Tuesday, February 17, 2015

እንባችንን ከዓይኖቻችን ላይ ያብሰዋልና ክብር ለእርሱ ይሁን፡፡ ኢሳ25፡8

‹‹እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ›› ዮሐ 844 በትላንትናው ዕለት አሕዛባዊው ጽንፈኛ አይ ኤስ፤አይ ኤስ (isis) 21 የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ እጅግ በጣም አሳዝኖናል ፡፡ መንበረ ማርቆስ ግብጽ ልጆችዋ በሚዲትራንያን ባሕር ላይ አንገታቸው እየተቀላ በደም ጎርፍ ሲጥለቀለቅ ማየት ምንኛ አሳዛኝ ይሆን !!! የአትናትዮስ ልጆች የእነ ጳውሊ መቃርስና እንጦንስ ፍሬዎች ሰማዕትነትን በጸጋ ሲቀበሉ በዓይን በብረታችን አየን ፡፡ ይህ ዓይነቱ ጸረ ክርስትና እንቅስቃሴ የመጀመርያይቱን / አስታወሰኝ ፡፡ ሮማዊው ኔሮን ክርስትናን ያጠፋ መስሎት ሰይፉን አስልቶ ክርስያኖችን አያደነ ቢሰይፋቸውም ለሞት ከመሽቀዳደም በቀር ሥጋውን ለማትረፍ ያሻ አልነበረም ፡፡ ቤተ ክርስትያንን ቶኮምቡ (ከምድር በታች ባሉ ጉድጓዶች) ለመግባት በተገደደችበት በዚያ ዘመን ክርስትና ግን ይበልጥ እያበበ መላውን ሮማ እስኪያሰጋ ድረስ ሰደድ ሆኖ ነበር ፡፡ ዛሬም ተረፈ ኔሮኖች ክርስትናን ያጠፉ መስሎአቸው በጭምብል ይጋልባሉ ፡፡ ክርስትና ግን አይደለም ዛሬ ጥንትም መገለጫዋ መከራ ነውና እስከ ምጽዓተ ክርስቶስ አትጠፋም ፡፡ ክርስትናን ሰይፍ የሚያሸንፈው ቢሆን ኖሮ እነ ትራጃን ድምጥያኖስና ዲዮቅልጥያኖስ በተሳካላቸው ነበር ፡፡ ወትሮውንም ክርስትና የጸናችው በሠማዕታት ደም ነው !!! 

ሁላችን አልቅሰናል፤ እጅጉን ተሰብረንበታል፤ አሁንም ውስጣችን እየተሰቃየ ሰላማችንን ነስቶናል፡፡ እንደውም ይህ ሁሉ ስለምን ሆነብን እያልን አንገታችን አቀርቅረን እያነባን ነው ግን እርሱ እንባችንን ከዓይኖቻችን ላይ ያብሰዋልና ክብር ለእርሱ ይሁን፡፡ ኢሳ258

ISIS አማካኝነት ተቀነባበረ በተባለው የተገደሉት የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ስለ ስሙ እውነተኛ ሰማእትነትን በመቀበላቸው የሕይወት መምህርነታቸውን በግልጽ አሳይተውናል ይሁንና እንደው ቢጠየቁ የሚመልሱት እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብለው ነበር ‹‹...እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም.. ›› ሐዋ 2113

እውነተኛ የእምነት ጽናት፤ እውነተኛ ድል፤ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ኑሮ፤ የሰማይን በር የሚከፍት ፍቅር፤ እኛን የሚያነቃ ደውል፤ የዘመኑን ፍጻሜ መድረስ የሚነግር ምልክት፤ ስለክብሩ ክብራችንን ልንተውለት እንደሚገባ የተማርንበት ሕይወት ነው፡፡
ነፍሳቸውን ይማረው አልልም ምክንያቱም አልሞቱምና፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ እውነት አስተምሮናል፡፡ ‹‹ኢየሱስም ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤›› ስለዚህ ላልሞቱት ነፍስ ይማር አልልም፡፡
ነገር ግን ወዳጆቼ የእኛን ነፍስ ይማረው እላለሁ፡፡ እኛ እኮ ለመንፈሳዊ ሕይወት ሞተን ለዓለማዊ ሕይወታችን የምንኖር፤ ለጽድቅ ሞተን ለኩነኔ የምንኖር፤ ለተጋድሎ ሞተን ለምቾት የምንኖር ክርስትናው ያልገባን ከንቱዎች ነን፤ለእኛ ለሞትነው ነፍሳችንን ይማረው፡፡ የነገረ መለኮት ሊቅ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ምሥጢረ ሥጋዌን በግልጽ ባስተማረበት እና ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም ላይ እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹ ሰማእታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፡፡ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ፡፡ እንደ ይቅርታህ ብዛት ይቅር በለን፡፡›› ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ

ወዳጆቼ ክርስትና በናጠጠ ቤት መኖር አይደለም፤ በዘመናዊ መኪናም መሄድ አይደለም፤ በብዙ ሰዎችም ታጅቦ መጓዝ አይደለም ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ለሞት መሽቀዳደም ነው፤  የሰማእታት ኑሮን ስንጀምር ዓለምን እንንቃለን፤ በሚከፈለን ጊዜያዊ ገንዘብ ሳይሆን በተከፈለልን የደም ዋጋ ጸንተን በፍቅር ለዓለም እናበራለን፡፡ ባለ ዕዳ መሆናችንን፤ ለዚህም ዓለም መጻተኛ እንደሆንን አምነን ዘወትር ለሰማእትነት የተዘጋጀን ሆነን እንጠብቃለን፡፡

ወዳጆቼ ስለ ዓለም ፍቅር የሞተነውን እኛን እንጂ የተማሩትን ነፍሳት ነፍሳቸውን ይማራቸው አልልም፡፡ 
ይቆየን


እግዚአብሔር በሐይማኖት በምግባር ያጽናን የድንግል ማርያም ምልጃዋ አይለየን


By:- Samuel Ayalneh

2 comments:

  1. wed shlmate endmehed sew eko neber akahadachew amlak betasdkan besmatete guan akumelen

    ReplyDelete
  2. መታደል ነው ሰማእት ሆኖ ማለፍ በረከታቸው ይደርብን

    ReplyDelete