Written by Dn. Birhanu Admass Anleye
የተፈጸመው ድርጊት ለብዙዎቻችን እጅግ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ፣ አዋራጅ እና ቅስም ሰባሪም ነው። ይልቁንም ደግሞ አንዳንድ እጅግ የምናከብራቸው እና የምንወድዳቸው ብቻ ሳይሆን የምናምናቸውም አባቶች ጭምር መካተታቸው የበለጠ እንድናዝን አድርጎናል። ይህም የዕውቀታችንን ውሱንነት ብቻ ሳይሆን መታመን መጥፋቷን፣ ፈተና እና ችግር እንኳ ቢኖር እርሱን ተቋቁሞ ማለፍ የመቻል አቅም መሳሳቱን፣ ፍቅረ ሲመትም ክንፍ አውጥቶ መብረሩን ይፋ አድርጎ አስጥቶታል።
በርግጥ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይህን መሰል ጥፋቶች እንደማይቀሩም የመጣንበት መንገድ አመላካች ነበር። ጌታችን በወንጌል “አልቦ ዕፅ ሠናይ ዘይፈሪ ፍሬ እኩየ፣ ወአልቦ ዕፅ እኩይ ዘይፈሪ ፍሬ ሠናየ” ሲል እንደገለጸው የመጣንበት የሲመት መንገድ የዚህ ዓይነት ፍሬ ላይ ሊያደርሰን እንደሚችል ብዙዎች ተናግረው ነበር፤ ይታወቃልም። የመጣንበት የሲመት ባህልም እንበለው መንገድ እጅግ ብዙ ጉድለቶች እና ውሱንነቶች እንደነበሩበት ቢያንስ አሁን እንኳ ዝም ልንል አንችልም። ዛፉ መልካም ከሆነ ፍሬው መጥፎ ሊሆን አይችልም የሚለውን የጠቀስኩት ለዚህ ነው። እውነቱን ለመናገር ከልክ ያለፈ ይሉኝታ እና ምን አገባኝ ብዙ ጥፋቶችን እያከተተለ እንዳመጣብን ለመረዳት አይቸግርም። ከዚህ በኋላ ግን እንታገስህ ብንለው ራሱ ችግሩ አይታገሰንም። እንቻልህም ብንለው ሞልቶ ፈስሷል እና አንችልም። መጠን የለሽ የጎጠኝነት፣ የተንኮል፣ የበቀለኝነት፣ የሌብነት፣ የጉቦ እና የቡድነኝነት ዛፋችን ያፈራውን ፍሬ ነው ዛሬ የተመለከትነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ “ዘዘርዐ ሰብእ የአርር” – ‘ሰው የዘራውን ያጭዳል' እንዳለ በገላትያ መልእክቱ ያጨድነው በዘመናት የዘራነውን መሆኑን ልንክድ አንችልም። በዚህ ጉዳይ አብረን ንስሐ ገብተን መታረም እንችላለን ብዬም አላምንም። ፈጽሞ ሲያጠፋን ግን ከዚህ በላይ ዝም ብለን ልናየው የሚገባን አይመስለኝም። ልምምጥም ሆነ ልመናም የሚያስፈልገው አይመስለኝም። የሚያስፈልገው ወደ ሕግ እና ሥርዓት ቀጥ ብሎ መግባት ብቻ ይመስለኛል። ይበቃል! በእውነት ይበቃል። ከዚህ በላይ ምን ልንሆን እንችላለን? ሹመትም ሆነ ምደባ በሕግ እና በሥርዓት ብቻ መፈጸም አለበት ። ይህ እስካልሆነ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል ብቻ ሳይሆን እንደጠፉት ሀገሮች እና ዛሬ እንዲህ ነበሩ እየተባለ እንደሚነግርላቸው እኛም እንጠፋለን። ዐፅመ ሐዋርያት እና ሰማዕታት ከተከማቹባት፣ ሦስቱ ዐለም አቀፍ ጉባኤዎች ከተካሔዱባት፣ እኛ ከምንቀድሳቸው ዐሥራ አራት ፍሬ ቅዳሴዎች ውስጥ ከስምንት ያላነሡት ካመጣንባት፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፣ ጎሮጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ካስተማሩባት እና ከገለገሉባት የቁስጥንጥንያ መንበር ሙሉ በሙሉ መጥፋት መማር ካልቻልን ከምን ልንማር እንችላለን በእውነት? እንደ እኔ ሕመማችንን በአግባቡ ካልታከምነው እንደ ጋንግሪትም በድን ያደረገውን ቆርጠን ካልጣልነው ሙሉ በሙሉ መጥፋታችን የሚቀር አይመስለኝም። ስለዚህ ከይሉኝታ መጋረጃ ወጥተን ነገር ግን ደግሞ ሕግ እና ሥርዐት ጠብቀን በችግሮቻችን ላይ መዝመት መጀመር አለብን ብዬ አምናለሁ። ምን ምን ችግሮቻችን ላይ ቆራጥ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? ለዛሬው እንደ አርእስተ ኃጣውዕ ያሰብኳቸውን ሦስቱን አነሣለሁ።
1) ባዕድ እጅ
አቡነ ቴዎፍሎስን ለማውረድ ደርግ አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር ይባላል። ኮሚቴው የተሐድሶ ኮሚቴ ይባል ነበር አሉ። ለዚህ ኮሚቴ በሰብሳቢነት የተሾሙት ደግሞ አንድ እጃቸው አርትፊሻል ነበረ። ታዲያ ብዙ የቤተ ክህነት ሊቃውንትን በደብዳቤ እያስገደዱ ወደ ኮሚቴው ሲያስገቡ መልአከ ብርሃናት ተስፋ ወርቅነህ የሚባሉት ሊቅ በእኒህ ሰብሳቢ የተፈረመ ደብዳቤ ሲደርሳቸው አዝነው ቤተ ክርስቲያን ባዕድ እጅ ገብቶባታል የምትሆነውን እንጃ ብለው ነበር፤ ቅኔም ተቅኝተውበት ነበር ይባላል።
ይህች ባዕድ እጅ ከዚያ ዘመን አንሥቶ እስካሁን ድረስ ትበጠብጣለች። ምንም እንኳ በየዋሕ ምእመናን፣ በጉባኤ ቤት መምህራን፣ በስውራን ቅዱሳን እና በየቦታው ባሉ ደጋግ ካህናት እና አገልጋዮች መኖር ምክንያት ረድኤተ እግዚአብሔር ስላልተለየን ፈጽመን ባንጠፋም በየዘመናቱ እየወረድን፣ እየተዋረድን እዚህ መድረሳችን ግን ከማንም የተሰወረ አይደለም።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከመምጣታቸው በፊት ጥሩ የምርጫ ሕግ እንዲኖረን እና በመጨረሻም በድምፅ ከተመረጡት ሦስት አባቶች መካከል ፓትርያርክ የሚሆነው በጸሎት እና በዕጣ ይለይ የሚለውን ረቂቅ ለማስቀረት ይህች ባዕድ እጅ ብዙ ሚና ተጫውታለች ። በተለይ አንተን ነው ፓትያርክ የምናደርግህ እያሉ ፖለቲከኞቹ ያባበሏቸው እና ቅዠት ውስጥ የከተቷቸው ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ያለ ይሉኝታ ተቃወሙት ። አሁንም ድረስ ልባቸው ተላላ የሆኑና ከዚያ የማይማሩ ሰዎችን ስናይ እጅግ እንገረማለን፣ እናዝናለንም። በእውነት ልብን ያደማል። እስከመቼስ ሲደበቅ ይኖራል?
ይህች ባዕድ እጅ ከባድ የምትሆነው ደግሞ ሁሌም ቤተ ክህነት ውስጥ ባለ እና እጁ በተቆረጠችበት ሰው በተቆረጠችበት እጁ ምትክ በባለሞያዎች እውነተኛ እጅ መስላ የምትቀጠል በመሆኗ ነበር። ይህች እጅ እስካሁን ታቦካለች፣ ትጋግራለች፣ ትሾማለች ፣ ትሽራለች ። ተላላ ልቦችን እያባበለች ወደ ጥፋት ገደሏ ትከታለች። እከብር ባይ ልቡናዎችን በሕልም ዐለም ይዛ ትጠፋለች፣ በምናባዊ ሹመት ታሳብዳለች ። ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዳየሁት ዛሬ ከተሾሙት ውስጥ ከመሾማቸው በፊት እንደ ጳጳስ ለብሰው ፎቶ የሚነሡ ነበሩበት ፤ ይገርማል፣ ያሳዝናል። ይህች እጅ የቅባት ጳጳሳትን በጥንቃቄ አዋልዳለች ። መንበረ ሰላማ የጵጵስና መንበረ ተክለ ሃይማኖት ደግም የእጨጌነት እንጂ የፓትርያርክ አለመሆኑን እንኳ የማያውቁ ሰዎችን አሰባስባ በትግራይም ታገሣለች ። ይህች ባዕድ እጅ አሁንም የልዩነት ገደላችን ትቆፍራለች፣ ታሰፋለች፣ ታስፋፋለች ። በእነዚህ ዘመናትም በሕጉ እና በተግባሩ መካከል ያለውን ገደል አስፍታ አስፍታ በአብርሃምና በነዌ መካከል ያለውን ገደል አድርጋዋለች ። በእውነት ያሳዝናል።
ይህች እጅ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለባት ። የምትወገደው ደግሞ እኛ ቆርጠን ስንነሣ ነው። ግብጾች አሁን ያላቸውን የምርጫ ሕግ ያወጡትን እና ብዙ ተደራራቢ የቆየ ችግራቸውን የፈቱት ሁሉም ምእመን በተሳተፈበት ሁለት ዐመት ተኩል በፈጀ ውይይት እና በመጨረሻም ሕግ አውጥተው በመፈጸም ነው። ቫቲካንም የፖፕ ምርጫውን በተዘጋ ቤት እና በጢስ ብቻ እንዲታወቅ አድርጋ በሯን የቆለፈችው ይህችን የባዕድ እጅ ላለማስገባት ነበር። ሌሎች አብያተክርስቲያንም ይህችን እጅ ቆርጠው ጥለው ቀኖናዊነታቸውን ለማስከበር በቅተዋል። እኛ ጋር ግን አሁንም ድረስ በየድስቱ እየገባች ታማስላለች ። እስከመቼ ግን እንዲህ ልንቀጥል እንችላለን? ይህች ባዕድ እጅ መሰብሰብ ይኖርባታል።
2) የምእመናን ድርሻ የረሳ ኢቀኖናዊ ሲመት
በቀኖናችን በሚሾምበት ሀገረ ስብከት ያሉት ምእመናን ያለተቀበሉት ሰው በጵጵስና እንዳይሾም የተከለከለ ነው። እኛ ሀገር ግን ያለው የተገላቢጦሽ ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ከላይ ያነሣናትን ባዕድ እጅ ጉልበት የሰጣት ይሔው የክርስቶስን በጎች ምእመናንን ፈጽሞ የረሳ እና የተወ ኢቀኖናዊ ሹመት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ኢቀኖናዊ ድርጊት ቢያንስ ከዚህ በኋላ በፍጹም ሊኖር አይገባውም። ይህ ቀደም ብሎ ተጀምሮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ በአንድ ሌሊት 25 ሰው ተሹሞ ሊያድር አይችልም ነበር። ምንም እንኳ ብቸኛ ምክንያቱ ይህ አለመኖሩ ባይሆንም ይህ ጉዳይ እስካሁን ለደረስንበት ውስብስብ ችግር አስተዋጽዖው ከፍተኛ መሆኑ ይታየኛል። ምክንያቱም በዘር የተሾመ በዘር ይሾማል። በፖለቲካም የተሾመ በፖለቲካ ይሾማል። በኮታ የገባ ኮታዬ ከዚህ በላይ ነው ብሎ ማሰቡ አይቀሬ ነው። በአንዱ ተገፍቻለሁ የሚለውም ወደ ሌላው ይጠጋል።
3) ጎጠኝነት
በአሜሪካን ሀገር እምነታቸውን ወደ ምሥራቅ ኦርቶዶክስነት የቀየሩ አንድ አሜሪካዊ አባት በአሜሪካ የሚኖሩ የተለያዩ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ሁኔታ ይተቻሉ። የሚተቹት አንድ ኦርቶዶክስ ከሆንን እና በአንድ ሀገር ከኖርን ለምንድን ነው የግሪክ፣ የሩሲያ ፣ የሰርቢያ፣ የሮማኒያ፣ ... እየተባባልን የምንለያየው? ለምን በአንድ መንበር እና አስተዳደር ውስጥ አንሆንም የሚለውን ሀሳባቸውን ለማስረዳት ያነሡት ጥያቄ አለ። አትናቴዎስ አሁን ቢመጣ የትኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው የሚሔደው? ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ኤፍሬም፣ ... ቢመጡ የትነው የሚሔዱት? እኛስ ማንኛውን ነው የምንጋብዘው ወይም የምንቀበለው የሚለውን ጥያቄ በማንሣት በተለያየ ሀገር እንኳ መከፋፈል እንደሌለባቸው ይሞግታሉ።
እኛ ደግሞ በአንድ ሀገር እንኳ ሆነን ቅዱሳኑን ሳይቀር የዚህ እና የዚያ አካባቢ እያልን እናቃልላለን። እጅግ እጅግ ምሳሌ የማይግኝለት ጎጥኝነት ውስጥ መኖራችንን መደበቅ አይቻልም። በዚህ ገምተናል፣ ተግማምተናልም። ባለፉት ሹመቶች እንኳ እገሌ ከዚህ አካባቢ ዘር አለበት እየተባሉ ዕጩ ከሆኑበት ሀገረ ስብከት የተተውትን እንዴት መርሳት ይቻላል። ያ መራራ ሒደት ነው ዛሬ ይህን መራራ ውጤት ያመጣው። ዛፉ መራራ ከሆነ ፍሬውም መራራ ነው የተባለው ነዋ እየሆነ ያለው። እነዚህን ችግሮች ፊት ለፊት መግጠም እና ማሸነፍ እስካልቻልን ድረስ እየተነቃቀፍን፣ እየተማማን፣ እየተጠላላን፣ እየተነዋወርን እንደምንጠፋ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ሁሉ ለዚህ ከፍታ ያበቃችው ግን ያች ባዕድ እጅ መሆኗን አምናለሁ። እነዚህ ለዚህች ባዕድ እጅ ጓንትና መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ስለሆነ በፍጥነት ካላሻሻልናቸው ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው እየተሳሳቅን እና እየተሳለቅን ልንጠፋ እንችላለን።
ድክመቶቻችን አርመን ከችግሮቻችን ወጥተን ለማየት እንድንችል ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ አሜን።
No comments:
Post a Comment