Friday, July 1, 2016

ከጵጵስና ሽሽት


ረዣዥሞቹ ወንድማማቾች ተብለው የሚጠሩት አውሳብዮስ አሞንዮስ ዲዮስቆሮስና አውሳሚዮስ በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ላይ በብዙ መልኩ ይጠቀሳሉ። "አውሳብዮስ አሞንዮስ ተናግረውታል" የሚል ማስረጃ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜ መጻሕፍት ላይ ማግኘት የተለመደ ነው። እነዚህ ቁመታምና መልከ መልካም የነበሩት ወንድማማቾች ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሠጡ የዘመኑን ፍልስፍና ተምረው በሃይማኖት እውቀት የመጠቁ ነበሩ። የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ቀደምት ሊቃውንትን መጻሕፍትም እጅግ ያነበቡ ከሊቃውንት ተርታ የሚመደቡ የታሪክና የትርጓሜ መምህራን ነበሩ።


ከእነዚህ ወንድማማቾች መካከል አንዱ አባ አሞንዮስ ነው። ይህ አባት ከእውቀት ጋር ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት የነበረው ነበር። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በዚያን ዘመን ዓለም ማእከል ወደነበረችውን ሮም በሔደበት ወቅት ከቅዱስ ጴጥሮስና ከቅዱስ ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናት ውጪ አንድም ነገር ሳይጎበኝ መመለሱ ነው።
አባ አሞንዮስ በበአቱ ተወስኖ በሚኖርባት ሄርሞፖሊስ የምትባል ከተማ የነበሩ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወቱንና ጥልቅ እውቀቱን ተመልክተው ጳጳስ ሆኖ እንዲሾምላቸው ተመኙ። ስለዚህም ወደ እስክንድርያው ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ ሔደው አመለከቱ። ፓትርያርኩ የአባ አሞንን መንፈሳዊነትና እውቀት በመረዳት ጳጳስ አድርጎ ሊሾምላቸው ፈቀደ። ምእመናኑ ተደስተው ወደ አባ አሞንዮስ እየገሰገሱ ደረሱ። ወደ በአቱ ሲገቡ ግን ያጋጠማቸው ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነበር።

አባ አሞንዮስ ሕዝቡ ወደ ፓትርያርኩ ሔደው ጳጳስ አድርገው ሊያሾሙት እንደሆነ ሰምቶ ጳጳስ ሆኖ ላለመሾም የቀኝ ጆሮውን ቆርጦት ነበር። ይህንን ያደረገው በሥርዓቱ መሠረት ጳጳስ የሚሆነው ለአገልግሎት የሚከለክል የአካል ጉድለት የሌለበት ሰው እንደሆነ ስለሚያውቅና ምእመናኑም "ጳጳሳቸው ጆሮው ቆራጣ ነውእንዳይባሉ ፈርተው ይተዉኛል" ብሎ አስቦ ነበር።

ይህን ያዩት ምእመናን በሁኔታው ቢደነግጡም ይህን የመሰለ አባት ማጣት ስላልፈለጉ ወደ ፓትርያርኩ ተመለሱ። ነገሩን የሰሙት ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ ግን "ይህን ሥርዓት አይሁድ ይጠብቁት እኔ ግን አፍንጫውም ቢቆረጥ እሾመዋለሁ" አሉ። ምእመናኑ ደስ ብሏቸው ወደ አባ አሞንዮስ ተመለሱ። አባ አሞንዮስ በአቱን ጥሎ ሮጠ። ምእመናኑ ተከታትለው ያዙት። እየተንፈራገጠ እያለቀሰ ወደ ፓትርያርኩ ሊወስዱት ሞከሩ። አባ አሞንዮስ ግን "እባካችሁ ተዉኝ ግድ ብላችሁ ብትወስዱኝና ብታሾሙኝ ምላሴን እቆርጣለሁ" አላቸው። ይህንን ከማድረግ እንደማይመለስ ስለተረዱ ምእመናኑ እያዘኑ ተዉት።

መጽሐፈ መነኮሳት ሹመትና ክብር እንደ ጥላ ነው ይላል። የሚከተሉትን ይሸሻል የሚሸሹትን ይከተላል። በቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት እንጂ ሥልጣን ባይኖርም ቤተ ክርስቲያን ግን ከትናንት እስከ ዛሬ መሾምን እንደ ጦር የሚፈሩና በግድ እያለቀሱ የሚሾሙ አባቶች ነበሯት ዛሬም አሏት። እያለቀሱ የተሾሙትም የቤተ ክርስቲያንን ዕንባ ይጠርጋሉ።

ይህን ታሪክ የጻፍሁት "ዛሬ ምን አባት አለና ..." የሚለውን የተለመደ የስድብ ዶፍ ለመቆስቆስ አይደለም። ይህን ማድረግ ለአሕዛብ መሳለቂያ ከመሆን በቀር ምንም አይጠቅምም። "ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪን የሚሠጥ" እያልን በማለዳ ደጅ የምንጠናው አምላካችን ወደ መንፈሳዊ ማዕረግ ሊመጡ የታሰቡትን የቀደሙትን አበው መንፈስ እንዲያድልልን የምንጸልይበት ብርቱ ጊዜ ግን አሁን ነው።

አንድ ገጣሚ እንዳለው "ቤተ ክርስቲያን እንደ ኦሪቱ ዘመን ምነው በድንኳን በሆነችና ምነው ጠቅልለን ይዘናት በሸሸን" የሚያሰኝ ጊዜ ላይ ነን። ለምናየው ክፉ ነገር የኛን ኃጢአት ምክንያት ብናደርግና ብናነባ የሚሻልበት ጊዜ ነው። ለአንዱ ደግ መሪ ለሙሴ ሕዝቡን አጥፍቼ ሌላ ሕዝብ ልቀይርልህ ያለ ፈጣሪ ሕዝቡ ቅን ሆኖ ቢገኝ ደግሞ መሪ መቀየር የሚሣነው አይምሰለን። መሰዳደቡን ትተን ሃይማኖታቸው የቀና ደገኛ አባቶችን እንዲሾምልን እንጸልይ። 

(
"ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን)

"በውስጥሸ ሰላም ይሁን አልሁ ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ። " (መዝ 122:9)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ 
henoktsehafi@gmail.com
ሰኔ 24 2008
ከለን ጀርመን



1 comment:

  1. ቃለ ህይወትን ያሰማህ። አቤቱ ይቅር ይበልን።

    ReplyDelete