Tuesday, July 25, 2017

አንድን መናፍቅ ለማውገዝ ስንት አመት ይበቃል ?


(አንድ አድርገን ሐምሌ 17 2009 ዓ.ም)፡- ባሳለፍናቸው ሁ

ለት አስርት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በፕሮቴስታንት ጥላ ሥር ለማድረግ በተሐድሶ ምግባር በርካቶች ከውስጥም ሆነ ከውጭ ፤ በቤተክርስቲያኒቱ በተለያዩ የአገልግሎት ማዕረጋት  ያሉ ሰዎችን መከታ በማድረግ መሰረቷን ለመናድ ፤ ቅጥሯን ለማፍረስ ፤ አስተምህሮዋን ለመበረዝ ፤ ቀኖናዋንና ዶግማዋን ለማስረሳት ፤ ካሕናቷን ለማዋረድ ፤ ስሟን የማጠልሸት ፤ ምዕመኗን ከእቅፏ የማስወጣት ሥራ ሲሰራ ነበር ፡፡ ምዕመኑን ከቤተክርስቲያን ቅጥር በማውጣት በአዳራሽ እየሰበሰቡ የ‹‹ወንጌል አገልግሎት›› ሲሰጡም ነበር ፤ በርካታ ሚሊየን ብሮች ከየአዳራሾች በመሰብሰብ የግለሰቦችን ሕይወት በመጠኑም ሲቀይር አይተናል ፤ ብዙዎች አዘቅት ሲወርዱ ጥቂቶች በሀብት ማማ ላይ ሲንሳፈፉም ተመልክተናል ፡፡


ለሃያ ዓመት የተሐድሶ አቀንቃኝ ሰዎችን ሥራቸውን ከነምግባራቸው በምስል ፤ በቪዲዮ ፤ በጽሑፍ ብዙ ጊዜ ለምዕመኑ እንዲደርስ የማድግ ሥራ በማኅበራት ፤ በሰንበት ተማሪዎችና በምዕመናን አማካኝነት ሲወጣ ቆይቷል ፤ ነገር ግን የተሀድሶ ፕሮቴስታንት አቀንቃኞችን ሥራቸው ሚዛን ላይ ተቀምጦ ሲወገዙ አይታይም ፤ በዚህ ዓመት አቶ አሰግድ ሳሕሉ የተወገዘበት አካሔይ ይበል የሚያስብል ቢሆንም በርካቶች ከአሰግድ ጋር አሁንም በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው በኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ እየሄዱ ሥራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ግን የተሀድሶ ፕሮቴስታንት አካሄድን መርምራ ምዕመኗን ከእነዚህ ተኩላዎች የምትጠብቅ ሆና አትታይም ፤ እነዚህ ሰዎችን ብዙ ጊዜ በአባቶች ተመክረዋል ተዘክረዋል ከእኩይ ተግባራቸው ግን ሲመለሱ አይታይም ፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ስራቸው ተመዝኖ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ውሳኔ ካልተሰጣቸው ይህ አምባጓሮ ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የተሐድሶያውያን አባት አርዮስ እጅግ የተማረ ፣ አይኑ ከማንበብ የማይቦዝኑ ፣ የብዙ እውቀቶች ባለቤት የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ ከእርሱ አስቀድሞ ነበሩ  አባቶችን (ሐዋርያነ አበው)ቅዱሳት መጻሕፍት በጥልቀት የመረመረ ነበር  ፤ የአሁኖቹ ልጆቹ ከመንፈሳዊ ሕይወት የተራቆተ ፣ በዚህ ጉባዔ ከእገሌ ሊቅ ተምሬአለሁ ብለው አንገታቸውን ቀና አድርገው  መናገር ማይችሉ(ሊቅ ስል አስተምረው የላኩት ፓስተሮች አይመለከትም) ፣ ከገቡበት መንፈሳዊ ኮሌጅ መማር ከነበረባቸውን ትምህር በአግባቡ ያልተማሩ ፤ እንደ ቁራ እንደወጡ የቀሩ ሰዎች ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስንም እንደሚገባ ባይረዱት እንኳ በጭራሽ በትውፊት  ያገኘናቸውን የሌሎች ቅዱሳን አባቶች ትምህርትና ገድል ለማንበብ የማይፈልጉ አንብበውም የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ እንዴት አንድ ሰባኪ ወንጌል የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ፣ የእነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ፣ ……ትምህርት ሳይጠቅስ እንዴት ሊያስተምር ይችላል? 

‹‹ገንዘብንም  በመመኘት  በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት  ጀምሮ  አይዘገይም  ጥፋታቸውም አያንቀላፋም። ›› ተብሏል  

እንግዲህ  እውነተኛ  የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህንን አስተውሉ በቤተ ክህነትም በውጭም አገልጋይ ነን ፤ ዘማሪ ነን ሲሉ የነበሩና አሁን የምናየውንና የምንሰማውን የተለዩ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሁሉ ለእውነተኛ የጽድቅ አገልግሎት ሳይሆን ‹‹ገንዘብን በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል›› እንደተባለ ስለገንዘብ የረቡብን ሰዎች ናቸው:: የምዕመናንን ገንዘብ የቤተክርስቲያንን ሃብት እንደ ልባቸው ለመዝረፍ ማንኛውንም ክፉ ነገር ከማድረግ አይመለሱምና ጸንተን ቤተክርስቲያናችንን መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታችን እንወጣ፡፡

እንግዲህ የዘመኑን ተሃድሶወች (አርዮሳውያን) እውነተኛ የተዋህዶ ዶግማና ቀኖናዋን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የሚፋጠኑትን (ቅዱስ ቄርሎስ ልጆች) በሁለት አጽናፍ ቆመዋል፡፡ምናልባት የአርዮስን ያክል ፍፁም ክህደትን የካደ ተሃድሶ ላይኖር እንደሚችል ሁላ የቅዱስ ቄርሎስን ያክል ቅድስናና ጥበብ ያለው የተዋህዶ አማኝ ላይኖር እንደሚችል እሙን ነው፡፡ አርዮስ ተፀፅቻለሁ እያለ ይቅር ሲባል ወደ ቀደመ ምንፍቅናው እንደሚገባ ሁሉ ተሃድሶወችም በእምባ ሆነው ይቅርታ ይጠይቁና መልሰው ቅዱሱንና ማደሪያውን ያሳዝናሉ የአርዮስ ትምህርት የረከሰና የተጠላ የማይጠቅምም እንደሆነ ሁሉ የተሃድሶወችም ትምህርት መልካምን ፍሬ የማያፈራ የማይጠቅም ዘር ነው፡፡ የአርዮስ እውቀት ከዲያቢሎስ እንደሆነ ጥበቡም ለክርስቲያኖች የማይሆን እንደሆነ ሁሉ የተሃድሶወችም ጥበብ ለመንግስተ ሰማያት የማያበቃ ባዶ ጥበብ ከንቱ ጩኅት ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ቄርሎስና አርዮስ ህብረት የላቸውምና ይቅር ተባብላችሁ በአንድነት ስሩ አይባልም !! እነዚህን ሰዎች በቤታችን ባቆየን መጠን የከበረ ማእድን የተከማቸበትን ቤት ለሌባ አሳልፈን እየሰጠን መሆኑን እንረዳ ፡፡

በአርዮስ ጥበብ የሚመላለሱትን ተሃድሶወች እሹሩሩ ማለት ትተን አስቀድመው የሃይማኖትን ትምህርት ይማሩ ዘንድ ይለዩ ቅዳሴን ካልቀደስኩ ንኡስ ክርስቲያናትን ካላጠመኩ በሰገነቱ ወጥቼ ምእመናንን ካላስተማርኩ ሲሉም ሳይማሩ ማስተማር አይገባም ሳያምኑ ማሳመን አይሆንም ያለስርአት ስርአት ማስያዝ አይቻልም በማለት በቅዱስ ቄርሎስ ጥበብ ሃይማኖታችንን እንጠብቅ ዘንድ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡

አባታችን አቡነ ገብርኤል የሲዳመ ፤ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቶ በጋሻው ደሳለኝ በሀገረ ስብከታቸው ሥር በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ማንኛውንም የወንጌል አገልግሎት እንዳይሰጥ ሐምሌ 14 2009 ዓ.ም በወጣ ደብዳቤ ማገዳቸውን አሳውቀዋል ፤ ጨምረውም ይህ ሰው ከሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በየትኛውም አዳራሽ በቤተክርስቲያናችን ስም እንዳያስተምር የታገደ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ይህ ይበል ለሚያሰኝ እገዳ አባታችን አቡነ ገብርኤልን ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በአቶ በጋሻው ላይ የሚቀርቡ መረጃዎችን መርምሮ ከጓደኛው ከአሰግድ ሳሕሉ ጋር እንደሚቀላቅላው ተስፋችን የጸና ነው፡፡

አንድን መናፍቅ ለማውገዝ ስንት አመት ይበቃል ?



No comments:

Post a Comment