(አንድ አድርገን ጥር 16 2005 ዓ.ም)፡- ቦታው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከጦር ኃይሎች ወደ ወይራ ሰፈር ሲሄዱ
ከ2 ኪሎሜትር በኋላ ከአጉስታ ልብስ ስፌት ፋብሪካ አለፍ ብሎ ይገኛል፡፡ በ14/05/2005 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ምክንያቱ
እስከ አሁን ያልታወቀ አሳት የአጉስታ ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ ከፍተኛ አደጋ አድርሷል ፤ ቤተመቅደሱ የተዘጋው ከጠዋቱ
3 ሰዓት በፊት ቢሆንም እሳቱ ግን የተነሳው 7 ሰዓት አካባቢ መሆኑ ሰዎችን አነጋግሯል ፤ ከቤተክርስቲያኒቱ በጣሪያ በኩል ትንሽ
ትንሽ ጭስ መውጣት ከታየ በኋላ ብዙም ጊዜ ሳይሰጥ ነዳጅ የተርከፈከፈበት እስኪመስል ድረስ ተንቦገቦገ ፤ በደቂቃዎች ውስጥ በርካታ
ሰዎች ከአካባቢው በመሰባሰብ እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት አደረጉ ፤ እሳቱን ለማጥፋት አካባቢው ላይ ባለው ነገር ከፍተኛ ጥረት
ቢደረግም በወቅቱ እሳቱን ማጥፋት ግን አልተቻለም ፤ ይህ ጉዳይ ከአቅም በላይ መሆኑን በመገንዘብ ለአዲስ አበባ እሳት አደጋ መስሪያ
ቤት ስልክ ተደውሎ የነበረ ቢሆንም እነርሱ እስኪመጡ ድረስ እሳቱ ከፍተኛ ጉዳይ አድርሶ ነበር ፤ በቦታው የደረሱበት ሰዓትም ብዙ
ነገሩ ወደ አመድነት የተቀየረበት ጊዜ ነበር ፤ ሕዝቡን እጅጉን ያስገረመው በውስጡ የነበሩት የእመቤታችን ፤ የቅዱስ ኡራኤልና ፤
የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሀንስ ታቦታት ምንም ያለመሆናቸው ጉዳይ ነበር ፤ ከዚህ በተጨማሪ ማገሩን የበላው እሳት አባቶች ቅዳሴ
ላይ የሚይዙት የእንጨት የነሀስና የብር መስቀሎች እና የተለያዩ ቅዱሳት
መጻህፍት ምንም እሳት ሳይነካቸው መገኝታቸው በምዕመኑን ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል ፡፡
ቤተክርስቲያኒቱ ውጯ በቆርቆሮ ውስጧ ደግሞ
በኮምፐልሳቶ የተሰራች ነበረች ፤ ውስጡ ወለሉ በሲሚንቶ የተሰራ ሲሆን በርካታ ምንጣፎች በአራቱም መአዘን መቅደስ ውስጥ መነጠፋቸው
ከሳምንት በፊት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ሳስቀድስ አስተውያለሁ ፤ የተደራረቡት ምንጣፎች በአንድ በኩል ብቻ ከ8 እንደሚበልጡም ተመልክቻለሁ
፤ በጊዜው ምንጣፎቹን ለማጽዳት ከውስጥ ወደ ውጭ በማውጣት ስራ ላይ ተሳትፌ በነበረበት ወቅት ለምን ይህን ያህል በአንድ በኩል?
ብዬ ለራሴም ጠይቄአለሁ ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የውስጥ ስፋት በጠቅላላው ከ120 ካሬ የማይበልጥ ይዞታ ነበራት ፤ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ
ጳውሎስ በሕይወት ሳሉ በየካቲት ወር 2001 ዓ.ም የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት በአሁኑ ሰዓት ከ70 በመቶ በላይ ስራው የተጠናቀቀ
እጅግ ውብ የሆነ ቤተክርስትያን በመሰራት ላይ ይገኛል ፡፡
እሳቱ ጉዳት ካደረሰ በኋላ አባቶች በጊዜው ከነበረው ምዕመን ብቻ ከ3 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 70 ሺህ ብር መሰብሰብ መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል ፤ በቀጣይ ቀን የተሰበሰበው
ብር ከ200 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ ለማወቅ ተችሏል ፡፡ ብዙዎች የሆነውን አይተው ጥጋቸውን ይዘው ሲያለቅሱ ተስተውሏል ፤ እሳቱ በብዙ መቶ ሺህ የሚገመት ንብረት ቢያጠፋም የጠፋው ንብረት ይህ
ነው ተብሎ መገመት በአሁኑ ሰዓት አልተቻለም ፤ ከቃጠሎ በኋላ ህዝቡን አንድ በማድረግ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመመካከር ስራው
ከቃጠሎ ከሰዓታት በኋላ ተጀምሯል ፤ ታቦታቱን የተረፉትን የቤተክርስቲያኒቱን መገልገያዎች ወደ አንድ ቦታ በማሳረፍ ወደ አመድነት
የተቀየረውን ቦታውን በማስለቀቅ ስራው ወዲያው የእጅ ሙያተኞች ባሉበት ተጀምሯል ፡፡
በፊት የነበረችበት ቦታን ሰፋ በማድረግ ሲባጎ በመወጠር የማዕዘን እንጨቶችን የማቆም ስራ ወዲያው ተሰርቶ ተጠናቀቀ ፤
በዚህ ሁኔታ ማክሰኞን ያደረው ስራ ረቡዕ ጠዋት በመቀጠል አናጺ ፤ ግንበኛ ፤ እና የተለያዩ የሙያ ባለቤት የሆኑ ሰዎች ከቅርብም
ከሩቅም በመምጣት ስራውን ተያያዙት ፡፡ ግንበኛው ውሀ ልክ የሚቆምበትን ለክቶ ሲያበቃ ምዕመኑ አካፋ እና ዶማ በመቀባበል ስራውን
መስራት ተያያዘው ፤ የምዕመኑ ተሳትፎ ለተመለከተው የእርከን ስራ ለመስራት የተሰበሰበ አርሶ አደር እንጂ አንዲትን ቤተክርስቲያን
ለማቆም የተሰበሰበ አይመስልም ነበር፡፡ ጠዋት 2 ሰዓት ላይ እኛ በቦታው ስንደርስ አራቱም መዓዘን እንጨት የማቆምና እርስ በእርሱን
በሚስማር የማያያዝ ስራ በበርካታ ወጣት አናጢዎች እየተሰራ ነበር ፤ ይህ በእንዲህ እያለ ሁኔታውን በማለዳ የሰሙ ምዕመናን ታቦታቱ
ያረፉበት ቦታ በመሄድ ጸሎት ሲያደርሱ እንባቸውን ሲያፈሱ ተስተውሏል ፤ ከአራት ዓመት በፊት በተጀመረው ቤተክርስቲያን ላይ የእመቤታችንን
ስዕል በማውጣት ምንጣፍ በመነጠፍ የማስተባበር ስራው አባቶቹ ሲሰሩ ነበር ፤ በዚህ ጊዜም በርካቶች ሚስማር ፤ ቆርቆሮ ፤ ማገር
፤ ሽቦ ፤ ሲሚንቶ በዚያኑ ቀን የሚያመጡት ብዛት እየተናገሩ ቃል እየገቡ ነበር ፤ እነዚህ ሰዎችም ብዙዎቹ እስከ ቀኑ 8 ሰዓት
ድረስ ቃላቸውን ጠብቀው በተለያዩ መኪናዎች እቃዎችን ሲያራግፉ ታይቷል ፤ በአካባቢው የሚገኙ የማነ ብርሀን አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች
እና የትንቢተ ኤርሚያስ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ከነ ዩኒፎርማቸው ለስራው የሚያስፈልጉ ድንጋዮችን ፤ ጠጠሮችንና አሸዋን ወደ
ሚሰራበት ቦታ ሲያመላልሱ ነበር ፤ እድሜያቸው ከ9 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በሚጢጢ እጃቸው የቻሉትን ኮረት ሲያመላልሱ ነበር
፤ በማለዳ የተጀመረው የማገር ማቆም ስራ ተጠናቅቆ ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ ዙሪያውን ምዕመኑ ባመጣው ቆርቆሮ አማካኝነት ዙሪያውን
የማልበስ ስራ ተከናውኗል፡፡ ጣሪያውን የሚሸከመው መሀል ላይ የሚቆመውን
ምሰሶ በአርማታ በማድረግ ከመሀል ወደ ግድግዳ የሚሄዱት ወራጆች ስራ እስከ ማታው ጊዜ ድረስ እየተከናወነ ነበር ፤ ማገሩ ላይ የሚያርፉ
ሞራሌዎችም በግዥና በምዕመኑ ቃል ተደርድረው ተመልክተናል ፤ ቤተክርስቲያቱ ዙሪያውን እንደ መሬቱ አቀማመጥ ውሃ ልክ ከ30 ሴንቲ
ሜትር እስከ አንድ ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያላቸው ውሃ ልኮች ተሰርተው ተጠናቅቀዋል ፡፡
ምዕመኑ ወጣት ሰራተኞች ድካም እንዳይሰማቸው አስተባባሪው
የጠየቀውን ነገር በአጭር ደቂቃ ውስጥ ሲያሟሉ ተስተውሏል ፤ በርካታ እናቶች ከቤታቸው እንጀራ ወጥ እና ውሃ ወደ ቦታው
በማምጣት ለስራው መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል ፤ አጋጣሚ በቦታው የተገኙ አንዳንድ ሰዎች ከ10 ሳጥን ያልተናነሰ
ለስላሳዎች በበርካታ ፌስታል የታጨቁ ዳቦዎች በመኪና በማምጣት ለአስተባባሪው ሲሰጡም ነበር፡፡ የተቃጠለችውን ቤተክርስቲያን ለደቂቃ
ላለማቋረጥ ግማሹ ምግብ ሲበላ ግማሹ ስራውን ሲያፋጥንም ነበር ፤ ምዕመኑ እያደረገ ባለው ነገር አባቶች የሚያመሰግኑበት ቃልም አጥተዋል፡፡
በቦታው ላይ የሚገኙ ወጣቶች ቤተክርስቲያኒቱ የደረሰባትን ነገር እና እየተሰራ ያለውን ስራ ማንም በፎቶም ይሁን በቪዲዮ ቀርጾ እንዳያስቀር
ትዕዘዛ ስለሰጡ አሁን ያለበትን ሁኔታ ትዕዛዛቸውን በማክበር በካሜራ ማስቀረት አልቻልንም ፡፡
ስራው ሀሙስ ቀጥሎ ሲውል የጣሪያ ማረፊያ ሞራሌዎችንና ጣሪያውን የመምታት ስራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል ፤ ከዚህ በተጨማሪም
ውስጡም በመቆፈር ድንጋይ በመሙላት ሲሚንቶ የማድረግ ስራ ይቀጥላል ፤ ጥር 21 በድምቀት ለሚከበረው በዓል ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ
ይደርሳል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
መርዳት የምትፈልጉ ከቻሉ በአካል በቦታው ላይ በመሄድ ሁኔታውን ተመልክተው የራስዎች እርዳታ ያድርጉ እንላለን ፤ በአካል
መሄድ ላልቻሉ ሰዎች አሰሪ ኮሚቴዎቹ የሚረዱበትን መንገድ ካስቀመጡ እሱን እናስታውቆታለን፡፡
ቀጣይ ሁኔታዎችን ይጠብቁን
I tend not to drop a comment, however I looked at through a few
ReplyDeleteresponses on "የአጉስታ ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ".
I actually do have 2 questions for you if it's okay. Is it only me or do a few of these comments appear like they are coming from brain dead individuals? :-P And, if you are writing at other places, I would like to keep up with anything new you have to post. Could you make a list of all of all your public pages like your linkedin profile, Facebook page or twitter feed?
my web blog; wiki.thewarz.com.es