Thursday, August 21, 2014

‹‹ከዚህ በኋላ ያሉት ዘመናት ሰው ትንሳኤ ልቡና የሚነሳባቸው ማንም ሳያስተምረው ከመንፈስ ቅዱስ የተማረና ፈጣሪውን ያወቀ የሚሆንባቸው ናቸው፡፡›› መምህር ተስፋዬ ሸዋዬ


(አንድ አድርገን ነሐሴ 16 2006 ዓ.ም)
በኦሪት ዘፍጥረት እንደተጻፈው በድርሳነ ጽዮንም እንደተተረጎመው ብርሃን ከመፈጠሩና ማታና ጠዋት ፤ ቀንና ሌሊት ከመለየቱ አስቀድሞ ሰማይና ምድር ሳይለያዩ በአንድ ሁነው በጨለማ ይኖሩ እንደነበር ምድርም በውኃ ተሸፍና በላይዋ ላይ የእግዚአብሔር መንፈሰ ይሰፍን እንደነበር ተብራርቷል፡፡ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን ባለ ጊዜ ማታና ጠዋት ፤ ቀንና ሌሊት ሆነ ሰማይና ምድርም እንዲለያዩ በባለቤቱ ቃል ታዘዙ ተለያዩም፡፡ ከመላእክት በዓለሙ ካለውም ሥነፍጥረት በኋላ የሥነ ፍጥረት ፍጻሜ አዳምና ሔዋን ተፈጠሩ፡፡ ግዙፍ ሥጋና ረቂቅ ነፍስ ያላቸውም እንዲሆኑ እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ እፍ አለባቸው፡፡ ልብ ንባብ እስትንፋስ ያላት ነፍስ ተሰጠቻቸው፡፡ በዚህም በተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ገዥነት ተሰጣቸው፡፡

በተድላ ገነትም የሚኖሩ ሁነው ነበር ፤ በኋላ ግን ምክንያት ስህተት አጋጠማቸውና ከገነት ተባረሩ፡፡ እግዚአብሔር የሚቀበለውን ፀፀትና ሀዘን ወደቀባቸው፡፡ እግዚአብሔርም ዓለም ሳይፈጠርና ሰማይና ምድር ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት ድርገታትም ሳይፈጠሩ በልቡ ያሰበውን በቃል ኪዳን ነገራቸው በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ  ለዕለት ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በሜዳህ ድኄ ፤ ተገፍፌ ፤ ተገርፌ ፤ ተሰቅዬ ፤ ሞቼ ፤ ሞትን ድል ነስቼ ተነስቼ እታደግኃለሁ አላቸው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን አንድ ተብሎ መቆጠር ተጀመረ ከዚያም በጥፋት ውኃ ምክንያት ኪዳነ ኖኅ ተፈታ ምድር እስክታልፍ ያለ ሰው ዘር አትቀርም ተባለ፡፡

ከዚያም ቆይቶ ኪዳነ መልከጼዴቅ ተፈታ፡፡ በስንዴ ፤ በወይን መስዋዕት የምታሳርግ የክህነት ሥልጣን ተሰጠች፡፡ ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ ስለነበረች እመቤታችን ድንግል ወላዲተ አምላክ ይህ ሁሉ በልበ ሥላሴ እንደተከናወነ ታወቀ ፤ ተረዳ ፤ ተገለጠ፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶው ዘመን ከተፈጸመ በኋላ ከሰው ወገን ለማንም ሊሆን የማይቻለው ኪዳነ እግዝእትነ ማርያም ተፈታ፡፡ ተጸነሰች ፤ ተወለደች ፤ በቤተመቅደስ አገደች፡፡ በሁለት ወገን ድንግል ሳለች ሰማይና ምድርን በቃሉ ያጸና አምላክ ከርሷ ከሥጋዋ ሥጋ ፤ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመዋኃድና እንደኛው ሰው በመሆን ግዕዘ ሕጻናትን ሳያፋልስ ማኅተመ ድንግልናዋን ግን ሳያፈርስ ተወለደ፡፡ ዓመተ ፍዳ ፤ ዓመተ ኩነኔ ተፈጽሞ ዓመተ ምህረት ተጀመረ፡፡ ሀዲስ ኪዳንም ተፈታ ክርስቶስ ለአዳም የሰጠውን ኪዳን ፈጸመለት ሞትን ድል ነስቶ አዳነው፡፡

እነሆ ዘመን ከተቆጠረ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ስድስት (የተስተካከለ) ዓመታት ሊፈጸም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያሉት ዘመናት ሰው ትንሳኤ ልቡና የሚነሳባቸው ማንም ሳያስተምረው ከመንፈስ ቅዱስ የተማረና ፈጣሪውን ያወቀ የሚሆንባቸው ናቸው፡፡ ሀሳውያን ስሙን አውቀው ኃይሉን የሚክዱም ሁሉ የሚከስሙባቸው ናቸው፡፡ ሰው ሊያውቅ ይገባል እግዚአብሔር አይዘበትበትም ተብሏልና በስህተት ሊጸና አይገባውምና፡፡ እግዚአብሔር በራሱ የታመነ ስለሆነ አይቃለልም፡፡ የሚባላም እሳት ስለሆነ ትዕግስቱ አይፈተንም፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በነቢያትም በሐዋርያትም የታወቅን ነን፡፡ የባለቤቱ መታሰቢያ ከማኅላችን እንዲጠፋ የተፈቀደልን አይደለንምና እንድንድን ፊታችንን ወደ ፈጣሪያችን ወደ እግዚአብሔር የምናዞርበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ሌላ ቀጠሮ የለም፡፡ እንወቅ ፤ እንጠንቀቅ አንሳት አንዘብት፡፡

እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን የፍስሐና የሰላም ያድግልን አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ ፤ ፎከስ መጽሔት

1 comment: