Friday, August 18, 2017

የዘመናችን ፈተና… … … .‹‹አብያተ ክርስቲያናትን ማፍረስና ማቃጠል …..››(አንድ አድርገን ነሐሴ 12 2009 ዓ.ም)፡- ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታ ውስጥ ብቻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ላይ በየጊዜው የሚደርሱት ጫናዎች ከቀን ቀን ፤ ከዓመት ዓመት እየጨመሩ ይገኛሉ ፡፡ በአጽራረ ቤተክርስቲያን አማካኝነት በውድቅት ሌሊት ከሚፈርሱ እና ከሚቃጠሉ አብያተክርስቲያናት እንስቶ ፤ መንግሥታዊ ሥልጣንን ፤ ሕዝብን ለማስተዳደር የተሰጣቸውን ጊዜያዊ አስተዳደራዊ ጡንቻን በመጠቀም በመዲናዋ አዲስ አበባ አንስቶ እስከ ሀገሪቱ ጠረፍ ድረስ በየጊዜው የሚፈርሱት እና የሚነሱት አብያተ ክርስቲያናት እየጨመሩ መምጣታቸው አሁን ላይ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል ፡፡ ለመፍረስ ቀን የተቆረጠላቸው ፤ የፈረሱ ፤ የተቃጠሉ ፤ ዶዘር የታረሱ አብያተ ክርስያናት የምዕመኑን ፤ የቤተክርስቲያኒቱን ሕልውና አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛሉ፡፡ እስኪ ይህን እውነታ በመረጃ ለማጠናከር ከዚህ በፊት ከ2002 ዓ.ም በኋላ በአንድም በሌላም መንገድ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰውንና እየደረሰ የሚገኝውን  አደጋ ለመመልከት እንሞክር፡፡

1.    በስልጤ የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስልጤና ሀድያ ሀገረ ስብከት በስልጤ የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ በወረዳው የፓሊስ አባላት እንዲፈርስ ተደርጓል ፡፡ በወቅቱ ይህን ቤተክርስቲያን ለማፍረስ በስልጢ ከተማ 1ኛ እና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያኑ እንዲፈርስ የሚደረገውን ተግባር እንዲፈጽሙ መቀስቀሳቸውንና ተማሪዎቹ ተሰባስበው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመሔድ ነዳጅ ጨምረው ቤተ ክርስቲያኑን ሙሉ በሙሉ ማቃጠላቸውን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ይኸ ቤተክርስቲያን በተሻለ ሁኔታ ተሰርቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
2.    በዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚፈርሱ 18 አብያተ ክርስቲያናትመንግሥት የስኳር ልማት ለማልማት በማሰብ ቦታውን ለሸንኮራ ተክል ለማዘጋጀት ሶስት አብያተ ክርስትያናት  እንደሚፈርሱ  ግንቦት  2004 .  ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ገዳምና በወልቃይት  የስኳር ልማት ፕሮጀክት አስመልክቶ አምስት  አባላት ያሉት  የልኡካን ቡድን በመላክ የደረሰበት  ሪፖርት  ላይ ሰፍሮ ይገኛል ፡፡  በገዳሙ የሚተዳደሩት ማይ ሐርገፅ ጊዮርጊስ ፤ ዕጣኖ ማርያም እና ማይጋባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያናትን ይፈርሳሉ ብሎናል፡፡ ከእነዚህ አብያተክርስቲያናት በተጨማሪ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ከሚነሱት የሰባት ቀበሌ ነዋሪ ከሆኑት ወደ ሰባት ሺህ ከሚጠጉ አባወራዎች  ሲነሱ የሚፈርሱትን 15 አብያተክርስቲያናት ይኖራሉ ተብሎ ታስቧል፡፡
3.   የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን (የኢንደስትሪ ዞን ነው በማለት ፈረሰ )
በሚያዚያ ወር  2005 ዓ.ም አዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የሚገኝው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በኢንደስትሪ ዞን ላይ የተሰራ ነው በሚል የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት መፍረሱ ይታወቃል፡፡  ይህ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ሲፈርስ ምዕመኑ አብይ ጾምን ባጋመሰበት ሳምንት ነበር ፤ ከቤተክርስቲያኑ ምንም ነገር የማውጣት ፍቃድ ሳይሰጥ የወረዳው የበላይ ሃላፊዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ በጻፉ 24 ሰዓት ሳይሞላው ማፍረሳው የሚታወስ ነው ፡፤ ይህ ቤተክርስቲያን በቦታው ከሦስት ዓመት በላይ እንዳገለገለ የሚታወቅ ነው፡፡ በወቅቱ የቤተክርስቲያኑ ግምዣ ቤት ኃላፊ የነበሩት ‹‹ ምንም አይነት ንብረት እንድናወጣ ሣይደረግ መፍረሱ ከግለሰብ መብት ባነሰ ሁኔታ አምልኮተ እግዚአብሔር  የሚከናወንበት ቦታ በሕገ ወጥነት የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ ማፍረሱ   ትልቅ ወንጀል ነው›› ብለው ነበር ፡፡

4.   የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን
በአዲስ አበባ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12፣ አባዶ ቁጥር 1 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተሠራችው፣ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፥ ድፍረት በተመላበት ኃይልና ሥልጣን፣ በወረዳው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት የፈረሰች በ2009 ዓ.ም በመጋቢት ወር ነበር፡፡ የቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የመሬት ጉዳዩ በሕግ ተይዞ ሳለ  በሚያሳዝን ኹኔታ፣ ታቦተ ሕጉ ያለበት መቃኞ ቤተ ክርስቲያን በመፍረሱ፥ ንዋያተ ቅድሳቱ ተመዝብሯል፤ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንም የድፍረት ሥራ ተፈጽሞባቸው አልፏል፡፡ በወቅቱ ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነና የቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰት የክፍለ ከተማው አፍራሽ ግብረ ኃሎች  በአደባባይ ሲፈጽሙ ታይቷል፡፡
5.   የጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን
በየካ አባዶ፣ ቁጥር 13  የሚገኝው ፣ የጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን  በ2009 ዓ.ም መፍረስ ካጋጠማቸው ቤተክርስቲያን አንዱ ነበር ፤ መጋቢት 25 ቀን  በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ግብረ ኃይል በወቅቱ ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ተደርጓል ፡፡ በወቅቱ ጽላቱ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ዋሻ ሲዛወር  ንዋያተ ቅድሳቱ ግን እዚያው ሜዳ ላይ ተቀምጠነው ይገኙ  ነበር ፡፡ የጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ፤ በአካባቢው በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ የፈረሰ ከቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን መፍረስ ከቀናት በኋላ ነበር ፡፡በጊዜው የየካ አባዶ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን  እንዲፈርስ በሥር ፍርድ ቤት በወቅቱ ቢወሰንበትም፣ የይግባኝ ቅሬታ በመቅረቡ፣ ውሳኔው ከመፈጸም ታግዶ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ይገኝ ነበር ፡፡
6.   የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን
በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኘው ለገጣፎ በሚባለው ቦታ ላይ፣ ሰኔ 30 ቀን 2009 .. የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በ‹‹ሕገ ወጥ ግንባታ ስም›› እንዲፈርስ የተደረገ ሲሆን ፤ ይህ ጉዳይ በሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አማካኝነት ፓትርያርኩ እንዲያውቁት ቢደረግም ፤ ለሚመለከተው አካል ግልባጭ ደብዳቤዎች ቢላኩም መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
የዚህ ቤተክርስቲያን መፍረስ ጉዳይ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲዎችም በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንዲያወጡ አድርጓል፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን ሲፈርስ ጽላቱ ክህነት በሌላቸው ሰዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲገባ ሲደረግ ንዋየ ቅድሳቱ በኦሕዴድ ጽ/ቤት መጋዘን ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡
የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትና  ገዳማት
ከላይ በመንግሥት አመራሮች ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተሰቶባቸው በቀንና በውድቅት ሌሊት ከፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን በሲራሮ ወረዳ የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም
1.      የሎቄ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን
2.    የብሊቶ ቅደስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
3.    የዓለም ጤና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በእሳት ቃጠሎ አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡
4.    በሽሜ ማርያም  ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ ፡- ከዓመት በፊት በደቡብ  ጎንደር ሀገረ ስብከት  በስማዳ ወረዳ  ሽሜ አዝማቾ  ቀበሌ  በጥንታዊቷ በሽሜ ማርያም  ቤተ ክርስቲያን ፤ በቃጠሎው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ  ሙሉ በሙሉ  በእሳት  በመውደሙ ከአገልግሎት ውጭ   ሆኗል ፤  ቃጠሎው  በሌሊት  በመሆኑ እሳቱን  ለማጥፋት  በወቅቱ አልተቻለም ነበር ፡፡ በቤተ ክርስተያኑ ውስጥ የሚገኙት ንዋያተ ቅድሳት ( መጻሕፍት፤መስቀሎችና አልባሳትሙሉ በሙሉ  አመድ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
5.    የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን  ቃጠሎ ፡- በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት፣ በዲታ ወረዳ፣ ጋና ደሬ ቀበሌ፣ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሌሊቱ በስድስት ሰዓት አካባቢ በተነሳው እሳት ቃጠሎ ምክንያት ቤተክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ይታወሳል ፤ በወቅቱ  ምንም ዓይነት ነዋያተ ቅድሳት ማትረፍ አልተቻለም ነበር፡፡
6.    በሰበታ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን በእሳት ቃጠሎ ፡- ከዓመት በፊት ይህ ቤተክርስያን በእሳት ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስበት በውስጡ የሚገኙት  ጽላቶቹ ግን በተአምር አንዳችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ተገኝተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ለወደፊት ገዳም እንዲሆን እቅድ ነበር ፡፡
7.    የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቃጠሎ  ፡- በደቡብ ክልል በከንባታ፣ሀዲያ፣ጉራጌና ስልጤ ሀገረ ስብከት፤ሆሳዕና ከተማ የሚገኘው ታሪካዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የካቲት 21 2007 ዓ.ም የመቃጠል አደጋ አጋጥሞታል ፡፡ ፡፡ በደሰው ቃጠሎ የቤተክርስቲያኗ ህንፃ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፤ ፡፡ በደረሰው የቃጠሎው አደጋ በቤተክርስቲያኗ የነበሩ ታሪካዊ ቅዱሳት መፃህፍትን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች በወቅቱ ወድመዋል ፤ የአካባቢው ህዝብ እሳቱን ለማጥፋት ባደረገው ርብርብ ታቦታቱን ከአደጋው ማትረፍ ችሎ ነበር፡፡1901 . እንደተተከለች የሚነገርላት የ106 ዓመት ባለቤት የሆነችው   የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ለማያምኑትም እና መናፍቅና አህዛብ ለሆኑትም የአካባቢው ሕዝቦች ጭምር ምሥክር እንደሆነች ይነገርላታል፡፡
  1. የመሐል ዘጌ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ፡- በጣና ሐይቅ ዙሪያ ከሚገኙት የዘጌ ገዳማት መካከል አንዱ የሆነው የመሐል ዘጌ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2002 .  ምክንያት ባልታወቀ እሳት ሙሉ በሙሉ ወድሟል::
  2. በአዲስ አበባ ወይራ ሰፈር አካባቢ የምትገኝው የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን በ2004 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ መቃኞ ቤቱ ወደ አመድነት የተቀየረው ቤተክርስቲያን
  3. ታላቁ የጨጎዴ ሐና የቅኔ ምስክር ጉባኤ ቤት ቃጠሎ ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቋሪት ወረዳ ቤተ ክህነት ልዩ ስሙ ፈንገጣ በሚባል ቀበሌ በጨጎዴ ሐናየተቋቋመው፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ሲያፈራ የኖረውና እስከ አሁን ድረስም ሊቃውንትን የመተካት ተልእኮውን በመወጣት ላይ ሲገኝ የነበረው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው የቅኔ ምስክር ጉባኤ ቤት ጥር 7 ቀን 2009 ዓ.ም ረፋድ ላይ በቃጠሎ መውደሙ ይታወቃል፡፡      
  4. የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም አካባቢ ቃጠሎ፡-  የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቡነ ሂሩተ አምላክ የተመሠረተና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ ጥንታዊ ፣ ታሪካዊና የብዙ ቅርሶች መገኛ ከሆኑት ገዳማት መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ገዳም በርካታ ንዋያተ ቅድሳት፣ መጻሕፍት ፣ የነገሥታት ዘውዶች፤ አጽሞች እና ሉሎችም ቅርሶች መገኛ ነው፡፡ እዚህ ገዳም ላይ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም ረፋድ ላይ የእሳት ቃጠሎ ደርሶ ነበር ፤ እሳቱ ከአንድ ሄክታር በላይ ቦታ መብላቱ ይታወሳል፡፡ እሳቱ የጠፋው ከቤተክርስቲያኑ 50 ሜትር ሲቀረው ነበር፡፡
  5. የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳም ደን የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ባልታወቀ ምክንያት በተነሣ እሳት ቃጠሎ እንደደረሰበት ይታወቃል ፤ ዳግም ይህ ቦታ ከሁለት ዓመት በፊት ሌላ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እሳት ማስተናገዱ አይረሳም፡፡
  6. ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ የሚነሳው ተደጋጋሚ የሰደድ እሳት አደጋ ፡-  በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ቀበሌ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ በሚገኘውና የመንግሥት ይዞታ በሆነው ደን ውስጥ ባለፉት 4 ዓመታት ሁለት ጊዜ ያህል ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ የእሳት አደጋ እንዳጋጠመው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ይህ አንድነት ገዳም በ1168 ዓ.ም. ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንደመሰረቱት ይታመናል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች በጥቂቱ ያህል ለማሳየት ያህል የተጠቀምንባቸው ናቸው ፤
                             3 comments:

 1. What a very Irritating and illegal activity!!!!!

  ReplyDelete
 2. EGZIABHERE wagachhun yekefelachewal, How dare they are to touch GOD's Church????

  ReplyDelete