Thursday, August 8, 2013

የእስልምና እምነት ተከታዮች በበዓላቸው ቀን በተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን ተጠልለው ዋሉ


(አንድ አድርገን ነሀሴ 2 2005 ዓ.ም)፡- ከወራት በፊት መልኩን እየቀየረ የመጣው የፌደራል ፖሊስና የእስልምና እምነት ተከታዮች ከቀን ቀን ወደ ሌላ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ በበዓሉ ቀን ከጠዋቱ 11 ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም በዓሉን ለማክበር ሰዎች በእግርም በመኪናም ሲተሙ ተስተውሏል፡፡ አድማ በታኝ የፌደራልና  የአዲስ አበባ ፖሊሶችም ከለሊቱ 8 ሰዓት አንስተው በተለያዩ መኪኖች ወደ መሀል ከተማ ወደ የምድባቸው ቦታ ሲሰማሩ ነበር፡፡ ፌደራል ፖሊስ በስታዲየም እና አካባቢው ፤ በኢቲቪ እና አካባቢው በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ በመሰግሰግ ሁኔታውን በአንክሮ ሲከታተሉም ነበር ፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠር አድማ በታኝ ፤ ፌደራል ፖሊስ ፤ደህንነት እና የከተማዋ ፖሊስ ከተማዋን ትንፋሽ እስክታጣ ድረስ በሙሉ የፖሊስና በሲቪል ልብስ ተበትነው ታይተዋል፡፡
የበዓል ስርዓቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ አንዳች ግጭትና የተቃውሞ ድምጽ እንዳልተሰማ በቦታው የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ ፤ ፍርሀት በሁለቱም ወገን የነገሰ ቢሆንም አንዳች ነገር እንደሚፈጠር ድባቡ ያመላክት ነበር ፤ የበዓሉ ስግደት ከተጠናቀቀ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎች አለፍ ሲሉ ከኢቲቪ እስከ ቴሌ ድረስ ያሉት ሰዎች ድምጻቸውን ማሰማት ጀመሩ ፡፡ ነገሩ እየጋለ እየጋለ ድምጹም እየጨመረ ሲሄድ ኢቲቪ አካባቢ በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ ፖሊስ ክፉኛ በድንጋይ በመመታት ተዝለፍልፎ ወደቀ ፤ ኢቲቪ ግቢ ውስጥ እና አካባቢው መሽገው የነበሩት አድማ በታኞች ሰልፉን የተለያየ ቦታ በመቁረጥ በቆመጣቸው ስራቸውን መስራት ጀመሩ ፤ በድንጋይ የተመቱ ፖሊሶች እና በዱላ የሚመቱ ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ሄደ ፤ ኢቲቪ አካባቢ ያለች አንድ መኪና የተጎዱትን የፖሊስ አባላት በአፋጣኝ ወደ ህክምና ስትወስዳቸው የሚቀጠቀጡት ሰዎች ግን እየተሰበሰቡ መታጎር ጀመሩ ፤ ሌላው ሰልፉን በአፋጣኝ ለመበተን ፖሊስ ተጠቀመበት የተባለው መንገድ ሂጃብ የለበሱ ቆመጥ የታጠቁ በርካታ አባሎቻቸው በውስጥ በመገኝታቸው ነበር ፤ እነዚህ ሰዎች የያዙት ዱላ እህል ውሃ የሚያሰኝ አይደለም ፤ እነዚህ የደህንነት ሰዎች አንድም ሁለትም በመሆን እየለዩ በቆመጥ አውራ አውራን እየቀጠቀጡ ሰዎችን እየሰበሰቡ ማስገባት ተያያዙት ፤ በዚህ ሁኔታ በሚወረወሩ ድንጋዮች ብዙዎችን ከሁለቱም ወገን ጎዱ ፤ በዚህ የሁለት ወገን ግርግር ሊሰግዱ ያወለቁትን ጫማ መልሰው ያጠለቁ ጥቂቶች ነበሩ ፤ በርካታ አንድ አንድ እግር ጫማዎች ከረብሻው በኋላ  በየቦታው ተበትነው ተስተውለዋል ፤ ይህን አይነት ሁኔታ በአንዋር መስኪድ እና በአውቶቡስ ተራ ኳስ ሜዳ አካባቢም እንደነበር በቦታው ከነበሩ ሰዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ መንግሥት ከኢቲቪ የካሜራ ሰራተኞች እና ከደህንነቱ በመጠቀም በርካታ ካሜራዎችን በተለያዩ ቦታች ላይ በመስቀል ሲቀርጽ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከተሰቀሉ ካሜራዎች መሀከል አንዱ የካሜራ ባለሙያ እና ካሜራ ላይ ጉዳት እንደደረሰም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ ሁኔታ እየተባባሰ መልኩን እየቀየረ ከኢቲቪ አካባቢ ተክለኃይማኖት አካባቢ ሲደርስ የተስተዋለው ሌላ ነገር ነበር ፤ በተለያዩ አቅጣጫዎች ትዕዛዝ ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት አማኙን መሄጃ መላወሻ ስላሳጣው የነበረው አማራጭ በሩ ክፍት የነበረው ተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን ሰተት ብሎ መግባት ነበር ፤ ውስጥም ገብተው ካበቁ በኋላ  ፖሊስ ወደ ውስጥ እንዳይዘልቅ ለሰዓታት በሩን በመዝጋት በጻድቁ በአቡነ ተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን ተጠልለው ሊውሉ ችለዋል፡፡

ቤተክርስቲያን ለብዙ ጊዜ በግጭቶች መሃል መጠለያ ሆና አገልግላለች ፤ ሀረር ድሬደዋ መስመር 250 ኪሎሜት ተጉዘው አዋሽን አለፍ እንዳሉ የቦርደዴ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንን ያገኛሉ ፤ ይህ ቤተክርስቲያን ዙሪያውን አህዛብ ቢኖሩበትም ፤ በየጊዜው ቀጥተኛ ፈተና በምዕመኑ ላይ እና በቤተክርስቲያኑ ላይ ቢያደርሱበትም በችግራቸው ጊዜ ግን መጠለያ ሆኖ ከመጣባቸው ሰይፍ ሊያድናቸው ችሏል፡፡ ቦታው በየጊዜው አፋሮች ፤ ኢሳዎች ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች በግጦሽና በእርሻ መሬት ምክንያት ጦር የሚማዘዙበት ወረዳ ነው ፡፡ በአንድ ወቅት ኢሳዎች አካባቢው ላይ ያሉትን ባላንጣዎቻቸውን ሊያጠፉ አድፍጠው በመጡበት ጊዜ በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ የሚገኙት አህዛቦች መትረፍ የቻሉት በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ገብተው እንደነበር በአንድ ወቅት አሰቦት ገዳም በሄድንበት ጊዜ ለማወቅ ችለናል፡፡


እግዚአብሔር ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን

1 comment:

  1. Amlake teklehaymanot betechristianachnin yitebik!

    ReplyDelete