሄደበት መንገድ ሁሉ እየሄድን ነው መልስ እየሰጠን ወንጌልን ማስተማር ያለብን፡፡ ከሀገራችን ጦር ማመር አለብን መንግስት ወዶ አይደለም ሱማሌ ክልል ሄዶ የሚዋጋው ወደ ውስጥ እንዳይገባ ነው፡፡ ከገባ መለየት ስለሚከብድ፡፡ እኛ ውስጥ ድረስ ገብቶ እስከሚያተረማምሰን እንኳን ገና ያልነቃን ብዙ አለን፡፡ ዛሬ እኮ የእኛ አለመንቃት ነው በየቤተክርስቲያኑ ያለው የሰበካ ጉባኤና የካህናት በዘር መከፋፈል፣ መጣላት ቅኔ መዝረፍ ትተው ሙዳይ ሙጽዋት የሚዘርፉት እኮ ተኩላው በደንብ ሰርቶ የሚያሳየው ውጤት ነው፡፡ እኛ ደግሞ በሐሜት ከተኩላው ጋር ተባባሪ ነን፡፡ ተኩላው እየመራ ነው፡፡ እኛ ግን አንድ ጎል እንኳን አላስገባንም፡፡ የተኩላው የስራ ውጤት ግን ሪከርዱን ሰብሯል፡፡

    ReplyDelete
  3. ለምሳሌ በገጠሩ ክልል ምንም አይነት ጣቢያ የለም፡፡ ነገር ግን የወንጌል ስርጭቱ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ዛሬም በአማራው ክልል እርስ በርስ መገዳደል አልቆመም ደመላሽ የሚለውን ስም ከማውጧት አልቦዘኑም፡፡ እነዚህንም ቆጥራ ነው መቼስ ቤተክርስቲያኗ ምእመኔ የምትላቸው፡፡ ስለዚህ አንድ አዲስ አበባ ላይ ብቻ አንስራ በሀገሪቷ ላይ ባለውም አካባቢ የሚሰራጭበት መንገድ ተፈጥሮ መሰራት ቢጀመር መልካም ነው፡፡

    ReplyDelete