Sunday, September 7, 2014

ቸል የተባለው ውቅር


ወደ አማራ ክልል ሲጓዙ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በርካታ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ በክልሉ በሚገኘው የዋግኽምራ ዞን ውስጥ ካሉ ጥንታዊ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ዘናቆ አቦ ገዳም፣ ዋሻ መድኃኔዓለም፣ ብርብር ጊዮርጊስ፣ ደብረ ፀሐይ ወይብላ ማርያም፣ ደብረ ሎዛ ውቅር ማርያምና አባ ዮሐንስ ይጠቀሳሉ፡፡ በዋግኽምራ ዞን በሚገኘው የሰቆጣ ከተማ ደግሞ ባር ኪዳነ ምሕረት ገዳምና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 
ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን 495 እስከ 525 .. አስተዳድሮ በነበረው አፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ ይነገራል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት 500 ዓመት ቀድሞ እንደተሠራና የላሊበላ ፍልፍል ሕንፃዎች መነሻ ሊሆን እንደሚችል በቤተ ክርስቲያኑ ያሉ ሊቃውንት ያምናሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ በሰቆጣ ከተማ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ያሉ ሰንሰለታማ ኮረብታዎች ያዋስነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሰባት ክፍሎች (ቅኔ ማህሌት፣ ቅድስትና መቅደሱን ጨምሮ) እና ጥንታዊ ሥዕሎች ያሉዋቸው አምስት ዐምዶች አሉ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያስገቡ አራት በሮችና ዙሪያውን አሥራ አራት መስኮቶች ይገኛሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑን ልዩ ከሚያደርጉት በዋነኛነት የሚጠቀሰው በውስጡ ያለው ዋሻ ነው፡፡ በጎበኘንበት ወቅት ዋሻው በእንጨት ርብራብ ተከድኖ ነበር፡፡ ዋሻው በሁለት አቅጣጫ (ሰሜንና ደቡብ) የተቦረቦረ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኑን ያስጎበኙን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም መርሐጥበብ በየነ እንደሚሉት፣ አንደኛው በር ወደ ላሊበላ ሌላኛው ደግሞ ወደ አክሱም ይወስዳሉ፡፡

እስከሚታወቀው ድረስ ዋሻው ውስጥ ከጥቂት ኪሎ ሜትሮች አልፎ የሄደ ሰው የለም፡፡ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ተጨባጭ ጥናት ባይካሄድም ውስጥ ለውስጥ ዋሻውን ተከትለው ከተጓዙ ወደ አክሱምና ላሊበላ እንደሚያስወጣ የቤተ ክርስቲያኑ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ እንደ ሊቃውንቱ፣ ዋሻው ከሰው ልጅ ዕይታ የተሰወሩ ቅዱሳን የሚመላለሱበት ሊሆን ይችላል፡፡ መልአከ ሰላም መርሐጥበብ እንደገለጹት፣ በዋሻው በሁለቱም አቅጣጫ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ በጭቃ የተሠራ ግድግዳ ይገኛል፡፡ እሳቸውም ይሁን ሌሎች አባቶች ከዚያ ማለፍ አለመቻላቸውና ለአጥኚዎች ክፍት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ዋሻው በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ንጉሡና ሹማምንት የከበሩ ዕቃዎችን ለማስቀመጥ ይገለገሉበት እንደነበርም ይገመታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በተለያየ ወቅት ዋግኽምራን ያስተዳደሩ መሪዎች አፅም ይገኛል፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ ለሦስት ዓመት የነገሡት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ዋግ ሥዩም ጎበዜ) አፅም በአንድ ክፍል፣ እንዲሁም ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ የነበሩ ዋግ ሹሞች አፅም በሌላ ክፍል ተሰባስቦ ይታያል፡፡
ዋግ ሥዩም ጎበዜ ለቤተ ክርስቲያኑ መገልገያ የሚሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በማድረግና ሰንበቴን የመሰሉ መሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች በማዘጋጀት ኅብረተሰቡን እንዳስተባበሩ ይነገራል፡፡ ሌላው ሹም ዋግ ሥዩም ክንፈ ሚካኤል፣ በርካታ የብራና መጻሕፍትና መስቀል ለቤተ ክርስቲያኑ አበርክተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ የዋግ ሥዩም አርአያ ክርስቶስ፣ የደጃች ፋሪስና የዋግ ሥዩም ወሰን አፅም በቆዳ ተከፍኖ ይገኛል፡፡ በተለያየ ወቅት ሹሞቹ ቤተ ክርስቲያኑ መገልገያዎች እንዳሟሉም ተገልጾልናል፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ ጣሪያ ላይ የተለያየ አሠራር ዘዬ ያላቸው መስቀሎች ይታያሉ፡፡ በጽሑፍ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በጣሪያው ላይ ካሉት መስቀሎች ሁለቱ የላቲንና አንዱ የግሪክ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ ጣሪያ ላይ በሁለት አቅጣጫ ያሉ መስቀሎች፣ እንዲሁም በቅድስቱ ጣሪያ በእብራይስጥ ፊደል የተጻፈ ጽሑፍ ይታያል፡፡
ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ አፄ ካሌብ ይጸልዩበት የነበረ ጠባብ ክፍል አለ፡፡ ከውቅር መስቀለ ክርስቶስ በታች የማርያም ታቦት ያለበት ጅምር ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ መልአከ ሰላም መርሐጥበብ እንደገለጹልን፣ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ በግንባታ ላይ በነበረበት ወቅት የመን ውስጥ ነግሦ የነበረው ፊንሀስ ናርጋን ያሉ ክርስቲያኖችን ሲፈጅ በወቅቱ የግሪክ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጢሞቲዎስ አፄ ካሌብ የመን ሄዶ ለክርስቲያኖች እንዲዋጋ ያሳስባሉ፡፡ የማርያም ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ከመጠናቀቁ በፊት አፄ ካሌብ ንጉሥ ፊንሀሰን ለመዋጋት ወደ የመን ሄዷል፡፡ 
ቤተ ክርስቲያኑ በቅርስነት ካስቀመጣቸው ውስጥ በወርቅ ቀለም የተዳጎሰው  ወንጌል ተጠቃሽ ነው፡፡ ወንጌል ሲነበብ መጽሐፉ ትልቅ በመሆኑ ሁለት ሰዎች ተባብረው የሚይዙት ሲሆን፣ በውስጡ የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የመድኃኔዓለም፣ የእግዚአብሔርና የማርያም ስም በወርቅ ቀለም ተጽፈዋል፡፡ 
ወንጌሉን ለቤተ ክርስቲያኑ ያበረከቱት እመቤት ላቀች (በወቅቱ የጎጃም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ባለቤትና የዋግ ሥዩም ገብረመድህን ልጅ) ሲሆኑ፣ የእሳቸውና የአባታቸውም አፅም በቤተ ክርስቲያኑ  ይገኛል፡፡ ዋግ ሥዩም ገብረ መድህን ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ብዙም ይስማሙ ስላልነበረ በግጭታቸው ገረገራ ላይ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በአፄ ካሌብ ለቤተክርሲቲያኑ የተበረከተው በብራና የተጻፈ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስ ለረዥም ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ መጽሐፉ አሁን በቅርስነት ተቀምጦ መስቀልን ለመሰሉ በዓላትና ለጎብኚ  ይወጣል፡፡ አብዛኛው በብራና የተጻፉ መጻሕፍት ለዓመታት ያገለገሉ በመሆናቸው እንዳይጐዱ ሲባል እንደማይሠራባቸው ይገልጻሉ፡፡ መጻሕፍቱ በጥንታዊ ሥዕሎች፣ ከብርና ከብረት በተሠሩ ጌጣ ጌጦች የተለበጡ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ በወርቅ የተሠሩ መስቀሎችና ሌሎች ወደ 13 የሚጠጉ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡
ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ የዋግኽምራ ሹማምንትና ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች አፅም ይገኛል፡፡ ከአፅሞቹ አንዳንዶቹ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወሩ በጥንቃቄ ጉድለት የፈራረሱ ናቸው፡፡ አሁን ያሉበትም ሁኔታ ለጉብኝት የማይመች ከመሆኑ በላይ በተገቢ መንገድ አልተያዙም፡፡ 
ስለ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ በጽሑፍ ያገኘነው እንደሚያሳየው፣ ቤተ ክርስቲያኑ የተገነባው እንደሰንሰለት የተያያዘ ኮረብታ ሥር ነው፡፡ በአካባቢው ‹‹የላሊበላ መንገድ›› በመባል የሚታወቀው የቋጥኝ ካብ በቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ትክክል በኮረበታው አናት ላይ ይታያል፡፡ ጽሑፉ የድንጋይ ቋጥኙ ንጉሥ ላሊበላ ከአክሱም ጀምሮ ወደ ላሊበላ በእግሩ የተጓዘበት እንደሆነና መነሻው አክሱም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዋግኽምራ ሲነሱ ዳግብድ ከሚባለው የትግራይ ወረዳ ጀምሮ የሰቆጣ ከተማን በአምስት ኪሎ ሜትር እያዋሰነ በውቅር መስቀለ ክርስቶስ ያልፍና የጋዝጊብላን ወረዳ ለሁለት ከፍሎ ላስታ ያደርሳል፡፡ መስመሩን ሳያቋርጡ የላሊበላው ቤተ ጊዮርጊስ ውቅር አብያተ ክርስቲያን እንደሚደርስም ይነገራል፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ በተገኘንበት ወቅት እንደታዘብነውና የቤተ ክርስቲያኑ ሊቃውንት እንደሚሉት፣ ቤተ ክርስቲያኑ ብዙም አይጎበኝም፡፡ የቱሪስት መዳረሻ መሆን የሚገባው ዕድሜ ጠገብ ቤተ ክርስቲያን ለምን አይጎበኝም? የሚል ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ እንደሚሉት፣ ስለ ቤተክርስቲያኑ ምንም ዓይነት የማስተዋወቅ ሥራ አልተሠራም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያኑ ለሰቆጣ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ቢሮና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የቱሪስት መሪ መጻሕፍት ላይ እንዲካተት በተደጋጋሚ ከማሳሰብ በመቀጠል ቤተ ክርስቲያኑ የሚያስፈልገው ጥገና እንዲያገኝ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ 
የቤተ ክርስቲያኑ ውጫዊ ክፍል እየተሰነጣጠቀ ውበቱ እየጠፋ ነው፤ ውስጡ ያሉ ሥዕሎችም እየደበዘዙ ከመሆኑም በላይ ፈጽሞ የተዘነጋ ቦታ መሆኑን ለሚኒስቴሩ ካሳወቁ በኋላ 200,000 ብር እርዳታ አግኝተው እድሳት ጀምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኑ ከእንጨት በተሠራ ድጋፍ የቆመ ሲሆን፣ ድጋፉ ወደ ብረት እንዲለወጥና ሙሉ እድሳት እንዲደረግለት ግፊት እያደረጉ መሆኑን አስተዳዳሪው ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ቤተ ክርስቲያኑን የደገፈው እንጨት በምስጥ የሚበላ በመሆኑ በብረት ካልተቀየረ በስተቀር ቋሚነቱ ያጠራጥራል፡፡
መልአከ ሰላም መርሐጥበብ እንደገለጹልን፣ ቤተ ክርስቲያኑ ያለውን ታሪክና ትውፊት በማሳወቅ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩባቸው የተዘጋጁ ቦታዎች ለዓመታት አልነበሩም፡፡ ከጥንቃቄ ጉድለት ይዘታቸውን የቀየሩ ቅርሶች እንዳሉና የጠፉም ሊኖሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ 
1990 .. አንስቶ የዋግኽምራ አስተዳዳሪ በነበሩት ልጃለም ወልዴ በተሠራ ካዝና ውስጥ ቅርሶች ይቀመጣሉ፡፡ ካዝናው ቅርሶቹን ለመጠበቅ ቢጠቅምም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ቁሳቁሶች ተደራርበው እንደሚገኙና በፍትጊያ የተላላጡም እንዳሉ አስተዳዳሪው ይናገራሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ቅርሶች የሚቀመጡበትና ለጎብኚዎች የተመቸ ሙዚየም እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ፡፡
ስለ ቤተ ክርስቲያኑ አመላካች መረጃዎች በከተማው፣ በዞኑ ወይም በአገር አቀፍ ደረጃ መሰራጨት እንዳለበትም ይገልጻሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሦስት መሪጌታዎች፣ 15 ቀሳውስትና 28 ዲያቆኖች ይገኛሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ወደ 20 የሚጠጉ የአብነት ተማሪዎች አሉ፡፡ የክፍያው መጠን አነስተኛ በመሆኑ እንዲሁም አብዛኛው ተማሪ ወደ መደበኛ ትምህርት እየሄደ ተማሪዎች ቁጥር እያነሰ መምጣቱን አስተዳዳሪው ይናገራሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ከዚህ ቀደም ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ጎብኚ በማጣት፣ በቅርሶች አያያዝም ችግሮች ይታዩ እንደነበረ የሚገልጹት አስተዳዳሪው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተ ክርስቲያኑና በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለሆነ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናሉ፡፡  
በሰቆጣ ከተማ ባሉ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ላይ ያነጋርናቸው የከተማው ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን መኰንን እንደሚሉት፣ በከተማው መስህብ የሆኑ ቋሚና ተንቀሳቃሸ ቅርሶች ቢኖሩም እምብዛም አይታወቁም፤ አይጎበኙምም፡፡ አቶ መስፍን እንደሚሉት፣ መጠነ ሰፊ ማስተዋወቂያ አለመደረጉና አመቺ መንገድ አለመኖሩ በአፋጣኝ መፈታት ያለባቸው ችግሮች ናቸው፡፡
በቅርስ አያያዝና ጥበቃ ረገድ ኃላፊው እንደሚሉት፣ ቢሮው በከተማው ያሉ ቅርሶችን መዝግቦ በመያዝ በየጊዜው ቆጠራ ይካሂዳል፡፡ ቢሆንም አሁንም ድረስ ያልተመዘገቡና ይጠፋሉ በሚል ሥጋት በየቤተ ክርስቲያኑ የተደበቁ በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ እንደገለጻቸው ቅርሶቹን ለመመዝገብና አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ቢሮው እየሠራ ነው፡፡ እንደ መልአከ ሰላም መርሐጥበብ ሁሉ ኃላፊው፣ ‹‹በሀብቶቻችን መጠቀም የሚገባንን ያህል አልተጠቀምንም፤›› ይላሉ፡፡


1 comment:

  1. Would you please post the picture again? thank you.

    ReplyDelete