Monday, October 29, 2012

ለበረሃ ቤተክርስትያኖች መልዕክታችሁን አድርሰናል

(አንድ አድርገን ጥቅምት 19 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- በበረሀ ያሉትን ጥቂት አብያተክርስትያኖች ተመልክተናል ፤ ምዕመናን እንዲረዷቸው ለማድረግ ትንሽ ስራ በመስራት ጥቂት ብር አግኝተናል ፤ ይህን ብር ምን አይነት ነገር ላይ እንደዋለ ሰጪዎቹ ማወቅ ስላለባቸው ብሩ የተገዛበትን ንዋየ ቅዱሳት ዋጋቸው ያለበትን ደረሰኝ ብናቀርብ ሌሎች ለመርዳት ይነሳሳሉ የሰጡትም ሰዎች ብራቸው ምን ነገር ላይ እንደዋለ ይገነዘባሉ ፤ ለእነዚህ አራት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ለኮራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ፤ ለቦርደዴ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፤ ለቡቤ ኪዳነ ምህረትና ለቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያናት የሚሆን ከ12 ኪሎ ግራም በላይ አንደኛ ደረጃ እጣን ፤ 5 ኪሎ ዘቢብ ፤ 500 ደረጃው የጠበቀ የሰም ጧፍ ፤ 2 ሞጣሂት፤ መስቀል እና ለቤተክርስቲያ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በመግዛት ወደ ቦታዎቹ ተልኳል ፤ ከሁለትና ከሶስት ቀን በኋላም ንዋየ ቅዱሳቱ ለአብያ ክርስትያናቱ ይደርሳቸዋል ፤ በዚህ አጋጣሚ የተረዳነው ነገር ቢኖር እጣንና ጧፍ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠርባቸው ለወራት ሙቀትን መቋቋም ሲችሉ ዘቢብ ግን በሙቀቱ ምክንያት በየጊዜው እንደሚበላሽ ፤ እንደሚሻግትና አገልግሎት የማይሰጥበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ነው ፤ በዚህ ምክንያት ዘቢብ በአንድ ጊዜ በርከት አድርጎ በረሀ ላይ ለሚገኙ አብያተክርስትያናት ከመስጠት ይልቅ ዘቢቡ ስያልቅባቸው እንዲገዙበት መግዣ ብሩን መስጠት ያለበለዚያ ደግሞ በየጊዜው እርጥብ የሆነ ዘቢብ ገዝቶ መላክ የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ 

ከላይ የተላው  የጥቂት ወር ችግራቸውን ሊቀርፍላቸው ይችል ይሆናል ፤ አብያተክርስትያናቱ የሁለት ካህናትና የአንድ ዲያቆን ደመወዝ ሸፍነው በተረፈው ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟሉበት ዘወትር ደመወዝ በቋሚነት ሸፍኖ አገልጋዮችን ለተወሰነ ጊዜ ማቆየት እንዳልቻሉ ተመልክተናል ፤ ይህ እንዳለ ሆኖ የአካባቢው በረሃማነት ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ለጥቂት ወራት ተረጋግተው እንዳይቀመጡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል ፤ ቀድሞ ኮራ ገብርኤልን የሚያስተዳድሩት እና በቦታው ሆነው ቅዳሴውን የሚመሩት አባት በደመወዝ ችግርና በአካባቢው ሙቀት እና ሌሎች ምክንያቶች ተነሳ ቦታውን ለቀው በመሄድ በደቡብ ክልል ውስጥ የአናጢነት ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል ፤ ከእሳቸው በኋላ የመጡም አባት በአሁኑ ወቅት በቦታው አይገኙም ፤ እዚህ ቦታ ላይ ለሁለት ቄስና ለአንድ ዲያቆን በወር ከ2500 እስከ 3000 ብር መክፈል ለአካባቢው ከ30 የማይበልጥ ምዕመን  አስቸጋሪ ነው ፤ ይህ ሊሆን የቻለው አንድም አብያተክርስትያናቱ አንድም ተመልካች ስለሌላቸውና ሰዎቹ በረሃማነቱን ቢቋቋሙት እንኳን ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ደመወዝ መሸፈን አለመቻላቸው ነው ፤ ይህ የደመወዝ እጥረት በወር 70 ብር ለዘበኛ መክፈል ተስኗቸው የቤተክርስትያኑን ጠባቂ ዘበኛ በማሰናበት ባለቤቱ ራሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቤቱን እንዲጠብቅ አደራ ጥለው በሄዱ በዚያኑ ቀን ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ዘንዶ ዘበኛው ከተሰናበተበት ቀን ጀምሮ ዘወትር ማታ ማታ እየመጣ ቤተልሔሙ ላይ ተጠቅልሎ አድሮ እንደሚጠብቅና ሊነጋጋ ሲል ካህናት ኪዳን ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ተነስቶ ይሄድ እንደነበር በአስተዳዳሪው ተነግሮናል፡፡  
አንዲት ጧፍ 3 ብር
ጧፍ እና እጣን ለመግዛት ጥሩ ይሰራሉ ጥሩም ያቀርባሉ የተባሉበት ቦታ በመዟዟር ተመልክተን ነበር ፤ ከንዋየ ቅዱሳት መሸጫ ሱቆች ውስጥ ስንባክን የተመለከቱ አንድ አባት “ልጆቼ ጧፍ መግዛት ፈልጋቸሁ ነው” አሉን አዎን ብለን መለስንላቸው ፤ ከዚያ “ለገጠር አብያተክርስትያናት የምትገዙ ከሆነ በሰም የተሰራውን ብትገዙላቸው ጥሩ ነው ፤ ምክንያቱም ቀዩ ጧፍ በሚሰራበት ጊዜ ኬሚካል ስለሚጨምሩበት ለአባቶች አይን ችግር ያመጣል ፤ ያለእድሜያቸው አባቶችን አይን ላይ ችግር እየፈጠረ ይገኛል ፤ በየቀኑ ድርሳናት ፤ ተዓምረ ማርያም ወንጌልና እና መሰል መጻህፍት በሚያነበቡበት ወቅት ጧፉን ወደ መጽሀፍቶቹ አቅርበው ስለሚያነቡ ችግር አለው ፤ ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለው ጧፍ ረዥም ሰዓት አይቆይም ፤  የሰሙ ጧፍ ግን ንጹህ ከመሆኑ በተጨማሪ የተሻለ ሰዓት የመቆየት አቅም አለው ፤ እንደ ቀዩ ጧፍም ጭስ የለውም” ብለው አባታዊ ምክራቸውን በመለገስ ምን ማድረግ እንዳለብን መከሩን ፤ እኛም ምክራቸውን በመስማት የሰም ጧፍ የሚገኝበት ቦታ ተመለከትን ፤ ዋጋቸው ግን የሚቀመስ አይደለም ፤ በጅምላ አንዲቷን ጧፍ ከሶስት ብር ጀምረው እንደሚሸጡ ተረዳን ፤ የበፊቱን የጧፍ አይነት ለመግዛት አንድ ብር የሚባለው ጧፍ ውፍረቱ መርፌ ውስጥ ለማስገባት የቀጠነ ክር ይመስላል ፤ ሁለት ብርም የሚባለው የጧፍ አይነት የድሮውን ጧፍ ያስመኛል ፤ ጧፎቹ እጅጉን ሲሰሩ ቀጥነዋል ዋጋቸው ግን ወፍሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንድ ቀን ልዩነት 275 ብር የነበረው ጧፍ በሚቀጥለው ቀን ራሱን የሚሰራበት ጥሬ እቃ ጨምሯል በሚል ምክንያት 300 ብር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በጅምላ ዋጋ ከአንድ ቀን በፊት 400 ጧፍ ያህል በ2.75 ገዝተን አስቀምጠን ነበር ፤ ከአንድ ቀን በኋላ ግን መቶው ጧፍ ስንጨምር 300 ብር ሆኖ አግኝተነዋል ፤ በችቻሮ ሂሳብ በሰም የተሰራው በ12 ብር ሶስት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ለአንድ የገጠር ቤተክርስትያን ሁለት ሞጣሂት በ700 ብር ነበር የገዛነው ፤ አሁን ሁለት ወር አሳልፈን ዋጋውን ስንጠይቅ 886 ብር ደርሶ አገኝነው ፤ እቃውን ለመግዛት ብሩን በነጋታው ጠዋት ይዘን ስንመጣ ደግሞ 910 ብር ሆኖ አገኝነው ፤ ይህ አግባብ የሆነም ሆነ አግባብ ያልሆነ የዋጋ ቁለላ በዚህው ከቀጠለ መቀደሻ ያጡትን አብያተ ክርስቲያናት ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡  ድሮ የአንድን ቤተክርስትያን የዓመት መቀደሻውን ለማሟላት የሚወጣው ብር ዘንድሮ ሁለትና ሶስት ወር ያህል ራሱ የሚያዘልቅ አልሆነም ፤ ብሩ ዋጋውን ሲያጣ እቃዎች ደግሞ ጣራ እየነኩ ይገኛሉ፡፡
ንዋየ ቅዱሳት የተገዙበት ደረሰኞች




እነዚህ ቤተክርስትያናት ለመርዳት የቤተክርስትያናቱን የባንክ አካውንት አስቀምጡልን ያላችሁ ሰዎች በስተመጨረሻ ላይ በተቀመጠው የባንክ አካውንት በመጠቀም መርዳት ትችላላችሁ ፤ ቦታው ድረስ በመሄድ ቦታውን እንመለከታለን መርዳትም እንፈልጋለን ካላችሁ በተቀመጠው ስልክ ቁጥር በመደወል እንዴት ወደ ቦታዎቹ ማምራት እንደምትችሉ የተሻለ መረጃ ማግኝት ትችላላችሁ ፤ ለቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ክብረ በአል ሲከበር ጎራ ብለን እናያለን የአቅማችንንም ረድተን እናልፋለን ካላችሁም ከቤተክርስትያናቱ አስተዳዳሪ ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደምትችሉ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ቃል ለገባችሁ ቃላችሁን ትጠብቁ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡
የአርባ ቦርደዴ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን
የባንክ የሂሳብ ቁጥር 6329
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዋሽ ሰባት ኪሎ ቅርንጫፍ
አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ
ስልክ 0913-833532 (የአስተዳዳሪው የሞባይል ቁጥር)
ስለ ቡቤ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን…. ? ……? ..  ይጠብቁ
መሰል አብያተ ክርስትያናትን አሁን ስላሉበት ሁኔታ መረጃዎችን እናደርስዎታለን…
ቸር ሰንብቱ

No comments:

Post a Comment