Monday, October 12, 2015

"ተሐድሶ የለም" ማለት የተሐድሶነት ማረጋገጫ

ዲ/ን አባይነህ ካሴ
አንዳንድ ጊዜ የሰጣቸው ቅሎች መድረክ ቢሰጣቸውም ቅሉ የሚተነፍሱትን እንኳ ለመቆጣጠር አልቻሉም፡፡ ሰሞኑን ደቡብ ምዕራብ በተካሄደ "ጉባኤ ከለባት" ላይ በተሰጣቸው መድረክ በአገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ከስድብ ናዳ በስተቀር ኦርቶዶክሳዊ ለዛ ባጣው አሳዛኝ ሕዝበ ክርስቲያኑን የማወክ ተልእኮ "ተሐድሶ የለም" በማለት አቋማቸውን የገለጡ ሰዎች እንዳሉ ስሰማ ውስጤ በኀዘን ደማ፡፡

በተለይም እንደ አውራ መስሎ ለመታየት የሚሞክረው አንዱ "እኔም ኢየሱስ የሚለውን ስም በመጥራቴ ተሐድሶ እየተባልኩ ነው፡፡ አስኪ መልክኣ ኢየሱስን ተመልከቱ እንዴት ኢየሱስ ማለት ተሐድሶ ያስብላል?" በማለት ስለ ተሐድሶ ጥብቅና ለመቆም ሙከራ አድርጓል፡፡ እንዲህ በማለት መናገሩ ብቻውን አላዋቂነቱን፣ በውስጡ ምንም ዓይነት ግብረ ክርስትና እንደሌለ ያሳብቅበታል፡፡

ተሐድሶ የለም?
ተሐድሶን ያወገዘ እኮ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ሲያወግዝም የቀረበለትን ማስረጃ በሚገባ አገላብጦ ሊቃውንትን መድቦ እና መርምሮ እንጂ በግብታዊነት አልወሠነም፡፡ በዚኽም ለመመከር እና ለመመለስ አሻፈረኝ ያሉቱ ተወግዘው ተለይተዋል፡፡ ራሳቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ያልተከረከሩለትን አቋም አዲሱ ተከራካሪ ከወዴት አገኘው?


አንድ ነገር አለ ወይም የለም የሚባለው መቼ ነው? ይኽስ ሊባል የሚገባው በማን ነው? አንድ ነገር አለ ወይም የለም ለማለት ጥልቅ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ከሁለቱም ዓይነት መደምደሚያዎች በፊት ማስረጃዎች ይቀድማሉ፡፡ ማስረጃዎቹም በብቁ ባለሙያ ይመረመራሉ፡፡ የምርመራው ስሌት አለ ወይም የለም ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳል፡፡ ስለዚህ "ተሀድሶ የለም" ወደሚል መደምደሚያ የደረሰ ማንኛውም አካል ከአዋጁ በፊት ይኽንን ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

ለመኾኑ ሰውየው ምን መረጃ ለማን አቅርቦ ያውቃል? "ተሐድሶ የለም" ብሎ ከመናገር መቅደም ያለበት ያሰባበሰበውን መረጃ ይዞ ሥልጣኑ ላለው አካል ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ነኝ ካለ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ማድረግ ነበረበት፡፡ ግን ምን ያደርጋል ብቻውን ጅምሮ ብቻውን ጨረሰው፡፡ ራሱ ይፈጫል፣ ራሱ ያቦካል፣ ራሱ ይጋግራል፣ ራሱ ይበላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ብቻን የመቆም ፍለጎት ተጠናውቶታል፡፡

ጎበዝ ተከራካሪ ማስረጃውን አጠናቅሮ በሚገባው ዐውደ ፍትሕ ተገኝቶ ይከራከራል፡፡ ግን ነገረ ጅራፍ ብቻ ኾነ፡፡ ራሱ ገርፎ ራሱ መጮኽ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አለ እያለ እርሱ የለም የሚል ከኾነ ሰልፉ ከእነማን ወገን ነው? ከአሥራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በተከታታይ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያወግዘው የኖረውን ይኽንን የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮ አንድ ጎረምሳ ተነሥቶ የለም ካለ ሰውየው ከእነማን ወገን ነው? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሣል፡፡

አባቱን የማይሰማ ለአባቱ የማይታዘዝ ልጅነቱ ሊካድ ሊደመሰስ ይችላል፡፡ አባቶቻችንን መስማት አንዱ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ግዴታ ነው፡፡ ልጅነትን ለመስጠት ሥልጣኑ የእነርሱ ነው፡፡ ልጅነትን የመከልከል ሥልጣኑም የእነርሱ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚኽ አሠራር የተገነባ መንፈሳዊ መዋቅር ነው፡፡ ይኽንን ጥሶ ገንፍሎ ወጥቶ የመንደር ተልእኮ ለማሳካት መሞከር መልእክቱ ሌላ ነው፡፡ እነ ተዐቀቡኬን የመሳሰሉ መጻሕፍት አሳትሞ ያሠራጨውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ በአንድ መድረክ ለመሻር ማን መብቱን ሰጠው? በሕግ፣ በሥርዓት አለመመራት አንዱ የተሐድሶነት መገለጫ ነው፡፡

እውን ተሐድሶነት ኢየሱስ ብሎ መጥራት ነውን?
ኢየሱስ ኢየሱስ ማለትማ አይደለም ተሐድሶው መልማዮቹም ፕሮቴስታንቶቹ ሲጮኹት የሚውሉት ነው፡፡ ምናልባትም በዘወርዋራ ለእነርሱ ጥብቅና ሊቆምላቸው ፈልጎ ካልኾነ በስተቀር፡፡ እንዲህ ብሎ የጌታን ስም መጥራት የንጹሕ ክርስቲያንነት መገለጫ ሊኾን እንደማይችል ገና በማለዳ ራሱ የስሙ ባለቤት ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲኽ ብሎ ነገሮናል፡፡

"በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።የዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።" ማቴ ፯፥፳፪።
እነዚህስ ቢያንስ በስሙ ያደረጉት የሚመስል ምትሐታዊ ተአምር አድርገዋል፣ እርሱ ግን ከምኑም የለበት፡፡ የሚድኑ አሉ፣ ከኤች አይቪ ቫይረስ በጸሎቴ አድኛለሁ እያለ ከማምታት በስተቀር ምንም የሌለበት ባዶ ክህደት፡፡ እምነት አይሉት ክህደት ወንገርጋራ ሕይወት፡፡ በጸሎቴ ድነውልኛል ያላቸውም ቢኾኑ በራሱ መዝገብ ብቻ ያሉ እንጂ ምስክርነት ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ በአንዳንድ የቴሌቪዥን ጣብያዎች እንደምናያቸው በአየር ላይ እንፈውሳለን እንጸልይላችሁ ከሚሉት በምንም በማያንስ ሁኔታ እየተውረገረገ ቤተ ክርስቲያንን ማተራመስ ብቻ፡፡ ችሎታው ካለ በራሱም በቤቱም ያለውን ቃልቻዊ ጠባይ ምነው አላጠፋው?

በመጮኽ ደረጃ ከኾነ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኢየሱስ የሚለውን ስም ደጋግሞ በመጥራት ይጮኻል፡፡ እኛም ጠባችን ኢየሱስን በሚገባ ልክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደምትጠራው አድርጋችሁ እስካልጠራችሁ ድረስ የቤተ ክርስቲያን አይደላችሁም ብለን ነው፡፡
እኛ፡-
ኢየሱስ ስንል አምላከ አማልእክት - የአማልክት አምላክ
ኢየሱስ ስንል እግዚእ ወአጋእዝት - የጌቶች ጌታ
ኢየሱስ ስንል ንጉሠ ነገሥት - የነገሥታት ንጉሥ
ኢየሱስ ስንል አልፋ - መጀመሪያው እና መጨረሻው፣ ፊተኛውና ኋለኛው
ኢየሱስ ስንል ንጉሠ ሰማይ ወምድር - የሰማይና የምድር ንጉሥ
ኢየሱስ ስንል ኤልሻዳይ - ኹሉን ቻይ
ኢየሱስ ስንል አዶናይ - መድኃኔዓለም
ኢየሱስ ስንል ወልደ አብ ወልደ ማርያም - የአብ ልጅ የማርያም ልጅ በተዋሕዶ ልደት የከበረ
ኢየሱስ ስንል ፈጣሬ ኩሉ - ኹሉን የፈጠረ
ኢየሱስ ስንል እግዚአብሔር ማለታችን ነው፡፡

ስሙን ስንጠራ ይኽ ሁሉ በልባችን ሰሌዳ ታስቦ ነው፡፡ በድፍረት አንጠራውም፣ በፍርሃት በረዐድ በመንቀጥቀጥም እንጂ፡፡ እነዚያን አላውቃችሁም ያላቸው በድፍረት የሚጠሩቱን ነው፡፡ ሳያምኑ፣ ሳያውቁት በስሙ ብቻ ቁማር የሚጫወቱትን ነው፡፡ እነጾም ፋሲካውም ሳያምኑ ሲጠሩት እንቃወማቸዋለን፡፡ ክርስቶስ እነዚያን አላውቃችሁም እንዳላቸው ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም አላውቃችሁም ትላቸዋለች፡፡

ከነቢያት አንዱ ብለው የሚያምኑት እና የሚከተሉት እኮ ሞልተዋል፡፡ ስሙንም በነጋ በጠባ ይጠሩታል፡፡ እነርሱ ግን ስሑታን ናቸው፡፡ ምእመናንም አይደሉም፡፡ የእነ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘገባ እኮ ያመለከተው ይኽንን እውነት ነበረ፡፡ ከነቢያት አንዱ አይደለም ጌታችን፡፡ እርሱ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ኢየሱስ ማለት ብቻ ዋስትና አይደለም ማለት ነው፡፡ እንዲች እንዲች እያሉ የውብድና ሥራ ለመሥራት በር መክፈት ለስርቆት ማመቻቸት ከተነቃባችሁ ቆይቷል፡፡ ይልቁንስ በቶሎ ንስሐ ግቡ!

ቤተ ክርስቲያን ቅድስቲቱ ዐውደ ምሕረት የዘፈን የዳንኪራ ቤት እስክትኾን መሥራት ስለኾነ ተልእኮው ይኸው ዘፈናችሁባት፡፡ እንደ ሲኒማ ቤት ዘለላችሁባት፡፡ ዳንኪራ ረገጣችሁ፡፡ እናንተማ ሥራችሁ ነውና አደረጋችሁ፡፡ ግን ሌሎቻችንስ ምነው ዝምታችን! አባቶችስ እዚያው በመድረኩ የነበራችሁ እንዴት አስቻላችሁ? ልጆቻችን በሰው ሀገር በአረመኔዎች ፊት ሃይማኖታቸውን መሰከሩ እኛ ግን በቤታችን ዝም አልን፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?

ማጠቃለያ
የምን ምስክር ምን እንዲሉ "ተሐድሶ የለም" ማለት የራስን ማንነት ማጋለጥ ነው፡፡ ዐይንን በጨው ታጥቦ የአደባባዩን እውነታ መካድ ሌላ ከሃዲነት ነው፡፡ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀውን እውነታ ሸምጥጦ መካድ ያው ከሃዲነት ነው፡፡ እናም "ተሐድሶ የለም" ማለት ራሱ ተሐድሶነት ነው፡፡

5 comments:

 1. Whether you like it or not Orthodox Church should be renewed. We are preaching Lord Jesus in every why and situations. Jesus is Lord!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ወደዳችሁም ጠላችሁም ነው ያልከን የማንን ቤት ማን ያድሳል ቤቱ /ቅድስት ቤተ ክርስቲያን/ እኮ ባለቤቷ እርሱ መድኃኒአለም ነውና፡፡ በዚህ ላይ አሮጌ ነው ያላችሁትን ለእኛ ለተዋህዶ ልጆች ብትተዎትና አዲስ ብታንፁ ምን ይመስላችኋል? መቼም ዓለምም የምትወደው ከአሮጌ ይልቅ አዲስ ነውና አሮጌ በማደስ ጊዜያችሁን ከምታባክኑ ራሳችሁን ግለፁና አዲስ ሁኑ፡፡ እኛ ግን በዛው በአሮጌ ቤታችን የተሰቀለውን ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ለእኛ ሲል የተገረፈውን የተንገላታውን የተዋረደውን የቆሰለ የደማውን አርባ ቀን አርባ ሌሊት በፆም ሲወድቅ ሲነሳ የነበረውን የጌቶች ጌታ የሆነውን እየሱስ ክርስቶስን በወግና በስርዓት ከምታስተምረን፣ መሠረቷ ጉልላቷ እርሱ ከሆነው ከተዋህዶ እምነታችን ከቅድስት ቤተክርስቲያን አዳራሽ አይሻለንም እና እባካችሁ ተዎን፡፡ Whether you like it or not Orthodox Tewahedo never renewed or improved,b/c Tewahedo is always new. ባለቤቷም መሠረቷም ጉልላቷም እየሱስ ክርስቶስ ነውና አንዴ በደሙ መስርቷታልና

   Delete
 2. "ተሐድሶ የለም" ማለት ራሱ ተሐድሶነት ነው" አራት ነጥብ!!!

  ReplyDelete
 3. በዚህ ዘመን ወደ አሥርት ዓመታት እና በላይ ያስቆጠረዉን የተሐድሶን ማንነት ከፅንሰት እስከ ዉልደት ብሎም እድገት ትዉልዱ አዉቆት ባለበት ዘመን እና ተዋናዮቹ ባለቤቶች ነን አዎን ብለዉ የተቀበሉትን ለማጠፍ መሞከር ከንቱ መፈራገጥ ነዉ። በጋሻዉ ካፈርኩ አይመልሰኝ ብሎ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ በደሰኮረ ቁጥር ማንነቱን እየገለጠ በመሆኑ ቆይ እስኪ ይህ ነገር ብሎ መመርመርን አይጠይቅም። እርግጥ ነዉ ልጁ በጋሻዉ ተሐድሶ በመሆኑ ነዉ እንዲህ ጊዜ ወስዶ መማሰኑ። እባካችሁ እዘኑለት። የበጋሳዉ ነገር ኦክስጂን እየተነፈሰ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ፈፅሞ የለም እንደማለት ነዉና የመተንፈሻ አካሉን መመርመር ይጠይቃል። ኃጢያት ሲደጋገም ጽድቅ እንዲመስል ወንድማችንም በተዋህዶ አዉድ ላይ በተደጋጋሚ መድረክ በማግኘቱ ለአንደበቱ ሠምሮለታል። አባቶችን ቢያንጓጥጥ፣ ቤተ ክርስቲያንን ቢደፋፈር፣ታሪክን ቢቆነጻጽል ለጊዜዉ መሆኑን የተረዳ አይመስልም። የስድብ አፍ የተሰጠዉ ለአዉሬዉ ለዲያብሎስ ብቻ ነዉ። ዉጊያዉ ደግሞ ከመናፍስትና ከግብረ አበሮቹ ስለሆነ እየሠራበት ያለዉን የድፍረት መንፈስ መገሰጽ ግድ ይላልና ለመልስ ጊዜ እንሰጣለን። የቤተ ክርስቲያንን አዉድ ለበጋሻዉ መስጠት መፍቀድ ራስን ለሰዳቢ መስጠት ነዉና ሰጪዎቹ ያስቡበት እላለሁ። ቤተ ክርስቲያንንም ባያስደፍሯት።" አንድ ሞኝ የተከለዉን አምሣ ሊቃዉንት አይነቅሉትም " እና ትናንትና በየዋህነት መድረክ ከመፍቀድ አልፈዉ በስንት ትግሃ ሕይወት የሚሰጠዉን የቤተ ክርስቲያን ማዕረግ የሸለሙት አባቶች ዝምታን ዛሬም ድረስ መምረጣቸዉ ያሳዝናል። ቤተ ክርስቲያን በቀን ዉስጥ በሰዓት እንኳ የተከፈለ ትምህርትና አገልግሎት ያላት፣ ከቀን እስከ ሌሊት፣ ከነግህ እስከ ሰርክ ፣ በሳምንታት በወራትና በዓመታት የተከፈሉ አስተምህሮዎች ቤተ መጻሕፍት መሆኗን የተገነዘበ ደርሶ የዘለቀ አይመስልምና ቢሰድብ አይፈረድበትም። የሌለዉንስ ከወዴት ያምጣዉ። ለሁሉም እርሱን እና ሰበር አንደበቱን ባነሳን ቁጥር መሥራት የሚገባንን ጊዜ እያባከንን ነዉና የዳኛ ያለህ እንበል። ዳኛ ከጠፋ ደግሞ እግዚአብሔር ጊዜ አለዉና ያነሳዉ ጊዜ መልሶ እስኪጥለዉ እንጠብቅ። ልዝብ ተ/ማርያም

  ReplyDelete
 4. ብቻ ምን አለፋችሁ በአንዳንድ የቴሌቪዥን ጣብያዎች እንደምናያቸው በአየር ላይ እንፈውሳለን እንጸልይላችሁ ከሚሉት በምንም በማያንስ ሁኔታ እየተውረገረገ ቤተ ክርስቲያንን ማተራመስ ብቻ፡፡ ችሎታው ካለ በራሱም በቤቱም ያለውን ቃልቻዊ ጠባይ ምነው አላጠፋው?ወንድሜ ልክ አልክ እኔ በግሌ የማውቀው ብዙ ታሪክ አለ፡፡ የአንድ ሰው ብቻ ታሪክ ልንገርህ ጎረቤቴ አንድ ልጅ አለ በቅርቡ ነው የኘሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው፡፡ የሚገርምህ እናቱ ጠንቋይ ናቸው!! እቤቱ ያለውን አጋንንት ሳያወጣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታየችን ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱትን እያስቆመ መዝገበ ጸሎት ምንድን ነው? እያለ ምእመኑን መንገድ አላሳልፍ ይል ነበር ዝምተኛው ልጅ ቅዱሳንን ለመሳደብ የተሰጠው አንደበት ይገርማኛልና ይህንን ሳነብ ትዝ አስባልከኝ፡፡የሚገርመው እኚህ እናት በብዙ ስቃይ ሞቱ፡፡ ማዳን ግን አልቻለም፡፡ ሚስቱ በኤች አይቪ ሞተች ብለው አስወሩና እኔ ግን ተፈወስኩኝ እያለ በመቀባጠር አንዲት እህትን አገባ፡፡ የሚገርመው እሷ ስትወልድ ምን እንደሆነች አላውቅም አፏን አጣመመው እስከአሁን ድረስ አፏ እንደተጣመመ ነው ግን መፈወስ አልቻለም፡፡ ሌላም ብዙ አሉ እቤታቸው ቤተሰቦቻቸው በአጋንንት እስራት ተይዘው ታመው እነርሱን ሳይፈውሱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመን ብቻ የሚቀይር ወይም በእነርሱ አነጋግር የሚፈውስ መንፈስ የጤና ነው ብላችሁ ነው? እኔ የምኖርበት አካባቢ ኘሮቴስታንት በብዛት ያሉበት አካባቢ ነው እና ሁሉም ማለት እችላለሁኝ ቤተሰቦቻቸው በአጋንንት እስራት ተይዘው በብዙ ችግር ውስጥ ያሉ ሆነው እያየናቸው ነገር ግን እንፈውሳለን እያሉ የሚለፍፉት ነገር ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ አንድ ወቅት ላይ ጊዜውን አላስታውስም በሙሉ ወንጌል አዳራሽ 5ቱ መነኮሳት አረጊቷ ሳራ ብለው የአባቶች የመነኮሳት ልብስን እንዴት ሲያንቋሽሹ ከነበሩት ውስጥ አንደኛው መነኩሴ ነበርኩ ሲል የነበረው ፊልሙን ማህበረ ቅዱሳን በትነውት ነበር፡፡ አባ ገብረክርስቶስ የማባለው ሰው እኛ አካባቢ ተከራይቶ ሚስት አግብቶ ነበር የሚኖረው የሚገርመው አሟሟቱን በእውነት ህሊና የሚከብድ በኤች አይቪ ነው የሞተው ሰውነቱ ተልቶ በአሳዛኝ ሁኔታ ነው ነፍሱ ያለፈው እና የተቀበረው ሜዳ ላይ ከዚያም የሚደርስለት አጥቶ የእኛ አካባቢ ገንዘብ አዋጥተው በሚያሣዝን ሁኔታ ነፍሱ ሲያልፍ አንድ ሰው የሚደርስለት አጥቶ የአካባቢው ሰው ነው የቀበረው፡፡ እርሱ ሲሞት እኔ አጋጣሚ አልነበርኩም እንዴት እንዳሳዘነኝ መሰላችሁ፡፡ ደግሞ በሐይማኖት ጉዳይ አንድ ቀን አግኝቼው በጣም አውርተን ስለነበር በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እኔ እኮ ይገርመኛል እንደው ምን ይሻላቸው ይሁን??? የታመሙ ወገኖቻችንን እግዚአብሔር ይማርልን የሞቱትን ነፍስ ይማር እነርሱን ማስተዋል ይስጥልን፡፡

  ReplyDelete