Monday, April 20, 2015

የኢትዮጵያውያንን ደም የተጠማች ምድር

  • በሊብያ ያለቁት ወገኖቻችንን ማንነት አውቆ በጉዳዩ ላይ መነጋገር የቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነት ነው፡፡ ግብጻውያኑ ሰማዕታት ብለው ለመሰየም የፈጀባቸው ሰዓታት ብቻ ነው፡፡ እኛም የሚገባውን ልናደርግ ይገባናል፡፡ ለመሞታቸው ምክንያት የኾነው እምነታቸው ብቻ ነውና፡፡

ከዲያቆን አባይነህ ካሴ
በሳዑዲ እና በሶርያ ምድር እንደ ጎርፍ የፈሰሰው የወገኖቻችን ደም ሳይደርቅ እንደገና ዛሬም አንገት የሚያስደፋ ትንግርት ቁጭ ብለን እየታዘብን መኾናችንን ሳየው እጅጉን ግራ ገባኝ፡፡ በየመን፣ በደቡብ አፍሪካ ደግሞም ትናንትና በሊብያ! ምድር በኢትዮጵያውያን ደም እየጨቀየች ነው፡፡ አልጀዚራ ሲል ሌሎች ደግሞ ፳፰ ይበሉ እንጂ ለእኔ ጉዳዩ የቁጥር አይደለም፡፡


ምንድን ነው እየኾነ ያለው? ትርጉም ትንታኔ ይፈልጋል፡፡ ለምን እኛ በሁሉም ስፍራ እንሞታለን? ደቡብ አፍሪካ ስንሄድ ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር እኛ አለንበት፡፡ ሳዑዲ ስንሄድ ከሌሎች ኤዥያውያን ጋር እኛ አለንበት፡፡ ሊብያ ስንሄድ ከግብጻውያን ክርስቲያኖች ጋር እኛ አለንበት፡፡ ይኽ ነገር እንዴት ነው? በብዙኃን መገናኛ ለአንድ ሰሞን ብቻ አገንፍለነው የምንረሳው ጉዳይ ነውን?

በኮንቴይነር ውስጥ ታፍነን የምናልቀው እኛ! በባሕር ላይ የባሕር አውሬ ሲሳይ እየኾንን ያለነው እኛ! እንዴት ምድር የእኛ ደም ጣፈጣት? ምንድን ነው ይኼ ጉድ? በምዕራባውያን የስደተኞች መንደር የሞላነው እኛ! እስር ቤቶቻቸውን ያደመቅነው እኛ! ጉዳዩ ትልቅ እንደኾነ ከእኔ ጀምሮ የገባን አልመሰለኝም፡፡ ቆም ብለን ካላሰብን እንዲህ እንዲህ እያልን ወሬ ነጋሪ ሳይቀርልን እንዳናልቅ ፈራሁ፡፡ በውጭ የተጀመረው በምድራችን በግዛታችን በውድ ሀገራችን በከፋ ሁኔታ ሳይከሰት ብንመክር ይሻላል፡፡

ሁሉም የሚመዝዘውን የግል አጀንዳ ትቶ በዚህ ጉዳይ በጋራ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ሀገር ሀገር ማለት ዋጋ አይኖረውም፡፡ ባለጉልበቱ ጉልበቱን ይተው፣ ባለኩርፊያውም ኩርፊያውን ይተው፣ ፖለቲካ ያጣላውም ቂም በቀሉን ይተው፣ ባለሥልጣኑም ሥልጣኑን ይርሳ፡፡ ተሰባስበን ዜጎቻችንን እናድን፡፡ ደመ ከንቱ አናድርጋቸው፡፡ እንጀራ ፍለጋ ሲወጡ ስንቶች ቁም ስቅል እንዳዩ እናውቃለን፡፡ በጨካኞች እጅ የወደቁ ወንድሞቻችን መርዶ ነጋሪ አጥተው በረሃ በልቶ አስቀርቷቸዋል፡፡ እኅቶቻችን በእስር ቤት ተቀፍድደው የደፋሪዎች መጫወቻ ኾነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ደም በጠማው ሰይፍ እና ገጀራ አንገታቸው እየተቀላ ዓይናችን ጉድ ዐየ፡፡ ሌላ ምን አስኪያሳዩን እንጠብቅ? ደማቸው ውኃ ያልቀመሰ መሬታቸውን ሊያረሰርስላቸው ይኾንን?

የውጭ ወራሪ ጠላት መጣ ቢሉን እንዴት እንደምንነሣ እናውቃለን፡፡ ይኽ የኢትዮጵያዊነት የደም ትስስራችን የፈጠረው ጥልቅ መለያችን ነው፡፡ ቀፎው እንደተነካ ንብ ብለን ያለሰባኪ ያለአዋጅ ነጋሪ ማንም ማንንም ሳይጠብቅ ያለውን የአቅሙን ይዞ እንደሚነሣ ይታቀወቃል፡፡ አሁን በተለያዩ ክፍለ ዓለማት እንዲህ የሚበላን እሳት ያንን የኢትዮጵያዊነት አቅም በግድ ይፈልጋል፡፡ ሁላችንም በየቤታችን በያየንበት መስኮት ፊት ለፊት ደም እንባ አልቅሰናል፡፡ ደግመን እንዳናለቅስስ ማልቀስ የለብንምን?

እምነት የልዩነት እንጂ የጠብ መነሻ አይደለም ሊኾንም አይገባውም፡፡ በሃይማኖት ምክንያት መሞትም ክብር ሰማዕትነት እንጂ የሚያሳፍር ነገር አይደለም፡፡ ድርጊቱ አንጀት ስለሚበላ አለቀስን እንጂ ለእነርሱስ የኾነው ክብር ነው፡፡ በሊብያ ያለቁት ወገኖቻችንን ማንነት አውቆ በጉዳዩ ላይ መነጋገር የቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነት ነው፡፡ ግብጻውያኑ ሰማዕታት ብለው ለመሰየም የፈጀባቸው ሰዓታት ብቻ ነው፡፡ እኛም የሚገባውን ልናደርግ ይገባናል፡፡ ለመሞታቸው ምክንያት የኾነው እምነታቸው ብቻ ነውና፡፡ ክርስቲያን መኾናቸው የሰይፍ እራት አደረጋቸው፡፡ ቢክዱ ኖሮ ባልተሰየፉ፡፡እንዳመኑ ሞተ ሰማዕታትን ተጎንጭተዋል፡፡ እንዲሁ ሳንነጋገርባቸው እንዳንቀር፡፡


3 comments:

  1. Wendim ehtoche silesematatu yetegeletsew endale hono silekerut beadega zurya silalut endet wedagerachew memeles endemichlum mikir asteyayet tikoma wezeta hulum biyawata memeles lemichlu beselamawi bemimeslu neger gin nege min endemifeterbachew bemaytaweku yeareb agerat yalutn hulu birbachhum bagerachu yishalachhulna yalachhun yizachu wedagerachu gibu enbelachew. be poletica chigir etaseralehu bilaw lemiferu bebaid kemetaser bager metaser yishalalna ebakachu wedagerachu gibu bians yemiatsnana teyaki wegen bagerachu atatumna bilen enaberetata.

    ReplyDelete
  2. የሆነው ልብ ይሰብራል ግን በጣም ተቀደምክ ቅ/ሲኖዶስ ቀድሞህ መግለጫ አወጣ ብዙ ጊዜ መጻፍ ስለምትችል ብቻ ነው የምትጽፈውና መናገር ስለምትች ነው የምትናረው ዲ/ን አባይነህ ለምንስ ሁሉ ጊዜ የውጭ ነገር ትናፍቃለህ ግብፆች በሰዓታት ውስጥ አልወሰኑም።

    ReplyDelete
  3. ግብጻውያኑ ሰማዕታት ብለው ለመሰየም የፈጀባቸው ሰዓታት ብቻ ነው፡፡ የኛ ሲኖዶስ አለ እንዴ?

    ReplyDelete