Tuesday, July 3, 2012

በሞንታቦ ቤተክርስትያን በር ላይ የሚካሄድ ህገ ወጥ ንግድ ከ10ሺህ ብር በላይ የሚስቀጣ አዋጅ ሊወጣ ነው



  • አዋጁ ሚኒባስ ላይ ሞንታርቦ በመስቀል በየትኛው ቦታ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ንግድ ከብሮድካስት ባለስልጣን ፍቃድ ያስፈልገዋል ይላል፡፡
  • አዋጁ በምክክር ላይ ስላለ ቤተክርስትያን በንብረቶቿ አማካኝነት የሚሰራን ማስታወቂያ እንዳይኖር በአዋጅ ውስጥ እንዲካተትላት መጠየቅ ትችላለች፡፡
  • አዋጁ ላይ ኦርቶዶክሳውያን ማንሳት የሚገባን ጥያቄ……..?????

(አንድ አድርገን ሰኔ 24 ፤ 2004 ዓ.ም)፡- በተለይ በአዲስ አበባ ልደታ ቤተክርስትያን ፤ ምስካየ ኃዙናን መድሃኔዓለም ፤ 5ኪሎ ቅድስተ ማርያም ፤ ቦሌ መድሃኔዓለም ፤ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስትያን ፤ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትን ፤ አዲሱ ሚካኤል እና መሰል ብዙ ምዕመናን በበዓላት ወቅት የሚገኙባቸው አድባራትና አብያተክርስትያናት መንገድ ላይ ሚኒባስ ተከራይተው ሞንታርቧውን ሰቅለው የተለያየ ማስታወቂያ የሚነግሩ የቤተክርስትያኒቱ አስተምህሮ የሆኑትንና ያልሆኑትን አንድ ላይ በመቀላቀል መዝሙሮችንና ስብከቶችን በመሸጥ ስውር ዓላማቸውን የሚያሳኩ ሰዎችንና ማህበራትን መመልከት ከጀመርን ሰንበትበት ብለናል ፤ ከአውደ ምህረት ሲባረሩ በቀላሉ በሚኒባሶች የፈለጉበት የሃገሪቱ ከተማ በመዘዋወር በዓላትን በማስታከክ መዝሙርና ስብከቶቻቸውን  በመሸጥ የንግድ ተግባራቸውን ሲያጧጡፉም ተመልክተን ይህን የሚያስቆም ህግ ባለመኖሩ አይተን እንዳላየን አልፈናል ፤ በተጨማሪ እነዚህ ህገወጦች ከሞንታርቦ ስፒከሮቻቸው አማካኝነት የሚለቁት የድምጽ መጠን የሰው ጆሮ መስማት ከሚችለው በላይ ስለሆነ በጊዜው በየአብያተክርስትያናቱ የሚቀደሰውን ቅዳሴ ፤ የአውደ ምህረቶችን ስብከት እና መዝሙር ለመስማት የተቸገርንበትና ሃይ የሚል የጠፋበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ይታወቃል ፤ እነዚህንና መሰል ስውር አላማ ይዘው በ500 መቶ ብር የቀን የሚኒባስ ኪራይ ምንፍቅናቸውን በአደባባይ የሚዘሩ ፤ ፍቅረ ነዋይ አይናቸውን የጋረዳቸው ሰዎችና ማህበራትን የሚመለከት አንድ አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ህግ ሊወጣለት መሆኑን በተባራሪ ወሬ ሰማን ፤ አዋጁንም ከአንድ የማስታወቂያ ባለሙያ ወዳጃችን ረቂቁን በመቀበል ማንበብ ችለን ነበር ፤በመሰረቱ አዋጁ በጠቅላላ ሀገሪቱ ላይ የሚደረጉትን የማስታወቂያ ስራች መስመር ለማስያዝ የወጣ ቢሆንም ይህ ጉዳይ ቤተክርስትያን ላይ ስለሚደረጉ ነገሮች በጥቂቱ ስለሚመለከት የእኛን ክፍል ብቻ በማንሳት የአዋጁን ሀሳብና ቅጣቱን ለእናንተው ለማቅረብ ወደድን፡፡


በቅርቡ መንግስት “የማስታወቂያ አዋጅ” ለማውጣት የሚመለከታቸውን አካላት በኢቲቪ እና በተለያዬ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች በአዋጁ ዙሪያ ለመነጋገር ማስታወቂያ ሲያስነግር ሰምተን ነበር ፤ ይህን በሚመለከት ከሳምት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ የጻፈውን ጽሁፍም መመልከት ችለናል ፤ የሚመለከታቸውም አካላት ባሳለፍነው ሳምንት ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከብሮድካስት ኤጀንሲ ሃላፊዎች ጋር መነጋገገር መቻላቸውንና ጠቃሚ ነገሮች በውይይቱ ላይ መገኝታቸውን ኢቲቪ ዜና ላይ ተመልክተናል ፤ እኛም ይህ የማስታወቂያ አዋጅ በተወሰነ መልኩ በማስታወቂያ ችግር ቤተክርስትያናችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታና እኛን ስለሚመለከተን ነገሮች ላይ ብቻ በመዳሰስ  አዋጁ ከመጽደቁ በፊት መጠየቅ የምንችላቸውን ጥያቄዎችን ለማንሳትና ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ በማሰብ ይችን ሀሳብ አቅርበንላችኋል፡፡

አዋጁ 37 አንቀጾች ያሉት ሲሆን  ሲጀምር “ማስታወቂያ በስርዓት ካልተመራ የህብረተሰቡን መብትና ጥቅም እንዲሁም የሀገርን ገጽታ ሊጎዳ የሚችል በመሆኑ የማስታወቂያ ወኪሎች ፤ የማስታወቂያ አሰራጮች እና የማስታወቂያ አስነጋሪዎችን መብት እና ግዴታ በግልጽ መወሰን በማስፈለጉ…..” በማለት የአዋጁን አስፈላጊነት ይተነትናል ፤ ትክክል ነው የአንዲት ሀገር የማስታወቂያ ስርዓት በአግባቡ ካልተመራ  ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል ፤ በየጊዜው በቤተክርስትያን አካባቢዎች በዓልን መሰረት አድርገው የሚደረጉ የማስታወቂያ ስራዎችና ህገወጥ ንግዶች ምዕመኑ በዓሉን በሰከነ መንፈስ እንዳናከብር እያደረጉት ይገኛሉ ፡፡
እኛ እንደችግር የሚታየን በየጊዜው ዓመታዊ እና ወርሃዊ በዓል ላይ በየቤተክርስትያኑ ደጃፍ ላይ ሚኒባስ በመከራየት ፤ ማይክራፎን በመያዝ ጆሯችንን የሚያደነቁሩንን የማስታወቂያዎች ጉዳይ ነው ፤ ለበርካታ ጊዜያት የት ሄደን አቤት የምንልበትን ቦታ በማጣት ችለናቸው መቀመጣችን በአሁኑ ጊዜ ያለ እውነታ ነው ፤ ይህ የማስታወቂያ ህግ ከጸደቀ በኋላ ግን እነዚህን ሰዎች እኛ አይተን ዝም ብንላቸው ህጉ ዝም የሚላቸው አይመስለንም ፡፡እስኪ ረቂቁን አዋጅ እንመልከት፡፡

የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 11 ላይ ትርጓሜው ክፍል ላይ ይህን ሰፍሮ እናገኛለን “የውጭ ማታወቂያ ማለት በቢልቦርድ ፤ በኤሌክትሮኒክስ ስክሪን ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል የሚሰራጭ ፤ በህንጻ ወይም በማናቸውም ስትራክቸር ወይም በትራንስፖርት ተሸከርካሪ ላይ የሚለጠፍ ፤ በተንጠልጣይ ነገር ፤ በፖስተር በስቲከር በብሮሸር ሊፍሌት ወይም በራሪ ወረቀት የሚሰራጭ ወይም በድምጽ ካሴት በድምጽ ማጉያ መሳሪያ የሚሰራጭ ወይም በሌላ መሰል ማሰራጫ መንገድ አማካኝነት የሚሰራጭ ማስታወቂያ ነው” ይላል፡፡ ይህ የውጭ ማስታወቂያ ትርጓሜ ላይ የእኛን አትኩሮት የሳበው ፤ በቀጥታ የሚመለከተንና ህገወጥ አካላትን አደብ የሚያስገዛልን  “በድምጽ ካሴት በድምጽ ማጉያ መሳሪያ የሚሰራጭ” የሚለው ይሆናል ፤

ይህን ጉዳይ በአንቀጽ 21 ላይ እንዲህ ብሎ ያስቀምጠዋል
21. ስለ ውጭ ማስታወቂያ
1.      ማንኛውም ሰው አግባብ ካለው የመንግስት አካል ፈቃድ ሳያገኝ እንደ አግባብነቱ ባለቤቱ ወይም ባለይዞታው ሳይስማማ
ሀ.  በማናቸውም ህንጻ ፤ ግድግዳ፤ አጥር ፤ የአውቶቡስ ፌርማታ ፤ ምሰሶ ፤ ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መስጫ አሳሪያ ወይም ሌሎች ነገሮች ላይ
ለ.   በማንኛውም መንገድ ፤ አውራ ጎዳና ፤ የባቡር ሃዲድ ወይም የህዝብ መጓጓዣ ላይ ወይም
ሐ.   በማናቸውም የህዝብ አገልግሎት በሚሰጥ ስፍራ ላይ
የውጭ ማስታወቂያ መለጠፍ ፤ መስቀል ፤ መትከል ወይም በሌላ መንገድ ማስተዋወቅ አይቻልም፡፡  በማለት ያስቀምጣል ፤

በመሰረቱ “ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም” ስለዚህ በበጎም ይሁን በሌላ መንገድ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሚኒባስና ሞንታርቦ በመከራየት ፤ በማይክራፎን መዝሙሮችን ፤ ስብከቶችንና  ለመሸጥ የተሰማሩ ሰዎች ይህን አዋጅ ከጸደቀ በኋላ ቢያነቡት መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለን፡፡ በቅን ልቦና ተነስቶ የጎዞ ማስታወቂያዎችን በየፈለጉት ቦታ መለጠፍም የማስታወቂያውን ባለቤት በህግ ስለሚያስጠይቅ መጠንቀቁ መልካም ነው ባዮች ነን ፤ በተጨማሪም የቤተክርስትያናት አስተዳዳሪዎች ፤ በተለያየ በስልጣን ተዋረድ ላይ የሚገኙ የቤተክርስትያን ኃላፊዎች ፤ መንፈሳዊ ማህበራት ፤ ይህን ተግባር ማስቆም ለሚፈልጉ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ፤ የቤተክርስትያን የደጃፍ ላይ ህገወጥ ነጋዴዎች ጉዳይ የሚያሳስባቸው አካላት ይህን አዋጅ በማየት የቤተክርስትያንን ስርአት የፍቅረ ንዋይ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ብለው በድምጽ የሚረብሹ ሰዎችን ህግ ዘንድ ለማቅረብ ይችሉ ዘንድ አዋጁ ጸድቆ ሲወጣ  ቢያነቡትና የቤተክርስትያንን ስርዓት ለማስከበር ቢጥሩ መልካም ነው ፡፡

አዋጁ እንደሚያስቀምጠው በሚኒባስ እና በማይክራፎን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማስታወቂያ ለመስራት ከብሮድካስት መስሪያ ቤቱ ፍቃድ እንደሚያስፈልግ ያስቀምጣል ፤ ለእነዚህ አካላት ፍቃድ  ቢሰጥ እንኳን አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ 7 ላይ አግባብ ያለው የመንግስት አካል የሚወስነውን የድምጽ መጠን በማናቸውም አይነት የድምጽ ማጉያ መሳሪያ አማካኝነት መተላለፍ እንደሌለበት ያስቀምጣል ፤

ይህን ህግ በመተላለፍ ጥፋት የፈጸመ ማንኛውም አካል አንቀጽ 34 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ “ከ10 ሺህ ብር የማያንስ  ከ100ሺህ ብር የማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ሀገሪቱ ህግ የማውጣት ችግር የለባትም ፤ ዋናው ችግር የማስፈጸም ችግር ነው ፤  ይህ ህግ ሲወጣ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎቹ የህገወጥ የሞንታርቦ ድምጽ ያስቸገራቸው ደብራት መሆናቸው እሙን ነው ፤ ስለሆነም ህጉን ይዞ መከልከልም ሆነ ማስከልከል ስለሚቻል እንደ ቀላል ጉዳይ መመልከት የለብንም፡፡ አነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጽ/ቤት ጋር ከወራት በፊት መነጋገሩን ይታወቃል ፤ ሲጀመር ሀገረ ስብከቱ የዚህን አዋጅ መውጣት በጉጉት የሚጠባበቅ ቢሆንም ሌላ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ አዋጁን በመመልከት ከሚመለከተው አካል ጋር ቀርቦ የራሱን ሃሳብ መስጠት ቢችል መልካም ነው፡፡

አዋጁ ላይ ኦርቶዶክሳውያን ማንሳት የሚገባን ጥያቄ
የአዋጁ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ 11 ላይ የሚከተሉት ማስታወቂያዎች ህግን ወይም መልካም ስነ ምግባርን የሚጻረር ይዘት ወይም አቀራረብ እንዳላቸው ሆነው ይቆጠራሉ በሚለው ስር “የመከላከያ ሰራዊት ወይም የፖሊስ የደንብ ልብስን ፤ ምልክትን ወይም ሽልማትን በመልበስ ወይም በማድረግ የሚቀርብ የንግድ ማስታወቂያ” እንደማይፈቀድ ያስቀምጣል ፤ ይህ አንቀፅ መንግስት ለፖሊስ እና ለመከላከያ አባላት ልብሶችና ኒሻኖች ምን ያህል እንደተጠቆረቆረ ያሳየናል ፤ እንደ ሀገር ስናየው መልካም ነው ፤ መንግስት ለራሱ ተቋማት ይህን ያህል የሚጠነቀቅ ከሆነ እኛም የቤተክርስትያናችን ንዋየ ቅዱሳትን ፤ የአባቶችን ቆብና ልብስ ፤ ከበሮ ፤ ጸናጸል ፤  እና መሰል የቤተክርስትያኒቱ መገልገያ መሳርያዎች የማስታወቂያ ስራ ግብአት እንዳይሆኑ መጠየቅና አዋጁ ላይ ማካተት አለብን የሚል አቋም አለን ፤ እኛ እንደ ግለሰብ አንዲት ደብዳቤ ላይ ሃሳባችንን ገልጸን ለብሮድካስት ኢጀንሲውና ይህን ለሚመለከተው የህዝብ ተወካዮች አባላት ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄያችንን ማቅረብ እንችላለን ፤ ቤተክህነቱም  ቤተክርስትያኒቱን ወክሎ ጥያቄ ቢያቀርብ መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለን ፤ እርስዎ ምን ይላሉ…? ይህ ጉዳይ ያሳስበናል የምትሉ ሰዎች ካላችሁ ለመጽደቅ ቀናት የቀረው አዋጅን ብሮድካስት መስሪያ ቤት ድረስ በግልም ይሁን በቡድን በመሄድ አዋጁን ማግኝት እንደምትችሉ ለመግለጽ እንወዳለን ፤ ሀገሪቱ የምታወጣውን ማንኛውንም ህጎች ላይ በማየት ሃሳቦትን የመስጠት መብት ስላለዎት ረቂቅ አዋጁን ለማግኝት ሀሳብ አይግባዎ ፤

ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሰረት ተዘጋጅተዋል ተብለው በማስታወቂያ ለምዕመኑ የሚሰራጩት የመጽሀፍት ፤ የመዝሙር እና የስብከት ስራዎች በማስታወቂያ አማካኝነት ከመሰራጨታቸው በፊት ቤተክርስቲያኒቱ የሚሰራጩትን የህትመት ውጤቶች መፍቀድ አለባት ፤ ይህን ጉዳይ በሀሳብ መልክ በማንሳት አዋጁ ላይ ይካተት ዘንድ ሃላፊነቱ የቤተክህነቱ ቢሆንም እኛም ከቻልን የአቅማችንን ማድረግ ይገባናል ፤  “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” ይላል የሀገሬ ሰው፡፡

ቸር ሰንብቱ

8 comments:

  1. በርግጥ ተፈፃሚ የሚሆን ከሆነ መልካም ነገር ነው

    ReplyDelete
  2. It is a good news.We will get relief in the near future.

    ReplyDelete
  3. yebele yemagen new

    ReplyDelete
  4. And Adrgen Good news Guys

    I support ur idea

    “የመከላከያ ሰራዊት ወይም የፖሊስ የደንብ ልብስን ፤ ምልክትን ወይም ሽልማትን በመልበስ ወይም በማድረግ የሚቀርብ የንግድ ማስታወቂያ” እንደማይፈቀድ ያስቀምጣል ፤ ይህ አንቀፅ መንግስት ለፖሊስ እና ለመከላከያ አባላት ልብሶችና ኒሻኖች ምን ያህል እንደተጠቆረቆረ ያሳየናል ፤ እንደ ሀገር ስናየው መልካም ነው ፤ መንግስት ለራሱ ተቋማት ይህን ያህል የሚጠነቀቅ ከሆነ እኛም የቤተክርስትያናችን ንዋየ ቅዱሳትን ፤ የአባቶችን ቆብና ልብስ ፤ ከበሮ ፤ ጸናጸል ፤ እና መሰል የቤተክርስትያኒቱ መገልገያ መሳርያዎች የማስታወቂያ ስራ ግብአት እንዳይሆኑ መጠየቅና አዋጁ ላይ ማካተት አለብን የሚል አቋም አለን

    ReplyDelete
  5. BETE KEHENT ATKESQUSUT A D E R A DEHENA ENKELF LAY NEW ENA !!! BAYHON LEZIHICH HAGERENA BETE CHRISTIAN SILU YEMIDEKMUTEN ETHIOPIAWEIAN HAWARIATOCHEN YE KEFU KEN WEGEN ENEHUNACEW ,ABREN NEN ENBELACHEW . EGZIABEHER HAIL NEW ,ELSHADAY BEBETU KENATEGHA NEW ,ENGHA LEJOCHU`S .MENEW YEABAT MEWRES EKO WEG NEW. AKRARI ORTHODXOCH YELUNAL AYDELENM NEW MELSACHEN , YEGED NACHU KALUENMA "YEHUNA" BLEN ZEMTAN ANMERTEM TERGUMUN BEANDENET ENASAYACHEW . YE SEMATU ABUNE PETROS EMNETENA DEM YALEW KAHEN YE ABUNUN GEZIT YEDGEMEW . HEZBE CHRISTIANM AAA MMM EEE NNNN YEBEL.

    ReplyDelete
  6. ተዉ ገዳማቱን መዳፈር ይቅርባችሁ
    በነሱ ፀሎት ነውና እዚህ መድሳችሁ
    እባካችሁ ገዳማቱን መዳፈር ይቅርባችሁ
    ሰለፊያ ስትሉን በአደባባይ ዝም አልናችሁ
    ለአምላካችን እርሱ ይየው አልናችሁ
    እርሱም የበቀል አምላክ ነውና መለሰው በአደባባይ
    ያውም አድርጎ ለዓለም እንዲታይ
    አሁን ተዉን አትንኩ ገዳማችንን ዋልድባን
    አትንኩብን አባቶቻችንን ቅዱሳን
    ለእኛም ለእናንተም ብሎም ለዓለም የሚፀልዩትን
    በረከታቸው ለሁላችን የሚደርስልንን
    እባካችሁ ዋልድባ እንኩዋን ፖለቲካ አይነገርበትም ወሬ
    መናኞቹ የሚኖሩ ናቸውና በመንፈስ ፍሬ
    አሁንም እንላለን አትንኩብን ገዳማችንን
    ለመኖራችሁ ምንም የላችሁም ተገን
    መጨረሻችሁ ይሆናል ማዘን
    ሳትባሉ ማኔ ቴቄል ፋሬስ
    የእውነት አምላክ በልባችሁ ይንገስ!!!

    ReplyDelete
  7. ደስ ይላል እኔም ስፈራበት የነበረ ጉዳይ ነው የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት አይጠብቁም የተባሉ ዘማሪያንንና የተሃድሶ ምንፍቅና አራማጆችን ምንም እንኳን ህብረተሠቡ ባይተባበራቸዉም ነገር ግን ‹‹ዘምረው›› እና ገጥመው ባልታዎቀባቸዉ አንዳንድ የዋሃን ሥም ድብቅ ሴራቼዉን ሊያራምዱ የሚችሉበት በር እንደሚዘጋ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ካሁን በኋላ ዘበርጋ በያሬድ ሥም የዉብዳር በለተ ፅዮን ስም ይወጉን ይሆናል የሚል ስጋቴ ቀረ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበት ሁኔታ አመቺ ሆኖ ስላገኙት በምንፍቅና የማይታሙና የአዘማመር ስርዓቷን ግን ያልተከተሉ አንዳንድ ዘማሪያን ንግዱን ከሌላዉ ጊዜ በተለየ ያጧጧፉት የማስተዋያ ጊዜ ይሰጣቸው የሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን!!

    ReplyDelete
  8. ደስ ይላል እኔም ስፈራበት የነበረ ጉዳይ ነው የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት አይጠብቁም የተባሉ ዘማሪያንንና የተሃድሶ ምንፍቅና አራማጆችን ምንም እንኳን ህብረተሠቡ ባይተባበራቸዉም ነገር ግን ‹‹ዘምረው›› እና ገጥመው ባልታዎቀባቸዉ አንዳንድ የዋሃን ሥም ድብቅ ሴራቼዉን ሊያራምዱ የሚችሉበት በር እንደሚዘጋ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ካሁን በኋላ ዘበርጋ በያሬድ ሥም የዉብዳር በለተ ፅዮን ስም ይወጉን ይሆናል የሚል ስጋቴ ቀረ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበት ሁኔታ አመቺ ሆኖ ስላገኙት በምንፍቅና የማይታሙና የአዘማመር ስርዓቷን ግን ያልተከተሉ አንዳንድ ዘማሪያን ንግዱን ከሌላዉ ጊዜ በተለየ ያጧጧፉት የማስተዋያ ጊዜ ይሰጣቸው የሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን!!

    ReplyDelete