Thursday, July 26, 2018

‹‹ኦርቶዶክስ ሀገር ናት ፤ በጣም ደስ ብሎኛል እንኳን ደስ አላችሁ ›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ

  • ሀገራችን ካለ እናንተ ጸሎት ውጪ ሰላሟም ልማቷም ሊረጋገጥ አይችልም
  • ዛሬ በኢትዮጵያ ወገኖቻችን ላይ ተገንብቶ የኖረው የመጀመሪያው የጥላቻ ግንብ ዋንኛው ምሰሶ በይፋ ተንዷል


(አንድ አድርገን ሐምሌ 19 2010 ዓ.ም)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ በእርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ የተናገሩትን እንዲህ አቅርበነዋል


‹‹በጣም ደስ ብሎኛል እንኳን ደስ አላችሁ ፤ ኢትዮጵያ ከዚች ታላቅ ቤተ ክርስቲያ ውጪ አትታሰብም ፤ እርቁ እንዲመጣ ያስፈለገበት ምክንያት ኦርቶዶክስ ሀገር ስለሆነው ነው ፤ ታላቅ ታሪክ ፣ ዝና እና ክብር ያላት ቤተክርስቲያን ናት ፤ እዚህ ሰላም ሲሆን ሁላችንም ሰላም እንሆናለን ፤ እዚህ ሰላም ሲጠፋ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪነት እያንዳንዳችንን ይነካናል ፤ አንድነቷ ከተጠበቀ ሌሎችን መርዳት ትችላለች ፤ የታሪክና የትውፊት ባለቤት የሆነች ቤተ ክርስቲያን ራሷ አንድነቷን በማጣቷ እሷ እያለች ሌሎች እኛን ሲያግዙን ኖረዋል ፤ የእሷ አንድነት ከምስራቅ አፍሪካ አልፎ ለአፍሪካ ትልቅ ዜና ፣ ትልቅ ብስራት እንደሆነ ይሰማኛል ፣ በተግባርም የምናየው ይሄንኑ ነው ፤ በህብረት ውስጥ የሚገኝ ትርፍ ፣ ሥምና ዝና አጥተናል ፤ ኦርቶዶክስ አንድ ሆና ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ እርቀ ሰላም እስከ አሁን ባልዘገየ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ከራሱ እንዲጣላ ፣ ከጎረቤትና ከሃይማኖቱ እንዲጣላ ፤ የሃይማኖት አባቶችን እንዳያከብር ፤ ሲገሰጽ እንዳይመከር ያደረገው አንዱ ነገር በዚች ታላቅ እና ቅድስት ቤተክርስቲያ ያጋጠመው ጸብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እኛ አንድ ስንሆን ለክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን ለእስልምናና ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ዜጎች በሙሉ ክብር ፣ አንድነትና ሰላም የሆነ ዜና መስማት እጅጉን የሚያስደስት ነገር ስለሆነ ዛሬ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ይህ የሰላም ብስራት ከቤተ ክርስቲያን አልፎ ለመላ ሕዝባችን እንዲደርስ የመጀመሪያ ጉባኤ በዋሽንግተን በሰው ሀገር የሆነ ቢሆንም በሀገራችን በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው ትልቁ እና መክፈቻ ጉባኤ ላይ ሁላችን በጋራ ተገኝተን የዚችን ቤተ ክርስቲያን እርቅ ፣ ሰላምና አንድነት የምናውጅበት  ፣ ከራሷ አልፋ ኢትዮጵያን እንደምታስታርቅ በይፋ የሚበሰርበት ጊዜ ቅርብ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡ ይህ እርቅ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ይህ የእርቅ ፕሮግራምና ኮንፍረንስ እየተካሄደ  በፖለቲካ ፣ በብሔርና በሃይማኖት የተጣሉ ቡድኖች ከእርቅና ከሰላም የሚገኝውን ደስታና ድል እነርሱም መቋደስ እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያቱ ራሷን ማስታረቅ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን እርቅ በር የሚከፍት ሥራ በሚቀጥሉት ወራት በተከታታይ በመስራት ኢትዮጵያችን ውስጥ ያለው ጥላቻ ቅራኔ እየቀነሰ ወደ መደመር የምንመጣበትን ብስራት ዳግም ታሰማለች የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ወገኖቻችን ላይ ተገንብቶ የኖረው የመጀመሪያው የጥላቻ ግንብ ዋንኛው ምሰሶ በይፋ ተናደ ፤ ይህ ምሰሶ የፈረ እንደሆነ በፖለቲካ ፣ በዘር ፣ በተለያየ ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ግንቡን ያጠናከሩ ትናንሽ ምሰሶዎች ከዚህ ምሰሶ ውጭ መቆም ስለማይችሉ ትንሽ ተባብረን ገፍተር በማድግ ፖለቲካችን ፣ ሃይማኖጻችን ፣ብሔራችን ፣ ቋንቋችን ፣ ኢተዮጵያዊነታችን በአንድ ጥላ ሥር ፣ ልዩነታችንም በዚያው ስር እንደውበት የሚታዩ እንደመሆኑ ሙሉ ተስፋ አለኝ ፡፡ ይህ ጉዳይ ከዚህ ጊዜ ቀድሞ እርቀ ሰላም እንዳይከናወን እኔ የምመራው መንግሥር ሚናውን ባለመወጣቱ በይፋ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በኢትዮጵ እና በአሜሪካ የምትገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ይህ ነገር እዲከናወን ላደረጋችሁን ልዩ አስተዋጽኦ በራሴና በኢፌድሪ መንግሥት ሥም እጅግ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ በሁለቱም ወገን የሆናችሁ የእርቅ ኮሚቴ አባላት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ፡፡ ግንብ የማፍረሱ ሥራ ዛሬ ተጀመረ እንጂ ስላልተጠናቀቀ ዛሬ የፈረሰው ምሰሶ ዋንኛውና ጠንካራው ስለሆነ አባቶች ከዛሬ ጀምራችሁ እንደልማዳችሁ በየዕለቱ በጸሎታችሁ እንድታስቡን ፣ ሀገራችን ካለእናንተ ጸሎት ውጪ ሰላሟም ልማቷም ሊረጋገጥ ስለማይችል ፣ ሥራችሁ ለእኛ መጸለይ ፣ እኛን መገሰጽ ፣ እኛን ማስታረቅ ፣ እኛን መምከር ነውና ይህን ተግባራችሁን እንድትፈጽ በትህትና እለምናችኋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ    ›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ በእርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ የተናገሩት

ቅድስት ቤተክርስቲያን ዛሬ ልደቷ ነው ፤ ላለፉት 26 ዓመታት ዘለቁ የመለያየት ጊዜያት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ፊት አውራሪነት እና በቅዱሳን አባቶች ያላሰለሰ ጥረት ዛሬ ሐምሌ 19 2010 ዓ .ም በዋሽንግተን ዲሲ ታላቅ ብስራት ለመላው የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እና ለመላው የሀገራችን ሕዝብ ተበስሯል፡፡ 

ዶ/ር አብይ አሕመድ ከባዱንና ወሳኙን ግንብ መፍረሱን ተናግረዋል ፤ በቀጣይም ትናንሽ ግንቦች በመተባበር እንደሚፈርሱ የዚህ ታላቅ ብስራት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በቀጣይ ቀናት የመለያየት ጊዜ እንዳበቃ እና የእርቅ ዘመን ፤ የአንድነት ዘመን ለመላው ሕዝባችን እንደሚበሰር አሳውቀዋል ፤ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ይህ የሩብ ክፍለዘመን ግድግዳ እንዲናድ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት አካላት ዶ/ር አብይ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በሁለቱም ወገን የተደረሰ ስምምነት ይህን ይመስላል፡፡

የኢ.ኦ.ተ.ቤ እርቀ ሰላም ሂደት መጠናቀቅ ዙሪያ የተደረሱ ዋና ዋና የስምምነት ነጥቦች:
1.    ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፓትያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ/እንዲገቡ፤
2.    ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ኢትዮጵያ ሲመለሱ በክብር የሚያርፉበትን የመኖሪያ ቦታ በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ ቦታ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤
3.     የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
4.    ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  በሕገ ቤተ ክርቲያን መሠረት የአስተዳደር ሥራውን በመሥራት ቅድስት ቤተ ክርስቲንን እንዲመሩ፤ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
5.     የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ አባቶቻችን ስም በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ፤
6.     ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሠጡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደተፈጸመ በሁለቱም ወገን ባሉት ልኡካን ታምኖበታል፡፡
7.     የተላላፈው ውግዘት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው የአንድነት ጉባኤ እንዲነሳ፡፡
8.     በልዩነቱ ዘመን የተሾሙ ጳጳሳት የስም መመሳሰል እንደ ሲመታቸው ቅደም ተከተል ቀዳማዊ፣ ዳግማዊ፣ ሣልሳዊ እየተባለ ይለያል እንጅ የስም ክለሳ እንዲደረግ ፡፡
9.     ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከጥሰት ለመጠበቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ኢንዲዘጋጅ እና በውጭ ሀገር ያለውን ሁኔታ ያገናዘበ መዋቅራዊ አስተዳደር እንዲኖር ስምምነት ተደርጓል
 
‹‹አንድ አድርገን›› እያላችሁ ለሁለት አስርት አመታት የጸለያችሁ ፤ ለአንድነቷ የበረታችሁ ፤ በእርቀ ሰላም ኮሚቴ ውስጥ ለተሳተፋችሁ ፤ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ ለተወጣችሁ ብጹአን አባቶች ፤ እንባችሁን ያፈሰሳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ 

ኦርዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀደመ ክብሯ እና ገናናነቷ ትመለስ ዘንድ ዛሬም ነገም የቤት ስራችን ብርቱ ነውና እንደ ትላንቱ በአንድነት እንድንበረታ  ‹‹አንድ አድርገን›› ታሳስባለች

ዳግም እንኳን ደስ አላችሁ

No comments:

Post a Comment