Friday, April 15, 2016

የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከተሐድሶ እንዴት ተላቀቀች?


በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ጊዜው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ለአንዳች ተልዕኮ የተነሡ ሞራቪያውያን (የቼክ ሪፐብሊክ ዜጎች የሆኑ) ፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ወደ ግብጽ ገቡ፡፡ ጌታችን ከእናቱ ጋር ወደ ተሰደደባት በፈጣን ደመና ተጭኖ እየበረረ ወደ ደረሰባት ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ወዳስተማረባት ሐዋርያዊት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንጌታን እንሰብካለንብለው ዘመቱ፡፡ የእነዚህ ሚስዮናውያን እንቅስቃሴም በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ሲነድና ሲበርድ ለቆየው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሴራ መነሻ ነበር፡፡

ሚስዮናውያኑ በሚያምኑበት እምነት ግብጻውያንን ለመማረክናነፍሳትን ለማዳንበሚል የተልዕኮ ስሜት መምጣታቸው በቅንነት ሊታይ የሚችል ቢሆንም ያተኮሩት ግን ከግብጽ ሕዝብ ዘጠና በመቶ በሚሆነው በወልደ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በማያምነው ሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ ሳይሆን በሐዋርያው ማርቆስ ወንጌል በተሰበከላትና ከግብፅ ሕዝብ ዐሥር በመቶ ብቻ በምትሸፍነው ቤተ ክርስቲያን ላይ ነበር፡፡ ወንጌል የሚያውቀውን ወንጌል ለማስተማር (Evangalizing the evangalised) የተነሡት የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ላይ የነበራቸው ከልክ ያለፈ ንቀት ደግሞ መገለጫቸው ነበር፡፡ ስለ ተልዕኮአቸው በሚጽፏቸው መጻሕፍት ላይ ቤተ ክርስቲያኗንና ምእመናኗን የሚገልጹበት ቋንቋ በንቀት የተሞላ ነበር፡፡ ‹‹ወንጌል ያልተሰበከላቸው›› ‹‹ልባቸው እንደ ድንጋይ የጠጠረ›› ‹‹ክርስቶስን በማርያም ልጅነቱ ያውቁታል እንጂ በጸጋው ስለመዳን የማያውቁ ከመሐመድ ተከታዮች በምንም የማይሻሉ ናቸው›› ‹‹በፒራሚድ ውስጥ በመሚ ደርቀው ከተቀበሩት የፈርኦኖች ሬሳ የማይለዩ›› የሚሉ ንግግሮች በየጽፎቻቸው ይነበቡም ነበር፡፡

በይፋ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተሐድሶ ዘመቻ የተጀመረው ግን 1820 ... ቸርች ሚሽን ሶሳይቲ (ሲኤምኤስ) የሚባል የእንግሊዝ ፕሮቴስታንት ድርጅት ወደ ግብፅ ሲመጣ ነበር፡፡ አንግሊካኖቹ ሥራቸውን የጀመሩት በወቅቱ በእስክንድርያ መንበር ፓትርያርክ ከነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን (በግብፆቹ አጠራር ፖፕ ቡትሮስን) በማነጋገር ነበር፡፡ በሀገሪቱ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ምእመናን የሚጠብቁት ፓትርያርኩም የእንግሊዞቹን ወደ ማርቆስ መንበር መምጣት ከጀርባው ያለውን ሴራ አልተመለከቱም ነበር፡፡ በመሆኑም ‹‹የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ማንኛውንም ድጋፍ እንቀበላለን›› የሚል ይሁንታን አሰሙ፡፡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅም ሲባል መጽሐፍ ቅዱስን ከኮፕቲክ ቋንቋ ወደ ዐረቢኛ በሚስዮናውያኑ መሪነት እንዲተረጎምና እንዲታተምም ተስማሙ፡፡

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፯ኛ ወዳጅነት የተሞላበት አቀባበል ያስደሰታቸው የሲኤምኤስ ሚስዮናውያን አስቀድመው ካሰቡት በላይ መሥራት የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ተረድተው ስልታዊ ዕቅዳቸውን መንደፍ ጀመሩ፡፡ በዕድሜ የበሰሉትን ኦርቶዶክሳውያን ወደ ፕሮቴስታንት መለወጥ እጅግ አስቸጋሪ ሥራ መሆኑን ከልምዳቸው ተምረዋልና በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉ ሕጻናትና ወጣቶች ላይ ለመሥራትም ከድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡

ለዚህ ዓላማ መተግበሪያ የተመረጠው ስልትም ትምህርት ቤትን ማቋቋም ነበር፡፡ ይህንን ሃሳብም ፓትርያርኩ ተቀብለውት ‹‹ለነገዋ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት የሚሆኑ ወጣቶችን የሚያሰለጥን ትምህርት ቤት በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሥር እንዲቋቋምልን እንፈልጋለን›› የሚል ደብዳቤን ለአንግሊካኑ ሊቀጳጳስ ጽፈው ላኩ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ ልጆቼን አሰልጥኑልኝ ብላ ለመናፍቃን የምትሠጥበት ይህ ትምህርት ቤት ከአመሠራረቱ ጀምሮ በሚስዮናውያኑ የተጠናና የታሰበበት ነበር፡፡ አጀማመሩም ሁለት ዋነኛ ዓላማዎች በማንገብ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ዓላማ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚገቡት ሕጻናትና ታዳጊ ዲያቆናት የፕሮቴስታንትን ትምህርት ተምረው የቅስና ማዕረግ ሲቀበሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነውን ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት እንዲያስተምሩ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የታሰበው ሌላ ዓላማ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ ፕሮቴስታንትነት ተለውጠው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጠቅልለው እንዲወጡና በግብጽ ውስጥ የፕሮቴስታንት ተቋም እንዲመሠርቱ ነበር፡፡

የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪ እንዲሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለመሉት ከዐሥራ ሁለት እስከ ዐሥራ አምስት የሚሆኑ ወጣት ዲያቆናት ነበሩ፡፡ እነዚህ ዲያቆናት በትምህርት ቤቱ አስተዳደር ልዩ ትኩረት የተደረገባቸው ሲሆን ከትምህርት ቤቱ ውጪ ካለው ማኅበረሰብ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲቋረጥም ትምህርት ቤቱ የአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሆን ተደረገ፡፡ ፋታ በማይሰጥ የትምህርት ፕሮግራም እንዲወጠሩ በማድረግም ዲያቆናቱ ከቅዳሴ ከጸሎትና ጉባኤ ርቀው ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸው ትስስር ቀስ በቀስ ተቋረጠ፡፡

በትምህርት ቤቱ ውስጥ በአንግሊካኖቹ የተዘጋጀው የፕሮቴስታንት ጸሎት በአረቢኛ ቋንቋ ይካሔድ ነበር፡፡ ዲያቆናቱም በዚህ ጸሎት ላይ በፍላጎትም በግዴታም ቀስ በቀስ መካፈል ጀመሩ፡፡ አንድሪው ዋትሰን የተባለው የትምህርት ቤቱ ሚስዮናዊ ስለ ሁኔታው ሲገልጽ
‹‹የሚያነቃቃው የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ብዙ ሰዎችን እንደሚማርክ አምናለሁ ... ወጣቶቹም (የእኛን አገልግሎት) ወንጌላዊ ካልሆነው ከሞተው ቋንቋቸው እና ከገዳይ የቅዳሴ ሥርዓታቸው ጋር ሲያነጻጽሩት በኅሊናቸው ላይ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ለውጥን ይፈጥርባቸዋል፡፡›› ብሏል፡፡

በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በዋናነት የሚሠጠው ትምህርት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን ተማሪዎቹ እንግሊዝኛን በሚገባ አውቀው የፕሮቴስታንት መጻሕፍትን ወደ አረቢኛ እንዲተረጉሙ ታቅዶ ነበር፡፡ ከእንግሊዝኛ ሌላ ሽፋን እንዲሆን በሚል ጥንታዊው የቅብጥ ቋንቋም ይሠጥ ነበር፡፡ ዋትሰን የቅብጥ ቋንቋን ለምን መሥጠት እንዳስፈለገ ሲገልጽም ‹‹የሚያሳዝነው ያንን የሞተ ቋንቋ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ አብሮ እንዲሠጥ መደረጉ ልናስቀረው የማንችለው ግዴታ ነበር፡፡›› ይላል፡፡

ከቋንቋ እና የሒሳብ ትምህርት ሌላ ትምህርት ቤቱ ትኩረት የሠጠው የዶግማ ትምህርት ሲሆን በግብፅ ቤተ ክርስቲያን የነገ ቀሳውስት ሊሆኑ የታሰቡት ዲያቆናት በዚህ የትምህርት ክፍል ፕሮቴስታንታዊውን የዶግማ ትምህርት እንደ ውኃ እንዲጋቱ ተደረጉ፡፡ በግብፅ እየተለመደ መጥቶ የነበረው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ግን በግብጽ ውስጥፓትርያርካዊ ሥርዓትንየማክበር ባሕል እንዲስፋፋ ተጽዕኖ ስለሚፈጥር በትምህርት ቤቱ ቦታ እንዳይኖረው ተደረገ፡፡

የዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት ተጽዕኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ጥላውን ማሳረፍ ቻለ፡፡ የትምህርት ቤቱን ስውር ዓላማ ያልተገነዘቡት አባቶችም ትምህርት ቤቱን እንደ ትልቅ የትምህርት ተቋም ተመልክተውት ነበር፡፡ የሚያሳዝነው በወቅቱ (1847) የኢስናህ ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የእኅታቸው ልጅ የሆነን ወጣት ዲያቆን አምጥተው ሌይድነር ለሚባል የአዳሪ ትምህርት ቤቱ አስተማሪይኼንን ልጅ አስተምርልኝብለው በአደራ አሳልፈው ሠጡት፡፡

ይህ ትምህርት ቤት ብዙ አልቆየም፡፡ የምንፈልገውን ያህል ውጤት አላገኘንበትም በሚል በራሳቸው በሚስዮናውያኑ ውሳኔ እንዲዘጋና የስልት ለውጥ እንዲደረግ ሆነ፡፡ ተቋሙ የቆየው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የረጨው የክህደት መርዝ ግን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤቱ የተማሩና በተዘዋዋሪ ተጽዕኖው ያረፈባቸው ካህናት ዲያቆናትና ምዕመናን በፕሮቴስታንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ኅሊናቸው ታውኮ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜ ጋር መዋሐድ አቅቷቸው ነበር፡፡ በየጊዜውም ለሚነሡ ውዝግቦችና ክርክሮች መነሻዎቹ ሲጣሩ ከዚያ ትምህርት ቤት የወጡ ሰዎች ነበሩ፡፡
ብዙ ግብፃውያን ምዕመናን የቅዱስ ማርቆስ መንበር ከሆነችው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ወጥተው ወደ ፕሮቴስታንት ሲኮበለሉ ከፊሎቹ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆነው ከሚስዮናውያኑ የተሠጣቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ መናፍቃኑ በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያሴሩት ሴራ ይህንን ያህል ርቀት ተጉዞ ባለማወቅ መንገድ የጠረጉለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ፯ኛ 1852 .. ሲያርፉ የመጀመሪያው ምዕራፍም አብሮ ተጠናቀቀ፡፡

1854 .. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፬ኛ ፓትርያርክ ሆነው በመንበረ ማርቆስ ሲቀመጡ ሌላው የፕሮቴስታንት ድርጅት ወደ ግብፅ መጣ፡፡ የአሜሪካ ፕሪቤተርያን ሚስዮን (American United Presbyterian Mission) የተሰኘው የዚህ ድርጅት ሰዎች በዚያን ዘመን ስለነበራቸው የግብፅ ተልዕኮ በጻፉበት መጽሐፍ ላይበፓትርያርኩ መሾምም ውስጥ የእኛ እጅ አለበትብለው እስከ መጻፍ ደርሰዋል፡፡ ይህ ድርጅት ከቀደመው የሲኤምኤስ ድርጅት የሚለየው ቤተ ክርስቲያኒቱን እንቀይራለን እናድሳለን ከሚል ስትራቴጂ ይልቅ ሕዝቡን ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የማስወጣትን ዓላማ ያነገበ ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ 1860 .. ድርጅቱ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘመቻውን ሲጀምር አይቢስ የተባለችን ጀልባ በመግዛት ሲሆን በዚህች ጀልባ እስከ ላዕላይ ግብፅ የገጠር መንደሮች ድረስ በአባይ ወንዝ ላይ በመጓዝ ተልዕኳቸውን ይፈጽሙና ቅኝት ያደርጉ ነበር፡፡

የዚህ ድርጅት ዋነኛ ሥራ አስፈጻሚ የነበረው ጋሊያን ላንሲንግ የፕሮቴስታንት ሚስዮናዊ ሲሆን ዋነኛ ትኩረታቸውን ያደረጉት በገጠሪቱ የግብፅ ክፍል ላይ ነበር፡፡ ‹‹በእስክንድርያ ያሉትን የተማሩና በመንሥት ሥራ ላይ የተሠማሩትን ኦርቶዶክሶች ማሳመንና መለወጥ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ድሆቹንና ያልተማሩትን የላዕላይ ግብፅ ሰዎች ማስተማር ይቀልለኛል›› ያለው ላንሲንግ ጀልባውን በአባይ ወንዝ ላይ እየቀዘፈ ከአጋሮቹ ጋር ወደ ላዕላይ ግብጽ ዘመተ፡፡

የላዕላይ ግብፅ ነዋሪዎች ያልተማሩና ድሆች ቢሆኑም ሃይማኖታቸውን በመለወጥ ጉዳይ ግን ሚስዮናዊው እንዳሰበው ያህል ቀላል አልነበሩም፡፡ ከዓይነ ሥውራን የቤተ ክርስቲያን ፊደል አስተማሪዎች (Blind Areefs) እግር ሥር ቁጭ ብለው የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያንን ጸሎታት በልጅነታቸው ከመማራቸው በስተቀር ስለ ሃይማኖታቸው የጠለቀ ዕውቀት ባይኖራቸውም ለቤተ ክርስቲያናቸው ግን አንገታቸውን የሚሠጡና ለአባቶችም ትእዛዝ ተገዢዎች ነበሩ፡፡ ላንሲንግ የገጠር ነዋሪዎችን ሲገልጻቸውም ‹‹ቄሱ ሲጾሙ እጾማለሁ ቄሱ ሲፈስኩ እፈስካለሁ የሚሉ ቂሎች›› እያለ ነበር፡፡

እርሱ ከቂልነት ቆጥሮ ይዘብትበት እንጂ የዋሃኑ የገጠር ነዋሪዎች ግን በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ካህናትን ማክበርና አሠረ ፍኖታቸውን መከተል ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ የተረዱ እደሆኑ የሚያሳይ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቸችሁን በኃይል አትግዙ፡፡ የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን ክብር ትቀበላላችሁ›› እንዳለውም ካህናቱ ለመንጋው ምሳሌ መሆን የቻሉና የእረኞች አለቃ መድኃኔዓለም ክርስቶስ መጥቶ የክብር አክሊል እንደሚሠጣቸው የሚጠብቁ ታማኞች መሆናቸውንም ያሳያል፡፡ (፩ጴጥ. ፭፥፫)
አስዩት ወደምትባለው የላዕላይ ግብጽ ከተማ እንደደረሰ ሚስዮናዊው ላንሲንግ ሊቀ ጳጳሱን በከተማዋ ያለውን የቀለም ትምህርት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳምኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር በሚገኘው ትምህርት ቤት ውስጥ ለአሜሪካ ሚሽን አስተማሪ አንድ ክፍል እንዲሠጠው ለማድረግ ችሎ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑ በከተማዋ የነበሩት ዓይነ ሥውራን ፊደል አስተማሪዎች ቅር ተሰኝተው ነበር፡፡ ዳዊት የሚያስደግሙና ጸሎት የሚያስተምሩት እነዚህ አባቶች በሚስዮናዊው ዓይን እጅግ የተናቁ ነበሩ፡፡ የሚያስተምሩትንም ጸሎቶች በመጽሐፉ ሲገልጻቸውየሞቱ የግብፅ ጸሎቶችእያለ በተለመደው የሚስዮናውያኑ ንቀት የተሞላ ንግግር ነበር፡፡

የአስዩቱን ሊቀ ጳጳስም የሚገልጻቸውየምንኩስና ኑሮቸውን በማክረር የሚታወቁበማለት ነበር፡፡
በገጠር ውስጥ ያሉት ኦርቶዶክሳዊያንን በቀላሉ እቀይራለሁ ብሎ ያሰበው ሚስዮናዊ ገጠሬዎቹ ከተማረው ከተሜ በላይ ፈታኝ ሆኑበት፡፡
በሃይማኖታቸው የማይበገሩ በጾም በጸሎትና አስቀድሶ በመቁረብ የበለጠ ጥብቅ ሆነው አገኛቸው፡፡ ተከራክሮ ለማሳመንም ያልተማሩት የበለጠ አስቸጋሪ ሆኑ፡፡ ከአንድ ልብስ ሰፊ ጋር ስላደረገው ክርክር እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡
‹‹ምስኪኑ ኬዴስና ጓደኞቹ ቁርስ አብረውን አልተመገቡም ነበር፡፡ ነገሩን ሳጣራ ለካ እየጾሙ ነው፡፡ ጾማቸው ብዙዎቹ የምሥራቅ ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት የእንስሳት ተዋጽኦን በአትክልት በመተካት ብቻ አይደለም፡፡ የግብጾች ጾምስ በጣም የከፋ ነው፡፡ ለረዥም ሰዓት ኬዴስና ጓደኞቹን አነጋገርኳቸው፡፡ጌታ (የጾምን) ቀንበር አልጫነባችሁምብዬ ላሳምናቸው ሞከርኩ፡፡ ... እነርሱ ግን ሥጋቸውን ለማድከምና ከኃጢአት ለመራቅ በዚያ እጅግ ሞቃት በሆነ አየር እንኳን መጾም እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ምስኪን ድሆች!!›› 
ስለ ጌታ እሰብካለሁ የሚለው ሚስዮናዊ ጌታችን ጾሞ ያስተማረንን ጾም ስትጾሙ...› እንዲህ አታድርጉ እንዲህ አድርጉ ብሎ የሰበከበትን ጾም እንደኃጢአት ቆጥሮ ቢዘባበትም ባያስተውለውም የግብፅ ባላገሮች ግን በጨዋ ቃላቸው የጾምን ጥቅም አስረድተውታል፡፡
በክህደት ትምህርቶቹ የፈለገውን ውጤት ያልቻለው ሚስዮናዊ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ክፍተቶች ተጠቅሞ ምእመናኑን ማወክ ጀመረ፡፡ በተለይም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር በሚተዳደሩት የቀለም ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሙያቸው ብቁ የሆኑ በቂ መምህራን አለመመደባቸው እና ሕዝቡ በዚህ ምክንያት በቅዱስ ፓትርያርኩ በአቡነ ቄርሎስ አስተዳደር ላይ ቅሬታ ያለው መሆኑ ለሚስዮናውያኑ ምቹ ሁኔታ ፈጠረለት፡፡ ሕዝቡ በትምህርት ቤቶቹ ደረጃ አለመደሰቱም ልጆቹን ወደ ፕሮቴስታንት ሚሽን ትምህርት ቤቶች እንዲልክ አስገድዶት ነበር፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ላይ ደግሞ በካይሮ ለሚሠራ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ከምእመናን ገንዘብ የሚሰበስቡ ተወካዮች ከቅዱስ ፓትርያርኩ ተልከው ወደ ገጠሪቱ ላዕላይ ግብፅ ተሰማሩ፡፡ ቀድሞም በማጉረምረም ላይ የነበረው ሕዝብ ገንዘብ አምጣ ሲባል የበለጠ ተቆጣ፡፡ ይህ ሁኔታ ለሚስዮናዊው ሰርግና ምላሽ ሆነለት
‹‹በጣም ምቹ የሆነ አጋጣሚ ተፈጠረልኝ፡፡ ፓትርያርኩ በካይሮ ለቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ የሚሆን ገንዘብ የሚሰበስቡ ሰዎችን ላኩ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ይኼን ጨርሶ አልወደደውም ነበር፡፡ ስለዚህ ለገጠሩ ሰው እንዲህ ብዬ መናገር ጀመርኩ፡፡በቅርቡ ከካይሮ ልመጣ ስል እንደሰማሁት ከሆነ ፓትርያርኩ ሃያ አምስት ሺህ ባውንድ የሚያወጣ ለቤተ ክርስቲያኑ የሚሆን ሥዕል ከአውሮፓ አዝዘዋልአልኳቸው፡፡ የሰው ጠባይ መቼም የትም ቢሆን አንድ ዓይነት ነው፡፡ የኪሳቸው ጉዳይ ሲሆን ሁሉም አሰፍስፈው ይሰሙኝ ነበር፡፡››
በቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ክፍተት ተጠቅሞ አባቶችን ማዋረድና ከምዕመናን ጋር ማላተም የመናፍቃን የተለመደ ሴራ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡

ለብዙ ዓመታት የዘለቀው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ስልቱን እየቀያየረ የግብፅ ቤተ ክርስቲያንን እንዲህ ሲያምሳት ቆየ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተሰግስገው ከአውሮፓና አሜሪካ የሚላክ ገንዘብ እየተቀበሉ ክህደት የሚዘሩ መናፍቃንም ቀስ በቀስ በገሃድ እየወጡ መጡ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፬ኛ እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችም ዘግይተውም ቢሆን ይህንን ሴራ እየተረዱ ስለመጡ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት የሚሠሩ መፍቀርያነ መናፍቃንን ማውገዝ ጀመሩ፡፡

የመጀመሪያው ውግዘት በአቡነ ቄርሎስ ዘመነ ፕትርክና የተላለፈው ቢሾይ በተባለ መነኩሴ ላይ ነበር፡፡ ይህ መነኩሴ በውስጥ ክህደት ሲዘራ ከቆየ በኋላ የምንኩስና ቃልኪዳኑን አፍርሶ ሚስት በማግባት ሳይነጋ የጠወለገ አበባ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ተወግዞ ተለይቷል፡፡ 
በተመሳሳይም በወቅቱ በሀገራችን በኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ለነበሩት (ምናልባትም አቡነ ሰላማ ሣልሳዊ) ረዳት ሆኖ ለሰባት ዓመታት ያገለገለው አባ ሚካኤል የተባለ መነኩሴ ወደ ግብፅ ሲመለስ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆች እጅ ወድቆ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቤተ መቅደስ የመናፍቃንን ትምህርት በድፍረት ማስተማር በመጀመሩም በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዞ ተለይቷል፡፡


በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ግለሰቦችን በተናጠል ከማውገዝ ያለፈ ጸረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘመቻ በይፋ የተካሔደውና የመናፍቃኑ ቅስም የተሰበረው በ፻፲፩ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ድሜጥሮስ ዘመነ ፕርትክና ወቅት ነበር፡፡ የቅድስት ዲምያና ገዳም አበምኔት የነበሩትና የመናፍቃኑን ሴራ በጥልቀት የተረዱት እኚህ ፓትርያርክ ፕሮቴስታንት በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘርግቶት የነበረውን ክንፉን በመስበር መጀመሪያ በተነሣበት መጠን ዳግመኛ ለመመለስ እንዳይችል አድርገው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ የማይረሳው ውለታን ለመናፍቃኑም በመንገሽገሽ የሚያስታውሱት ጠባሳን ጥለውባቸዋል፡፡

ፓትርያርኩ የተሐድሶ ነገር ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተረዱት የገዛ ታናሽ ወንድማቸው ከቤታቸው ቁጭ ብሎ የፕሮቴስታንቶችንየመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያየተሰኘ መጽሐፍ ሲያነብ ባገኙት ጊዜ ነበር፡፡ በምሥጢራዊ ትርጓሜ (allegorical interpretation) ባህል የሚታወቀውና እነ ቀሌምንጦስን እነ ዲዮናስዮስን እነ ዲዲሞስን እነ ቄርሎስን ያፈራው የእስክንድርያ ትምህርት ቤት መገኛ የሆነችው የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆን የሆነው ወንድማቸው በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረውን የነሉተርን የነካልቪንን የነሜላንችተንን እንቶፈንቶ ትርጓሜ ሲያነብ ሲመለከቱ በመንፈሳዊ ቅናት ተቃጠሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተሰግስጎ የቀለም ትምህርት በማስፋፋት በሚል ሽፋን የተጀመረውን ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶም በአስቸኳይ ድራሹን ለማጥፋትም ቆርጠው ካልተነሡ የተቀመጡበት የቅዱስ ማርቆስ መንበር እሳት ሆኖ እንደሚፈጃቸው ተረዱ፡፡ስለዚህም አቡነ ድሜጥሮስ ካልዕ ጅራፋቸውን አነሡ፡፡

የፓትርያርኩ ፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘመቻ የተጀመረው በመላው ሀገሪቱ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በዐውደ ምሕረት የሚነበብ ባለ አምስት ገጽ መግለጫን በማውጣትና በማሠራጨት ነበር፡፡ በአባታዊ ጸሎተ ቡራኬ በሚጀምረው በዚህ መግለጫ የፕሮቴስታንቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያደረሱትና ሊያደርሱ ያቀዱትን ጥፋት በዝርዝር ካስቀመጡ በኋላ ለኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምእመናን የሚከተሉትን ትእዛዛት አስተላለፈዋል፡፡
1. ፕሮቴስታንታዊ መጻሕፍትን ማንበብ አቁሙ፡፡
2.
ከዚህ በፊት የተሠጧችሁን የፕሮቴስታንት መጻሕፍት በአስቸኳይ እንድታቃጥሉ፡፡
3.
በቃልም ሆነ በመጽሐፍ ማንኛውንም የፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ተቀብላችሁ እንዳትሰሙ፡፡
4.
ከፕሮቴስታንቶች ጋር ምንም አይነት ንክኪ አይኑራችሁ ተልዕኮአቸውን እንዲፈጽሙም ምንም ዓይነት ትብብር እንዳታደርጉላቸው፡፡
5.
በውስጥም ሆነ በውጪ የሚደረገውን ፕሮቴስታንታዊ ተጽዕኖም በጥንቃቄ ለይታችሁ እወቁ (ተጠበቁ)

ከዚህ የቅዱስ ፓትርያርኩ መግለጫ በኋላ በመላው ግብፅ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመጠበቅ ታጥቀው ተነሡ፡፡ በወቅቱ የነበረውም የግብፅ መሪ ነገሩ የምዕራባውያን ሴራ መሆኑን በመረዳቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጎን ቆመ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶችን አስፋፋች፡፡ ብዙ ኦርቶዶክሳውያንም ልጆቻቸውን ከፕሮቴስታንት ሚሽን ትምህርት ቤት እያስወጡ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች ማስገባት ጀመሩ፡፡
በተፈጠረው ሁኔታ ኦርቶዶክሳዊያኑ የተሠራባቸውን ሴራ ሲያውቁ የቁጣ እርምጃ እስከመውሰድ እስከ መማታት ቤትና መሬት ለፕሮቴስታንቶቹ አናከራይም አንሸጥም እስከማለት ደረሱ፡፡ ከፕሮቴስታንቶቹም ወገን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ቅዱሳት ሥዕላትን እስከመሰባበርም የደረሱ ነበሩ፡፡ ነገሮች ሲረጋጉ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በብዙ ድካምና ጥረት በፓትርያርክ ድሜጥሮስ ካልዕ ቆራጥነት በተሐድሶ ስልት የእስክንድርያን መንበር ፕሮቴስታንት ለማድረግ ብዙ ገንዘብ ተመድቦ የተሴረውን የረዥም ጊዜ ሴራ ለማክሸፍ ቻለች፡፡

የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በ፻፲፩ኛው ፓትርያርኳ ጊዜ የተሐድሶን አከርካሪ ብትሰብረውም ጨርሶ ማጥፋት ችላለች ማለት ግን አይደለም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ስለ ጌታችን በዲያቢሎስ መፈተን ከጻፈ በኋላ ‹‹ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ›› እንዳለው ለጊዜውሂድ አንተ ሰይጣንተብለው የተባረሩት መናፍቃን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ፈተና መሆናቸውን እስከዛሬም ከአቡነ ድሜጥሮስ በኋላ በተሾሙት ሰባት ፓትርያርኮች ዘመናትም እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱን መፈተናቸውን አላቆሙም፡፡

የግብፅ ቤተ ክርስቲያን በቀሩት ዘመናት ከተሐድሶ ጋር በተያያዘ ምን አሳለፈች? ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ዘመነ ፕትርክና እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ ዘመነ ፕትርክና ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? በግብፅ ቅዱስ ሲኖዶስ ተሐድሶን ለማስቆም ምን እርምጃ ተወሰደ? ምን ዓይነት መመሪያስ ተላለፈ? ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑ ስብከቶችና መዝሙራትስ ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስላወጣችው መመሪያስ ምን ያህ? በሰሜን አሜሪካ ስለተነሣው የቅርብ ጊዜ ነውጥና የቤተ ክርስቲያኒቱ እርምጃስ ምን ያህል ትምህርት ሠጪ ይሆን?
ክፍል ሁለት እንመለስበታለን

በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሐመር መጋቢት 2008


No comments:

Post a Comment