Tuesday, October 13, 2015

አንድ ሞኝ የተከለዉን አምሣ ሊቃዉንት አይነቅሉትም

  • ‹‹ዘርፌ ፤ ምርትነሽ ፤ ትዝታው ፤  ድምፀ ጎርናናው በጋሻው  እዚህ ግቡ የማትሏቸው ቄስም ጳጳስም ሳይሆኑ ተነስተው በዜማ ቤተ ክርስቲያኗን አናወጧት፡፡›› በተሃድሶ አዳራሽ ማንነታቸውን ሲገልጽ
  • ማኅበራችን ከሳቴ ብርሃን በዚች ቤተክርስቲያን ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ላለፉት 18 ዓመታት በቡድንና በተናጠል በመሆን ፤በማኅበር ደረጃ በመደራጀት ለውጥ እንዲመጣ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

(አንድ አድርገን ጥቅምት 3 2008 ዓ.ም)፡- ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት ከደረሱባት መከራዎችና ስደቶች ተርፋ ለዚህ ትውልድ የደረሰችው በጠንካራዎቹ አባቶቻችን ተጋድሎና በደሙ በመሠረታት በመድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ ቸርነት እንደሆነ አባቶቻችን ያስተማሩን የታሪክ እውነት ነው፡፡ የግራኝ አህመድን ሰይፍ ዮዲትን እሳት ፤ የእነአልፎንሱ ሜንዴዝና ተከታዮቹን ቅሰጣ አልፋ እነሆ ለእኛ ደርሳለች፡፡ ተጋድሎ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ጸጋ ነውና አባቶቻችን ያለፉበት መከራ ዛሬም መልኩን ቀይሮ መከሰቱ አልቀረም. ‹‹ተሐድሶ›› 

 በዚህ ዘመን ወደ አሥርት ዓመታት እና በላይ ያስቆጠረዉን የተሐድሶን ማንነት ከፅንሰት እስከ ዉልደት ብሎም እድገት ትዉልዱ አዉቆት ባለበት ዘመን እና ተዋናዮቹ ባለቤቶች ነን አዎን ብለዉ የተቀበሉትን ለማጠፍ መሞከር ከንቱ መፈራገጥ ነዉ። ተሐድሶያውያን ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በደሰኮሩ ቁጥር ማንነታቸውን እየገለጠ መሆኑ አንዘንጋ።


በተሐድሶያውያን እንቅስቃሴ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የአቶ በጋሻዉ ነገር ኦክስጂን እየተነፈሰ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ፈፅሞ የለም እንደማለት ነዉና የመተንፈሻ አካሉን መመርመር ይጠይቃል። ኃጢያት ሲደጋገም ጽድቅ እንዲመስል ወንድማችንም በተዋህዶ አዉድ ላይ በተደጋጋሚ መድረክ በማግኘቱ ለአንደበቱ ሠምሮለታል። አባቶችን ቢያንጓጥጥ፣ ቤተ ክርስቲያንን ቢደፋፈር ፣ ታሪክን ቢቆነጻጽል ለጊዜዉ መሆኑን የተረዳ አይመስልም።
የስድብ አፍ የተሰጠዉ ለአዉሬዉ ለዲያብሎስ ብቻ ነዉ። ዉጊያዉ ደግሞ ከመናፍስትና ከግብረ አበሮቹ ስለሆነ እየሠራበት ያለዉን የድፍረት መንፈስ መገሰጽ ግድ የቤተ ክርስቲያንን አዉድ ለእነዚህ ለመሰሉ ሰዎች መፍቀድ ራስን ለሰዳቢ መስጠት ነዉና ሰጪዎቹ ሊያስቡበት ይገባል። አንዲት እናት ቤተ ክርስቲያንንም ባያስደፍሯት መልካም ነው ። አበው " አንድ ሞኝ የተከለዉን አምሣ ሊቃዉንት አይነቅሉትም " ይላሉ፡፡

ትናንትና በየዋህነት ለእነዚህ የበሉበትን ረግጠው ለወጡ ፤ የበሉበትን እጅ ለነከሱ ሰዎች መድረክ ከመፍቀድ አልፈዉ በስንት ትግሃ ሕይወት የሚሰጠዉን የቤተ ክርስቲያን ማዕረግ የሸለሙ አባቶች ዝምታን ዛሬም ድረስ መምረጣቸዉ ያሳዝናል። ቤተ ክርስቲያን በቀን ዉስጥ በሰዓት እንኳ የተከፈለ ትምህርትና አገልግሎት ያላት፣ ከቀን እስከ ሌሊት፣ ከነግህ እስከ ሰርክ በሳምንታት በወራትና በዓመታት የተከፈሉ አስተምህሮዎች ቤተ መጻሕፍት መሆኗን የተገነዘቡ ደርሶም የዘለቁ አይመስልምና ቢሰድቡም አይፈረድባቸውም። ተሐድሶያውያን አንደበታቸውን ባነሱ ቁጥር መሥራት የሚገባንን ጊዜ እያባከንን ነዉና የዳኛ ያለህ እንበል። ዳኛ ከጠፋ ደግሞ እግዚአብሔር ጊዜ አለዉና ያነሳዉ ጊዜ መልሶ እስኪጥለዉ እንጠብቅ።

ይህ ከዚህ በታች ያለው ጽሑፍ በምንፍቅናቸው በጊዜ ከቤተ ክርስቲያን የተገለሉት ከሳቴ ብርሃን እና መሰሎቻቸው በቤተክርስቲያን ላይ ምን ያህል እሾኽ ለመትከል ሲሰሩ እንደነበር ፤ ምን ያህል የጥፋት ሰራዊቶቻቸውን አሰማርተው እንደነበር ፤ ምን ያህል በጎችን ከቤተክርስቲያን ቅጥር እንዳስወጡ ፤ በጠቅላላ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በማደስ ሊደርሱበት ያቀዱት ግብን ለማሳካት ምን ያህል ዳገት እንደወጡ እና ቁልቁለት እንደወረዱ ከግብ አበሮቻቸው ላያቸው ተዋሕዶ ውስጣቸው ተሐድሶ ከሆኑት አቶ በጋሻው ፤ ወ/ሬ ዘርፌ ፤ ምርትነሽ ፤ አቶ ትዝታውና ከመሰሎቻቸው ጋር መርፌና ክር ሆነው ሲሠሩ እንደነበሩ በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከተቀዳው የምስልና የድምጽ ማስረጃ የሁለት ደቂቃውን እንዲህ አድርገን ሳንጨምር ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል( የዚህን የድምጽ ወምስል ማስረጃ ለማየት የፌስቡክ ገጻችንን ይመልከቱ)፡፡
‹‹.... ቤተ ክርስቲያን የለውጥ እሳት እየመጣ መሆኑን አላወቀችም ነበር ፤ በትንሽ በትልቁ የለውጥ እሳት  እግዚአብሔር ለኮሰ ፤ የመማር እሳት ፤ የመለወጥ እሳት ፤ የማደግ እሳት ፤ የመበልጸግ እሳት እግዚአብሔር ጨመረ ፤ ታሥራበት የነበረው ገመድ ስለተበጠሰላት ብቻ ልታስተውል አልቻለችም ፤  ይቅርታ ይህንን ብዬ ስናገር አብያተ ክርስቲያናትን አከብራለሁ ፤ ይህ ለውጥ ባልታሰቡ ሰዎች አማካኝነት ነው የተጀመረው ፤ በዚህ ጊዜ የመዘምራን ኅብረቶች ተነሱ ፤ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ታውቃላችሁ ዘርፌ ፤ ምርትነሽ ፤ትዝታ ፤ ማነው ይህ ድምጸ ጎርናናው በጋሻው ፤ እዚህ ግቡ የማትሏቸው ቄስም ጳጳስም ሳይሆኑ ተነስተው በዜማ ቤተ ክርስቲያንን አናወጧት፡፡ በእነሱ ምክንያት ኢየሱስዬ ማለት ተለመደ ፤ የሚገርማችሁ እኔ የእዛን ያህል ጊዜ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ስኖር ኢየሱስ ‹‹የናርዶስ ሽቶዬ›› አይባልም ነበር ፡፡ ኢየሱስዬ አይባልም  ፤ አሁን ሂዱልኝ ካሴቶች ሁሉ ‹‹የኔ ናርዶስ ኢየሱስ›› ነው የሚሉት፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም በቀላሉ እንዲለመድ እግዚአብሔር በዚህ ተጠቀመ፡፡ ስለዚህ ነው አሁን ደስ ሊላችሁ የሚገባው ፤ አሁን እየዘመሩ እየሰበኩ ነው ፤ ወደ እግዚአብሔር እየሔዱ ነው ፤ ነገር ግን የዚህ የለውጥ ማዕበል እሳቱ እንዲጠፋ ተመታ ፤ ማኅበራችን ከሳቴ ብርሃን በዚች ቤተክርስቲያን ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ላለፉት 18 ዓመታት በቡድንና በተናጠል በመሆን ፤በማኅበር ደረጃ በመደራጀት ለውጥ እንዲመጣ ሲሰራ ቆየ ፡፡  እና በተከታታይ አስርት አመታት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ጌታ እንዲመጡ ተደረገ ፤ በርካታ ካህናትን እያሰለጠነ ወደ ውስጥ የማስገባት ሥራን ሲሰራ ቆየ ፤ በእነዚያ ጊዜያት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዲያቆናት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና መነኮሳት እየሰለጠኑ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል፡፡ በስልጠናችንም በወንጌላውያን እና በኦርቶዶክስ መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠብ ረዥም ርቀት ተሄዷል፡፡ ወደ አምስት ሺህ የሚደርሱ ወንጌላውያንን በማሰልጠን በሁለታችን መካከል ያለን ልዩነት ለማጥበብ ብዙ ሰርተናል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ አገልግሎት ተጠቅሟል ፤ በስነ ጽሑፍም ስናገለግል ሰው የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን እድል አንድ ጊዜ በሕይወቱ እንዲሰማ እግዚአብሔር በሰጠን በእጅ በእስኪቢርቶ የተጀመረ ጋዜጣ እስከ 24 ዕትም እስኪደርስ ድረስ ተሰርቷል፡፡  ››

3 comments:

  1. this is an indication of your ignorance please no body need not to be a priest to serve the church and sing a religious song. I Think you lost your followers and financial subscription .B?c every body is going to Begashaw.

    ReplyDelete
  2. እንደዚህ ዓይነቱን ፈተና ለማለፍ እጅጉን መጸለይ፣ መጾም፣ መስገድ ይገባናል፡፡ የምናቀርበውን የምስጋናና የጸሎት የስግደት የቤተክርስቲያንን ፈተና በተመለከተና ከልብ መሆን አለበት ስጋውንና ደሙን የምንቀበል ምእመን ይህንን በተመለከተ እስኪ እንቀበልና መስራት እንጀምር፡፡ ከዚያም እንደዚህ አይነቱን መልእክት በተለያየ መንገድ ማሰራጨትና ህዝቡን ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም እነርሱን ባሉበት የተዋህዶ ልጆች ሆነው እንዲቀሩ ማድረግ የሚቻልበትን ስራ መስራት!! እግዚአብሔር እንዲሰራ ለሰዎቹ ያለንን ጥላቻ አንስተን እግዚአብሔር ልቦናና ማስተዋል እንዲሰጣቸው ጸልየን እግዚአብሔርን አስቀድመን ለፍቅርና ለአንድነት እንስራ፡፡ መድሀኒያዓለም ያደረገውን ጠላት ባዘጋጀው መስቀል ተሰቅሎ የዓለሙን ኃጢያት ይቅር እንዳለ እኛ ደግሞ በፍቅር እያደረጉ ያለውን ነገር ስህተት እንደሆነ በመገሰጽ አስረድተን ያለፈውን ነገር ትተን አንድ ትልቅ መድረክ ተዘጋጅቶ ምእመኑን ያሳተፈ ስራ ቢሰራና ቃላቸውን ለምእመኑ ቢያሳውቁና ስህተት ነው ብለን ያመንበትን ጉዳይ በፊት ለፊት ተገናኝቶ የመነጋገሪያ መድረክ ቢዘጋጅ ደስ የሚል አካሄድ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ተኩላው ውስጥ ድረስ ነው የገባው ይህንን ለመለየት ደግሞ አረሙን እንነቅላለን ብለን እህሉንም አብረን እንዳንነቅል ፍራቻ አለኝ፡፡ ፍቅር የማይሰራው ስራ የለምና ተጠንቅቀን ይህንን ጉዳይ ትኩረት ብንሰጠው መልካም ይመስለኛል፡፡ ሳንሰለች ለፍቅር እንስራ፡፡ አለበለዚያ እጅጉን አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር ስለሁሉም ነገር ኦርቶዶክስ ተዋህዶን እምነታችንን ስለእናቱና ስለቅዱሳኑ፣ ስለሰማእታት ደም ብሎ እንዲጠብቅልን እርሱ ይርዳን፡፡ አሜን

    ReplyDelete