Sunday, July 28, 2013

‹‹ከነበሩት ጳጳሳት የባሰ እንጂ የተለየ ሥራ አልሰራንም ሥራችን ይመሰክራል፡፡›› አቡነ ጢሞቴዎስ

   
 (አንድ አድርገን  ሐምሌ 21 2005 ዓ.ም )፡- ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ህዳር 8 1992 ዓ.ም አቡነ ጢሞቴዎስ ከ”ምኒልክ መጽሄት” ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ዘወር ብለን ለናንተው ለማቅረብ ወደድን ፤

ጥያቄ፡- ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመርቀው የሚወጡ አንዳንድ ወጣቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በመክዳት ወደ ሌላ ኃይማኖቶች ሲለወጡ ይስተዋላል፡፡ ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ ኃይማኖታቸውን ለመለወጥ የሚገደዱበት ምክንያት ምንድነው? በትምህርት አሰጣጡ ላይ እምነታቸውን የሚያስለውጡ ትምህርቶች ይሰጣሉ ወይ?
አቡነ ጢሞቲዎስ፡-  አሉባልታ ይመስለኛል አስተማሪዎቹ በጣም የታወቁ የኦርቶዶክስ ሊቃውንት ናቸው፡፡ ትምህርቱም የተጣራ ነው፡፡ ነገሩ ያለው ከስድስተኛው ጥያቄ ጋር ነው ፡፡ ይኽውም ተወራ እንጂ የካደ ልጅ ካለ ባውቀው ደስ ባለኝ ነበር፡፡

ጥያቄ፡- በስልጣን ላይ በተቀመጠ መንግስት በአደባባይ የሚሰራቸውን ስህተቶች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ከፓትርያርኳና ከጳጳሶቿ የነቀፈችበትና የእርምት እርምጃ የወሰደችበት ጊዜ የለም ይባላል፡፡ በዚህ መሰረትነ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክነት የሚገኙትና ሌሎቻችሁም ጳጳሶች ቀደም ብለው ከነበሩት ጳጳሶች የተለየ ነገር አልሰራችሁም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎን አስተያየት ቢያካፍሉን?
አቡነ ጢሞቲዎስ፡ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚሰራቸውን ስህተቶች ምን ዓይነት መሆናቸው ባይገለጹም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክና በጳጳሶቿ የነቀፈችበትና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀችበት ጊዜ የለም የሚባለው ትክክል ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በስተቀር ማንም ፓትርያርክና ጳጳስ መንግስትን አጥፍተሀል ተመለስ ያለ አልነበረም፡፡ አሁንም የለም፡፡ ምክንያቱም የቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በሩ ሲታጠር ማንም የተነፈሰ አልነበረም፡፡ አሁንም የቤተክርስቲያኒቱ  መብት በተለየ ቦታ ጊዜ ሲደፈር ማንም የቤተክርስቲያን መሪ የተነፈሰ የለም፡፡ ይልቁንም መንግስት ለራሱ ጸጥታ ሲል በእያንዳንዱ ቦታ ጣልቃ ሲገባ ይታያል፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ዝምታ ለመንግስት የሚመች አይመስልም፡፡ እንዲያውም የቤተክርስቲያኒቱን መብት ከተጠበቀ ጸጥታ ይሰፍና መንግስትም በሰላም ይገዛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን መሪዎች መንግስት እዳይነቀፍ ብለው ቤተክርስትያኒቱና ክርስትያኖች መብታቸው ሲነካ ዝም ብለው ካዩ የእግዚአብሔርን አደራ አልጠበቁም ፤ መንግስትንም ባለመምከራቸው ጎዱት እንጂ አልጠቀሙትም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከነበሩት ጳጳሳት የባሰ እንጂ የተለየ ሥራ አልሰራንም ሥራችን ይመሰክራል፡፡

ጥያቄ ፡- የቤተክህነት ቀዳሚ ተግባር መንፈሳዊ ስራ እንዲጎለብት ማድረግ ነው፡፡ ይሁንና በውስጡ በከፋ ሽኩቻዎች እየታመሰች ትገኛለች ፤ እንዲህ አይነት ውጥረት ውስጥ ያለ መንፈሳዊ ድርጅት አንዴት አድርጎ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይችላል? በዚህ ላይ አስተያየት ቢሰጡን?
አቡነ ጢሞቲዎስ፡- እርግጥ የቤተክህነት ቀዳሚ ተግባር መንፈሳዊ ስራ እንዲጎለብት ከዚያም በላይ የበጎ ምግባር አብነት መሆን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር የመጣው መዓት እግዚአብሔር መዓቱን እስኪመልሰው ድረስ ከመጸለይ በስተቀር ምንም ለማድረግ አይቻልም፡፡

‹‹በአሁኑ ሰዓት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ አስተዳዳሪነታቸውን ባሳለፍነው ሳምንት ብጹዕ አቡነ ጤሞቴዎስ መነሳታቸው ይታወቃል ፤ እስኪ ሰው በማንሳት እና ሌላ በማስቀመጠ የሚመጣ ለውጥ የሚመለስ መልስ እንዳለ እናያለን… ካቶሊካውያን በአዲስ አበባ በአንዱ ጫፍ ከሶስት መቶ ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር በላይ የሚያወጣና ደረጃውን የጠበቀ በቫቲካውያን የሚደገፍ  ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ እያሰሩ በሚገኙበት ሰዓት እኛ በአንዲቱ ደሳሳ ኮሌጅ ከአብነት ትምህርት ቤት መሻሏን ትምህርት ሚኒስቴር አልመሰክር ያላት  ተዝረክርከን ያዝረከረክናት ኮሌጅ ላይ እዚህ መድረሳችን ይገልማል፡፡››


·         አስፈላጊ ከሆነ ሙሉ ቃለ መጠይቁን ለማቅረብ እንሞክራለን

3 comments:

  1. The Angry Ethiopian/ቆሽቱ የበገነውJuly 28, 2013 at 5:42 PM

    please put the whole interview up. Thank you.

    ReplyDelete
  2. Please, let us read the whole interview. Thanks

    ReplyDelete