በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
ከሰንደቅ ጋዜጣ የተወሰደ
አንድ አድርገን ጥቅምት 27 2007 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤ/ን መሆኗ ይታወቃል። የክርስትና ሃይማኖት በእስራኤልና በአካባቢው ገና ብዙም ባልተስፋፋበት በ፩ኛውመቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ወንጌልን የተቀበለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን በዓለም አቀፍ የክርስትና መድረክ ያላት ስፍራ ልዩ ነው። የክርስትናን ሃይማኖትን ያጠኑ የታሪክና የሥነ መለኮት ምሁራን የዳጎሱ ድርሳናትም የኢትዮጵያ ቤ/ን በአፍሪካ የክርስትና እምነት መስፋፋት ሂደት ውስጥ ቀደምትና ልዩ ታሪክ ያላት ሐዋርያዊትና ጥንታዊት ቤ/ን መሆኗንም አስረግጠው ጽፈዋል።
በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በሚገኙ ሕዝቦች ዘንድ የነጻነት ተምሳሌትና የተስፋ ምድር ተደርጋ የምትወሰደው የኢትዮጵያ ቤ/ን በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አሁንም ድረስ ልዩ ክብርና ስፍራ ያላት ናት። በወንጌል ስብከት ስም የምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች የባህል ወረራ ያልነካት፣ ለበርካታ ዘመናት ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ፣ ጥንታዊውን የክርስትና ሃይማኖትን አስተምህሮ፣ መንፈሳዊ ሥርዓት፣ ባህልና ትውፊት ጠብቃ የቆየች፣ ሐዋርያዊት ትክክለኛ፣ አፍሪካዊት እናት ቤ/ን (Genuine, Independent African Mother Church) በሚል ክብር የሚጠሯት ናት።
ይህችውን ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት የሆነች ምዕራባዊው ባህል ያልበረዛት፣ አፍሪካዊት እናት ቤ/ን በሚል ቅፅል የምትሞካሸውን የኢትዮጵያ ቤ/ን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ታሪኳን ጠለቅ ብለን ስናጠና፣ ስንፈትሽ ግን ቤተ ክርስቲያናችን የታሪኳንና የዕድሜዋን ያህል በታላቅ ጉጉት፣ በናፍቆት ለሚጠብቋት አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ወንጌልን በመስበክ ረገድ ሐዋርያዊውና መንፈሳዊ ግዴታዋን በሚገባ ተወጥታለች ብልን ለማለት የሚያስደፍሩን የታሪክ ሰነዶች እምብዛም አይገኙም።
እንደውም በወንጌል ስብከት ስም በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢ ኃይላት በአፍሪካውያን ላይ ያደረሱትን ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ሰብአዊ ቀውስን ያጠኑ አንዳንድ አፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራንም ደፈር ብለው፡- “የኢትዮጵያ ቤ/ን ከሁሉ የዓለም ሕዝቦች አስቀድማ የተቀበለችውን የወንጌል አደራ ለአፍሪካውያን ባለመስጠቷ በክርስትና ስብከት ስም ለመጡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች በር በመክፈት ተባብራለች” ሲሉ ይሞግታሉ።
ይህ የአፍሪካውያንና የአፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራን ሙግት የተጋነነ ቢመስልም አንዳንች እውነታ የለውም ለማለት ግን የምንችል አይመስለኝም። በእርግጥ ከመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ እስከ መካከለኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክን በጨረፍታ ስንመለከት ከዚህ ምሁራዊ ሙግት ውጭ ነው። ወደ ዝርዝር አሳቦችና ቀደምት ታሪካዊ ማስረጃዎች ለመግባት በዚህ ጽሑፌ ላነሳው ካሰብኩት ዐቢይ ርእሰ ጉዳይ ብዙም እንዳይርቀኝ ስል በዚሁ ልግታው።
ግና እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር ግን አስረግጬ ላልፍ እፈልጋለኹ። ቤተ ክርስትያናችን በዓለም አቀፍ መድረክ ካላት ክብርና ረጅም ታሪክ አንፃር ልንቆጭበት የሚገባ ነገር አለ። ይኸውም ለሺሕ ዘመናት በሕገ ልቦና፣ በሕገ ኦሪት፣ ከዛም በሕግ ወንጌል ጸንታ የቆየች፣ የራሷ የኾነ ቋንቋና ፊደል ያላት፣ ዜማን ከእነምልክቱ ለዓለም ያስተዋወቀች፣ ሰማያዊ የኾነ የአምልኮ ሥርዓት፣ ጠንካራ መንፈሳዊ ባህልና ትውፊት ያላት ቤ/ን፤ ግንእንደው ለመሆኑ እነዚህ መንፈሳዊ ሀብቶቿና ቅርሶቿ በየትኞቹ አፍሪካ አገራትና ሕዝቦች መካከል መንፈሳዊ አሻራውን ትቷል ብለን ብንጠይቅ ምላሹ አሳፋሪ ነው የሚሆነው።
እናም የአሁኑ የቤተ ክርስቲያናችን ወጣት ትውልድ፣ መንፈሳዊ መሪዎችና አገልጋዮች ለዚህ የዘመናት የአፍሪካውያን ጥያቄ፣ ክስናሙግት መልስ መስጠት ግዴታችንም ኃላፊነታችንም መሆን ያለበት ይመስለኛል። ይህን ተጠየቅ መሠረት በማድረግም በዚህ አጭር ጹሑፌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን ሐዋርያዊ ተልዕኮና በደቡብ አፍሪካ ባለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን ዙሪያ ከታሪካችንና ቤተ ክርስቲያናችን ካለችበት ነባራዊው ኹኔታ በመነሳት ጥቂት ነገሮችን ለማንሳት ወደድኹ።
በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያ ቤ/ን በዓለም አቀፉ የክርስትና ሃይማኖት መድረክ ካላት የረጅም ዘመን ታሪክና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ የተነሣ በተለይ በአፍሪካውያን ሕዝቦች መካከል የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትቆጠር ሐዋርያዊትና አፍሪካዊት እናት ቤ/ን ናት። ከዚህ ታሪካዊ ሐቅ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ ለየት ያለ ጅማሬና ታሪክ ያላት ናት።
ከአፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች የፀረ-ባርነት፣ የቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ መራራ ትግል ጋር በእጅጉ ተቆራኝታ የምትነሣው የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦችና የነጻነት ፋኖዎች በኾኑት በኔልሰን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ፣ ልዩ ክብር ያላት መንፈሳዊ ተቋማት ናት። ይህን የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ በአጠቃላይም በአፍሪካና በመላው በጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር ውስጥ ያላትን ጉልህ ድርሻ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዛዳንትና የነጻነት ታጋይ የኾኑት ታምቦ እምቤኪ እንዲህ ገልጸውታል፡-
The
Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of
the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures,
their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the
independent African churches, called themselves the Ethiopian Church.
ይህ ቤተ ክርስቲያናችን በደቡብ አፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በአጠቃላይ በጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን በሚያፈቅሩ የሰው ልጆች መካከል የነበራትና፣ ያላት የከበረ ታሪክ ለአገራችን ኢትዮጵያም ልዩ ክብርን እንድትጎናጸፍ አድርጓታል። እናም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮ፣ መንፈሳዊ ሀብቶቿና ቅርሶቿ ለሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት፣ የአገራት የባህል ልውውጥ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የራሱ የኾነ ትልቅ ድርሻን ማበርከቱ ግልጽ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የምትገኘው የኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪካዊ መነሻ በ፲፱ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ገደማ የተነሣው ፀረ-ባርነትና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። በዚሁ ክ/ዘመን በ፲፰፻፹፰ ዓ.ም ዓለምን ሁሉ ያስደመመውና ከአድማስ አድማስ የናኘው የዐድዋ ድል፣ በቅኝ ግዛት ሥር ለሚማቅቁ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ትልቅ መነሳሳትንና ወኔን ፈጥሮላቸው ነበር።
የዐድዋው ግንባር ዐፄ ምኒልክ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሣይሉና ሳይለዩ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ወገናቸውንና ነጻነቱን የሚያፈቅር ታላቅ ሕዝባቸውን ያስከተቱበት ዘመቻ ነበር። በዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ታቦተ ሕጉም ጭምር ሳይቀር በተሳተፉበት ዘመቻ የተገኘው የዐድዋ ድል መላውን አውሮፓን በሐፍረት አንገት ያስደፋ፣ አሳፋሪ ሽንፈት ነበር።
በተጨማሪም የዐድዋው ድል በጎልያድ የተመሰለችው የሮማ ካቶሊካዊት ቤ/ን በእረኛው ዳዊት በተመሰለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን ወንጭፍ ተመትታ የተሸነፈችበት ድል ተደርጎ ነበር የተቆጠረው። ይህች ነጻነታቸውን ከሚያፈቅሩና ለሰው ልጆች ኹሉ ከፈጣሪ በተሰጣቸው ነጻነት ላይ ድርድር የማታውቅ የኢትዮጵያ ቤ/ን ለደቡብ አፍሪካ የነጻነት ፋኖዎች ወኔ፣ የክብርና የኩራት ምንጭ ኾና አግልግላለች። የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ ምድር ዕውን የመኾን የታሪክ ውሉም ከዚሁ ቤተ ክርስቲያናችን በአገራችን ሕዝቦች የነጻት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ከነበራት ጉልህና ስፍራና ታሪካዊ ድርሻ የሚመዘዝ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሠሥ በኋላ በአሜሪካና በካረቢያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ን እና በኢትዮጵያ እናት ቤ/ን ግንኙነት መካከል ታሪካዊ ሊባል የሚችል የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ። ከዛም በመቀጠል ነፍሰ ኄር ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች በ፲፱፻፺ዎቹ መጨረሻ ገደማ በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በኹለቱ አገራት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የእናትና ልጅ ግንኙነትን እውን አደረገው።
በወቅቱም አቡነ ጳውሎስ በደቡብ አፍሪካዊቷ የወደብ ከተማ በፖርት ኤልዛቤት በሚገኘው የደቡብ አፍሪካውያኑ ቅዱስ መስቀል ቤ/ን ተገኝተው ቀድሰው ካቆረቡ በኋላ ባስተላለፉት መንፈሳዊ መልእክታቸውም፡- “… የአፓርታይድ ዘረኛ መንግሥት ቅዱስ ወንጌል በአንድ መንፈስ ያስተሳሰራቸው ሕዝቦች እንዳይገናኙ የጋረደው ፅልመታዊ መጋረጃ ተነሥቷል፣ ከአሁን ወዲያ ቤተ ክርስቲያናችን ቤተ ክርስቲያናችሁ፣ ሕዝባችንም ሕዝባችሁ፣ ታሪካችንም ታሪካችሁ ነው …!” በማለት ነበር የወንጌል ቃል እውነትያስተሳሰራቸውን የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናትን የእናትና ልጅ ግንኙነትን ያበሰሩት።
አቡነ ጳውሎስ በተጨማሪም ከደቡብ አፍሪካውያኑ መካከል በርካታ ካህናትና ዲያቆናት በመሾም በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል። ከእነዚህ ካህናት መካከልም በአቡነ ጳውሎስ ግብዣ በኢትዮጵያ ተገኝተው የከተራንና የጥምቀትን በዓል አብረውን እንዲያከብሩ፣ በአገሪቱ ታላቅ ገደማትና አድባራት በመጓዝም የቤተ ክርስቲያናችንን ጥንታዊ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና ትውፊት በማየት ለሕዝባቸው በሚገባ እንዲያስተምሩ ዕድል አመቻችተውላቸውም ነበር። በተጨማሪም ሦስት የቤ/ቱ መምህራን በደቡብ አፍሪካ የስድስት ወራት ቆይታ በማድረግ ለደቡብ አፍሪካውያኑ ኦርቶዶክሳውያን ሥልጠናም ሰጥተው ነበር።
በመቀጠልም የዛን ጊዜው ቆሞስ አባ ገብርኤል የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ የመላው አፍሪካ ሊቀ ጳጳስና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሹመው መምጣት በደቡብ አፍሪካ ምድር፣ የአገር ቤቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እናት ቤ/ን ህልውና እና ሐዋርያ ተልዕኮዋን ዕውንእንዲኾን አደረገው። ይህ የቤተ ክርስቲያኒቷ ምስረታና ሐዋርያዊ አገልግሎትም ለኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያንና ደቡብ አፍሪካውያን ታላቅ የምስራች ነበር።
በ፲፱፻፺ዎቹ ጆሐንስበርግ ከተማ የተጀመረው የቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተስፋፍቶ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ምድር አምስት አብያተ ክርስቲያናት፣ በርካታ ጉባኤያትና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ውጭ ኹሉተኛ የኾነውን ገዳም በደቡብ አፍሪካዊቷ የሊጅስትሌቲቭ ከተማ በብሉምፎንቴን ለማቋቋም ተችሏል። ይህን አገልግሎት በማስፋፋት ረገድ ከቤ/ቱ መንፈሳዊ አባቶች፣ መሪዎችና አገልጋዮች ባሻገርም ኢትዮጵያውያንና ደቡብ አፍሪካውያን ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ትልቅ ተሳትፎና ድርሻ ነበራቸው፤ አላቸውም።
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን በአፍሪካ ምድር ቀደምት፣ ሐዋርያዊትና እናት ቤ/ን ተብላ የምትጠራውን ያህል ባለፉትም ሆነ በአሁን ዘመን ለአፍሪካውያን ሕዝቦች የሚጠበቅባትን ያህል ተገቢ የሆነ አገልግሎት እየሰጠች ነው ብሎ ለማለት አያስደፍርም። ለዚህ ደግሞ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ቢኖሩም በዚህ አጭር መጣጥፍ ኹሉንም ችግሮችና ክፍተቶች ማንሳት የሚሞከር አይሆንም። ስለዚህም በደቡብ አፍሪካ የትምህርት ቆይታዬና አገልግሎቴ ያስተዋልኳቸውን ዐበይት ክፍቶችና ችግሮች ብቻ ላይ በማተኮር በመፍትሔ አሳቦቹ ላይ ትኩረት ማድረግ እንድንችል ጥቂት ነገሮችን ብቻ ልበል።
ቤተ ክርስቲያናችን በደቡብ አፍሪካ ምድር ካላት ግዙፍ የሆነ ታሪካዊ መሠረትና ተቀባይነት አንፃር የስብከተ ወንጌል አገልግሎቷን ከራሷ ሕዝቦች አልፋ ሌሎች አፍሪካውያንና የዓለም ሕዝቦች በማዳረስ ረገድ ብዙ ርቀት መሔድ አልተቻላትም። ይኽም ቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮዋ የሆነውን የስብከተ ወንጌል ሥራ ቸል በማለቷ ነው። በዘመናችንም በቤተ ክርስቲያናችን የነገሠው ዘረኝነት፣ መከፋፈሉ፣ መለያየቱ፣ ሙስናው፣ የመንፈሳዊ ሕይወት እጦቱ፣ የሞራል ውድቀትና ዝቅጠቱ የቤተ ክርስቲያንሁለተናዊ መንፈሳዊ አገልግሎት ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው እንዳለ እያየን ነው።
በተደጋጋሚ እንደታዘብነውም አባቶቻችንም በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በተገናኙ ቁጥር አብዝቶ የሚያነጋግራቸው የጥቅማ ጥቅም፣ የአገረ ስብከት ቅየራ፣ ተደጋጋሚና የሆኑና ተግባራዊ መፍትሔ ያልተሰጣቸው በየዓመቱ እንደ አዲስ የሚነሡ አስተዳደራዊ ጉዳዮችና በደሎች ናቸው። በአንጻሩ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ያህል ሰው አምኖ ተጠመቀ፣ ምን ያህል መንፈሳዊ ት/ቤቶች፣ መንፈሳዊ የሥልጠና ተቋማትና ማዕከሎች ተቋቋመዋል በሚሉ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲህ ዓይነቱን መንፈሳዊ አጀንዳ እንደ ዋና ርእሰ ጉዳዩ ወይም አጀንዳ አድርጎ አንስቶ የተነጋገረበት ጊዜው ሩቅ እየሆነ ነው።
የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ሥራውን ዘንግቶም በሂደት የጠብ፣ የክርክርና የሙግት፣ የመወራረፊያ መድረክ እየሆነ መምጣቱን እየታዘብን ነው። በሰሞኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ውዝግብ ባሻገርም ቅዱስ ፓትርያሪኩ ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠር ምእመናኖቿን እንዳጣች፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትም እየተዘጉ መሆናቸውን የገለጹበት አሳዛኝ ዜና የቤተ ክርስቲያንዋና ተልዕኮ በሆነው በስብከት ወንጌል ላይ ላጋጠማት ተግዳሮት ትልቅ ማሳያ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በደቡብ አፍሪካ በምትገኘው ቤ/ን አገልግሎት ላይ ወዳሉ ክፍተቶችና ችግሮችም ስንመጣም ቅዱስ ሲኖዶስ በደቡብ አፍሪካ ቤ/ን በሚመደቡ አባቶች፣ አገልጋዮችና መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ላነሳ እወዳለኹ። በደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ የተላኩ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል በአገሩ ቋንቋ አሊያም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚገባ ለመግባባት ችግር ያለባቸው፣ ቤተ ክርስቲያናችን በአፍሪካ ሕዝቦች ዘንድ ያላትን ታሪካዊ መሠረትና ቁርኝት በሚገባ የማያውቁ፣ የሄዱበትን ሕዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና ቀርበው ለማወቅ እምብዛም ማይጥሩ መሆናቸውን ነው የታዘብኩት።
እናም በአብዛኛው የእነዚህ ሰባክያነ ወንጌል አገልግሎታቸው በዛ ላሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን፣ በአገሪኛ ቋንቋ ብቻ የተወሰነ እንጂ ደቡብ አፍሪካውያን የቤተ ክርስቲያናችንን አባላትና ሌሎች ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎትና ታሪክ ማወቅ የሚፈልጉ የውጭ አገር ሰዎችን ማዕከል ሊያደርግ የቻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉ አይደሉም።
በእርግጥ በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ያዕቆብና በቤተ ክርስቲያናችን እያገለገሉ ከሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያን ካህናትና ዲያቆናት ትብብር በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚደረግ የቅዳሴና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አለ። በተጨማሪም በትምህርትና በተለያዩ የሥራ ጉዳዮች በደቡብ አፍሪካ ያሉ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመግባባት ክፍተትን በመሙላትና የቤተ ክርስቲያኒቱን በአፍሪካና በዓለም መድረክ ያላትን ልዩ ስፍራ፣ ጥንታዊ ታሪኳን፣ መንፈሳዊ ቅርሶቿንና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ መድረኮች የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉ እንደነበር አስታውሳለኹ።
ይሁን እንጂ ከአገልግሎቱ ስፋት አንጻር ይህ በቂ ሊሆን አይችልምና በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል። ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያላትን ሐዋርያው አገልግሎት ምሉዕ ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ ልትሠራ ይገባል። ቅዱስ ሲኖዶስምዋናው ተልዕኮውና ሥራው የሆነውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ዋናው አጀንዳው አድርጎ አጠናክሮ ሊይዘው ይገባዋል።
ወንጌልን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ሊሰብኩ የሚችሉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስተዋውቁ ወንጌል መምህራንንን በጥራትና በብዛት አሰልጥነው የሚያወጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትንና የሥልጠና ማዕከሎችን መገንባትም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመን ላላት ቤ/ን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተገነባ አንድ ለእናቱ የሆነ የሥነ መለኮት ኮሌጅ ብቻ ባለቤት ሆና መቅረቷ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን የሚያስቆጭም ጭምር ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮ የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ፣ የምርምርና የልቀት ማዕከል የሆነ የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ ማቋቋምን አጥብቆ ሊያስብበት ይገባዋል። በፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ዘመን መሠረቱ የተቀመጠው የማሕሌታዊው የቅዱስ ያሬድ የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ ጉዳይም ይኸው ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም እንዲሉ ተነስቶ አያውቅም።
ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በትምህርትና በስብከተ ወንጌል ሥራ ላይ ሊጠናከር ይገባዋል። ቤተ ክርስቲያንን ከዘረኞችና ከጎጠኞች፣ ከጥቅመኞች፣ ከሙሰኞች፣ ከአጭበርባሪዎችና ከነጋዴዎች ምሽግ ከመሆን ሊታደጋት የሚችሉ የወንጌል አርበኞችን በሚገባ አስተምረውና አሰልጥነው የሚልኩ መንፈሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መምህራን በብዛትና በጥራት ያስፈልጉናል።
ቅዱስ ሲኖዶሱም እንደ ስሙ ቅዱስ የሆነ፣ ከፖለቲካና ከፖለቲከኞች አጀንዳ የጸዳ፣ የቅዱስ ወንጌል እውነት የሆነውን ፍቅርን፣ ሰላምንና ዕርቅን የሚሰብክ፣ መንፈሳዊ አባቶቻችንም ለእውነትና ለፍትሕ ድምፃቸው ከፍ ብሎ የሚሰማ የእውነት፣ የድሆችና የግፉአን ጠበቃ ሆነው እንዲቆሙ ነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ፍላጎትም፣ ምኞትም!!
አበቃሁ!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
Thank you so much! It is great for those who have ears and heart. I want to forward why the church not donate our people in Ebola affected region of the continent. Synodos gave 16.4 Billion E Birr to Abay bond. But which one is prioritized to the christian? Dame or Human-being? Please our fathers do something to these people! At least you can donate some money through Africa Union to reach to the people. If we people are not help each other, how could wish to get the kingdom of God? Wish God take away this epidemic from us! God bless you my dear!
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ ያነሳኸው ጉዳይ ትክክለኛ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን ማድረግ አለባት። ነገር ግን በመጀመሪያ የውስጥ ጉዳይዋን በፍጥነት መፍታት ይጠበቅባታል፤ ይህ ካልሆነ ግን "የራስዋ አሮባት የሰው ታማስላለች" እንዳይሆንብን እሰጋለሁ። እነዚህ የአፍሪካ ሀገራት ነገ እናት ቤተ ክርስቲያንን እንጎብኛት፤ ሄደንም በረከት እናግኝ ብለው ሲመጡ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻውን እና እምነት መሸርሸሩን ሲያዩ የሚፈጠርባቸው የእምነት ቀውስ ቀላል እንደማይሆን ማሰብ መቻል አለብን።
ReplyDelete