Wednesday, April 22, 2015

አብረን ልናስባቸው የሚገቡ ሌሎች በስቃይ ውስጥ ያሉ ዜጎች

Diakon Abayneh Kasse
ትናንት በአሜሪካ ድምጽ አሁንም እዚያው ሊብያ ትሪፖሊ ውስጥ በተዘጋ ቤት ውስጥ በጭንቅ እነዚያን የሞት መልእክተኞች ፈርተው የተደበቁ መኖራቸውን ስሰማ የበለጠ ሰውነቴን ነዘረኝ፡፡ ድምጻቸው የተማኅጽኖ ነው፡፡ ተናጋሪው ወንድማችን ክርስቲያን መኾናቸውን ለጋዜጠኛው ነግረውታል፡፡ በዚህም ላይ ከአሁን አሁን ይመጡብናል የሚል ፍርሃት እና ሽብር ላይ መኾናቸው በድምጻቸው ይታወቃል፡፡ እኔም እዚያ ውስጥ ያለሁ መሰለኝ፡፡ ውስጤ ተረበሸ፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት ከኾነ ከወለደች ጥቂት ቀን የኾናት አንዲት እኅታችንን እና እርጉዞች የኾኑ እኅቶቻችንን ማንነታቸው የማይታወቁ ገጻቸውን የተሸፋፈኑ ሰዎች አፍሰው ወስደዋቸዋል፡፡ አብረውም ሌሎች ወንዶች ታፍሰዋል፡፡ ደግሞ ምን ሊያደርጉ ይኾን? ይኽንን ሳስብ ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ አንተው ድረስላቸው፡፡ የጭንቅ አማላጃችን ድንግል ማርያም ሆይ መንገዱን አብጅላቸው፡፡


በቤንጋዚ በትሪፖሊ እና በሌሎችም ከተሞች እንዲሁም እስር ቤቶች በርካቶች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፡፡ እንደ ምርጥ ዘር እየተለቀሙ የሚጋዙት ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ እንደገና ከአሥራ ዘጠኝ ምዕተ ዓመታት በኋላ ክርስትና ለሞት የሚያበቃ ወንጀል ኾነ፡፡ እናስ ሌላ የሞት ዜና እስክንሰማ እንጠብቅን?

አንዳንድ ባለሥልጣናት ለስደተኞቹ ምክር ሲለግሱ በየኤምባሲው ተመዝገቡ ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደሀገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ያሳውቁ ይላሉ፡፡ ምን እየኾንን ነው? መመዝገብ እኮ የሚቻለው መንቀሳቀስ ሲቻል ነው፡፡ ማሳወቅ እኮ የሚቻለው መስመሩ ሲዘረጋ ነው፡፡ በተዘጋ ቤት እና በየጉራንጉሩ የወደቁ ሰዎች እንዴት እንዲህ ይባላሉ? ደረቅ ዳቦ የሚያቀብላቸው አጥተው ከፍርሃት ጋር ረሃብና ጥሙን እየተጋፈጡ ላሉ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ጥሪ ነው? እየሞትሁ ያለሁት እኔ ነኝ፡፡ እነርሱ የደረሰባቸውን ስቃይ በሰማሁ ቁጥር እኔም በቁስል ላይ ቁስል በላዬ ላይ እየነደደብኝ ነው፡፡ እንቅልፍም አሳጥቶኛል፡፡እናም እየሞትሁ ያለሁት እኔም ነኝ፡፡
ሲሞቱ ለማልቀስ ከኾነ ቤተሰቦቻቸው እና አንጀት ያላቸው ይበቃሉ፡፡ መንግሥት አንድ ዕድር ከሚሠራው ሥራ ጋር ዝቅ ብሎ መታየት አለበት ብየ አላምንም፡፡ የመንግሥት ድርሻ ግን ከዚህ በጣም የላቀ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ማስተባበር የቀበሌ ነዋሪዎች ድርሻ ነው፡፡ መንግሥት ግን ዜጎቹን ለመከላከል ዓለማቀፋዊ መብቱን መጠቀም አለበት፡፡ ዜጎቹን የመከላከል ሙሉ መብት አለው፡፡ እንኳንስ መንግሥት በሌለባት ሀገር በሊብያ ቀርቶ በሌላም ሀገር ቢኾን ዜጋውን ለማዳን አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በትሪፖሊ ያሉት መጻተኛ ከተናገሩት መካከል የሚገርመው ግን እንደ እነርሱ የተሰደዱ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ወንድሞቻቸው የሚያደርጉላቸውን እንክብካቤ የገለጹበት መንገድ ነው፡፡ መረጃ የሚሰጡን በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ የሚሉን የምንልሰው የምንቀምሰውን የሚያቀብሉን አይዞን የሚሉን እነርሱ ናቸው ብለዋል፡፡ ዓለም ይፍረድ ልዩነቱ ከኾነ በእነርሱም መካከል አለ፡፡ እነዚህም ክርስቲያኖች እነዚያ ደግሞ ሙስሊሞች፡፡ ግን የእኛዎቹን ሙስሊሞች ከዳኢሾች የለያቸው ምን እንደኾነ ተመልከቱ፡፡

ዳኢሾች ደም ለማፍሰስ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ደግሞ ወገኖቻቸውን ለመታደግ! እናስ እነዚያ ሙስሊም ሊባሉ ይገባቸዋልን? ጭራቆች፣ ሰይጣን በላያቸው ላይ ቤት የሠራባቸው አውሬዎች፡፡ በሀገራችን የጫካ አውሬ እየተባለ የሚጠራው አንበሳ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጃገረድን ከጠላፊዎች አስጥሎ ሦስት ቀን ሙሉ በጫካው ውስጥ ጠብቆ ቤተሰቦች ሲመጡ መሰስ ብሎ ስፍራውን ለቅቆ መሄዱን እናውቃለን፡፡ ስለኾነም እነዚህን አውሬ የሚለው አይገልጣቸውም፡፡ የሰይጣን ፈረሶች፣ የጭራቅ መንግሥት ጭፍራዎች ነፍሰ በላ ጉግ ማንጉጎች ናቸው፡፡
ሰልፋችን ለሞቱት ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬም የሞት ወረፋቸውን ለሚጠብቁት ጭምር እንጂ፡፡ በሕይወት ያሉትን በመታደግ ከሐዘናችን እናገግም ዘንድ ሁላችንም የተቻለንን እናድርግ፡፡ አውሮፕላን ሳይልኩ ዜጎችን አወጣለሁ ማለት አይቻልም፡፡ በምትሃት ሊመጡ አይችሉም፡፡ የሚቻለው ሁሉ ይደረግ፡፡ የተባበሩት መንግሥታትም ትብብር እንዲያደርግ ይጠየቅ፡፡ ሌሎችም አቅሙ ያላቸው መንግሥታት ይጠየቁ፡፡ ብቻ እንረባረብ፡፡ መንግሥት ከትናንት ቢዘገይም ከነገ ግን መቅደም አለበት፡፡ የሚቻለውን ሁሉ እስኪያደርግ ድረስ እንተጋገዝ፡፡ ጉዳዩን አንሸዋርሮ ከመመልከት ይልቅ በቅንነት እንየው፡፡ ይህንን ምለው ለዚህ እና ለዚያ አይደለም፡፡ የሚታዩኝ እኅት ወንድሞቼ ናቸው፡፡ እናተርፋቸው ዘንድ ግዴታ አለብን፡፡

ሳይሞቱ ሞት እየሰተታቸው ያሉትን እናስብ፡፡ ሳይቀሉ በአንገታቸው ሰይፍ እንዳለ ቆጥረው ያቀረቀሩትን እናስብ፡፡ በሚሰሙት ዜና እና በሚያዩት ዘገባ ጭንቅላታቸው ልትፈነዳ የደረሱትን ወገኖቻችንን እናስብ፡፡ በእቅፎቻቸው ያሉትን ሕፃናት እናስብ፡፡ የሲቃ ድምጻቸውን እንስማ፡፡


2 comments:

  1. Awo Tikikil Belehal Wendimachin Abayne Kase, Egziabhere Yerdane

    ReplyDelete
  2. ይሕን አሳዛኝ፤የአንድረስላቸው ጥሪ እየሰማን እንዲት ዝም ይባላል።መቸስ በየቤቱ እንቅልፍ የለ ፤እስኬ ለዛሬ ይፈቀድልኝ፤ እኔው ሐጤአተኛ
    ለዜያዉም ሴት በቀን አንድ ግዜ ሰላም ለኪ እንፀልይ ብየ ልናገር። የጌታየ እናት ፤ የምድረ በዳን መንገድ ፤ የርሀብ ጥማቱን ፣ የስደቱን ነገር ታውቀው አለችና ድረሽላቸዉ ፣ ድረሽልን እንበላት እመኑኝ ውጤቱ እሩቅ አይሆንም።

    ReplyDelete