Saturday, March 5, 2016

አቡነ ማትያስና ሦስቱ የአዙሪት ዓመታት


  • ‹‹እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር በታሪክና በሃይማኖት የምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን›› አቡነ ማትያስ ከ15 ዓመት በፊት ካሉት የተወሰደ

(አንድ አድርገን የካቲት 27 2008 ዓ.ም)፡- ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት›› ብላ ቤተክርስቲያን አምስተኛውን ፓትርያርክ ለጥቃ ከሾመቻቸው ይህው ሦስት ድፍን ዓመት አለፋቸው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ በአምስተኛው ፕትርክና ዘመን ያሳለፈችውን ረመጥ የሆነን መንገድ ያስተካክላሉ ፤ ቤተክርስቲያኒቱንና ምዕመኗን ወደ ቀደመ ክብራቸው ይመልሳሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው አቡነ ማትያስ መንበሩ ላይ ከተሾሙ ይህው ሦስት ድፍን ዓመት አለፋቸው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ችግር የምዕመኑን መከራ ፤ የአብያተ ክርስቲያናትን መቃጠል ፤ የተሀድሶያውያንን እንቅስቃሴ ፤ የመልካም አስተዳደርን እጦትን ከቁብ ያልቆጠሩት አባታችን ይህው እንደዋዛ ከሳምንት በፊት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትላልቅ ባለስልጣናት በተገኙበት በቤተክርስቲያቱ ዓይን ትልቅ የማይመስል ፤ የመገናኛ ብዙሀን ምንም ያልተነፈሱበት የካቲት 24 2008 ዓ.ም የሦስት ዓመት ውዝግብ፤ ክስ ፤  ለሰሚው የሚያሳፍር ባዶ ዛቻና ማስፈራሪያ ሦስተኛ ዓመት አክብረዋል፡፡


በሁለት ሺህ ብር ደመወዝ የሁለት ሚሊየን ብር መኪና በሚያሽከረክሩ ሰዎች የተከበቡት አቡነ ማትያስ ለሦስተኛ ዓመት በዓለ ሲመታቸው የታሰበውን 500 ሺህ ብር በርሀብ ለተጎዶ ወገኖች መለገሳቸውን በመገናኛ ብዙሐን ተነግሮላቸዋል፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ከአንድ ከአዲስ አበባ አጥቢያ ብቻ በሚመዘበርባት ቤተክርስቲያን ፤ ከአርባ ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላት እምነት ፤ ለ15 ሚሊየን በላይ ለሆነ የድቅ ተጎጂ 500ሺህ ብር መስጠት ማለት ከዜና የዘለለ ፤ ከስላቅ የበለጠ ሆኖ አይታይም፡፡

አባታችን ቀድሞ በአሜሪካ ሳሉ ለአምስተኛው ፓትርያርክ ‹‹የሲኖዶስ ሕልውና ይከበር›› በማለት በርካታ ደብዳቤዎችን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እና በወቅቱ ለነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች እየላኩ ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ያላቸውን ተቆርቋሪነት ፤ ፖለቲካው ስርዓተ ቤተክርስቲያንን እያበላሸ ስለመሆኑ ፤ መንገድ እና አካሄዱን ሳይጠብቁ ከመንበረ ፓትርያርክ የሚወጡ ደብዳቤዎች ሊታሰብባቸው እንደሚገባ አበክረው ሲመክሩ ሲዘክሩ ነበር፡፡ ጊዜ የሄደውን ሲያሳልፍ የመጣውን ሲያስቀምጥ ይህው ወቅቱ ደርሶ ሲቃወሟቸው ፤ ሲመክሯቸው ፤ ሲዘክሯቸው በነበሩት በአምስተኛው ፓትርያርክ ተተክተው ስድስተኛ ተብለው ከተሾሙ ይህው ሦስት ዓመት ሞላቸው፡፡ በጊዜው አቡነ ማትያስ የሚጽፉትን መልዕክት አንድም አቡነ ጳውሎስ መልስ አይሰጡም ነበር ፤ አንድም መልዕክቱ ቢደርሳቸውም ለቅዱስ ሲኖዶስ አያቀርቡትም ነበር፡፡ አሁንም ከሳሽ የተከሳሽ ቦታን ይዞ የቀድሞውን አዙሪት እያስቀጠሉት ይገኛሉ፡፡ 

አቡነ ማትያስ ከ15 ዓመት በፊት ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለፓትርያርኩ መልዕክት ሲጽፉ ‹‹ተከታዩ ምዕመናንም ቢሆን ክብሩን የተጠበቀ  መንፈሳዊ አባት ማየት ይፈልጋል››  ብለው ነበር ፡፡ አዎን እውነት ነው ፤ በአሁን ሰዓት የሚገኝ ምዕመንም ከዘረኝነት ፤ ከሙሰኝነት ፤ ከጎጠኝነት እና ከምንፍቅና የጸዳ ፤ ቤተክርስቲያኒቱ የጣለችበትን ታላቅ ሃላፊነት በአግባቡ የሚወጣ ፤ ያለባትን ችግር እንደ ራሱ ችግር በመቁጠር የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያመላክት ፤ አባቶች ያስተላለፉልንን ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን በቀሳጥያን ሳይበጣጠስ ለቀጣይ ትውልድ የሚያስተላልፍ ፤ ቤተክርስቲያኒቱን ወደ ቀድሞ ልዕልናዋ የሚመልስ ፤ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር ስለ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን አንድ አቋም ያለው ፤ የራሱ ክብር የቤተክርስቲያኒቱ ክብር ፤ የቤተክርስቲያኒቱ ክብር የራሱ ክብር አድርጎ የሚያይ አባት ይፈልጋል፡፡  ይህን ፍላጎት ይሟላል ብለን ተስፋ ብናደርግም አባታችን ዙሩ በከረረ በቀድሞ አዙሪት ውስጥ ወድቀው ይህው ሦስተኛ በዓለ ሲመታቸውን አከበሩ፡፡

አባታችን  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከ15 ዓመት በፊት በምድረ አሜሪካ ሳሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ ብለው ጽፈው ነበር ‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕግ አውጪና የመጨረሻው አካል እንደመሆኑ መጠን እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር ተራና ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ  ይዘባርቃል ብለን አናምንም ፤ በስመ ሲኖዶስ  የሚጠቀሙት ባለስልጣኖች ሲኖዶሱን ባያሰድቡ መልካም ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ አርማና ማህተብ የሚበሩ ደብዳቤዎች እጅግ ከፍተኛ ለሆኑት ጉዳዮች ብቻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ግን ነገሩ ሁሉ ጨዋታ መሆኑ ነው፡፡›› ብለው ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ ቀድሞ በስመ ሲኖዶስ ስም የሚወጣ አንድ ደብዳቤ እንዲህ አሳስቧቸው ከሺህ ማይሎች ርቀት ላይ ይህን ብለው ነበር፡፡ አሁን ግን ዙሪያቸውን በከበቧቻ ግሪሳ እና አንበጣዎች አማካኝነት በመመራት በየጊዜው ለሰሚውም ሆነ ለአንባቢው ግራ የሆኑ ደብዳቤዎች ፤ ክሶችና አሉባልታዎችን በስማቸው እና በፊርማቸው ማውጣት ከጀመሩ ይህው ሦስት ድፍን ዓመት ሆናቸው፡፡ ከደብዳቤዎቹም በተጨማሪ እጅግ ለምዕመኑ አሳፋሪ የሆነ ‹‹አባ ማትያስ አላበደም ፤ መልዕክት እያስተላለፈ ነው›› በማለት 40 ሚሊየን ምዕመን አባት ይሁኑ ብሎ የሾማቸው አባት የሚናገሩትን የሚያውቁ እስከማይመስሉ ድረስ የነገሯቸውን ሲነግሩን እኛም ስንሰማ ይህው ሦስት ድፍን ዓመት ሆናቸው፡፡

ቀድሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና የሚያስጨንቃቸው አቡነ ማትያስ አሁን ላይ ያሉበትን መንበር እየሄዱበት ያለው መንገድ ያስተዋሉት አይመስልም ፤ በታሪክ ወቃሽ ሆነው እነዚያን ከ20 ገጽ የሚበለጡ ገጾችን የጻፉ ጣቶች አሁን ላይ የቤተክርስቲያኒቱንና የምዕመኑን ሰላም በማናጋት ፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውጪ እየሰሩ ከሚገኙት ግልጽ  ስህተት የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አያድናቸውም፡፡ እርሳቸው ከዓመታት በፊት እንዳሉት ‹‹የእግዚአብሔር ባለ አደራ መሆን ቀላል ስላይደለ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፤ በታሪክና በሃይማኖት በምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን፡፡››

ትውልድ ያልፋል ተውልድም ይተካል ፤ ያለፉት አባቶች ቤተክርስቲያቱ ላይ ጥለው የሚሄዱት ያስተካከሉትም ሆነ ያጠለሹት ሥራ ተጽፎ የሚቀመጥበት ዘመን ይመጣል ፡፡ ሹመት ለሰራበት ክብርን ፤ ሞገስን ፤ መልካም ነገርን ይዞ እንደሚመጣ ሁላ ፤ ሹመቱን በአግባቡ ላልተወጣው ግን ነቀፌታን ይዞ ማኖሩ የማይቀር ነው፡፡ አሁንም በዚህ አዙሪት ውስጥ በአቡነ ማትያስ በዓለ ሲመት ላይ በመገኝት ‹‹እንኳን አደረሰዎ›› የምንልበት መልካም ነገር ባለፉት ሦስት ዓመታት አልተመለከትንም፡፡  ነገር ግን እግዚአብሔር እድሜ ሰጥቶዎ ለተቀመጡበትን መንበር የሚመጥን ሥራ እንዲያሰራዎ ‹‹ እግዚአብሔር ሆይ ለአባቶቻችን ማስተዋል ፤ ልቦናንና ጥበብን አድልልን›› እያልን ዘወትር እንጸልያለን፡፡
 


2 comments:

  1. ''በቅዱስ ሲኖዶስ አርማና ማህተብ የሚበሩ ደብዳቤዎች እጅግ ከፍተኛ ለሆኑት ጉዳዮች ብቻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ግን ነገሩ ሁሉ ጨዋታ መሆኑ ነው፡፡›› ብለው ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ

    ReplyDelete