Wednesday, October 21, 2015

የኦርቶዶክስ ገቢ በቢሊዮን ቢቆጠርም የምዕመናኑ ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ



  • ‹‹ምዕመናንን የመጠበቅ ተልዕኮ እየተወጣን አይደለም›› አቡነ ማትያስ
  • ‹‹ለመሆኑ ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ወደ ሌላ ካምፕ ለመሄድ ለምን መረጡ? የሚያስተምራቸው ካህን አጥተው? የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት? አስተዳደሩ የማያረካ ሆኖ? የካህን እጥረት? ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው?››  ፓትርያርኩ፣


(ሪፖርተር ጥቅምት 10 2008 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባዔ መደራጀት ስትጀምር ገቢዋ በመቶ ሺሕ ብር የነበረ ቢሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቢሊዮኖች ብር ማደጉን የገለጹት ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ፣ የምዕመናኗ ቁጥር ግን እየቀነሰ መሆኑን አስታወቁ፡፡ 
 
ፓትርያርኩ 34ኛውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔን አስመልክቶ ጥቅምት 8 ቀን 2008 .. እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያኗ ገቢ በቂ ነው ባይባልም፣ በየጊዜው እያደገ መጥቶ ከመቶ ሺዎች ብር ወደ ቢሊዮኖች ብር አድጓል፡፡ ይኼ የሆነውም ቤተ ክርስቲያኗ ከልጆቿ (ምዕመናን) ከምታገኘው ገቢ ባለፈ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፏ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡


 የምዕመናን ዕድገት የኋልዮሽ እየሄደ መሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ዕድገቱ የኋልዮሽ መሆኑን የሚያውቅ ይኖር ይሆን? ችግሩንስ በሚገባ ተገንዝቦና በቁጭት ተነሳስቶ ችግሩን ለመቀልበስ የተደረገ ሙከራ አለ?›› የሚሉ ጥያቄዎቹን በማንሳት፣ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2008 .. የሚቆየው የሲኖዶስ ጉባዔ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ 

 የኦርቶዶክሳውያን ተልዕኮ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መሆኑን ሁሉም የዕምነቱ ተከታዮች፣ በተለይ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አባቶች እንደሚያውቁ የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ከህሊና መቆርቆር እስከ ሕልፈተ ሕይወት የሚዘልቅ የመስዋዕትነት ዋጋ የሚጠይቅም መሆኑን መዘንጋት እንደሌለባቸው ለጉባዔው ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ 
 
ባህር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ፣ እስከ ምድር ጽንፍ ተጉዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረጉ ይቅርና በአገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምዕመናንን ማባዛት ብዙ እንዳልተሄደበት ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ትናንትና ስመ ክርስትና ሰጥታ በአባልነት የተቀበለቻቸው ልጆቿ፣ ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እየካዱ ወደ ሌላ ጎራ መቀላቀላቸው እየናረ መምጣቱን አክለዋል፡፡ 
 
‹‹ለመሆኑ ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ወደ ሌላ ካምፕ ለመሄድ ለምን መረጡ? የሚያስተምራቸው ካህን አጥተው? የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት? አስተዳደሩ የማያረካ ሆኖ? የካህን እጥረት? ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሱት ፓትርያርኩ፣ መልሱን የጉባዔው ተሳታፊዎች የሚያውቁት ቢሆንም፣ ለሲኖዶሱ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

 ቤተ ክርስቲያኗ ምዕመኗን የመጠበቅ ተልዕኮ እየተወጣች ባለመሆኗ ባዶዋን ከመቅረቷ በፊት፣ ለተደራጀና ድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል መነሳት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ሥራ ለምዕመናን ኅሊና እንቅፋት እየሆነ መሆኑን የገለጹት ፓትርያርኩ የሃይማኖቱን መርህ ጠብቀው፣ አስተዳደሩ የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተዓማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ፣ የምዕመናንን ልብ የሚያረካ ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
 
በመጨረሻው የሕዝብና ቤት ቆጠራ አሥር በመቶ ምዕመናን ቁጥር መቀነሱ የታወቀ መሆኑን፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አበ እምኔት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ፣ በየገዳማቱ የሚኖሩ መነኮሳትና ሌሎች በድጋሚ ቆጠራ የተደረገላቸው ቢሆንም፣ እንዳልተካተተና ለምዕመናኑ ቁጥር መቀነስም ሌላው ምክንያት መሆኑንም የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምርያ ዋና ኃላፊ ሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጨ ተናግረዋል፡፡ ለምዕመናን ትምህርተ ወንጌልን በማዳረስ አማኙን ለማብዛት እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት መምርያ ኃላፊው፣ በጋምቤላ ክልል በራሳቸው ቋንቋ ወንጌልን በማዳረስ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊዎችን የሃይማኖቱ አባላት ማድረግ መቻሉን አክለዋል፡፡ 

ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ ቤተ ክርስቲያኗ ጠንክራ እየሠራች መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ትልቅ ሙስና ይፈጸምበታል የሚባለው የቤተ ክርስቲያኗ ሰፋፊ መሬት ጥናት ተደርጐበት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የሚመደቡ አስተዳዳሪዎች ጥፋት ፈጽመው ሲገኙ፣ ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ተነስተው ወደ ሌላ መዘዋወራቸው ቀርቶ ሙሉ በሙሉ የሚባረሩበት፣ በዘር፣ በመግባባትና ያለችሎታ የሚመደቡበት አሠራር ቀርቶ፣ በዕምነቱ ጥንካሬ፣ በላቀ ዕውቀት ምዕመናኑን በአግባቡ ሊያስተምር የሚችል የታመነበት አስተዳዳሪ የሚሾምበት አሠራር መዘርጋቱን የመምርያ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡    

2 comments:

  1. አባታችን ይህንን ለማለት ያስደፈራቸ ው ምን እንደሆነ የተገለጸ ቢሆንም ነገር ግን በየቤተክርስቲያን ያለውን ችግር መፍታት ካልተቻለ አሁንም ከዚህ የበለጠ እንደሚቀንስ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያኗ ከጊዜው ጋር ተነስታ በተለያየ መንገድ ወንጌል ማስፋፋት ስራ ማድረግ አለባት፡፡ ይህንን ያህል ቢሉየኖች ገቢ አድርጋ ነገር ግን ምንም አይነት የሚዲያ ኘሮግራም የላትም፡፡ ለምን? ሌሎች እምነቶች እኮ የራሳቸው የሬድየና የቴሌቭን ኘሮግራም አላቸው፡፡ አንድ ለእናቱ ማህበረ ቅዱሳን ብቻ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ይህንን ለማስቆም ብዙ መከራ እየደረሰበት ነው፡፡ የወንጌል ትምህርቷን አንድ ቦታ ላይ ብቻ ቆሟ ብታስተምር ማን ይሰማታል? የተባለው እኮ ሂዱና አህዛብን ሁሉ አስተምሯቸው ነው የተባለው፡፡ ካዲያ ዛሬ ባለው ቴክኖሎጂ እየተጠቀመች ለምን አታስተምርም? የትኛው ቀኖና እና ቃለ አዋዲ ወይም ፍትሀ ነገስት ነው የሚከለክለው? ዛሬ ምእመኑ በጣም በስራ፣ በተለያየ ምክንያት ጊዜው ተይዞበታል፡፡ ቤተክርስቲያኗ እቤት ድረስ ገብታ ወንጌል የማስተማር ግዴታ አለባት፡፡ የንስሀ አባት እኮ የተዘጋጁ እኛ ፈልገን ልንማር ሳይሆን እነርሱ ፈልገው እንዲያስተምሩን ነበር፡፡ ስለዚህ ሁሉም ካህናት የተጣለባቸውን ግዴታ እየተወጡ አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን መሄድ ሆረር በሆነበት ጊዜ ማን ይሰማቸዋል፡፡ ስለዚህ ፍቅር፣ አንድነት የጎደላት ቤተክርስቲያን ማንም አይፈልጋትም፡፡ ካህናት የራሳቸው አጀንዳ ይዘው ነው ያሉት፤ ስብከተ ወንጌል እየሰራ ያለው ለደመወዙ እንጂ ለወንጌል አገልግሎት አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያኗ የማንም የተሀድሶና የመናፍቅ አውደምህረት ሆናለች፡፡ ምእመኑ በራሱ በተለያየ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ቤተክህነት ወጥ የሆነ አሰራር እስከሌለው ድረስ ከዚህ የበለጠ ገና የሚቀንስ የመስለኛል፡፡ እባካችሁ የአስተምሮ አካሄዳችሁን አስተካክሎ፡፡ እናንተ አንድ ሁኑ፣ ፍቅር፣ አንድነት ላይ ተግታትሁ ስሩ፡፡ ማስተዋል ይስጠን፡፡

    ReplyDelete
  2. አባት ሆይ ይሕነ የማንሰማበት ቀን እሩቅ አታርገው። እንደበደላቸን ሳይሆን ኦንደቸርነትህ ይሑነ ።አሜን

    ReplyDelete