Thursday, February 19, 2015

በእንጦጦ ማርያም ሙዚየም የወርቅ መስቀሎች ጠፍተዋል መባሉ ተቃውሞ አስነሳ

አንድ አድርገን የካቲት 12 2007 ዓ.ም
ሪፖርተር ጋዜጣ የተወሰደ
 -‹‹የተባለው ሁሉ ሐሰትና ምንም የጠፋ ነገር የለም›› የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ
-‹‹ከመንግሥትና ከሀገረ ስብከቱ አጣሪ ኮሚቴ ተሰይሞ እየተመረመረ ነው›› የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት 

ለርዕሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ ከተለያዩ ምዕመናን በስለትና በስጦታ የተሰጡና እስከ አራት ኪሎ ግራም ሊመዝኑ ይችላሉ የተባሉ ሁለት የወርቅ መስቀሎችና አንድ የወርቅ ሐብል፣ በቅርስነት ከተቀመጡበት ሙዚየም ውስጥ መጥፋታቸውን የደብሩ ካህናትና የአካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡ 
የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት፣ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች የደብሩን አስተዳዳሪና ሌሎች ኃላፊዎች ተባብረው ወርቆቹን ማጥፋታቸውን፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሠራተኞች ላይ በደልና ብልሹ አሠራር እንዲደርስ ማድረጋቸውን በመግለጽ ተቃውሟቸውን ለመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ ለሀገረ ስብከቱ ቅርሳ ቅርስ ክፍል፣ ለአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ በፊርማ የተረጋገጠ ተቃውሟቸውን አስገብተዋል፡፡ 

የደብሩ ካህናት፣ የተለያዩ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በቤተ ክርስቲያኗ የቅርስ ማስቀመጫ ሙዚየም ውስጥ የአፄ ምኒልክ የወርቅ ጫማ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የተለያዩ አልባሳት፣ አልጋና ብዛት ያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ለቤተ ክርስቲያኗ የገቡ የወርቅ፣ የብር፣ የነሐስ፣ የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችና ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ በቱሪስቶች በመጎብኘትም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ናቸው፡፡ ቅርሶቹ በማንና በምን ሁኔታ እንደተወሰዱ ባይታወቅም፣ የተለያዩ ቅርሶች መጥፋታቸው ቆይቷል ብለዋል፡፡
 የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መልዓከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ገብረኢየሱስ መኮንን ጥቅምት 21 ቀን 2007 .. ለሙዚየሙ ቁልፍ ያዥ ለመምሬ አስፋው ገብረ ማርያም ደብዳቤ መጻፋቸውን ገልጸዋል፡፡
አስተዳዳሪው ለሙዚየሙ ቁልፍ ያዥ የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ በቅርሶች መመዝገቢያ (መረካከቢያ) ቁጥር 170 ላይ የሚገኙት ሁለት የወርቅ መስቀሎችና አንድ የአንገት ወርቅ ሐብል  ወጪ አድርገው ለሊቀ ህሩያን ቃለጽድቅ ኃይሌ እንዲሰጡ የሚያዝ ደብዳቤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከቅርስ ማስቀመጫ ሙዚየሙ ወጥተዋል የተባሉት ወርቆች የት እንደደረሱ ባለመታወቁ ካህናቱ፣ ሠራተኞቹና ምዕመናን ግራ ተጋብተው ባለበት ሁኔታ፣ አስተዳዳሪው ታኅሳስ 27 ቀን 2007 .. ሠራተኞችን ሰብስበው ለዓባይ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ለመግዛት በሙዚየሙ ውስጥ ያሉ ወርቆች መሸጥ እንዳለባቸው ሐሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ታሪክ አጥፍተን ታሪክ አንሠራም፤›› በማለት ሠራተኞች በሙሉ የአስተዳዳሪውን ሐሳብ በመቃወም፣ ደመወዛቸውን በማዋጣት ለህዳሴ ግድብ ቦንድ እንደሚገዙ የተናገሩ ቢሆንም፣ አስተዳዳሪው ግን ሠራተኞችን ማስፈራራታቸውን ሠራተኞቹ አስረድተዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 58 (1 2 እና 3) ማለትም በቤተ ክርስቲያን ስም የሚገኙት ንዋያተ ቅድሳትና ጥንታውያን ቅርሶች አመዘጋገብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቋንቋ የግዕዝ ፊደልና አኃዝ እንዲሁም የተለመደው የመለያ ቁጥር (ኮድ) እየተሰጣቸው በቋሚ ባሕር መዝገብ ተመዝግበው በጥንቃቄ ይቀመጣሉ፡፡ በየገዳማት፣ በአድባራትና በገጠር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት ጥንታዊያን የሆኑት ቅርሶች በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ ሲታመንበት፣ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሐሳብ ቀርቦ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ እንዲንቀሳቀሱ ከማድረግ በስተቀር ካሉበት ታሪካዊ ቦታ በምንም ዓይነት መንቀሳቀስ የለባቸውም ብለዋል፡፡
የአንዱ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ ወይም ንብረት ካለበት ቦታ ወደ ሌላ  ያዛወረ ወይም የሰወረ ወይም የሰረቀና ያሰረቀ ወይም የሸጠና የለወጠ ግለሰብ ወይም ድርጅት ቢኖር፣ በፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ከመሆኑ ጋር አድራጎቱን የፈጸመው ሰው ካህን ከሆነ ከሥልጣን ክህነቱ፣ ከማናቸውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ከጥቅሙ ሁሉ ታግዶ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ወይም በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊው ቅጣት እንደሚወሰንበት የተደነገገውን በመተላለፍ ድርጊቱን የፈጸሙት አስተዳዳሪው አባ ገብረ ኢየሱስ መኮንን፣ ጸሐፊው መጋቤ ሐዲስ ዲበኩሉ ገብረዋህድና ገንዘብ ያዥ እንዲጠየቁላቸው ከላይ ለተጠቀሱ መሥሪያ ቤቶች ተቃውሟቸውንና ቅሬታቸውን በፊርማቸው አረጋግጠው አስገብተዋል፡፡ 
የደብሩ ካህናት፣ ልዩ ልዩ ሠራተኞችና የአካባቢው ምዕመናን ያቀረቡትን ተቃውሞና ቅሬታ በሚመለከት የተጠየቁት የርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልዓከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኮንን፣ ‹‹የተባለው ሁሉ በተለይ ቦንድ የተባለው ጉዳይ ውሸትና ሐሰት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ከወሰነበት ውጪ የተደረገ ነገር እንደሌለም አክለዋል፡፡ ጸሐፊው መጋቤ ሐዲስ ዲበኩሉ ገብረዋህድ በበኩላቸው፣ ተሰጠ የሚባለው ወርቅ የአንገት ሐብልና የጣት ቀለበት ከምዕመናኑ በስለት የሚገባና ሀገረ ስብከቱ የወሰነበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩን ያውቀዋል የተባለውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት የደብሩ ካህናት፣ ልዩ ልዩ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ያቀረቡት አቤቱታ፣ ‹‹የቤተ ክርትስቲያኗ አስተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ተቆጣጣሪና ገንዘብ ያዥ ይባረሩ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ይዛወሩ የሚል ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ 
ወርቅ ጠፍቷል በሚል ያቀረቡት ተቃውሞ ዝም ተብሎ የሚታይ ሳይሆን መጀመርያ ማጣራት ተገቢ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ሀገረ ስብከቱ የካቲት 10 ቀን 2007 .. ጉባዔ አድርጎ አጣሪ ኮሚቴ መሰየሙን ተናግረዋል፡፡ ከቅርስ ጥበቃና ባላደራ ባለሥልጣን፣ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት፣ ከሀገረ ስብከቱ ካህናት አስተዳዳሪ መምርያ፣ ከቅርሳ ቅርስና ከክፍለ ከተማው ሀገረ ስብከት አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተሰይሞ የካቲት 11 ቀን 2007 .. በደብሩ በመገኘትና ኃላፊዎቹ ባሉበት እንደሚያጣሩም አስታውቀዋል፡፡ ምዕመናን ሰብስቦና ቢሮ በማሸግ ኃላፊዎች እንዲነሱ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑንና በዚህ ይቀጥል ቢባል የት ሊቆም እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ ስለሚሆን በአግባቡ በመመርመር ጠፍቷል የተባለው ወርቅም ይሁን ሌላ ነገር በማረጋገጥ ተጠያቂውን መለየት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ጉዳዩን ቀደም ብሎ የሰማ ቢሆንም፣ በራሱ ለማጣራት እንዳልፈለገ የገለጹት ቀሲስ በላይ፣ ምክንያቱ ደግሞ ማጣራት አድርጎ ‹‹ወርቁ አልተሸጠም›› ቢል ‹‹ለአስተዳዳሪዎቹ አዳልቷል›› የሚል ችግር እንዳይፈጠር መሆኑንም አስተድተዋል፡፡ ጉባዔው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀለምንጦስ የሚመራና 15 በላይ አባላት ያሉት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


1 comment:

  1. ቆይ ምን የሚሉት ቅዠት ነው ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅምና በሚያስተች አኳኋን ለሦስተኛ ወገን የሚተላለፉ የአድባራት የንግድ ማዕከላት ኪራይ ላይ ጥናት የሚያደርገውን ኮሚቴ አላሰራ ያሉትን ሊቀ ጳጳስ አሁን ደግሞ________?

    ReplyDelete