- ይህችም የሕዝብና የአሕዛብ ተስፋ የተመሠረተባት ፤ የእግዚአብሔር ሕጉ የተጻፈባት፤ አምልኮቱ የታወቀባት ፤ ኪዳኑ የጸናባት ጽሌ የሥግው ቃል እናት የእመቤታችን ማርያም ምሳሌ ስለ ኾነች መታሰቢያነቷ ሳይለወጥ ጽዮን በጽዮንነቷ ጸንታ ትኖራለች፡፡
- አክሱም ጽዮን ማርያምን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በወቅቱ አንድ ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር ወጪ
ተደርጓል፡፡
አንድ አድርገን ኅዳር 22 ቀን
2007 ዓ.ም
ለአክሱም ጽዮን ይህን የአዲሱን
ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ስንመሠርትላት ከዚህ ሰዓት ላደረሰን አምላካችን ውለታውን ለመመለስ የሚያበቃ ዐቅም የለንም፡፡ በ1928 ዓ.ም
ስለ ሀገራችን ነጻነት እየተዋጋን በትግሬ ላይ በነበርንበት ጊዜያት ከሰላማዊ ሰዓት ይህን ሥራ እንድንሠራ ያበቃን ፈጣሪያችንን በሃይማኖት
ለምነነው ነበር፡፡ ሀገራችን በጠላት ከተወረረች በኋላ በስደት አገር በነበርንበት ዘመን ኹሉ ስለዚሁ ነገር ሃይማኖትና ተስፋ ከሕሊናችን
አልተለዩም፡፡
አምላካችን በይቅርታው በጎበኝን
ጊዜ አገራችንን ከጠላት ቀንበር አውጥቶ ፤ እኛን ከዚህ ሰዓት አድርሶ የሐልዮውን በገቢር እንዲፈጸም አደረገልን፡፡ አክሱም በሐውልቶቹዋ
ስመ ጥሩነት ፤ በቤተ ክርስቲያንዋ ጥንታዊነት የኢትዮጵያ የታሪክ ፋና ናት፡፡ ሲያያዝ እንደሚገኝው በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን የመጣችው
ቅድስት ጽዮን በጥንቱ ዘመን እንሰባ ደግሞም መዝበር እየተባለ የሚጠራው በዚሁ አቅራቢያ በሚገኝው ቦታ በምኩራብ ኦሪት ነበረች፡፡
የክርስትናን ስርዐት የጀመሩት አብርሃና
አጽብሓ በነገሡበት ዘመን ግን ውሃ ሰፍሮበት የነበረው ይኽ ስፍራ ባሕሩ በተአምራት ደርቆላቸው መጀመሪያይቱን ቤተክርስቲያን አሳነጹላት፡፡ በዚያን ጊዜ ዐሥራ ሁለቱ የመቅደስ ክፍሎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን
በጉዲት ከተቃጠለ በኋላ አንበሳ ውድም ባለ ሰባት ክፍል አድር አሳንጾት ነበር፡፡ ከዚያም ወዲህ 1527 ዓ.ም በግራኝ ሰራዊት ስለ
ተመዘበረች አንድ መቶ ዓመት ያህል ቆይቶ የተነሣው አጼ ፋሲል ይህን አሁን ያለውን ሕንጻ አሠርቶላት በየዘመኑም የነበሩ ታላላቅ
ሰዎች እያደሱላት እስከ አሁን ቆይታለች፡፡
እኛም በዚህች ቀን የዛሬ 67 ዓመት ከኢትዮጵያ ተነጥላ የነበረች ኤርትራ
ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ ባደረግንበት በመጀመሪያው ዓመት ለእምነ ጽዮን የዚህን ቤተክርስቲያን ደንጊያ ስናኖር ስለታችን ከመፈጸሙም
በላይ የደረሰው ድርብ ዕጽፍ ደስታ የሚሆን የኤርትራ መመለስ አጋጣሚነት በፈጣሪያችን ፈቃድ የተፈጸመ ነው፡፡
በአብርሃ ወአጽብሓ ጊዜ የነበሩትም የቤተ መቅደስ ክፍሎች አሁንም እንዲኖሩ
ምኞታችን ስለ ኾነ መካከሉ የእምነ ጽዮን መቅደስ ኾኖ በግራና በቀኝ ስድስት ስድስት መቅደሶች እንዲገኙበት አድርገናል፡፡ የጥንቱ
ቤተ ክርስቲያን ለሴቶቸ የተከለከለ ነበር፡፡ ይህ እኛ የምናሠራው መቅደስ ግን ሳይከለከሉ እንደ ወንዶቹ ምእመናን ጸሎታቸውን ለማድረስ
የተፈቀደላቸው እንዲኾኑ አድርገናል፡፡ የጥንቱም ሕንጻ በየዘመናቸው ላሠሩት ለጥንታውያን ነገሥታት መታሠቢያነቱ እንደያዘ እንዲኖር
ትተነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አንደኛው ስመ ጥሩ ግዛታችን ትግሬ ለመጀመሪያ
ጊዜ እንደ ደረስን የሥራ መጀመሪያ ያደረግነው ይህ የጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መሠረት መጣል ስለ ኾነ አንድ የተከበረና የተቀደሰ ታላቅ ነገር ለመፈጸም
ፈጣሪያችን አበቃን፡፡ ስለዚህም ለዘወትር እናመሰግነዋለን፡፡
የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት (ከሊቀ ጠበብት አለቃ አያሌው)
መጽሐፍ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment