Saturday, October 17, 2015

ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ተግባራዊ አደረገ
34ኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ሰኞ ይጀመራል

(አዲስ አድማስ ጥቅምት 6 2008 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ማዕከል የሆነው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት /ቤት፣ የሁለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዐትን በመከተል አሠራሩን ዘመናዊ ማድረጉ ተገለጸ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ዘመናዊውን የሁለትዮሽ የሒሳብ አሠራር /Double entry accounting system/ እንድትከተል፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ /ቤት በባለሞያዎች ያካሔደውን የፋይናንስ ፖሊሲና ማኑዋል ጥናት በቋሚ ሲኖዶስ በማስወሰን ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በዚህምቤተ ክርስቲያኒቱ ዘወትር ስትወቀስበትና ስትተችበት የነበረውን፣ ለቁጥጥር የማያመቸውንና በሕግም ተቀባይነት የሌለውን የነጠላ ሒሳብ አሠራር/ቤቱ ማስቀረቱ ተገልጧል፡፡በፖሊሲው ላይ የተመሠረቱና ከማኑዋሉ ጋር የሚስማሙ የሒሳብ ሰነዶችና ቅጻቅጾች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን የጽ/ቤቱ የሒሳብና በጀት መመሪያ ሠራተኞችም ለትግበራው የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡


የተቋሙን አጠቃላይ ሀብትና ዕዳ በማወቅ፣ የፋይናንስና የንብረት አጠቃላይ አስተዳደሩንና እንቅስቃሴውን ለቁጥጥር ግልጽ ለማድረግ፤ ተፈላጊውን መረጃ በሪፖርት በማውጣትና በመተንተን ተገቢ ውሳኔ ለመስጠት ምቹ የሆነውን የሁለትዮሽ አመዘጋገብ ተግባራዊነት ተከትሎ፣ /ቤቱ ማዕከላዊ የሒሳብ አሠራር በመከተሉ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን መቻሉ ተገልጧል፡፡ 16 የጽ/ቤቱ መመሪያዎችና ድርጅቶች፣ በጀታቸውን በራሳቸው እያንቀሳቀሱ ሲሠሩ የነበሩት የሰባቱ የገቢና ወጪ ሒሳብ በአንድ ቋት ተጠቃልሎ በሁለትዮሽ አመዘጋገብ ዘዴ በመሠራቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 .. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2007 .. ድረስ የተሠራው ሒሳብ ተመርምሮ ተዘግቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየጊዜው በሚታየው የዋጋ ግሽበት ተጎጂ ሆና የቆየች ሲሆን በሕጋዊና አስተማማኝ የግዢ ሥርዐት ዓመታዊ ግዥ በመፈጸም ዕቃዎች በመጋዘን እንዲቀመጡ በማድረግ፣ ከጉዳቱ ለመዳን መቻሉ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ፣ የቤቶችና ሕንፃዎች ኪራይ አሰባሰብ በባንክ በኩል በማስፈጸም ሒደቱን ቀልጣፋ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሠራቱ ተመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ ለተቋቋሙት 50 አህጉረ ስብከት የበላይ ሓላፊና አመራር ሰጪ የሆነው የጠቅላይ ቤተ ክህነት /ቤት ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ፣ ቤተ ክርስቲያኒቷ በየአጥቢያው ባቋቋመቻቸው ሰበካ ጉባኤያት የሚሰበሰበው የገንዘብ አስተዋፅኦ ነው፡፡ 34 ዓመታት በፊት በሳንቲም ደረጃ የተጀመረውና ለጽ/ቤቱ ፈሰስ የተደረገው የሰበካ ጉባኤያት ጠቅላላ ገቢ በበጀት ዓመቱ ከብር 125 ሚሊዮን በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት 30 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተመዝግቧል፡፡

የገቢዋ ዕድገት ቤተ ክርስቲያኒቷ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎቶቿን በራስዋ አቅም ለማከናወን እንደሚያስችላት የሚታመን ሲሆን ለዚህም ጠቅላይ /ቤቱ መከተል የጀመረው ዘመናዊው የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ በተዋረድ በሁሉም አህጉረስብከት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ እንዲሆን ተጠይቋል፡፡ በቀጣዩ ሰኞ በጽ/ቤቱ አዳራሽ የሚጀመረውና 800 ያላነሱ የመላው አህጉረ ስብከት ልኡካን የሚሳተፉበት 34ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ጠንካራ የጋራ አቋምና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment