Tuesday, July 17, 2012

መከራና ስደትን በቃችሁ ይበለን


ይህ ጉዳይ እንደ አንድ ዜጋ ሊያሳስበን ይገባል
ከጊዜ ለኩሉ

በታንዛኒያ የ43 ኢትዮጵያውያን ቀብር
(አንድ አድርገን ሐምሌ 11 ፤ 2004 ዓ.ም)፡- ከጥቂት የሰቆቃ ዜና እረፍት በኋላ ዳግም የወገኖቻችንን የስቃይ እና ሞት ባልተለመደ አኳኋን ካልተለመደ ስፍራ ሰማን። ከጊዜ ወደ ጊዜ ወገኖቻችንን እዚሁ እትብታቸው በተቀበረበት፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው፣ዘመድ አዝማድ ከሚኖሩበት ፣የልጅነት ትውስታቸው አሻራ ካረፈበት፣ የአመት በዓል ግርግሩ ከሚደምቅበት፣ ቅዳሴው በተመሳሳይ ከሚሰማበት……አገር ይልቅ የባዕዳንን ምድር እየመረጡ በስደት ሕይወት መከራቸውን መጋት ቀጥለዋል። በቀድሞ ጊዜ፣ በዚያ ትውልድ፣ በደጉ ዘመን ኢትዮጵያዊ መባል ኩራትና ክብር እንዳልነበር ሁሉ አሁን የማንም መሳቂያና መሳለቂያ ለመሆን በቃን። በንጉሰ ነገስቱ ጊዜ አንድም ኢትዮጵያዊ እንኳን እንጀራ ፍለጋ ይቅርና ለትምህርትም ቢሆን ወደ ውጭ አገራት ተልኮ የቀረ አልያም በሌሎች አገራት ጥገኝነት የጠየቀ እንዳልነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በደርግ ዘመን በፖለቲካ አለመረጋጋትና በህይወት የመኖር ዋስትና ማጣት ምክንያት የተጀመረው የሕዝብ ስደት ማዕበል አሁን ይበልጥ ተባብሶ ቀጥሏል።


ከዚህ ቀደም እንደምንሰማው የዜጎቻችን የሞት መልዕክት ሁሉ በዚህ ሳምንትም ሌላ አስደንጋጭ ዜና ሰማን። የተሻለ ኑሮ ይኖራል በሚል ተስፋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ በጉዞ ላይ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 43 ያህሉ መሞታቸውን ከታንዛኒያ መንግሥት ተሰማ። ለኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ አይነት ዜናዎች አዲስ ባለመሆናቸው የተነሳ ብዙም የሚያስደነግጥና የሌሎችን እርብርቦሽ እና ድጋፍ የሚያስጠይቅ ሆኖ አላገኘውም።

ከዚህ ቀደምም በጅቡቲ አቋርጠው ወደ ስደት ለመሄድ የሞከሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ኮንቴይነር ውስጥ ታጭቀው በመጓዝ ላይ እያሉ ከተሳፋሪዎቹ መካከል ብዙዎቹ መሞታቸውን ሰምተናል። የዜጐቻችንን ስደት ተከትሎ የሚሰማው የሞት ወሬ እያስተናገድንም ቢሆን አሁንም ከዚህ ስህተት ብዙዎቹ ለመማር ፍቃደኞች አልሆኑም። መቼም ማንም ሰው በሕይወት ከመቆየት ይልቅ ሞትን የመረጠበት ፣ከመኖር ይልቅ አለመኖርን የናፈቀበት፣ በአገር ከመሰንበት ይልቅ ስደትን ብቸኛ አማራጭ ያደረገበት……በታሪክ እንደአሁኑ የከፋ ወቅት አላጋጠመንም። ኢትዮጵያ ውስጥ በረሃብና በሥራ እጦት እየተንገላቱ ከማለቅ፣ በወጣትነት እድሜ የቤተሰብ ሸክም ከመሆን ቢያንስ ቢያንስ በባዕዳን አገር ስራ ፍለጋ በሚል ሕይወታቸውን ለመገበር መንቀሳቀስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖባቸው እንጂ ማን ከአገሩ፣ ከርስቱ፣ ከቀዬው ይሰደድ ነበር።

በብሔር ግጭት፣ በረሃብ፣ በጦርነት፣ በፖለቲካ ነፃነት እጦት፣ በቂም በቀል፣ በሃይማኖት ግጭት፣ በመሬት ይዞታ እና በመሳሰሉት ሰበቦች ስንት ፍዳችንን አየን። አሁንም በከፋ ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ቀጣዩ ትውልድ የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቷል። ሕፃናት ያለ እድሜያቸው ከወላጆቻቸው ተነጥለው በጐዳና ላይ ወደቁ። አብዛኛው ህብረተሰብ በከፋ ድህነት ሲማቅቅ ሌሎች ጥቂት ግለሰቦች (ባለስልጣናት እና ከባለስልጣናት ጋር የተወዳጁ ባለሃብቶች) ከደሃው ጉሮሮ እየነጠቁ በክብር ላይ ክብር፣ በሀብት ላይ ሀብትን አከማቹ። ይሄ የሀገርን ምንነት እና በሀገር ውስጥ ለመቆየት የሚያግዝ የማንነት መንፈስ የሚያሳጣ ትልቅ የአድሏዊነትና የልዩነት መስመር ነው። አገር አለኝ የምንለው እንደማንኛውም ዜጋ በጋራ ሃብታችን ላይ እኩል የመጠቀም መብት የተከበረልን ጊዜ ነው። እንደማንኛውም ዜጋ እኩል የመወዳደር እድል ሲኖረን ነው፡፡ አለበለዚያማ በአገሬ መድልኦ እና መገለል ከደረሰብኝ፤ የሌላም አገር ሥርዓት ከዚህ የከፋ ምን ሊያመጣብኝ ይችላል በማለት ስደትን ምርጫቸው እንዲያደርጉ ተገደዋል። ከገዢው ፓርቲ ፖለቲካ ፍልስፍና የተለየ ርዕዮተ አለም በማራመዳቸው ምክንያት ለስደት የተጋለጡ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችም ሞልተዋል። ፍትሕ ለገዢዎቹ ወገን ብቻ ካደላ፣ በሕግ ፊት ሁላችንም ያለምንም ልዩነት እኩል የመዳኘት መብታችን ሳይከበርልን ሲቀር፣ ከራሳችን አብራክ የወጡ መሪዎቻችን ባዕዳን ሲሆኑብን…… በሀገር የመኖር፣ አገር አለኝ የማለት መተማመኛችን ምንም ሲሆንብን የቀረን አማራጭ ስደት ብቻ ይሆናል። እዚሁ ችግሮችን ተጋፍጦ ከመኖር በሌሎች አገራት ሌላ የመኖር እድልን ሞክሮ የመጣውን መቀበል የመጨረሻው መፍትሄ ይሆናል።በሀገሩ ከሚኖር ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይልቅ የውጭ አገር ዜጐች በነፃነት የመኖር፣ ንብረት የማፍራት መብታቸው ሲጠበቅላቸው ያየ ሰው የኔስ ሀገር ከወዴት ነው? ሲል ይጠይቃል። ተምሮ በነፃነት ማሰብና መስራት ያለመቻል ውጤት ዜጐቻችንን ከቀዬቸው እያራቀብን ይገኛል። የደሃ ገንዘብ ተሰብስቦ እንዲማሩ ዕድል የተሰጣቸው ብዙ ምሁራን የመስራት ነፃነታቸው በፖለቲካ ፍቃድ ላይ በመመስረቱ ምክንያት ሳይወዱ በግድ የሌላ አገር ዜጐች አገልጋይ ለመሆን ተገደዋል።

የአገራችን ምሁራን ከራሳቸው አልፈው የሌሎች አገራትን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል እንደሆነ ይታወቃል። ሴት እህቶቻችን የቤተሰብ ሸክም ከመሆን በሌሎች አገራት ገረድ ሆነው መስራትን ይሻሉ። ከእነርሱ አስቀድመው ወደ አረቡ የአለም ክፍል ተጉዘው ከፍተኛ ችግር ደረሰባቸውን እህቶቻቸውን እያዩ እንኳን ወደኋላ አላሉም። ሞትን፣አስገድዶ መደፈርን፣ ከፎቅ ላይ መወርወርን፣ በፈላ ውሃ መቀቀልን፣ በአደባባይ አንገታቸው ታንቆ በሀገራቸው ኢምባሲ ፊት ለፊት መጐተታቸውን፣ ሰውነታቸው በስለት መወጋቱን እያዩ እንኳን ድርጊቱ ወደተፈጸመባቸው ሀገራት ለመሄድ አያመነቱም። በረሀብ ከመማቀቅ፣የቤተሰብ ሸክም ከመሆን ሞት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ከእነዚህ እህቶቻችን መማር እንችላለን። በኢምግሬሽን መስሪያ ቤት ተገኝቶ ወደ ውጭ አገራት ለመሄድ የተሰለፉትን ሴት እህቶቻችን ያየን እንደሆነ የስደት ምክንያቱ  ምን ያህል መራር እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል።

በረሃብ የብዙ ህፃናት ህይወትን አጥተናል። በብሔር ግጭት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን ተላልቀናል። በጦርነት ሰበብ ትርፍ የሌለው የህይወት ዋጋን ከፍለናል። በፍትሕ እጦት ለዚህች አገር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ ምሁራንን ለሌሎች ባዕድ ሀገራት አሳልፈን ሰጥተናል። የተሻለ ኑሮን ፍለጋ በመኪና ኮንቴነሮች ውስጥ -ሰብአዊ በሆነ መንገድ የብዙ ዜጐቻችን ህይወት እንደ ቅጠል ረግፏል። ከዚህም የባሰ ብዙ ብዙ መከራዎችን አሳልፈናል።እያሳለፍንም ነው፡፡

ያለፉትን ሃያ አመታት ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሄ ይሆናሉ የተባሉ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ረቅቀው በተግባር ቢውሉም አንዳቸውም ለችግሮቻችን የመፍትሄ አካል መሆን ተስኗቸዋል። ይባስ ብሎ በታሪካችን ሰምተንና አይተን የማናውቃቸውን የእልቂት ዜናዎች ይህ ትውልድ መመልከት ጀምሯል። በችግሮቹ አሁንም ቢሆን በቅንነት መንፈስ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ እንደ ተራ ክስተትና አጋጣሚ ሰምተንና አይተን ከማለፍ ውጭ አንዳችም የመፍትሄ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተነጋገረ፣ ለተግባራዊነቱም የደፈረ ዜጋ የለም። በሰዎች ዘንድ መፍትሄ ለማግኘት ያሰብናቸው አማራጮች ሁሉ መፍትሄን አላስገኙልንም። መፍትሄው ያለው እግዚአብሄር ጋር ብቻ ነው፡፡ በዳዊት መዝሙር 91(92) ላይ ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የሚፀልይ የችግረኛ ፀሎት እንዲህ ይላል፡
‹‹አቤቱ ጸሎቴን ስማኝ፣ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ። በመከራዬ ቀን ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፣ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ። ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና አጥንቶቼም እንደ መቃጠያ ተቃጥለዋልና። እህል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሰፍሁም ልቤም እንደ ሣር ደረቀ። ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ። አመድን እንደ እህል ቅሜያለሁና…›› እግዚአብሄር መፍትሄውን ያበጅልን፡፡
የመከራና የስደት ጊዜያትን በቃችሁ ይበለን፡፡እዚሁ ሀገራችን ላይ ሰርተን የምንኖርበትን መልካም ጊዜ ያምጣልን፡፡ አሜን ያምጣልን__

1 comment:

  1. EGZIABHER amlak nefsachewun yimar kedegagochu kidusan abatoch gar yidemirlin AMEN!!!

    ReplyDelete