Tuesday, April 21, 2015

ክርስትና የመናቅና የመጠላት ሃይማኖትከሁለት ወራት በፊት የግብፅ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን አንገት ቀልተው ወጣቶቹንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሰማዕትነት ክብር ያበቁ አረመኔዎች ሰሞኑን ደግሞ ተራው የኢትዮጵያውያን ወጣቶች እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን በተግባር የወንድሞቻንን አንገት ከመቅላት እና በጥይት ከመደብደብ አልፈው በቃልም ሰማዕታቱንየጠላታችን የኢትዮጵያ የመስቀል ተከታዮችብለው በመደንፋት ገልጸውልናል። ለሃይማኖታቸው የቆረጡ ዕድለኞቹ ወንድሞቻችንም አንገታቸውን ለስለት፣ ጀርባቸውንም ለጥይት እሩምታ በመስጠት ፈጣሪያቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን በሰማዕትነት ሞት አክብረዋል።ፈጣሪ ለምን ዝም አለ? እንዴትስ በእነዚህ ጨካኞች እጅ ሕይወታቸው እስኪያልፍ ተዋቸው?” በማለት የእምነታቸውን መላላት ያሳዩንም አሉ።


የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ክርስትናን የመሠረተልን በወንጌል ነው። በወንጌል ደግሞ ስለክርትናችሁ ትመሰገናላችሁ የሚል አልተጻፈም። ይልቁንም 8ኛው ሺህ ዋዜማ ላይ ሆነን መገንዘብ ካላቃተን ጌታችን በማቴ 24÷9 “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችሁማል፣ ስለስሜም በአሕዛብ ኹሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁብሎናል። ክርስትና የተመሠረተችው በክርስቶስ መስቀል ላይ ነው። መስቀል ባለበት መከራ አለ፤ መስቀል ባለበት ስደት አለ፤ መስቀል ባለበት መስዋዕትነት አለ፤ መስቀለ ክርስቶስ የተተከለው በቀራንዮ ላይ ነውና ዛሬም የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ወጣ ገባ የበዛበት የቀራንዮ ጉዞ ነው። መዘንጋት የለሌበት ግን ከመስቀል በኋላ እንደ አዲስ መወለድ መኖሩ ነው። ይህም በላይኛው ቤት የሚገኘው የክብር አክሊል ነው። ይህ ሁል ጊዜም የማይካድ ነባር ሐቅ ግን በብዙዎች ሲዘነጋ እናስተውላለን። የክርስቶስ ሃይማኖት ሲሆን ለምን በዚህ ምድር ክብር አያገኝም? ክርስቲያኖችስ ለምን አይከበሩም? የሚል አይጠፋም ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች እስኪያጉረመርሙ ድረስ በዚህ ነገር ሲስቱ ይስተዋላሉ። የሰማዕትነት ዋጋው ቢገባንና ብናውቅ ኖሮ ባለፈው የግብጻውያን ወጣቶች የታረዱ ወቅት የአንዱ ሰማዕት ባለቤት ከሕጻን ልጇ ጋር በጉባኤ ፊት ቀርባባለቤቴን ያረደውን ISIS አባል ባገኘው ኖሮ እግሩ ስር ወድቄ አመሰግነው ነበር፣ ምክንያቱም ባለቤቴን ለዚህ ትልቅ ክብር እንዲበቃ ምክንያት ሆኖታልናብላ በፍጹም የይቅርታ መንፈስ እንደተናገረችው ግብጻዊት እኛም ለይቅርታ እና ለምስጋና እንቸኩል ነበር። ግና ደረጃችን ተለያየና ሃሳባችን ለየቅል እየሆነ ነው።

ከመጀመሪያው ለክርስትናና ለወንጌል አገልግሎት የተመረጡት ደካሞች፣ በዚህ ዓለም ዕውቀት እና ልከት እዚህ ግባ የማይባሉ ዓሣ አጥማጆች፣ ቀራጮች እና የመሳሰሉ የተናቁና የተጠሉ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ግን በክርስትና እምነት ከታነጹ በኋላ የላይኛውን ቤት መሥራት የቻሉ መንፈሳውያን መሃንዲሶች፣ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ መነጠቅ የቻሉ በእምነት መነጽር አስትሮኖመሮች፣ ሁሉንም እንደየአገባቡ መምራትና ማሰማራት የቻሉ መንፈሳውያን አስተዳዳሪዎችና እረኞች፣ አንዳንዶችም ከተፈጥሮ ሕግ በላይ በመሆን ደመና ጠቅሰው ከሀገር ሀገር ተዘዋውረው መንፈሳዊ ሥራዎችን ያከናወኑ ለመሆን በቅተዋል። በኋላ የሕይወትን መንገድ ያስተማሩ መምህራን ቢሆኑም በጊዜው ዓለም አላወቃቸውም። ይባስ ብሎም የዚህ ዓለም ገዢዎች ልዩ ልዩ መከራን እንዲቀበሉ አድርገዋቸዋል። ምንም በደል ሳይኖርባቸው ከቦታ ቦታ ተሰደዱ፣ መጻተኞችም ሆኑ። ሰማያዊው ዋጋ ከሁሉም እንደሚበልጥ ተረድተዋልና ሁሉን እየታገሱ ስለነፍሳቸው መዳን መከራን ተቀበሉ። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልዕክቱ እነዚህን ሲዘክርእነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ (አላውያን ነገሥታት አምላካችሁን ካዱ፣ ለጣዖት ስገዱ ቢሏቸውም በስጋቸው ላይ በመጨከን በእምነታቸው በሰማዕትነት በማለፍ የመንግሥታትን ጥያቄ እምቢ አሉ) ጽድቅን አደረጉ፣ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፣ የአንበሳዎችን አፍ ዘጉ፣ የእሳትንም ሃይል አጠፉ፣ ከሰይፍ ስለት አመለጡ (ምንም እንኳን በሥጋቸው በሰይፍ ቢገደሉም በመጨረሻ መንግሥተ ሰማያትን ወረሱ) ከድካማቸውም በረቱ፣ በጦርነት ሃይለኞች ሆኑ (ከሰይጣን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ድል ነሡ) የባዕድ ጭፍራዎችን (ሰይጣንን) አባረሩ፣ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፣ ሌላዎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ (እንዲማሩባቸውና እንዲጸኑባቸው) እስከሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ፣ ከዚህም በላይ በእስራትና በወሂኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፣ ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፣ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ቆዳ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።” (ዕብ 11÷33-38) ብሏል።

በክርስትና ስነ ምግባር ታንጾ መኖር በዚህ ምድር ላያስከብር ይችላል። ዓለም የምታከብረው አብረዋት የሚሰርቁትን፣ አብረዋት የሚሰክሩትን፣ አብረዋት የሚጨፍሩትን፣ አብረዋት ለሌሎች ጉድጓድ የሚቆፍሩትን ነውና። ዓለም ለፍጡራን ክርስቲያኖች ይቅርና ፈጣሪዋ ለሆነው ለክርስቶስም ችሎት ከመሰየም፣ መስቀልን ከማበጀት፣ መቃብርን ከመቆፈር አልታቀበችም። ክርስቶስን በመቃብር ሆድ ማስቀረት ሲያቅታ በተከታዮቹ ላይ በረታች። ደግና ታዛዡ እስጢፋኖስ ያለጥፋት ተወግረው በኩረ ሰማዕታት ሆኖ ሞተ። በዚህ ሳያበቃም በክርስትና እምነት እንደ ከዋክብት ዜና ገድላቸው በስንክሳሩ የሰፈሩ እና ያልሰፈሩ እልፍ አዕላፍ ሰማዕታት ተፈጠሩባት። ይህ ደግሞ እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ድረስ ይቀጥላል።

በክርስትና ጥያቄ የሌለው ግን የኋላ ኋላ መንፈሳዊ ዋጋ ማሰጠቷ ነው። የእኛ ስህተት በኖርናት ጥቂት ክርስትና ምድራዊ ክብርና እና ዋጋ ለማግኘት መመኘታችን ነው። ቀድሞውኑ ክርስትና መች ለዚህ ዓለም ተፈጠረችና? ይልቁንም ክርስትና ዓለምን ከነግሳንግሷ መናቅ ነው። በተቃራኒውም በዓለም መናቅና መጠላት ነው።

ክርስትና እንደዚህ ናት። በሐዘን ውስጥ ታልፎ ደስታ የሚገኝባት። በክርስትና ከስር መሠረቱ ሐዘን እንጂ ደስታ የለም። የክርስትና ደስታ ከሞት ወዲያ ብቻ ነው። ዛሬ ዛሬ አንዳንዶች አስለመዱን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ድሮም የልቅሶ ቦታ እንጂ የእልልታ ቦታ አይደለችም። እንደ አባቶቻን አስተምህሮ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዕለተ ዓርብ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ በማሰብ ብቻ ቀሪ ሰባ ዓመት ዕድሜውን በለቅሶ የፈጸመ አባት ነው። ባይገባንም፣ ባንኖርባትም የእኛ እምነት ግን የቅዱስ ዮሐንስ እምነት ናት። ሞተ ወልደ እግዚአብሔር ዘወትር የሚታሰብባት፣ ግፍዓ ሰማዕታ የሚዘከርባት፣ ዕለተ ሞት የሚታሰብባት እምነት። እነዚህን ሁል ጊዜ ካዘከሩ በዚህ ምድር ደስታ ከየት ይገኛል? ይልቁንም ልቅሶ፣ የንስሃ እንባ፣ ከልብ የሆነ ሐዘን እንጂ። እኛ አሠረ ፍኖታቸውን የምንከተላቸው አባቶቻችን እኮ ሲገረፉ ቢያማቸውም፣ ሲሰደቡ ቢጸናቸውም፣ ደማቸው ሲፈስ እንዲሁ በብላሽ ፈሶ እንደማይቀር ነገር ግን አንድ ቀን ፈጣሪ እንደሚበቀል ስለሚያምኑ ትዕግሥታቸው ብዙ ነው። በእርግጥ የእግዚአብሔር ቸርነቱ ለፍጥረቱ ሁሉም ነውና እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ተግባራትን ለሚፈጽሙም አብዝቶ መራራቱና መታገሱ የሰማዕታት ነፍሳት ሳይቀር ሲገርማቸውበታላቅ ድምፅም እየጮሁ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም፣ ደማችንንስ በምድር ላይ በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም?” (ዮሐ ራዕ 6÷10) እስኪሉ ድረስ ያስገድዳቸዋል። በጊዜውእንደ እነርሱ ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ" ቢነገራቸውም (ዮሐ ራዕ 6÷11) እንደ እነዚህ ዓይነት ጨካኞች ባይኖሩ እኮ ሰማዕትነትም አይገኝም ነበር። የእነቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕትነት በተመሳሳይ የጭካኔ ሂደት የተገኘ እንጂ እንዲሁ አልጋ በአልጋ በሆነ ሕይወት የተገኘ አለመሆኑንም መርሳት የለብንም። ክርስትና እስካለ መጠላት፣ መናቅ አለ። ክርስትና እስካለ ግፍ እና ሰማዕትነት ይኖራል። በፍጻሜው እግዚአብሔርም የእነዚህን ሰማዕታት ደም በከንቱ በመተው አያሳፍራቸውምናእነሆ በቶሎ እመጣለሁ፣ ለእያንዳንዱም እንደሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።ይላቸዋል። (ዮሐ ራዕ 22÷12)

አምላከ ሰማዕታት የሰማዕታቱን ቤተሰቦች ያጽናናልን፤ ከሰማዕታቱም በረከት ረድኤት ይክፈለን። አሜን።

5 comments: