Friday, August 23, 2013

ሰውን መልአክ እያደረግን ሙት አመት ማሰብ አግባብም ስርዓትም አይደለም

  • አቶ መለስ ለአንድም ቀን ተሳስተው እንኳ ‹‹እኔ ከአብ ዘንድ ተልኬ መጣሁ!›› ሲሉ ተሰምቶ አይታወቅም   አናንያ ሶሪ

(አንድ አድርገን ነሀሴ 17 2005 ዓ.ም)፡- የዛሬ ዓመት በዚህ ሰዓት በፆመ ፍልሰታ ነሀሴ 9 ቀን ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አረፉ ፤ ነሀሴ 15 ከስድስት ቀን በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን ኢቲቪ በጠዋት ዜና አቀረበ፡፡ አሁን ሁለቱም ካለፉ አንድ አመት ሞላቸው ፤ መንግሥትም በዝግ የፓርላማ ስብሰባ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን እንዲቋቋም ወሰነ ፤ የቦርዱ ሰብሳቤዎች ወ/ሮ አዜብ መስፍንና አቶ ካሳ ተክለብርሀን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ተደርገው በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ተመረጡ ፡፡ በየተንቀሳቀሱበት የመንግሥት ፤ የግል ተቋማትና መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎች ውስጥ የመለስን ፎቶ ከአንዳድ ጥቅሶች ጋር ተሰቅለው ይመለከታሉ ፡፡ ፎቷቸውን ኢቲቪ ለበርካታ ወራት የዜናው background  አድርጎትም ተስተውሏል ፤ ኢቲቪ ልብ ገዝቶ ፎቶውን ዘወር ሲያደርግ የኦሮሚያ ቴሌቪዥን እስከ አሁን ድረስ ፎቶውን ከዜና አቅራቢው ጀርባ ላይ አለማንሳቱም ይታወቃል ፤ ሲጀመር ‹‹የአቶ መለስን አስከሬን መቀበር የለበትም በሙዚየም መቀመጥ አለበት›› የሚሉ ጥቂት ሰዎች ሃሳብ በማንሳታቸው መንግሥትም ሃሳባቸውን በመቀበል ‹‹ለማሰራት ያሰብኩት ሙዚየም ሲያልቅ አስከሬኑን በግልጽ በሙዚየም አስቀምጠዋለሁ›› የሚል አቋም መያዙ ይታወቃል ፤ አንድ ደፋር መናፍቅም ‹‹እግዚአብሔር አመላክቶኛል መለስ አልተሞተም›› እያለ ለቀናት ቤተ-መንግሥቱ በር ላይ እንደሰነበተ እንደሚያስነሳውም ሲናገር ነበር ፤ በማወቅም ባለማወቅም በየቦታው የተሰቀሉት ፎቶዎች ማኅረሰቡ ላይ የማይታይ ተጽህኖ በመፍጠራቸው ሰውየውን ከመላዕክት ከጻድቃንና ሰማዕታት ጋር በማሰለፍ እጃቸውን ወደ ላይ አድርገው ፤ በጉልበታቸውም ተንበርክከው ለፎቶ የሰገዱ ብዙዎች ነበሩ ፡፡


አሁን ነገሮች ያለፉ ቢመስሉም የሰውየው ሙት ዓመት በመድረሱ ሁኔታዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እየተመለሱ ይመስላሉ ፤ ኢቲቪ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ በማለት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እና የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት በቀጥታ እያስተላለፈ ይገኛል ፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹አንደኛ ዓመት መታሰቢያ›› የሚለው ጽሁፍ ላይ ለምን ኢቲቪ ‹‹ሙት ዓመት›› የሚለውን አልጨመረበትም ሲሉ አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡ ወይስ ባለ ራዕይ አይሞትም? የሚለውን ብሂል በመጠቀም ነው ‹‹ሙት ዓመት›› መሆኑ ያልተገለጸው… ?ይላሉ፡፡ አንዳንዶች አሁን መንግሥት የያዘው አያያዝ የሰሜን ኮሪያውን ልጅ እና አባትን እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል ፤  የአያት Kim Il-Sung እና የልጅ  Kim Jong Il ልደታቸው ፤ ንግሥናቸው እና ሙት አመታቸው በዚህ ዓመት አንድ ጊዜ መንበረ ስልጣኑን በተቆናጠጠው በልጅ ልጃቸውKim Jong-un   እና ቀድሞ በመንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ለአራት አስርት አመታት ሲከበር ቆይቷል ፡፡ ከወራት በፊት የአያትየውን Kim Il-Sung የተወለዱበት 100ኛ ዓመት ሲከበር ከቀናት በኋላ ደግሞ ልጃቸው ያረፉበትን ቀን ህዝቡ ሲያከብር ነበር፡፡ አሁንም ኢህአዴግ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙት ዓመት ነሀሴ በመጣ ቁጥር እንደ ሰሜን ኮሪያው ያለፉ መሪዎች ዝክር እንዳያደርገው እንሰጋለን ፤ ሌሎች ደግሞ የሙት ዓመታቸው አይግረማችሁ ገና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልደት ህዝቡ ከዚሀ በላይ እንዲያስበው ይደረጋል በማለት የወደፊቱን ይተነብያሉ፡፡    

ግራም ነፈሰ ቀኝ እየሆነ ያለው ነገር የብዙዎች መነጋገሪያ አርዕስ ሆኗል ፤ ባሳለፍነው ሳምንት በጉለሌ አረንጓዴ ፓርክ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛ ሙት ዓመት በሚከበርበት ጊዜ አንድ እጅግ የተጋነነ ነገር ሰማን … እርሱም ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት ቢኖሩ ለአለም የምጣኔ ሀብት ቀውስ መፍትሄ ማምጣት የሚችል አቅም ነበራቸው›› የሚል ፡፡ የአለም የምጣኔ ሀብት ቀውስ ከተፈጠረ 5 ዓመታት ሊሞላው ነው ፤ እርሳቸው ያለፉት ከአንድ አመት በፊት ነው ፤ ታዲያ መፍትሄው ባለፉት በኖሩበት አራት አመታት መቼ መጣ?  የዓለሙን እንተወው እና ይህው ህዝባችን በቀን ሶስት ጊዜ ትበላለህ ተብሎ ቃል ከተገባለት 20 ዓመት አለፈው ፤ አሁንም ከእጅ ወደ አፍ የሚኖረውን የህብረተሰባችን ክፍል ቤቱ ይቁጠረው ፤ ታዲያ ይህን ያህል ማጋነን ለምን አስፈለገ ? ጋዜጠኞች በዚህ ዙሪያ ሲዘግቡ አዕምሮውን የሳተ ሰውን ይመስላሉ ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል አንድ ነገር ተሰምቷል ፤ ህጻናት ሲያድጉ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ እና ራዕያቸውን ለማሳካት ትጥቅና ስንቅ እንዲሆናቸው ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢያቸው ውስጥ ‹‹የመለስ ቤት›› የሚባል ክፍል ተሰርቶላቸዋል ፤ እዚህ ክፍል ለመግባት ጫማ ማውለቅ የመጀመሪያው መስፈርት ነው ፤ ታዲያ በትምህርት ቤት ውስጥ ‹‹የመለስ ቤት›› ተብሎ ጫማ አውልቆ መግባት ለህጻናት ምን ይቀርጽባቸው ይሆን..? ውስጡ ያለው ምንም ይሁን ምን ከአምልኮ ቦታስ ምን ይለየዋል ? እየሆነ ያለው ነገር ቆም ብሎ ላሰበበት ብዙ የሚያስብል ነገር አለው፡፡ ታዲያ የሚሰራው ሁሉ እየታሰበበት ቢሆን መልካም ነው ፤ አቶ መለስ ያላቸውን ስብዕና ብቻ ማስቀመጡ ጥሩ ነው ፤ ማጋነኑ ግን የሌለውን መደረብ ትዝብት ላይም የሚጥል ይሆናል፡፡  

ከቀናት በፊት በጣም በርካታ እናቶች በሰልፍ ከስድስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ እየወረዱ ይታያሉ ፤ አንዲት ጥቁር መኪና የአቶ መለስን ፎቶ በትልቁ በግራ በቀኝ ሰቅላ ዙሪያዋን በጉንጉን አበባ ተከባለች ፤ የእናቶች ነጠላ አለባበስ እና የመኪናዋ ፤ የፎቶው እና የአበባውን ሁኔታ ሲመለከቱ አስከሬን ለመቅበር ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ እንጂ ሙት አመት ነው ብሎ መገመት ያስቸግራል ፡፡ አንድ ነጭ ጸጉር ማረፊያ ያደረጋቸው አዛውንት ‹‹ደሞ ምንድነው ?›› ብለው ሲጠይቁ የመለስ ሙት አመት መሆኑን ተረዱ ‹‹አይ ከዚህ ህዝብ ጋር መቆጠሬ ነው የሚያበግነኝም የሚያንገበግበኝም ብለው…..›› የተናገሩትን ሳይጨርሱ መንገዳቸውን ቀጠሉ ፤ ሙት ዓመት እስከ ሰባት ሟች እንዲታወስ ቤተክርስቲያንም ታዛለች ፤ ሟችን ስናስበው ግን የራባቸውን በማብላት ፤ የጠማቸውን በማጠጣት ፤ የታረዙትን በማልበስ ፤ የሟች ስመ ክርስትናውን ‹‹ነፍስ ይማር›› እያሉ እንዲያስቡ ፤ ነዲያንን በመመጽወት እና ጸሎት ላይ ስሙን በማንሳት ነው፡፡ ሙት ዓመትን የምናስብበት አግባብ አለው…. ሰውን መላዕክት እያደረግን ሙት አመት ማሰብ አግባብም ስርዓትም አይደለም፡፡  

አናንያ ሶሪ የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ በሰላ ብዕሩ የሰሞኑ የኢቲቪ ሙት ዓመት ምናምን ወሬ በጣሙን የሰለቸውና የታከተው እንዲህ ብሎ በ‹‹ፋክት መጽሄት›› ሃሳቡን አስቀምጧል
………አቶ መለስ ለአንድም ቀን ተሳስተው እንኳ ‹‹እኔ ከአብ ዘንድ ተልኬ መጣሁ!›› ሲሉ ተሰምቶ አይታወቅም ፡፡‹‹እኔ ከዚህ እንደ ወርቅ በእሳት ከተፈተነ ህዝብ ወጣሁ!›› ሲሉ እንጂ፡፡ ታዲያ የትግራይ ማኅጸን ከአንድ መለስ በላይ ‹‹መሪ›› ወይም ‹‹ታላቅ መሪ›› የማታፈራ የወላድ መካን ናትን? አቶ መለስ በስማቸውና በአስተምህሮታቸው ዙሪያ ቀን ተቀድሶለት እና ጠበል ጻዲቅ ተደርጎለት በየወሩ እና በየዓመቱ የሚደገስ ‹‹ዝክር›› የሚያሻቸው ፤ መልአክ ወይም ቅዱስ-ሰማዕት ናቸው እንዴ? ደግሞስ በአስተምህሮታቸው ላይ ቀኖና እና ዶግማ ተበጅቶላቸው ልክ እንደ ክርስቶስ የሚከተሏቸው መሲህ ወይም የእምነት መሪ ናቸው? ዳግመኛም በኢትዮጵያ እና በህዝቦቿ ላይ ለመፍረድ በዚያች ከአብ በስተቀር ማንም በማያውቃት የፍርድ ቀን በታላቅ ግርማ እስኪመለሱ ድረስ በ‹‹መንፈስ-መለስ››( ለእነሱ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ማለት) ተከታዮቻቸውንና አማኞቻቸውን (አሞኚዎቻቸውን ቢባል ይቀላል) የሚመሩ የአምላክ ልጅ ናቸውን? ኧረ እፈሩ 
‹‹ኢህአዴግን አናውቀውም ፤ እናውቀው ዘንድ እንከተለው !›› ልትሉን እኮ ምንም ታህል አልቀራችሁም፡፡ ከአውራ ፓርቲ አልፋችሁ አምላክ ፓርቲ አላችሁሳ!..... እያለ ይቀጥላል ፋክት መጽት ነሀሴ 2005 ዓ.ም ቁጥር 7


No comments:

Post a Comment