Thursday, December 3, 2015

‹‹እኛ አሁን ቁጭ ያልነው እግዚአብሔርን አምነን ነው ፤ ዝናብ ከቀረ መልቀቅ ነው ፤ መሄድ ነው ፤ መሞት ነው›› የአካባቢው ገበሬ(አንድ አድርን ህዳር 24 2008 ዓ.ም)፡- በድርቅ በተጎዶ የደቡብ ወሎ ዞኖች ውስጥ ባደረግነው ዳሰሳ በሦስተኛ ቀናችን በአሸዋ መኪና ከአጂባር ተነስተን  ፉርቃቄ ፤ ጎሽ ሜዳ ፤ ዋልካ ሜዳ እና ሰንበሌጤን ተመልክተን ነበር፡፡ መንገዱ የተጎዳ ፒስታ መንገድ ስለሆነ ጉዞው ሰውነትን የሚያንዘፈዝፍ አድካሚ ነበር፡፡ እነዚህ አካባቢ ቆላማ ቦታዎች ሲሆኑ  የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው  አካባቢዎች ነበሩ፡፡በቦታዎቹ በተገኝንበት ወቅት እድሜያቸው ከ60 የሚዘልቁ ሁለት አርሶ አደር ገበሬዎችን በመቅረጸ ድምጽ ፍቃዳቸውን ሳንጠይቅ በውይይት መልክ ከቀረጽነው ውስጥ ለአንባቢ እንዲሆን እንዲህ አዘጋጅተን አቅርበነዋል፡፡


ከመጀመሪያው አርሶ አደር ጋር የተደረገ ውይይት..
መቼ ነው ዝናብ እናንተ ጋር የዘነበው ?
ዝናቡ ሃምሌ 20 አካባቢ ነበር የጀመረው ፤ ትንሽ ጥሎ ሲያበቃ ፤ አድሮ ሲያካፋ አድሮ ሲያካፋ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ በዚያው  ቆመ፡፡

ዝናቡ ቆላው ላይ ብቻ ነው ያልጣለው? ሌላ ቦታ ላይ ዝናብ ጥሎላቸዋል ?
እኛ አካባቢ ብቻ ነው ወደ ላይ(ደጋው ክፍል) ይሻላል፡፡

ከአሁን በኋላ ዝናብ የምጠብቁት መቼ ነው ?
መጋቢትን ይዘን ወደ ሚያዚያ…

አካባው የበልግ ዝናብ አለው ?

        የለውም ፤ አያውቅም ፤


አሁን ለከብቶች የሚሆን ነገር ምንድነው የምታገኙት ?
        ዘንድሮማ ምን አለን ? ከብቶቻችንን እየሸጥን ነው የምናበላቸው ምንም ስለሌለን …..

ከብቶቻችሁን ሽጣችሁ ይህን ጊዜ እንዴት ነው የምትዘልቁት ?
መቼስ ተፈጥሮ ከታረቀን ከመጋቢት ጀምሮ  ከጣለልን ከብቱም ብላጊ(ዝናብ ጥሎ የሚበቅል) ያገኛል ፤ ቦታውም ትንሽ ይለመልማል እኛም ማሽላ እንዘራለን ፤ መንሥትም እተባበራችኋለሁ ከጎናችሁ ነኝ ይላል ፤ አንግዲህ ልናየው ነው፡፡

መንግሥት እስከ አሁን ያመጣው ነገር አለ ? የተሰጣችሁ ነገር አለ ?
        የለም ፤ ባይሆን በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈን ብር እየተረዳን ነበር፡፡

በምን ያህል ጊዜ ነው የሚረዷችሁ በወር በወር ነው.. ወይስ ?
        በወር አይደለም አልፎ አልፎ ይረዱና…

ምን ያህል ይረዷችኋል ?
በቤተሰብ 1000 ብር ፤ አራት የቤተሰብ አባል ያለው አስርም ያለው እኩል ነው የሚረዳው፡፡(በአካባቢው ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ምግብ ለስራ የሚባል አይነት ነው የሚገኝው ፤ ገበሬውን በቀን ሥራ ያሰሩትን በቤተሰብ 30 ብር ይታሰብለታል)

1000 ብር አሁን እህል ይገዛል ?
እስከ አሁን ይገዛ ነበር አሁን ግን ሊወደድ ነው ፤ ከዚህ በፊት በቆሎ ኩንታል 600 ብር እንገዛ ነበር አሁን ግን ዋጋው ይቃናል ፤ እንጃ….. 

እርሻው እንዴት ነው….
በዚህ ወዲያ ባለው መሬት ላይ ማሽላው በቅሎ ሲያበቃ በዚያው ቀረ ፤ አምስት ስድስት ክንድ አልፎ አልፎ ይዞ ነበር እሱንም ወፉ ጨርሶ በላው ፤ ታዲያ ይህ አላስቸገረንም ነበር ፤ እኛን አሁን የቸገረን ውሃው ነው፡፡ ውሃ ፈጽሞ የለም ችግር አለ ፤ መንግሥት ቦቲ አመጣለው ውሃ ማጠራቀሚያ  ሥሩ ብሎን ነበር ፤ ታንከር አመጣላችኋለሁ በቦቲ እየመጣ ውሃው ይከፋፈላል ብሎን ነበር ፤ ነገር ግን ከማውራት ውጪ ምንም የሰራው ሥራ የለም ፡፡ በወዲያ ግድም ደላንታ አካባቢ በአንድ ቀበሌ ከመሬት ውሃ ወጥቶ በጄነሬተር እየተከፋፈለ ነው ፤ እዛ እንኳን ጥሩ ነው…..

ከሁለተኛው  አርሶ አደር ጋር የተደረገ ውይይት..
ባለፉት ዓመታት ዝናብ እንዴት ነበር አካባቢያችሁ ላይ?
ባለፈው ዓመት እስከ ጥቅምት ዝናብ ነበር ፤ ብዙም ምርት አግኝተን ነበር ፤አሁን ግን ምንም የለውም …

አካባቢያችሁ የበልግ ዝናብ አለው  ?
አካባቢው ቆላ ስለሆነ በልግ አያውቅም ፤ መሕር ብቻ ነው ያለው ፤ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚያገኝው ፤ በዚያች ነው ከዓመት ዓመት የምንዘልቀው ፤ ከወዲያ ግድም ያሉት ሁለት ጊዜ የሚያገኙ አካባቢዎች አሉ ፤ ይህ ግን ቆላ ስለሆነ አንድ ጊዜ ነው የሚያገኝው፡፡ መሬቱ ዝናብ ካገኝ እስከ ሁሉት ዓመት የሚሆን ምርት ይሰጣል፡፡ ካገኝ ችግር የለውም ፤ ዝናብ ግን ያጥረዋል….

ከአሁን በኋላ መቼ ነው የሚዘንበው ?
መጋቢት ተከትሎ ሚያዚያን ከጣለ ፤ ዳጉሳ ማሽላ ስለሚያዝ እሱን እንዘራለን ፤ ከዚያ ወዲህ ቢጥል ሀገሩ በበልግ ማሽላ ያበቅል ነበር ፤ ቦታው ሁሉን ያበቅላል ችግር የለም ነበር ፤ አሁን ዝናቡ ነው ችግር የፈጠረብን..

ወደዚህ ስመጣ  ብዙ ቦታዎች እህ ደርል ፤ እህሉ አሯል ፤ ምንድነው የሚደረገው ይሰበሰባል  ?

        ለከብቶች ይሆናል ፤ ለከብት የማይሆንም አለ፡፡

ውሃ የሚታቆር በአካባቢያችሁ የለም  ? ምንጮችስ  ?
        የለም ፤ ምንጮች ደርቀው ነው በችግር ላይ ችግር የሆነው…

መንግሥት ርዳታ ይሰጣል ?
ድርቅ ከበላው እንረዳለን እያለ ነው ፤ አሁን እየመዘገበ ነው ፤ እንጃለት የሚረዳው ሕዝብም በርክቷል ፤ ሕዝቡ እርዳታ ያስፈልገዋል ፤ እስከሚቀጥለው ዓመት ዝናብ ዘንቦ ምርት እስኪሰበሰብ እርዳታ ስፈልገዋል ፤ ቦታው ቆላ ነው ሰኔ ላይ ትንሽ ቢጥል መስከረም ላይ የሚደርሱትን እንዘራ ነበር፡፡ ምስር ቦሎቄ አተር ይደርሳል፡፡ 

እስከዛ ከብቶቹ እንዴት ይዘልቃሉ ?
አካባቢው ላይ ያለው ውሃ እያጠረ እያጠረ ሲሄድ በሽሎ(ራቅ ብሎ የሚገኝ ወንዝ) መሄዳችን አይቀርም ፤ እሱም ስለሚርቅ ብዙ ችግር ነው ገና የሚያጋጥመን …

ወደዚህ ስንመጣ ከብቶች የሚጠጡበት የነበረው ወንዝ መንገዳችን ላይ ያለው ደርቋል
        መቼ ዘንቦ ውሃ ይኖረዋል እሱ…

ከዚህ አካባቢ የሚብስ ቆላ አለ ?
        በደላንታ ፤ በመቅደላ ፤ በሳይትን ግርጌ የሚብሱ ቆላዎች አሉ ፡፡

አጂባር ገበያ ነበርን ገበሬው በሬውን እየሸጠ ነው ፤ ታዲያ በሬ ተሽጦ ምን ይኮናል ?
        አዎን እየሸጥን ነው ፤ ጊዜውን ለመግፋት

በአንድ ቀበሌ ስንት አባወራ ይኖራል ? እርዳታስ እንዴት ነው የሚሰጠው?
እስከ ሁለት ሺ አባወራ ይኖራል ፤ ቀበሌው ደግሞ በቀጠና የተከፋፈለ ነው፡፡ እስከ አሁን የሚረዳው ጠና ጠና ያለበት ነበር ፤ ዘንድሮ ግን ሁሉም ችግረኛ ነው፡፡ ዝናብ ለሁሉም ስላልጣለ ሁሉም ይረዳ እየተባለ ነው፡፡

ይህ አካባቢ ምንም ያለ ዝናብ ተስፋ የለውም ?
ምንም የለውም ፤ በ77 ዝናብ መላውን ቀርቶ ሀገሩ ለቆ ነው የወጣው ፡፡ በጅማ ፤ በወለጋ በኢሊባቡር በአሶሳ በቴፒ ሕዝቡ ተበትኖ ቀርቷል ፤ ዝናብ መለስ ሲል ግማሹ ሲመለስ ሌላው በዛው ቀርቷል ፤ ከፊሉ ሲሰደድ ከፊሉ እዚህው በርሃብ አለቀ ፤ ይህን ጊዜ ከብቱም ሰውም የሚበላው አጥቶ እየወደቀ ነበር ፤ መንግሥትም ያኔ ሲረዳን ነበር ፤ ተመጽዋቹን አጅባር ሜዳ ላይ ሰብስቦ እህል በአየር እየጣለ ሲረዳ ነበር ፤ በ1977 ምንም አንዲት ዝናብ አልጣለም ነበር፡፡ 

መፍትሄው ምንድነው ፤ ዝናቡ በቀረ ቁጥር እንዲህ የሚሆን ከሆነ ?

መፍትሄው ተወን እስኪ…. እኛ አሁን ቁጭ ያልነው እግዚአብሔርን አምነን ነው ፤ ከቀረ ያው መሄድ ወይም ሞት ነው ፤ ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡ ፈረንጅ ብሏል አሉ ፤ በ1928 የመጣ ጊዜ ‹‹እንዲያው ሀበሻ ስራሽ ምንድነው አለ ?›› ዝናብ ከጣለ እንዘራለን መሬቱም ያበቅላል አሉት አባቶች ፤  ‹ ጉድሽን ልይ ብሎ ዝናብ ቢጠፋ ምን ትበያለሽ ያለው ነገር በ77 ደረሰ ›› አለ፡፡ ተው እስኪ ዝናብ ከቀረ መልቀቅ ነው ፤ መሄድ ነው ፤ መሞት ነው ይኽው ነው ….
3 comments: