Saturday, July 21, 2018

እርቀ ሰላም



( አንድ አድርገን  ሐምሌ 15 ፤ 2010 ዓ.ም ) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም ፤ ነገር ግን  ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው ። ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” 

የፍቅር እጦት እንጂ ሰውም በወንድሙ ላይ በክፋትና በአመፅ አይነሳምና ቃየል አቤልን በምቀኝነትና በጥላቻ ተነሳስቶ እንደገደለው ሁሉ ዛሬም ብዙ ቃየላውያን በወንድሞቻቸው ላይ በትዕቢት እና በእብሪት ተነሳስተው የሚሞት ስጋቸውን ለመግደል ያሴራሉ። መግደል ለእነርሱ እጅግ የቀለለ ተግባር ነው፤ ቀድመው ህሊናቸውን ገድለዋልና። ማሳት ለእነርሱ እጅግ የቀለለ ተግባር ነው፤ ቀድሞ ህሊናቸውን ስተዋልና። ነገር ግን ዛሬም አሁንም በዚች ቅጽበትም በንስሃ ለተመለሰ ሁሉ ምህረት አለ። ከጥፋት መንገድ ዘወር ላለ መዳን ይሆንለታል። ነገር ግን እንደቀደመው ጊዜ በክፋትና በተንኮል ለመመላለስ ልቡን ያደነደነ፣ ፍቅርን የገፋ፣ ምህረትን የናቀ፣ ለወገኖቹ መጥፊያ ያሴረ፣ ጥላቻን ያነገበ እርቅን የጠላ ሰው ወይም ቡድን የኋላ ኋላ በታላቅ አወዳደቅ መንኮታኮቱ አይቀርም።


እርቅና ሰላም ያልተጠጋው ጉልበትና ሃይሉን ፤ ሴራና ተንኮሉን ፤ የተመካም ሲምስ በዋለው ጉድጓድ ገብቶ እስከወዲያኛው ማለፉን ታሪክ ይነግረናል። በግርማቸው አስፈሪ የነበሩትም ነገሥታት እስከጭፍራ ሠራዊቶቻቸው በውሃ ሙላት ሲወሰዱ፣ እንደ እንስሳ በጫካ ሲቅበዘበዙ፣ እና ከነመታሰቢያቸው ትቢያ ሲሆኑ ዓለም ታዝባለች።

ሃይልን እና እብሪትን በፍቅር እና ርህራሄ፣ በይቅርታ እና ታጋሽነት፣ በትህትና እና ጨዋነት የሚመክቱ ግን በስተመጨረሻ አሸናፊዎች ናቸው። እስከመጨረሻዋ አስፈሪ ቅጽበትም ባመኑበት ነገር ፀንተው የሚቆሙ፣ የመጨረሻዋን ጽዋ ለመጐንጨት የታመኑ፣ በህይወታቸውም ባይሆን በህልፈታቸው ዛሬም ፍቅር ህያው እንደሆነ የሚሰብኩ ሰማዕታት በየዘመኑ መነሳታቸው ደግሞ ለሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ ነው። በሰው ልጅ ላይ ያለንን የመልካምነት እምነትም ያጠናክርልናል።

ዛሬም በመተዛዘን፣ በመዋደድ፣ በአንተ ትብስ አንቺ መከባበር፣ ራስን አሳልፎ በመስጠት፣ በመረዳዳት፣ ደስታና ሀዘን በመካፈል፣ ያለንን ሁሉ በማካፈል፣ ለወገንና ለቤተክርስቲያን  በመቆርቆር የወደፊቱን ትውልድ ህይወት የእኛንም ጭምር ብሩህ ማድረግ እንችላለን። እኛ ከተዋደድን ብዙዎቹ ተራሮቻችን በፊታችን ደልዳላ ሜዳ ይሆናሉ። ፍቅር ሃያል ነው፤ ፍቅር ያላቸውም ኃያላን ናቸው። በመሆኑም ፍቅር ያላቸው ሁሉ የኃያላን ተግባራትን ይከውናሉ። በልበ-ሙሉነት እና በፍፁም በራስ-መተማመን ስሜት ሊገላቸው ጭምር ከመጣው ሰው ፊት የፍቅር ምላሽ ይሰጣሉ። ሰይፍን በሰይፍ አይመልሱም፤ ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ እንደሚጠፉ ያውቃሉና! ይልቁንም ግራ ጉንጫቸው ሲመታ ቀኙን ለማዞር ይዘጋጃሉ። ሊገላቸው የመጣውን ሰው በክፋት አይተባበሩትም። የገዳይ ግብረ-አበርም አይሆኑም፤ ለመሞት ይመቻቹለታል እንጂ። በዚህም ተግባራቸው የፍቅርን ሃያልነትና ረቂቅነት ይገልጣሉ! እየሞቱ፡- ‹‹አባት ሆይ፡- የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!›› እያሉ ስለገዳዮች ይማፀናሉ። ምክንያቱስ ቢሉ፡ ‹‹ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም ፤ የራሱንም አይፈልግም፤ አይበሣጭም፤ በደልን አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለዓመፅ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉንተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይፀናል።›› ይህም የተገለፀው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው።

ታዲያ ዛሬ ሕይወታችንን መለስ ብለን ስንቃኘው፣ ወደውስጣችን ስንመለከት፣ ጓዳችንን ስንመረምረው፣ ልባችንን ስንፈትሸው ፍቅርን እናገኘው ይሆን? ወይስ በቦታው ጥርጣሬ፣ አለመተማመን፣ ፍርሃት፣ ቂም በቀል እና ጥላቻ ነግሶበታል? ቀስ-በቀስ ውስጣችንን እየቦረቦረው እና እየገደለው ያለውን ይህንን መርዘኛ ሰንኮፍ የምንነቅለውስ በምንድን ነው? ምንም መልካም እንዳንሠራ ብቻ ሳይሆን የምንሠራው ሁሉ ጥፋት እንዲሆን ከሚያንደረድረን ጥላቻስ የምንወጣው በምን መላ ነው? ከራሳችን፣ ከቤተሰባችን፣ ከጐረቤቶቻችን ፣ ከአባቶቻችን ጋር ተጣልተንስ የምንኖረው እስከመቼ ነው? መቼስ እርቅ እናወርዳለን? መቼስ የቀደመውን ፍቅር ከወደቀበት እናነሳዋለን?

ለመሆኑ “እርቅ” ማለትስ ምንድነው?
የፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም “አገቱኒ” ላይ እንዲህ ይነበባል ፡ - ‹‹ እርቅ ማለት ጠብን በሰላም ፣ ጥላቻን በፍቅር ፣ አለመግባባትን በስምምነት ፣ ጥርጣሬን በመተማመን ፣ መራራቅን በመቀራረብ ፣ ኩርፊያን በመነጋገርና በመወያየት መለወጥ ነው፤ እርቅ ማለት የበደለ ጥፋቱን አምኖና ካሣ ከፍሎ፣ የተበደለ ቂሙን ከልቡ ፍቆ ለአዲስ ግንኙነት በንጹሕ መንፈስ መታደስ ነው።
በእውነት እርቅን የሚፈልግ ማን ነው? እርቅን የሚፈልግ ሰላምን የሚፈልግ ነው፤ እርቅን የሚፈልግ ከራሱ በላይ የአምላክም ሆነ ፣ የሕግም ሆነ ፣ እግዚአብሔር ኃይል መኖሩን የሚያምንና አርቆ የሚያስብ ሰው ነው፤ እርቅን የሚፈልግ ዘመን ተሸጋሪ እይታ ያለው ሰው ነው ፤ እርቅን የሚፈልግ ያለ ሰላም የተጓዘበትን መንገድ ዞር ብሎ መመልከት የሚችል ሰው ነው ::  ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌለበት መስሎ የሚታየው፣ እያጠቃሁ ለመኖር የሚያስችለኝ ጉልበት አለኝ ብሎ የሚያምን ሰው፣ ከጉልበቱ ውጭ የሚተማመንበት ምንም ኃይል ስለሌለ እርቅን የሚፈልግበት ምክንያት አይታየውም፡፡ ተበዳይም ቢሆን አቅሙን አሳንሶ ገምቶ “ደሀ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ” እንደሚባለው አለመቀየሙንም ለመግለጽ ሲል ራሱን በደለኛ አድርጎ በማቅረብ ጉዳዩን በዳዩ እንዲረሳለት ይሞክራል ፤ ነገር ግን በዳዩም ሆነ ተበዳዩ ከሚያቆራኛቸው የበደል ሰንሰለት አይላቀቁም ፤ በዳዩ ተበዳዩ አይተኛልኝም ብሎ በስጋትና በፍርሃት ይኖራል ፤ ተበዳዩም የበዳዩን ፍርሃትና ስጋት ስለሚያውቅ ሲመቸው ያጠፋኛል ብሎ በስጋትና በፍርሃት ይኖራል፤ እርቅ የሚያስወግደው ይህንን በሁለቱም በኩል ያለውን ስጋትና ፍርሃት ነው፤ እውነት ነጻ ያወጣል የሚባለው የሚሠራው ለዚህ ነው፤ ሽምግልና በእውነት ላይ እንዲቆም የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው።

እርቅ ማለት እግዚአብሔር ነው፤ እርቅ የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው፤ እግዚአብሔር ማለት እርቅ ነው፤ በክርስትና የመስቀል ትክክለኛ ትርጉሙ እርቅ ነው፤ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መከራውን የተቀበለውና የተሰቀለው ለእርቅ ነው፤ አዳም በበደለ መድኃኔዓለም ካሠ የሚባለው ለዚህ ነው፤  እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ ነው ትንሽና ትልቅ፣ አለቃና ምንዝር፣ ሴትና ወንድ፣ ሽማግሌና ወጣት፣ ንጉሠ ነገሥትና ሎሌ የማይለየው፤ ለዚህ ነው በጦርነት ድልን የተጎናፀፈውና የተሸነፈው በእርቅ ደማቸውን የሚያጥቡት ፣ ለዚህ ነው ማራኪና ምርኮኛ ቂማቸውን በእርቅ የሚፍቁት ፣ ለዚህ ነው አሳሪና ታሳሪ ከሁለቱም ለበለጠ ፋይዳ በእርቅ የሚስተካከሉት፤ እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ አይናቅም ፤ እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ አይደበቅም፤ እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ ያስከብራል እንጂ አያሳፍርም፤ እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ ጽድቅ ነው፤ እውነት ነው፤ ክቡር ነው፤ እርቅ ክቡር በመሆኑም ያስከብራል። በዳይና ተበዳይ መሀል እርቅ ሲወርድ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኝት ነው ፡፡

ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ኩራት የሆኑ ትልልቅ ሰዎች የሚገኙት እርቅ የእግዚአብሔር መሆኑን በመገንዘባቸው ነው፤ አሳሪ ደክላርክና ታሳሪ ኔልሰን ማንዴላ ከሁለቱም በላይ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ፣ ደቡብ አፍሪካ የሚባል አገር፣ ሰላምና ብልጽግና፣ እግዚአብሔር ከነሱ በላይ እንዳሉ በማወቃቸው ለእርቅ ልባቸውን በመክፈታቸው ነው፤ ታሳሪውን ኔልሰን ማንዴላን በደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ጭምር ለትልቅነት ያበቃው አሳሪው ደክላርክ ነው፤ የደክላርክ ትልቅነት በእምነትና በተስፋ የጉልበት አስተሳሰቡን ለውጦ ልቡን ለእርቅ በመክፈቱና በተጨባጭም የእርቁን መንፈስ ለመግለጽ ማንዴላን ከእስር አውጥቶ እኩያው ማድረጉ ነው፤ በእርቅ ትልቅ ሰው ትልቅ ሰውን ወለደ፤ ጉልህ መንፈሳዊ ወኔን አሳየ።››

ሁላችንም የምናሸንፈው ፍቅር ሲያሸንፍ ነው። ፍቅር ሲያሸንፍ አባት ያሸንፋል! ፍቅር ሲያሸንፍ እናት ታሸንፋለች! ፍቅር ሲያሸንፍ ልጆች ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ አባቶች ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ ህዝበ ክርስቲያን ሁሉ ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ የሰው ልጆች ሁሉ ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ ለሁላችን ሰላም አንድነትና ይሆናል!


በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየነፈሰ ያለው የሰላም ፤ የፍቅር እና የመደመር ንፋስ ቀድሞ አንድ የነበሩ እና የያለፈው ጊዜ ቁማርተኞች ሁለት የሆኑ ሀገረ ኤርትራ እና ኢትዮጵያን ጎብኝቶ በጦርነት ምክንያት የተለያዩ ቤተሰቦችን  ፤ እናትና ልጅን ፤ እህትና ወንድምን ፤ ለዘመናት የተራራቁ ጓደኛሞችን አገናኝቷል፡፡ ይህ ንፋስ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በሁለት ሲኖዶስ ስትመራ ለነበረችው ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ላይ በመንፈስ ብጹአን አባቶች ለእርቀ ሰላም ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አሜሪካ ማቅናታቸው ታውቋል ፤ ሕዝብ ክርስቲያንም መልካም ዜና የሚሰማበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋችን ጽኑ ነው ፡፡

No comments:

Post a Comment