ዛሬ ጥር 16 ምሽት ማኅበረ ቅዱሳን፣ አገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት፣ ምእመናን ኅብረት ፣ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት፣ የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት በጋራ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የማኅበራቱ ተወካዮች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካጋጠማት ታሪካዊ ክስተት አንጻር ከመቼውም ጊዜ በላይ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የምናስጠብቅበት እና ከአባቶቻችን ጎን የምንቆምበት ወቅት በመሆኑ በኅብረት መክረን አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል ብለዋል።
ማኅበረ ቅዱሳንን ወክለው የተገኙት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሙሉጌታ ሥዩም በመግለጫው እንደተናገሩት የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ያቃለለ የነገ የሐዋርያዊ አገልግሎትን ያሰናከለ በመሆኑ አባቶቻችን ይህንን ያማከለ ውስኔ እንዲወስኑ እንጠይቃለን ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም መንግሥት እጁን ከዚህ ሂደት እንዲያነሳ ይልቁንም የእሱ ግዴታ የሆነውን ጥበቃ እንዳያነሳ ይህ ካልሆነ ግን ኦርቶዶክሳውያን ቤተ ክርስቲያን እስከሰማእትነት ለመታደግ የታመኑ ናቸው ብለዋል። ምእመናንም ሳይደናገጡ በጸሎት እንዲተጉ እና ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከመንግሥት ጋርም በቀጣይ ችግሩን እንዲረዳና ቤተ ክርስቲያን የራሷን ችግር በራሷ እንድትፈታ እድል እንዲሰጣት መወያየታቸውን በመግለጽ የዜጎችን ደህንነት ካልጠበቀ ግን ከተጠያቂነት አይድንም ሲሉ ገልጸዋል።
አንድ ያደረገን ድርጊቱ ሕገ ወጥ መሆኑና ሀገርና ቤተ ክርስቲያን የሚንድ በመሆኑ ነው ያሉት ደግሞ አገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት ተወካይ አቶ ያሬድ ዮናስ ናቸው። ችግሩን ከማወገዝ ባለፈ ከእኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ተዘጋጅተናል፤በእያንዳንዳችን መዋቅርም ስራዎችን ለመስራትም ተነጋግረናል ብለዋል።
የምእመናን ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳ ቤጥ አምዴ በበኩላቸው ውይይት በአንድ ሃሳብና ልብ መከናወኑን ገልጸው ቅዱስ ሲኖዶስ ተደፍሯል፣አባቶች ተደፍረዋል፤ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ችግር ለማውጣት ሁላችንም በቁርጠኝነት ተነስተናል ብለዋል። በውይይታቸውም በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንደማይደራደሩ አፅንዖት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና በአባቶች ላይ የተቃጣውን ለመመለስ በአባቶቻችን ጥሪና መመሪያ ተመስርተን ለመሄድ ቃል ገብተናል ያሉት ደግሞ የጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ተወካይ አቶ አያልነህ ተሾመ ናቸው። አክለውም ይህ የህልውና ጉዳይ ሀገር የማፍረስ ጉዳይ በመሆኑም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ተወካይ ወ/ት ፌቨን ዘሪሁን በበኩላቸው ዛሬ በነበረን ውይይት ሁላችንም ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንድንሆንና የድርሻችንን ለመወጣት መስማማታቸውን በመግለጽ ለዚህም የአባቶችን መመሪያ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቅድስት ቤተ ክርስትያንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተገኝተው ለማስረዳት ዝግጅት መጨረሳቸውንም በመግለጫቸው ገልጸዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግስት ከለላውን አንስቷል ሲሉ ዛሬ ምሽት መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
ከማኅበረ ቅዱሳን ኤፍ ቢ ገጽ
No comments:
Post a Comment