‹‹አባ ቦሩና ወርጠጅ›› ነዋሪ አልባ መንደሮች
(አንድ አድርገን ህዳር 22
2008 ዓ.ም)፡- የመጀመሪያ ጉዟችንን ከደሴ ወደ መቅደላ ባደረግንበት ወቅት አባ ቦሩ እና ወር ጠጅ ከተማዎችን በመንገዳችን ላይ
አገኝናቸው ፤ በርካታ ቤቶች በግራ እና በቀኝ መስመር ላይ ተሰርተዋል ፤ ጸጥ ረጭ ያሉ አካባቢዎች ፤ ሽው ከሚል ከንፋስ ድምጽ
በቀር የሰዎች እና የቤት እንስሳት ድምጽ የማይሰማባቸው ቦታዎች ፤ በመንደሮች
ውስጥ ብዙዎቹ ቤቶች የእንጨት አጥር አላቸው ፤ እነዚህ
መንደሮች ውስጥ ሁሉም ቤቶች ተዘግተዋል ፤ የተዘጉት በበር ቁልፍ ሳይሆን መስኮትና በራቸው በውጭ በኩል በተመቱ ተላላፊ እንጨቶች
ነው ፤ ለጥቂት
እረፍት በቦታዎቹ ላይ በወረድንበት ሰዓት በአካባቢው አንድም የሰውም ሆነ የቤት እንስሳት የሌሉበት ቦታ መሆናቸውን ተገነዝበናል
፤ ሁለት መንገደኞችን አስቁመን ስለ መንደሮቹ ትንሽ እንዲያጫውቱን ጠየቅናቸው እነርሱም እንዲህ
አሉን
‹‹ይህ አካባቢ በፊት ሰዎች ይኖሩባቸው ነበሩ ፤ ነዋሪዎቹ ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ሴት ልጆቻቸውን በደሴ ፤ በአዲስ አበባ እና በአረብ ሀገራት ለስራ ያሰማሩ ይገኙባቸዋል ፤ ከዚህ ውጪ ግን እርሻውን እንደምታዩት ፍሬ አይታይበትም አካባቢውም ውሃ ለማግኝት አስቸጋሪ ሆኗል በዚህ ምክንያት ነዋሪው በሩን ዘግቶ ቦታውን ሊለቅ ችሏል ፤ ጥቂቶች ቆላውን መሬት ስላላቸው ወደዚያው አምርተዋል ፤ የተወሰኑ ሰዎች ቆላውን መሬት ስላላቸው ወደዚያው አምርተዋል ፤ ሌሎች ደግሞ ወዴት እንደሄዱ እንኳን አይታወቅም›› የሚል መልስ ሰጥተውናል፡፡
እነዚህ አካባቢዎች አሁን በተፈጠረው
ችግር አማካኝነት ወይንም ቀድሞ ባለ አሳማኝ ምክንያት መኖሪያ ቤቶቻቸው ተዘግተዋል፡፡
ኮሬና የውሃ ችግሯ
ይህ አካባቢ እንደ ሌሎች አካባቢዎች የዝናብ ውሃ ያገኝው ለጥቂት ቀናት
ብቻ እንደሆነ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ችለናል፡፡አካባቢው የጀግና
መፍለቂያ መሆኑ በነዋሪዎቹ ይነገርለታል፡፡ ነዋሪዎቹ ‹‹አሁን ግን መሳሪያ ያላነገተ ጠላት ከፊታችን ተደቅኗል›› ይላሉ፡፡ ይህም
የዝናብ እጥረት የፈጠረው ድርቅ ነው፡፡ አካባቢው በዓመቱ ዝናብ ሲዘንብ ከዓመት ዓመት የሚበቃ የጉድጓድ ውሃ እና ምንጭ በየሚገኝበት
ስፍራ ነው ፤ አሁን ግን ገና ከማለዳ ቀዬውን ክፉኛ የውሃ ችግር እያሰቃየው ይገኛል፡፡ ከአካባቢው በመጀመሪያ ደረጃ በአደጋ ላይ
የሚገኝ ቦታ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ የጎጥ ነዋሪውም ከሌሎች አካባቢዎች ከሚመጡ ሰዎች ይልቅ ለውሃ እርስ በእርስ መፋጠጥ ጀምረዋል፡፡
አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደነገረን ከሆነ ‹‹ወረዳው የጉድጓድ ውሃ ቆፍሩ ብሎን ነበር ፤ ነገር ግን እኛ በየትኛው አንጀታችን
ነው ከአስር እስከ ሃያ ሜትር የጉድጓድ ውሃ ቆፍረን የምናወጣው ፤ እህሉም ውሃውም ችግር ሆኖ በየትኛው ጉልበታችን እንቆፍር››
በማለት መልስ ሰጥቶናል፡፡
‹‹በራራ›› ነጭ ጤፍ አብቃይ የነበረ ቦታ
ይህ ቦታ ቀድሞ ነጭ ጤፍ አብቃነቱ ይታወቃል፡፡ አሁን ግን የቀን ጎዶሎ
አጋጥሞት መሬቱ እህል ማብቀል አልሆነለትም፡፡ ቦታው በድርቁ ምክንያት
የበፊት ስሙን ይዞ መቀጠል አልሆነለትም፡፡ እንደ ሌሎች አካባቢዎች ማሽላ አልፎ አልፎ ቢታይም ጤፍ ግን የተዘራበት እርሻ ያለ እስከማይመስል
ድረስ የዝናብ እጥረቱ ክፉኛ አካባቢውን ጎድቶታል፡፡ በዚህ ዓመት በራራ ስሙን ብቻ ተሸክሞ ዓመቱን ለመግፋት የተዘጋጀ ይመስላል፡፡
የተዘራው ማሽላ ለሰው ከመትረፍ ይልቅ ለከብቶች መኖ ለመሆን ያሰበ ይመስል ረዥሙን ጉዞውን በአጭር ቋጭቶታል፡፡
የዳውዶ አባጋሮ አካባቢ
በወረሂመኑ አካባቢ ጨህና ቦታ ይገኛል፡፡
ይህ የዳውዶ አባጋሮች ቦታ ነው፡፡ ሁለት ደመኞች የሚማማሉበት የበሊ ቦታ ነው፡፡ አባጋሮች(ታዋቂ የሚከበሩ አስታራቂ አባቶች) ከትውልድ
ትውልድና በዘር የሚሸጋጋሩ ናቸው፡፡ ዋናው ተግባራቸው ሰውን ማታረቅ ነው፡፡
ሰው በመግደል ፤ ቤት በማቃተል ፤ ንብረት በመዝረፍ ወንጀል የፈጸመ ሰው ከዳውዶ አባጋሮ በመግባት እርቅ ይጠይቃል፡፡
አባጋሮች ሁለቱን ደመኞች አስማምተውና
አማምለው በሊ(ከእምነት ጋር የተያያ እውነትን ለማውጣት የሚጠቀሙበት ዘዴ) አስገብተው አንካሴ አስነቅለው ፤ ጉማ አስከፍለው ያስታርቃሉ፡፡በሊውን
ጥሶ እርቁን ያረሰ ሰው ያልተጠበቀ አደጋ እንደሚደርስበት ስለሚታመን እርቁ አይፈልስም፡፡
ይህ አካባቢ እንደ ሌላው አካባቢ
የደረሰበት የድርቅ አደጋ ተመሳሳይነት አለው፡፡ አባጋሮዎች ሰውን
ከሰው አንጂ ሰውን ከተፈጥሮ ስለማያስታርቁ ድርቁ በውሃ ፤ በእርሻው እና በከብቶች ግጦሽ ማጣት ላይ ያጠላውን ንፉግ ደመና አባጋሮዎች
መግፈፍ አልተቻላቸውም፡፡ እርሻዎች ግማሽ ያህሉ አፍርተዋል ፤ ውሃ እጦቶ ፤ ምንጭ መድረቁ እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው የድርቅ
አደጋዎች በቀጣይ ወራት አንዣቦበት የሚቀጥልበት አካባቢ መሆኑን ተረድተናል፡፡
ወደ መቅደላ አምባው ያሉ አካባዎች
እስክንደርስ ድረስ በአካባቢው ያገኝነውን ሰው ሁሉ ስለ ድርቁ ሁኔታና መንግሥት አደርጋለው ስለሚለው ድጋፍ ስንጠይቅ ነበር ፤ ሹፌራችን
እንዲህ አለን
‹‹የዚህ አካባቢ ገበሬ እጅግ የተጎሳቆለ ኑሮ ከሚገፉት የሀገራችን አካባቢዎች አንዱ ነው ፤ ሕዝቡን መንግሥት እርዳታ አለ ካለው በርካታ ኪሎሜትሮች በእግሩ አቋርጦ ይመጣል ፤ ገበሬው አይደለም ለ10 ኪሎ ስንዴ ለአንድ ቁና እህልም ከእህሉ ዋጋ በላይ የትራንስፖርት ከፍሎ የሚመጣ ገበሬ ነው ያለው›› ብሎናል፡፡
No comments:
Post a Comment