Tuesday, November 4, 2014

ስድስተኛው ዘመነ ፕትርክና፡- ከመጥበሻው ወደ እሳቱ ወይስ ከእሳቱ ወደ መጥበሻው ?


አንድ አድርገን ጥቅምት 26 2007 ዓ.ም
ከታደሰ ወርቁ
የመንፈሳዊነት ልምላሚ እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የወለዳቸው ጎሰኝነት- ብልሹ አሠራር- ንቅዘቅ- ብኩንነት- ምዝበራ የአምስተኛው ዘመነ ፕትርክና ገጽታ ነበሩ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የደከሙበትን የሽበት እንጀራቸውን ለመብላት ያልታደሉበትና ይልቁንም የተሰቃዩበት ነበር፡፡ ተቋማዊ ቀውሱም ተባብሱ በመቀጠሉ ምእመኑም ሐቀኛ የኾነ ፓትርያርክ ሲሻ የኖረበት መልካም አባት እንዲኖረው ጸሎት ከማድረስ እስከ ትግል መሥዋዕትነት የከፈለበት ነበር፡፡

በዚኽ የመከራ ፍጻሜ ዘመን ላይ ደረስን ባልንበት ስድስተኛው ዘመነ ፕትርክና ላይም  መከራው ቀጥሏል፡፡ በዚኽም የተነሣ ‹‹ከመጥበሻው ወደ እሳቱ ወይስ ከእሳቱ ወደመጥበሻው? ›› የሚለው የወቅቱ ጥያቄ ኾኗል፡፡ የፈለግነውን ፣ የሚባልንን መልካም አስተዳደር ፣ ዘመናዊ የፋይናስ አያያዝ ፣ ከሙስና የጸዳ አሠራርን የሚያረጋግጥ አባት አገኘን ወይስ እስከናካቴው ቤተ ክህነት የሚባለ አስተዳደራዊ ተቋም ከመፈጠሩ በፊት በነበሩት ዓመታት እንደነበሩት ከቶውንም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥቅም የሚቆረቆሩ አባቶችን መናፈቅ ጀመርን?


የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ህልውና ከምንም ጊዜ በበለጠ አኳኃን ዛሬ የጨለማ ገጽታ ፣ የተስፋ ውድመት የሚታይበት ነው ወይስ የለመለመ ተስፋና የገነት ፍሰሐ? ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሐቃቸውንና መብታቸውን ሥልጣንን ሃይማኖት ባደረጉ ፓትርያርክና ሙሰኞች ተቀምተዋል ወይስ የዘመናት ሕልማቸው እውን ኾኖአል? ምኞታችንና ተስፋችን አንድ ታላቅ ቤተ ክርስቲያንና ሥልጣኔ፣ ፍትሕ የሰፈነባት ቤተ ክህነት ለመፍጠር እንዳልነበረ ኹሉ አሐቲነታችን ራሱ ነቀዝ እንደበላው ተክል፣ ጥንጣን እንደመደመደው ቤት እየተፍረከረከ የሚገኘው ለምንድነው?

የሽምብራ አፍንጫ… 
ኹላችንም ይኽች ቤተ ክርስቲያን የጋራ ቤታችንና የህልውናችን መሠረት መኾኗን በማያወላውል ኹኔታ ብናምንበት ኖሮ በአሐቲነታች፣ በተቋማዊ ነጻነታች በብሔራዊ ተደማጭነታችን ላይ ሳንካ ባልገባ ነበር፡፡ ይኽች ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ የሚፈልጉ ኀይላት ያጠመዱትን መረብና ሴራ ባሕርይ ለመገንዘብ የምንችል ብንኾን ኖሮ በልዩነቶቻችን ላይ አንዳች የነፋስ መግቢያ ቀዳዳ አንከፍትም ነበር፡፡ አንዳንድ አባቶቻችንም ኾኑ ወንድሞቻችን ከራሳቸው ጌትነት ይልቅ ለሥርዐቱ ሹማምንት ሎሌ መኾንን በመምረጥ ቤተ ክርስቲያናቸውንም ኦርቶዶክሳዊ ማንነታቸውንም እያዋረዱ ባልተገኙ ነበር፡፡ በዚኽም የተነሣ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ባለቤት የሌለው ተቋም በመኾንዋ ጴጥሮሳዊነትን እየተጣራች ይመስለኛል፡፡

በቅርቡ ታሪካችን ለቤተ ክህነቱ የዕድገቱና የልማቱ፣ የአንድነቱና የተስፋው ፋና ወጊ አባት ስላልነበረውና ስለሌለው ቤተ ክርስቲያን የየሥርዐቱ ባለሥልጣናት የጥላቻ ቅርሻት ማረገፊያ ከኾነች ውላ አደረች ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዚኽ የአብዮታዊ  ዲሞክራሲ ጠርዘኛ ትውልድ መዳፍ ውስጥም ኾና ታሪኳ አንድነቷ መሠረተ እምነቷና ሥርዐተ አምልኮዋ እየፈረሰ ነው  የሚል የብዙኃን ጩኸት ይሰማል፡፡ እስካኹን ድረስ የብዙኃን ግንዛቤ ይህን ጩኸት በሓላፊነት አዳምጦ መልስ የሚሰጥ ተቆርቋሪ ፓትርያርክ እንዳላገች እና ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ እንደሚያስፈልጋትም ነው፡፡

ከዚኽም ሲቀጥል የብዙ ሰዎች አመለካከት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዕደገት ረገድ ከሌሎች አኀተ አብያተ ክርስቲያናት ዕድገት አኳያ ጭራ የመኾንዋ ቁጭት ላይም ነው፡፡ በመጪው ክፍለ ዘመን ውስጥ ከመግባታችን በፊት ከዚኽ ትውልድ መካከል ያንን ወቅት ለማየት የሚታደለው እጅግ ጥቂቱ ብቻ ሊኾን እንደሚችልም ነው፡፡እውነታው ግን ወደ ዕድገትና ወደ ልማት መሸጋገር ቀርቶ ትልቁ ትግላችን ሐቀኛ ፓትርያርክ የመፈለግ ጥረት ሊኾን ነው፡፡ ይኽ ተስፋ መቁረጥ አይደለም፡፡ በፓትርያርክ ማትያስ የቅዱስ ሲኖዶስ እና የቋሚ ሲኖዶስ ልዕልናናሥልጣን ተገፍፏል፡፡የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሥልጣንና ተግባር በልዮ /ቤቱ ሓላፊ ተቀምቷል፡፡ አዲሱ ሐቅ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ የማስፈለጉ እውነታ ነው፡፡

በዚኽ የተነሣ የኦርቶዶክስና የኦቶዶክሳዊነት ምልክትና ተስፋ ጨርሶ እየጠፋ ከሚሔድበት ጐዳና ውስጥ የገባን ካልመሰለን ራሳችንን በከንቱ የምናጽናና እንኾናለን፡፡ ለምን? የኢትዮጵያ ሊቃውንት ለዘመናት የታገሉለት መንበረ ፕትርክና መምጣቱ ቀርቶ የሽምብራ አፍንጫ የሚያህል ባል እንደምትፈልግ ት ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ የመሾሙ ፍላጐት የጊዜያችንና የቤተ ክርስቲያናችን ትኩረት ኾኖአል፡፡

የደረቁ ሙሰኞች የሞሉበት ሸለቆ!
ከሰሞኑ ከአዲሳባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ  በድል አድራጊነትና መንበረ ፕትርክናውን በተቆጣጠርነው መንፈስ ከሰከሩትም መካከል ሲገለጥልን የነበረውና ከዚኽም ቀደም ባሎት ጊዚያት ሲነገረን የባጀው ‹‹እኛ እንዳሸን ያልተጠቀምንባት እና የማንጠቀምባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትባል አትኖርም ነው፡፡››

ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ የተሳሰረው ይኽ የቤተ ክርስቲያኒቱ አተራማሽ ኀይል ግብር ይኽንኑ ሳይገልጥ ያለፈበት ጊዜም የለም፡፡ ዛሬ ኦርቶዶክሳውያን የሚረዱት ደግሞ የኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ እጦት ይኽን እያባባሰው መሔዱን ነው፡፡ እነዚኽ ሰዎች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን መፍረስ ለምን እንደሚፈልጉ አብዛኛው ሰው እንደኔው አይገባውም፡፡የደከሙላትና እየደከሙላት ያሉት ሊቃውንትና ቤተ ሰቦቻቸው በድኽነት እየማቀቁ በችጋር ሲያልቁ እነርሱ ግን ከነንቅዘታቸውና አንቃዥነታቸው የሚደላቀቁባት ቤተ ክርስቲያን ነችና፡፡

 ዛሬ የቤተ ክህነቱን ፖለቲካ እንደምንገመግመው ከኾነ በዚኽ ጉዞና የጥፋት ማዕበል ውስጥ ወደ መጪው ክፍለ ዘመን የመግባታችን ምልክቱም ተስፋውም የጨለመ ነው፡፡ይኽም እንዳይኾን የዛሬን ያልተቆጠበ ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ ዳግም ወደ አምስተኛው ዘመነ ፕትርክና ጥፋት የመጓዝ ኹኔታም መቆም አለበት፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን ከማእሰረ ሰላም ወደ ማእሰረ ዐመፃ ለመቀየር እየተጉ ያሉት ፓትርያርክ  ማትያስም ኾኑ ዓላማዬን ያስፈጽሙልኛል ያሏቸው የደረቁ ሙሰኛ አማካሪዎቻቸው ከቀኖናዊ ቅጣቱ ጎን ለጎን በአገሪቱ ሕግ አደብ እንዲገዙ መደረግ ይኖርበታል፡፡

ቤተ ክህነቱ የደረቁ ሙሰኞች የሞሉበት ሸለቆ መኾኑን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያኒቱን በጠላትነት የሚመለከቱ ኀይሎች የፈለጉትን ሊገልጹና ምንደኛ ሹማምንትን ቀጥረው አዲስ የፈጠራ ድርሳን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይኽ የሚጠበቅ ነው፡፡የሚገርመው ግን ጮኸታቸውን ተቀብለው እንደገደል ማሚቱ የሚያስተጋቡት ጥቂት አባቶች ናቸው፡፡ ከቶውንም የእነዚኽ አባቶች ጮኸት መብዛቱ አፈ ቀላጤነታቸውና የታሪክ ቅልበሳ ሥራቸው የመባባሱን ጉዳይ ነው የሚገልጥልን፤ ይኽች ቤተ ክርስቲያን ጠባቂና ተሟጋች እየተጠራች መኾንዋንም ጭምር ፡፡

ቤተ ክርስቲያንን የማያውቁ የ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› ሰዎች !
የአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ ቅዱስ ሲኖዶሱ ራሱ ነው ቢባልም በግንባር ቀደምነት ለቤተ ክርስቲያን የቆምኹና የምመራው፣ የማውቅላትና የማውቃት እኔ ነኝ የሚለው ፓትርያርክ ነበር፡፡ ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕመም የሚያውቅ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን የጉዞ አቅጣጫ የሚያሳይ፣ በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል ልዩነት ሳይኖር በኦርቶዶክሳዊ አንድነትና ጥቅም አንጻር ብቻ የሚያይ ነበር፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የፕትርክና ሢመት ርካብ የያዙት ሰው ይኸ ኹሉ ኦርቶዶክሳዊ አጀንዳ ያላቸው ናቸው ወይስ አንድ ቀን ይኽች ቤተ ክርስቲያን የራሷ እውነተኛ ፓትርያርክ ሊኖራት እንደሚችል ‹‹ሕልም ዐያለሁ›› የሚል ጮኸትና ዋይታ እንድናሰማ ምክንያት የኾኑን?

ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቻው፤ ቤተ ክርስቲያንንም የማያውቁ፣ የቤተ ክህነቱ ሕመም ያልተሰማቸው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕልም ያልተረዱ፣ ይኽች ቤተ ክርስቲያን ወዴት መጓዝ እንደሚገባት ያልተገነዘቡና በጉልበት ብቻ በመንበረ ፕትርክናው ላይ የተፈናጠጡ መኾናቸውን ራሳቸውም ጀሌዎቻቸውም አያውቁም አልልም፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፓትርያርክ ምእመኑ ወንጌል እንዳይመገብ፣ ሊቃውንቱ ማኩረፊያ ጎጆ ገላቸውን የሚደብቁበት ልብስ እንዳያገኙ የሚከለክል ከኾነ ራሱም የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው፡፡ ፓትርያርክ ማትያስ ከማኀበረ ቅዱሳን ጋራ የጀመሩት እሰጣ ገባ የዚኹ እውነታ ነጸብራቅ ነው ቢባል ማጋነን አይኾንም ፡፡

አንድ ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያን ለመኾን የቤተ ክርስቲያንን ፈቃድ በቀኖናዊ ምርጫ ማግኘት አለበት፡፡ ዛሬ አብዛኛዎቹ ሊቃውንት ሲናገሩ እንደሚሰማው የወጡበት መንገድና ባሕርያቸው ራሱ  የማይፈቅድላቸው መኾኑን ›› ነው፡፡

ከዚኽ በፊት ተደጋግሞ እንደተገለጸው ፓትርያርክ ማትያስ ፅልመታዊ ቡድኑን በተመለከተ በሚከተሉትና በሚያራምዱት ጎሰኛ አቋም የተነሣ ባለፈው አንድ ዓመት ሲተቹም ነበር፡፡ በዚኽ ረገድ በተፈጠረው አስተዳደራዊና ተቋማዊ ቀውስ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊ አንድነት ለድርድር አቅርበዋል፡፡በዚኽም የተነሣ ብዙው ኦርቶዶክሳዊ እንደማይፈልጋቸው በግልጽም በስውርም እየወሰነ ነው፡፡ ደገጡሮቻቸውም እያደመጡ ነው፡፡ ለፓትርያርኩም የራሳቸው ጆሮ ባዕዳ ኾኖባቸዋል አልልም፡፡ በደንብ ይሰሙበታል፡፡

 በቤተ ክህነቱ የደመወዝ ትክለኛ ኾኖ ፓትርያርኩን መገዳደር አደገኛና ከባድ መሥዋዕትነት የሚጠይቅ መኾኑን በመረዳት ከውጭ ኾነው የሚጯጯኹ ሊቃውንት ቁጥር በየዕለቱም እየጨመረ ነው፡፡ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ ማምጣት -ማስገኘ-ማብቃት አለብን፤›› እያሉም ነው ፡፡ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ ሲባል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ለማለት ነው፡፡

የሰብዐ ዐይን ቅኝት
 በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክነት ስም ያሉት ፓትርያርክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና-ክብር-አንድነትና ገበና የሚከላከሉ ናቸው ወይስ መንበረ ፕትርክናውን ከያዙ ወዲኽ የሚያሸበሽቡት በሥርዐቱ ሰብዐ ዐይን ቅኝት የተቀነባበረ ነው? በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ታሪክ ኪሣራ የሥርዐቱን አዲስ ታሪክ የሚጽፉም ኾነዋል፡፡ መራራው ነገር ስለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመናገር የሚፈልጉት ከውጭ መኾናቸውና እዚኽ ያሉት ግን ድምፃቸው በሰበብ አስባቡ መታፈኑ ነው፡፡ይኽም በቤተ ክህነቱ እንደ ነቢያት የተናቁ፤እንደ ሐዋርያት የተጠቁ ሊቃውንት ቁጥርን እያበራከተው ነው፡፡

ይኽ የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንቢ ኀይላት፣ የአሐቲነቷ መከታ ኾኖ የኖረውን የሊቃውንት ኀይል በማግለል ብቻ ያለተገቱት ፓትርያርክ ማትያስ፤ቋሚ ሲኖዶስ የውሳኔ ድምፁን ባለሳረፈበት ኹኔታ፣ የፅልመታዊ ቡድኑን ፈቃድ ለመፈጸም ከሥልጣናቸውና ከቀኖናዊ ይዘታቸው ውጭ በመሔድ፤ ባልተሰጣቸው  ሥልጣን የአዲስ አበባ አድባራትንና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን   መሰብሰብ፣ ማዘዋወር ተያይዘውት ነበር፡፡

ይኽም ርምጃቸው ቀናዒ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን የአገልግሎት እንቅስቃሴ በመግታትና የቤተ ክርስቲያኒቱን ተጻባይ ኀይላት ኅበርት እስከ መመሥረት መስሎም ታይቷል ፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች (በተለይ ፓትርያርክ ማትያስ) ከኦርቶዶክሳዊነት ይልቅ ጐሳዊነትን በማስቀደም በአገራዊነት አመለካከት አርአያነት የነበራትን ቤተ ክርስቲያን በጎሳዊነት መከፋፈላቸውም አስተችቷቸዋል፡፡እያስተቻቸውም ነው፡፡ ትችቱን የሚሸከም ትከሻ ያላቸውን ያህል አንዳችም ለውጥ አምጥተው አያውቁም፡፡ ጎሰኝነት መታየትም መገኘትም በማይገባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሠራፋ በማድረግ የተወገዙባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው፡፡ከአሜሪካ እሰከ ኢየሩሳሌም ከዚያም አኹን እስካሉበት ድረስ ፡፡ እርሳቸው ግን ለተቀመጡበት ሢመት ይቅርና ለእርግናቸው እንኳን በማይመጥን ጀብደኝነት ‹‹ እቀጥልበታለው ›› ብለዋል ፡፡ከዚኽ አኳያ በታላቅ መሥዋዕትነት የተመሠረተችውና የዕውቀትና የሥነ ምግባር ምንጭ የኾነች ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ የትነች? ሠልስት ያልወጣላት፣ አርባ ያልተደገሰላት ምውት ኾናለች የሚያሰኝ ነው፡፡

የመንጋው እምነት ያላረፈባት አባትነት መንጋውን እያሸሸበት የሚሔድ ብቻ ሳይኾን መንጋውን የእረኛው ቁስለኛና ሰለባ እያደረገው መሔዱንም መካድ የሚቻል አይደለም፡፡ የእረኛው ሰለባ የኾነ መንጋ የቆሰለ አውሬ ዐይነት ነው፡፡ እረኛው አብሮት ሊተኛም ሊጓዝም አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንድ አዳኝ ካቆሰለው አውሬ ጐን ሊተኛ ወይም ጐን ለጐ ሊራመድ አይችልምና ነው፡፡

  እንዲኽ ዓይነት እረኛ በአካለ ሥጋ ለቤተ ክርስቲያን ቅርብ ከእግዚአብሔር ግን ሩቅ ነው ማለት ነው፡፡ ይኽ ምን ማለት ነው? ራሱን ከመንጋው የሚጠብቅ እረኛ ነው ያለን ማለት ነው ፡፡ በዚኹ ልክ መንጋውም ራሱን ከእረኛው የሚጠብቅ ይኾን? አቅም የለውም እንጂ ነገሩ እንዲያነው፡፡እናም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ እየዋሉ ከእግዚአብሔር እና ከኦርቶዶክሳዊ እሴቶች የራቁ ናቸው ለማለት እደፍራለኹ፡፡

ታላቋ ቤተ ክርስቲያናችን በየጊዜው እየወደቀች የሔደችው በምእመኑ ስንፍና፣ በእምነትና በኦርቶዶክሳዊ ሕልም ዕጦት ብቻ ሳይኾን በአባቶቻችን ድክመት መኾኑን መካድ አይቻልም፡፡ ምናልባት ራሳችንን መጠየቅ የሚገባን ጆሮአችንን አደንቁረን ቤተ ክርስቲያናችን ስትመዘበር፣ አንድነቷ ለድርድር ሲቀርብና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ሴራ ኹሉ ሲፈጸምባት እንዳላዋቂ ስንመለከት ኖረን እንደኾነ ነው፡፡

ከታሪክ እንደተረዳነው ጠባቂ የሌላት ቤተ ክርስቲያን የተዋረደችና የተናቀች ለመኾን ትበቃለች፡፡ ቤተ መንግሥቱ መሪዎቿንና ምእመኗን የናቀ፣ ቤተ ክህነቱም ከቤተ ክርስቲያኒቷ የራቀና ሃይማኖትን የማይጠብቅ ከኾነ፣ ፓትርያርኩም ለምእመኑ የማይጨነቁ ከኾኑ ቤተ ክርስቲያን ያለጠባቂ፣ እምነት ያለተከባካቢ ቀሩ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ቤተ ክርስቲያን መከበር ይቀርና ቤተ ሐኖት ትኾናለች፡፡ ገመናም የላት፡፡ባለቤት ከሌላት ገመናዋን ማይ ይጠብቅላታል ? በኢትዮጵያ የኾነው ይኸው ነው፡፡

እነ አባ ከርሡና እነ ደብተራ ክብሪት
በምልዓተ ጉባኤው እንደተወሳው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክብሯ ተደፍሮ እንደ ንቡረ እድ ኤልያስ ያሉት ምስለኔዎች በተለያዩ ጊዜያት ሀብቷን ለመዘረፍ ይልቁንም ልዩ /ቤቱን ለመያዝ የተደፋፈሩት በጊዜው ጠባቂና መልካም አባት በማጣት ነው፡፡ ከዚኽ አሳብ ጋር ሊታከል የሚገባውና በብዙ ዘመን ልምድ የታየውም በየጊዜው ጥቅምዋን፣ ገመናዋንና ምስጢሯን ለአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የሚሸጡ እነአባ ከርሡና እነደብተራ ክብሪት መከሰት ነው፡፡

ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወር ለጊዜያዊ ጥቅም ቤተ ክርስቲያናቸውን አሳልፈው የሰጡ ጳጳሳት ነበሩ፡፡ በወረራው ወቅት ለአገራቸው እና ለቤተ ክርስቲያናቸው ክብርና ልዕልና ከአርበኛው ጋር ተደባልቀው  የተዋደቁ የመኖራቸውን ያህል ከጣሊያን ጐን ተሰልፈው ከቤተ ክርስቲያን አልፈውም አገራቸውን የወጉ ነበሩ፡፡ ፋሽስት ጣልያን መላዋን ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር በተነሣች ጊዜም ቢኾን መንገድ መሪ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገመና ከፋች ኾነው ጠላትን ጐትተው ያሰገቡ ውስጥ በቀል ጠላቶች እነአባ ከርሡና እነደብተራ ክብሪት ነበሩ፡፡

 ለኢትዮጵያዊነትና ለኦርቶዶክሳዊነት ክብርና መብት የታገሉና መሥዋዕት የኾኑ በርካታ አበው የነበሩትን ያህል ከጠላት ጐን ተሰልፈው ቀናዒ አባቶቻችንን፣ አርበኞቻችንን ሲያሳድዱ የኖሩ ባንዳዎችም ብዙዎች ነበሩ፡፡ ዛሬም በመንፈስም በሌላ ቅርጽም እያየናቸው ነው፡፡ ዛሬም ለጥቃቅን ጥቅምና ጊዜያዊ ደስታ የቤተ ክርስቲያን ጥቅም፣ አንድነትና ኦርቶዶክሳዊ ክብር እየተሸጠ የተገኘበትን ኹኔታ በአዲሳባ አበባ አገረ ስብከት የመሰብሰቢ አዳራሽ በተሰበሰቡት የአጥቢያ ሙሰኞች ላይ ዐይተናል፡፡

በዚኽ መነሻ ብቻ ባለፈው ሃያ ሦስት ዓመት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ኹኔታ ስናጤን ቤተ ክርስቲያኒቱም፣ አንድነቷም፣ ክብሯም ምንኛ ሲሸጥ ሲለወጥ እንደኖረ እንገነዘባለን፡፡ አራተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ደርግን ሰማያዊት ኢየሩሳሌም አድርገው በመገመት የቤተ ክርስቲያንን ጥቅም ለሥርዐቱ አስገዝተው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጓዳና ጐድጓዳ ለሰው በላው መንግሥት ከፍተው እስከመሰጠት ደረሱ፤ ይኽ እርሳቸውን ብቻ ሳይኾን በእርሳቸው ዙሪያ የነበሩትን የቤተ ክህነቱን ገላግልት ባንዳዎችን ኹሉ ይመለከታል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ከአንድ አምባገነን መንግሥት እግር ሥር በመጣላቸውና የቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ መንበር እና ሲኖዶሳዊ ልዕልና በማዋረዳቸው  ሲወገዙም ነበር፡፡ በእርሳቸው እግር የተተኩትም ፓትርያርክ ጳውሎስም ቤተ ክርስቲያኒቱ የጋለሞታ ቤት ይመስል ማንም እንደፈለገው ሲኾንባት፣ በአዱኛዋ ከልጅቿ ይልቅ ባዕዳን የሚያዝዙበት ስትኾን አባሪ ተባባሪ ነበሩ፡፡ ይኼ ዛሬም ያልተዘጋ ምዕራፍ ይመስለኛል፡፡ ልዩነቱ የፓትርያርክ ለውጥ መደረጉ ብቻ ነው፡፡ የሐቀኛ ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ አስፈላጊነት የሚሰማንም በዚኽ የተነሣ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተፈታችና አሐቲነቷን እንዴት ልታስከብር እንዳልቻለ ይጠይቃሉ፡፡ መብታቸው ነው፡፡ በመልስ መልክ አንድ ነጥብ አለኝ፡፡ ጠላቶቿ የበለጠ ጉልበትና ሐቀኛ ዓላማ ስለነበራቸው አይመስለኝም፡፡ የዕለት ጥቅምና ደስታ የመጨረሻው የሕይወት ትሩፋት ነው ብለው የሚያምኑ አንዳንድ አባቶች በጥቅም እየተታለሉና፣ በጎጠኝነት ክር እየተጐተቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን አሳልፈው መስጠታቸው ይመስለኛል፡፡ የማዝነው ብዙዎች ሐቀኞች ከእነዚኽ ደካሞች ጐን ወደፊት በታሪክ ውስጥ ተወቃሽ ሊኾኑ መቻላቸው ነው፡፡

ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርኩት ይኽች ቤተ ክርስቲያን በፓትርያርክነት ወይም በሊቀ ጵጵስና መንበር ያገኘቻቸው አበው ኑሮአቸውን ለማመቻቸት፣ ተንደላቀው ለመኖር በነበራቸው ፍላጐት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱንና የተቀመጡበትን ሐዋርያዊ መንበር ረግጠው እንደ ኖኅ አሞራ ጥንብ  /ሀብትና አዱኛ/ ፍለጋ ሲልከሰከሱ ሐዋርያዊ ክብርና ልዕልና ከዳቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሔደች ፤ህልውናዋ ላይም የሞት ድባብ አጠላ፡፡

በተለያዩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ወቅት አንዳንድ አባቶች፣ አንዳንድ የቤተ ክህነቱ ጥቁር ራስ ሹማምንት፣ አንዳንድ ሰብኣ ዐይኖች በደካማነት በፈጸሙት በደል ዛሬ ይኽችቤተ ክርስቲያን ባለቤት አልባ ከመኾን ደረጃ እንደደረሰች ነው የሚሰማኝ፡፡ ሌላው ቀርቶ ህልውናችን ከአጠራጣሪ ደረጀ ላይ ከሚገኝበት አሳዛኝ ዘመነ ፕትርክና ላይ እንገኛለን፡፡ከዚኽም ሲልቅ ስለኦርቶዶክሳዊነት፣ ስለቤተ ክርስቲያን አሐቲነት መናገር እንደ ወንጀል በሚታይበት ዘመነ ፕትርክና ላይ ደርሰናል፡፡

ለዚኽ ብዙ ብዙ መዘዝና ምክንያት መደርደር ቢቻልም የቤተ ክህነቱ ደካማ ሹማምንት ቤተ ክርስቲያኒቱን በመሸጣቸው፣ ንጹሐን ነን የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳን ጉልሕ የኾነ መሥዋዕትነት ባለመከፈላቸው ነው ፡፡ኹላችንም ከተወቃሽነትና ከተጠያቂነት ልንድን የምንችል አይመስለኝም፡፡

በታሪክ እንደተረዳነው ያለፉት አርባ ዓመታት አባቶቻችን አንዱ ለአንዱ ሥርዐተ መንግሥት፣ ሌላው ለሌላው ሥርዐተ መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ልዕልና ለመሸጥ  ሲሽቀዳደሙና ሲጫረቱ የነበረበትን ኹኔታ ያስረዳል፡፡ ከአንድ የጥናት ወረቀት ላይ እንደተገነዘብኩት ከኾነ በእነዚኽ ዓመታት ውስጥ መንበረ ፕትርክናውን የተቆጣጠሩት አንዳንድ አበው ለየ ሥርዐተ መንግሥታቱ የስለላ ተቋማት ብቻ ሳይኾን ከሶቪየቱ .. እስከ አሜሪካው .አይ. ድረስ የሚሠሩ ይገኙበት ነበር፤ አሉ፡፡ እነዚኽ አበው የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያንን የምስጢር ጓዳ የሚያውቁና በብዙ ውሳኔ ውስጥም ተሳታፊ የነበሩ ናቸው፡፡

ሲኖዶሱ ከላእላይ መዋቅሩ ውስጥ እንዲኽ የቤተ ክርስቲያን ምስጢርና ክብር እያዋረዱ በሚከብሩ አበው ጉያው እየሞቀው ሳለ በታኅታይ መዋቅሩ የሓላፊነት ደረጃ ላይ ያሉትን የቤተ ክህነቱን ሠራተኞች ለማኅበረ ቅዱሳን  ይሰልላሉ በማለት ከባድ ከባድ ርምጃ ሲወሰድባቸው በዝምታ ሲያልፍ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡

በዚኽ ኹኔታ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ደግሞ ከየማዕዘኑ ከመፈረካከስ ባሻገር ገመናዋን የሚጠብቅ ሲኖዶስ፣ የሃይማኖት ድንበርዋን የሚከላከል ፓትርያርክ የላትም፡፡ ሥርዐተ አምልኮዋን የሚከላከል አባት የላትም፡፡ እነዚኽ አሉ ከተባሉ በዚኽ የጥቅምት ቅዱሰ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ ፍጻሜ ለማየት ምኞቴ ነው ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለው ቤተ ክህነት በተግባር የታየው አንድ ፓትርያርክ በሌላው እግር የሚተካው ባለው ሃይማኖታዊ ጥብዐት እና የቤተ ክርስቲያናዊ ርእይ አይደለም፡፡ ያለፈው ፓትርያርክ መሠረታዊ ታሪካዊ እውነታዎችን መዘንጋቱን መጠቀሚያ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ፓትርያርክ ማትያስም ያደረጉት ይኽንኑ ነው ፡፡

ወሬ ብቻ !
 እናም በያዝነው ስድስተኛው ዘመነ ፕትርክና ወሬ በዛ፤ተግባር ግን የለም፡፡ፓትርያርክ ማትያስ ራሳቸው ሰለመንፈሳዊነት ያወራለ፤ በተግባር ግን የሉም፡፡ፓትርያርክ ማትያስ ራሳቸው ሰለጎሰኝነት ያወራሉ፤በተግበር ግን የሉም ፡፡ ፓትርያርክ ማትያስ ራሳቸው ሰለሙስና ያወራሉ፤በተግባር ግን  የሉም፡፡ፓትርያርክ ማትያስ ራሳቸው ሰለመልካም አስተዳደር ዕጦት ያወራሉ፤
በተግባር ግን የሉም፡፡

የፓትርያርኩን ተግባር ያጣው ምእመን ‹‹ፓትርያርክ ማትያስ መንፈሳዊነት የለም፣ገሰኝነት አለ፣ሙስኝነት አለ፣መልካም አስተዳደር የለም  ብለው ሲያበቁ ርምጃ የማይወስዱት ለምንድ ነው ?>>  እያለ ነው ፡፡እውነትም ነው፡፡‹‹ዓለማዬን ያስፈጽሙልኛል›› ያሏቸው የፅልመታዊ ቡድኑ አባላት በመንፈሳዊነት ነቀፋ ያለባቸው፣ በጎሰኝነታቸውና በሙሰኝነታቸው ቤተ ክርስቲያን ያጠፉ፤ የመልካም አስተዳደር ፀሮች መኾናቸውን እያወቁና እያመኑ ለምን ርምጃ አይወስዱም ?

በዚኽም የተነሣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ኾኑ ምእመናን የራሰቸውን ድምዳሜ እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡ ይኸውም ‹‹ ርምጃ የማይወስዱት ራሳቸው መንፈሳዊ ድቀት ሰላገኛቸው፤የሙስናውም ኾነ የጎሰኝነቱ ተከባካቢ በመኾናቸውና የመልካም አስተዳደርን ዕጦት እያባባሱ በመኾናቸው መድፈር አቅቷቸው ነው፤›› እያሉ ነው ፡፡ እንዲኹም ‹‹ለመንፈሳዊ እሴቶች መከበር በተግባር የቆሙ ባለመኾናቸው ለእነዚኽ እሴቶች ሥር መያዝ ጠንቅ በኾኑት ላይ ርምጃ መውሰድ አይችሉም ›› እያሉም ነው፡፡

ለዚኽም ነው ፓትርያርክ ማትያስ የደብር አለቆችንና ጽሐፊዎችን ሰብስቦ መግለጫ ከማውጣት አልፈው፣ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የመዋቅርና አደረጃጀት ጥናትን ከማጣጣልና ማኀበረ ቅዱሳንን የኦሪት ፍየል ለማድረግ ከመወራጨት ታዓቅበው እንደ አንድ አርቆ ተመልካች አባት ‹‹ይኸው የመንፈሳዊነት ማበልጽጊያ ስልቴ፣ ይኸው የሙስናውም ኾነ የጎሰኝነቱ ርምጃዬ ፣ይኸው የመልካም አስተዳደር ርምጃዬ ይኸው የተቋማዊ ለውጥ ርምጃዬ ›› ብለው በተግባር እንዲያሳዩን የምንለው፡፡

እንዲኽ ዐይነት ርምጃ በቆራጥነት ባለመውሰዳቸው በቤተ ክህነቱ አስተዳደር አማሳኝ አንቃዦች መዋቅራዊ የበላይነትን እየያዙ መጡ ፡፡የበላይነታቸውንም በመጠቀም ከልዩ /ቤት እሰከ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያን የተዘረጋ የሥርዐት አልበኝነት ሰንሰለት ዘረጉ ፡፡የሥርዐት አልበኝነት ሰንሰለት የሚያቆራኘው ደግሞ በአዲስ አበባ አገረ ስብከት የመስብሰቢያ አዳራሽ ተሰብሰበው ‹‹በድመቷ አንገት ላይ ቃጭሉን ማን ይሠረው ›› ሲሉ እንደነበሩት ያሉትን የሙዳይ ምጽዋት አይጦችን ነው ፡፡ በዚኽም ምክንያት ወንጀል ፣ምግባረ ብሎሽነት ጎሰኝነት-ሙሰኝነት ግጭት ፍርሐትና ሥጋት የነገሠበት ቤተ ክህነትን ለመጪው ትውልድ የማውረስ ጉዟቸውን ‹‹ በእቀጥልበታለው እብሪት ›› አጧጥፈውታል ፡፡ዳግም ‹‹ፓትርያርክ ማትያስ ኾይ ከወሬ ወደ ተግባር ይሸጋገሩ ›› የሚባሉት ለዚኽ ነው ፡፡

ስደተኛው ዘመነ ፕትርክና በዚኽ ሒደት የሚቀጥል ከኾነ ይህ ትውልድ ምናልባት ተቋማዊ ነጻነቷና ልዕልናዋ የተከበረላትን ቤተ ክርስቲያን እና የራሱን ሐቀኛ ፓትርያርክ በምንም መልኩ ለማየት የሚቻለው አይኾንም፡፡ ውትወታም ማካሔድ የሚገባን ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክና ሲኖዶስ እንዲኖረን መኾን አለበት፡፡ ዛሬ ከምን ጊዜውም የበለጠ ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እሴቶች የተገኝ ከኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት ማኅፀን የተወለደ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን አባታዊ አመኔታ ያለው ፓትርያርክ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ችግርዋን ፓትርያርኩ ከሲኖዶስ ጋር ኹኖ ሊፈታ ይችላል፡፡

እናም
 ጠንካራ ፓትርያርክ እንፈልጋለን፤ተጠናክሮ የሚለውን የሚተገብር፤ተጠናክሮ መልካም አስተዳደርንና ፍትሕ ርትዕን የሚያሰፍን ፤ተጠናክሮ ሙሰኝነትንና ጎሰኝነትን የሚያስወግደ፤ተጠናክሮ ብሔራዊ ልዕልናችንና ክብራችን የሚያስጠብቅ ፤ተጠናክሮ ብሔራዊ ተደማጭነታችንን ከፍ የሚያደርግ ፤ተጠናክሮ ተቋማዊ ለውጥንና ምናኔያዊ ልማትን እውን አድርጎ በችጋር እየማቀቁ ያሉትን ካህናት ሕይወት የሚታደግ ፓትርያርክ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትፈልጋለች፡፡ሊቃውንቱ ይፈልጋሉ ፡፡ ምእመኑ ይፈልጋል ፡፡ይኽ ኹሉ ግን እውን እንዲኾን ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመጥበሻው ወደ እሳቱ እያሸጋገረ ያለውን ስድስተኛውን ዘመነ ፕትርክና በቀኖና አበውና በሕግ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌዎች መሠረትነት መገላገል አለብን ፡፡




10 comments:

  1. እውነት ነው ኦርቶዶክሳዊ ፓትርያርክ እንፈልጋለን፡፡ ስለ እውነት፣ ለእውነት፣ በእውነት የሚኖር አባት እንፈልጋለን፡፡ ለጽልመት፣በጽልመት የሚኖር አባት የኦርቶዶክሳዊያን አባት መገለጫ አይደለም፡፡

    ReplyDelete
  2. The Church is led by the Synod, and the synod is working the right way. The Church is not led by few polarized deber leaders and clapping. The synod has ruled the right way. Furthermore we have to see the Church beyond the management and the hierarchy and the Church continues to prepare souls to heaven despite the challenges. So no dispair.

    ReplyDelete
  3. Although some errors are commuted the Holy Synod has controlled it. We shall continue to pray sothtat God shall give for our Father the wisdom to lead EOTC rather than reflecting emotions!

    ReplyDelete
  4. ጠንካራ ፓትርያርክ እንፈልጋለን

    ReplyDelete
  5. ስደተኛው ዘመነ ፕትርክና በዚኽ ሒደት የሚቀጥል ከኾነ ይህ ትውልድ ምናልባት ተቋማዊ ነጻነቷና ልዕልናዋ የተከበረላትን ቤተ ክርስቲያን እና የራሱን ሐቀኛ ፓትርያርክ በምንም መልኩ ለማየት የሚቻለው አይኾንም፡ i agree

    ReplyDelete
  6. ጠንካራ ፓትርያርክ እንፈልጋለን

    ReplyDelete
  7. የቤ/ክ እና አባቶችን ክፉ ለመናገር ብቻ በአደባባይ መሰየም ይበቃናል፡፡ድሮ ብዙ ስትጮኹ ችግሩ ከአቡነ ጳውሎስ መስሎን አብረናችሁ ጀፍ-ጀፍ ብለናል፡፡አሁን ስናጤነው ግን በማኅበሩ ወገንም “ከኔ በላይ ላሳር” ባይነት መግነኑን ታዘብን፡፡ከእንግዲህ ወዲያ ባለዲግሪ ዲያቆናት አይሳሳቱም እያልን በሐሜት ጎዳና ተከትለናችሁ አንዘምትም፡፡አባቶቻችንን ከነደካማ ጎናቸው ተቀብለን እናግዛለን፡፡በየጋዜጣውና በየብሎጉ ስንሰቅላቸው አንውልም፡፡ካለፈው ዘመን መጠላለፍ ምንም አላተረፍንም፡፡እንታረማለን፡፡ከቻልክ ዲያቆን ታደሰ ወርቁም ተከተለን፡፡ስድብ የሚያነጽ ከመሰለህም “ጉዱ ካሳ፣ከኅለተሙሴ ወደ ኅለተ ወርቅ” እያለ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት አልሞ (ቤተመንግሥቱንና ቤተክሕነቱን) እና ጥላቻን ምሁራዊነት ለማልበስ በሚጥር ብእር ማተትህን ቀጥልበት፡፡እኛ ግን አንሰማህም፡፡
    ድስቱ ከነመጥበሻው ተቀይሮለት ማብሰል ያልቻለን ተውት፡፡ሆዱ ሲጮኽ ይኑር፡፡

    ReplyDelete
  8. መቼ ይሆን ከዚህ ግራመጋባት የምንወጣው?.....ለዚች ቤተክርስቲንያን የሚበጀውን በምን አግባብ መለየት ያቅታል ?.....ምእመኑስ ይህን አውቆ መቼ ይሆን አላግባብ የሆነውን ይቁም የሚለው?.......እውነት ዛሬ ካህናቱ ምን እየሰሩ ነው?...ክህነታቸውን መጠበቅ ተችላቸዋል?...የቤተመቅደሱ አገልግሎት መንፈሳዊነት አለበት…….መንግስት ቤተክርስቲያን ላይ እየሳደረ ላለው ተጽኖ ማን አድብ እያለ ነው?.......ታድያ እነዚህ ችግሮች ሳይታዩ እውነት ማህበረ ቅዱሳን የቤተክረስቲያን ችግር ነው እንካን ቢባል የማህበሩ ችግር ብሶ ነው?.......እኔ እንካን በግሌ እስከማውቀው ከማህበሩ ጋር ጠብ ያለበት የሃይማኖት ችግር ያለበት ለመሆኑ ነጋሪ አልፈልግም

    ReplyDelete
  9. እኔ ግራ የገባኝ የኢትዮጲያ ፓትርያሪከ ለምን በነገስታተ ይመረጣሉ በነገስታቱ ከተመረጡ ለእነሱ ፍላጎት አሳልፎ ይሰጣቸዋል። ሐዋርያት መሰርተዋታል ሐዋርያት እንዳደረጉት መከተል አለብን። ሐዋርያት በዩሁዳ ምትክ ማትያስን ሲተኩ በጸሎት እና በዕጣ ነው። የሐዋርያት ስራ ምዕራፍ፧ ፩ ፧ ፳፫፦፳፮። የጌታን መንገድ ካልተከተልን ለፍላጎታችን አሳልፎ ይሰጠናል። ፈቃዱ በእኛ ዉስጥ አይፈፀምም። መንገዱ ጥርጊያው ይስተካክል፨፨፨

    ReplyDelete
  10. my name selam the Ethiopia , my comment is the patriarch is doing what he can also his best...one thing we all need to realize is he just got to his job a year ago .. aba mathias is the perfect ( MENKOSE) 4 this job..you and I have to leason and do what he ask to do.........also how are we to ???? what is our personality look like ,to talk about patriarch....................I am wishing him long live and a great secess in his job..............SELAME EGZIABHIER KE HULACHINIM GAR YIHUNNNNNNNNNNNNNNNNNNNNNNN .....selam from canada

    ReplyDelete