Wednesday, October 21, 2015

ክርስትና እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ኑሮ መምራት ነው

ከጽሙና መልካሙ
(አንድ አድርገን ጥቅምት 10 2008 ዓ.ም)፡- በእውነት ቤተክርስቲያን ስትበረታ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ሲሰፋ እንደማየት የሚያስደስት ነገር ከወዴት ይገኛል? ከሁለት ቀን በፊት የተጀመረው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር 34 ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ በ2007 ዓ.ም ሰላሳ ስድስት ሺሕ ስምንት መቶ ሰዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባል ሆኑ የሚል ዜና መስማት እንዴት ደስ ያሰኛል ፡፡ እኛ ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ  አለን፡፡ የሚያኩራራ ምንም ነገርም አልሠራንም፡፡ ሰላሳ ስድስት ሺሕ ስምንት መቶ ሰዎች መጡ፡፡ ጥሩ! ግን በውስጥ ያሉት 40 ሚሊየን እንዴት እየኖሩ ነው ብለን ስንጠይቅ መልሱ አስፈሪ ይመስለኛል፡፡ 


ክርስትናም የሰው ቁጥር ከመጨመር በላይ ጉዳዮች አሉት፡፡ ለምሳሌ፣ ቤተክርስቲያናችን ዛሬ በሙሰኛ ካህናት ተጥለቅልቃለች፡፡ መንፈሳዊነት የራቃቸው ካህናትን ማየት በጣም ከመልመዳችን የተነሣ አሁን አሁን መንፈሳዊ ካህን ማየት ብርቅ ሆኖብናል፡፡ በጣም ብዙው ምእመንም ክርስትናው ትዝ የሚለው ቤተክርስቲያን ሲሄድ ነው፡፡  ኑሮው ውስጥም ኢፍትሐዊነት፣ ከእኔ በላይ ላሣር ባይነት፣ ኩራት እንጂ ክርስቶስ ማዕከል ሆኖ አይገኝም፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ግንየክርስትና ማዕከሉ ክርስቶስ ነው፡፡ይሉ ነበር፡፡ ክርስቲያን መሆን ማለት እግዚአብሔርን የኑሮ ማዕከል፣ የእይታ አንጻር አድርጎ መኖር ማለት እንጂ እሑድ እሑድ ቤተክርስቲያን እየሄዱ ሌሎቹን የሳምንቱን ቀናት ራስን ማዕከል አድርጎ መኖር ማለት አይደለም፡፡ ክርስትና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መገንባት አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ ማካሄድ አይደለም፡፡ እገሌ የሚባል ማኅበር ማቋቋም አይደለም፡፡ የመዝሙር ሲዲ ማሳተም አይደለም፡፡ ጥምቀት ሲሆን ታቦት ማጀብ አይደለም፡፡ ነጠላ ለብሶ መታየት አይደለም፡፡ ቀሚስ ማስረዘም አይደለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ገንዘብ መስጠት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ የክርስትና ትውፊትና ትሩፋት እንጂ ክርስትና አይደሉም፡፡ ክርስትና እንደ እመቤታችን እግዚአብሔር የሕይወቴ ጌታ ነው፤ እኔም የእግዚአብሔር ባርያው ነኝ ብሎ እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ኑሮ መምራት ነው፡፡ እመቤታችንን እንወዳለን እንላለን፡፡ የእመቤታችን ሕይወት ግን ፈጽሞ በእኛ ዘንድ የለም፡፡ የእመቤታችን ስሟ እንኳ ትዝ የሚለን ወይ ችግር ሲያጋጥመን አለበለዚያ በዓል ሲሆን ነው፡፡ ወይም ደግሞ ለመሓላ፡፡

ኩራት፣ ስስታምነት፣ ጭካኔ ልቦቻችንን ሞልቷል፡፡ እነዚህ ዛሬ መጡ ያልናቸው 36 000 ሰዎች ከኑሯችን ክርስቶስን አግኝተው በመንፈሳዊ ሕይወት በልጽገው ይኖራሉ ወይስ በውጪ አማንያን በሥራችን ግን ኢአማንያን ከሆንነው ከእኛ ክፋትን፣ መለያየትን ተምረው፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላም ከእኛ ብሰው የኢአማኒ ሥራ ይሠሩ ይሆን? ጌታችን ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፡፡ ያለው በእውነት ዛሬ በእኛ ላይ ይታያል፡፡ ሁላችንም በልቦቻችን ቄሣሮች ነን- ዓለምን በሙሉ በእኛ ማዕከልነት ማሽከርከር የምንፈልግ ኩራተኞች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስኢየሱስ ጌታ ነው!” ሲልኮ መፎከሩ አልነበረም- ቄሣር ጌታ አይደለም ማለቱ እንጂ፡፡ አዳም አምላክነትን ፈልጎ እንደወደቀ ሁላችንም እግዚአብሔርን የአምላክነቱን የማዕከልነቱን ስፍራ ነፍገነዋልና ወድቀናል፡፡ ልክ አይሁድእኛ የአብርሃም ልጆች ነንይሉ እንደነበረው እኛም ክርስቲያኖች ነን እንላለን፡፡ ሕይወታችን ግን ክርስቶስ የሌለበት ሆኖ ይታያል፡፡ ክርስቲያኖች ከሆንን ከራሳችን ጋርም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በፍቅር፣ በተስፋና በርኅራኄ ክርስቶስ የሚነግሥበት ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ የእኛ ግን እንዲህ አይደለም፡፡
 
እነሆ! በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ጨዋታውጥሎ ማለፍነው፡፡ ነጋዴው ሱቁ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሰቅሎ ገበያተኞቹን አለአግባብ ሲዘርፍ፣ ሲዋሽ ይውላል፡፡ የቢሮ ሠራተኛዋ ጠረጴዛዋና ኮምፒውተሯ ላይ ቅዱሳት ሥዕላትን ደርድራ ባለጉዳዮችን ስታጉላላ፣ ስትገላምጥ ትውላለች፡፡ አስተማሪው፣ አንገቱ ላይ ትልቅ መስቀል አንጠልጥሎ ተማሪዎቹን ሲሳደብ፣ ሲያንጓጥጥ ይውላል፡፡ ባለሥልጣን በሥልጣኑ ተመክቶ የሰው ሚስት ሲቀማ፣ በሚስቱ ላይ ሲወሽም ያድራል፡፡ ሁሉም ራሱን ማዕከል አድርጎ ይሮጣል፡፡ እንግዲህ፣ እግዚአብሔር የነገሠበት የክርስቲያን ሕይወት ወደየት ይገኝ? የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ ይህንን ነውከንቱ! ከንቱ! የከንቱ ከንቱ!… ነፋስንም መከተልብሎ የገለጸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣቱ ከዚህ የከንቱና ትርጉም አልባ ኑሮ ሊያላቅቀን ነበር፡፡ እርሱ አባቱን ማዕከል አድርጎ እንደኖረ እኛም እርሱን ማዕከል አድርገን እንድንኖር አስተማረን፡፡ አሳየን፡፡ ያውም እስከ መስቀል ሞት ድረስ!

ጸሐፍት ፈሪሳውያን ራሳቸውንየአብርሃም ልጆችይሉ ነበር- ልክ እኛ ዛሬ ራሳችንን የሥላሴ ልጆች እንደምንለው፡፡ አብርሃም ግን የእግዚአብሔር ወዳጅ የተባለው እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ በማመኑ ነበር፡፡ እነርሱ የአብርሃም ልጆች ነን ያሉት ግን ቤተመቅደስ ስለገነቡ፤ የአባቶቻቸውን ባህልና ትውፊት ይጠብቁ ስለነበር ነው፡፡ ባህሉን ያዙትና የባህሉን መነሻ የነበረውን እግዚአብሔርን የሕይወታቸው ጌታ አድርጎ ማመንን ግን ዘነጉት፡፡ እግዚአብሔርን በምሕረትና በፍትሕ ሳይሆን በመሥዋዕትና በሥጦታ ሊገለገሉበት እየሞከሩ ነበር፡፡ የመንገዳቸውን ትክክለኛነትም አይጠራጠሩም ነበር- ኃጢኣት ሲለመድ ጽድቅ ይመስላል እንዲሉ አበው፡፡
ምናልባትም ጌታችንእናንተ አንድ ሰው ለማሳመን በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፣ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት ዕጥፍ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፣ ወዮላችሁ!” (ማቴ 23 13) ያለው ተግሣፅ እንዳይደርስብን ማስተዋል መልካም ነው፡፡

2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ የውስጤን ነው የተናገርከው እግዚአብሔር ይባርክህ ምን ዋጋ አለው ይህንን በወረቀት በትኖ ለሁሉም ለካህናትና ለምእመኑ ቢበተን እንዴት አሪፍ ነበር፡፡

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ በትክክል ገልፀኸዋል ከዚህ በኋላ በልምምጥ የምንጓዝበት ዘመን አይደለም የቤ/ክ ትምህርት መማር ያስፈልጋል ሁል ጊዜ በሌሎች ዘንድ የኦ/ክ ምዕመን ምንም እንደማያውቅ ነው የሚታሰበው እንደተባው ብዙዎቹ የሚያተኩሩት ወንድሜ ከላይ እንደገለፀው ነው፡፡ ደስ የሚል ት/ት ነው ያስከማርከን እ/ር መጨረሻሕን ያሣምረው፡፡

    ReplyDelete