Monday, June 12, 2017

በሰዓሊተ ምሕረት ጉዳይ ያልተመለሱልን ጥያቄዎች!

·        ፓስተር ኦላቭ (Rev.Dr Olav Fyske የኖርዌይ ሉተራን እምነት ፓስተር፣ የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ) ጸሎት አድርጌያለሁ ብሎ ሲፈጽም እየተጠራሩ መቀባባት ተጀመረ።
·        የእኛዋ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ / አባ /ማርያምም ቀርበው ተቀቡ:: እርሳቸው ደግሞ ፓስተር ዮናስ ይገዙን (በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የመካነ ኢየሱስ ፕሬዘዳንት) በአደባባይ ቀቡ።
በሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተፈፀመው ድርጊት ይፋ ከሆነ ጀምሮ ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ጉዳዮቹን አድበስብሶ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት ደግሞ የበለ ለምን እንዴት የሚሉ ጥያቄዎችን በመላው ዓለም በሚገኙ የቤተክርስቲያን ልጆች ላይ ፈጥሯል።
ይህ ጉዳይ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እኔንም ይመለከተኛልና እስኪ የተፈጠሩትን ጥያቄዎችን መልስ ለማግኘት አንድ ሰው ላነጋግር ብዬ ተነሳሁ። እናም በቀጥታ ጄኔቫ ደውዬ / ንጉሡ ለገሠ (በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ) ጋር በስልክ ተነጋገርኩ። / ንጉሡን ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲህ ያለ ጫና ለምን አሳደረ? ይህ አካሄድ ሕዝቡ በምክር ቤቱ ላይ ያለውን አስተሳሰብ አያበላሽውም ወይ? አልኳቸው። እርሳቸውም ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በአክብሮት መልስ ሰጡኝ። የሰጡኝን መልስ በራሴ መንገድ ለንባብ እንዲሆን ፅፌ አቅርቤዋለሁ። ጽሁፉ ያልተመለሰላችሁን ጥያቄ ከመለሰ መልካም ነው። ከዚያ በተረፈ ግን በሌሎቹ መምህራን የተሰጠውን ጠንካራ አስተያየት በማጠናከር እንደፃፍኩት ይታወቅልኝ።

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በዘንድሮ ዓመት ስብሰባውን በኢትዮጵያ ላይ ለማድረግ ወስኖ ነበር። ከየካቲት 20 እስከ 22 ቀን 2009 / ለማድረግ በወሰነው በዚህ ስብሰባውም ላይ የምክር ቤቱ ልኡካን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ እምነት መሪዎችና ተወካዮች ከተለያዩ ሥፍራ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መሥራች አባል የሆነችው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር 1948 / ነው። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ከምክር ቤቱ ጋር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ስትሠራ ቆይታለች። ምክር ቤቱ አንዱ ከአንዱ እምነት ጋር ሳይጣላ ሁሉም እምነት የየራሱን አስተምህሮ እንደያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሰላም ስለልማት ለመነጋገር የተቋቋመ እና ይህንኑ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሠራ እንደሆነ ተወካዩ ይገልፃሉ።
በዚህ ዓመት በተደረገው ስብሰባ አፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ለመወያየት አጀንዳ ተይዞ ነበር። ይህንን ጉባኤ እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው አካላት አንዱ ደግሞ / ንጉሡ ለገሠ (በምክር ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አንዱ ናቸው) / ንጉሡ ባለባቸው ተደራራቢ የሥራ ጫና ምክንያት አብሯቸው የሚሠራ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ተወካይ ስላስፈለገ አባ ኃይለ ማርያም ይህንን ተግባር እንዲያከናውኑ ኃላፊነት ተሰጣቸው። እርሳቸው የምክር ቤቱ አባል እንደመሆናቸው በስብሰባው ላይ ሊተገበሩ የታሰቡ ጉዳዮችን ጠንቅቀው ያውቃሉ በሚል ኃላፊነቱን ወሰዱ።
በዚህ መሠረት / አባ /ማርያም ይህንን የሥራ ኃላፊነት ለመወጣት ከኢትዮጵያ ሆነው ነገሮችን ያቀናጁ ነበር። አዳራሽ መፈለግ፣ በዕለቱ የሚካሄደውን መርሐ ግብር ለተጋባዥ እንግዶች በአማርኛ ቋንቋ ጭምር እየተረጎሙ ማሳወቅ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች በእንግድነት እንዲገኙ መጋበዝ፣ እና ሌሎችንም ሥራዎችን ከሀገር ቤት ሆነው ሲያከናውኑ ቆዩ።
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት መርሐ ግብሩን የሚያወጣው ቀደም ብሎ ነው። ይህ መርሐ ግብር ደግሞ ለዶ/ አባ /ማርያም ቢያንስ ከስድስት ወር በፊት ስለሚደርሳቸው ያውቁታል። መርሐ ግብሩ አልደረሰኝም እንዳይሉ እንግሊዘኛውን ወደ አማርኛ ተርጉመው/ አስተርጉመው ኢትዮጵያ ውስጥ ለተለያዩ አካላት አሰራጭተውታል።ለፕሮግራሙ የተዘጋጀው ቦታ ሰዓሊተ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሆነ እነ / አባ /ማርያም ለምክር ቤቱ አሳወቁ። ( መቼም የምክር ቤቱ ተወካዮች ባህር ማዶ ሆነው እዚህ ቦታ ይደረግ እንደማይሏቸው ግልፅ ነው። ) ስብሰባው በአዳራሽ ውስጥ ሊደረግ ይችል ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሊካሄድባቸው የሚችሉ አዳራሾች አሉ።
ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከሕዝብ እይታ ለመራቅ ተመርጣ የመግቢያ ካርድ (ባጅ) እያሳዩ የሚገቡ እንግዶች ብቻ እንዲገቡባት ተደርጎ ስብሰባው በጥንቃቄ ተዘጋጀ። የባህር ማዶ ሰዎች የእኛን ቤተ ክርስቲያን ለማየት መግባታቸው አዲስ ነገር አይደለም። ላሊበላ፣ አክሱም ሲጎበኙ የሚውሉት እነርሱ ናቸው። ወደዚህ ቦታ WCC ተወካዮች ሲገቡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት አይተው አድንቀው እንዲወጡ ብቻ ቢፈለግ ጉዳዩን መደባበቅ አያስፈልግም ነበር። ሕዝቡም በቦታው ቢኖር እንግዶቹ ገብተው በመውጣታቸው ችግር እንደማይፈጥር ይታወቃል። የመግቢያ ካርድ ያስፈለገው፣ ሕዝቡ ከአካባቢው እንዲርቅ የተደረገው፣ ሕዝቡን ሊያስቆጣ የሚችል መርሐ ግብር ስላለ ነው። ይህም የፕሮቴስታንት እምነት አራማጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ከውጭ ሃገር የገቡ ፓስተሮች የሚሳተፉበት ጸሎት በቤተ መቅደስ ውስጥ ለማድረግ ስለታሰበ ነው። ይህ ደግሞ በአማርኛ በተተረጎመውና ለእንግዶች በተበተነው ፕሮግራም ላይ አስቀድሞ ተሰራጭቷል። " Ash Wednesday" በመባል የሚታወቀውና በምዕራቡ ዓለም የተለመደውን ጸሎት ከሀገር ቤት እና ከውጭ ከመጡ ፓስተሮች ጋር በአንድነት ለመፀለይ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
/ አባ /ማርያም ይህ ጉዳይ እንደ ውሃ ደራሽ ድንገት የመጣባቸው አይደለም። ኃላፊነቱን ወስደው ሥራውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ያውቁታል። ጸሎቱ ከእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ሥርዓት የተለየ እንደሆነ፣ የጸሎቱ መሪዎችም የፕሮቴስታንት እምነት መሪዎች እንደሆኑ መርሐ ግብሩ ላይ ስለተፃፈ ሊመጣ ያለውን ሁሉ በትክክል ያውቃሉ። ይህ "ጸሎት" መርሐ ግብር በአዳራሽ ውስጥ ቢካሄድ እንኳን በእምነት ጉዳይ ማንንም የማስገደድ ጠባይ የለውም። ምክር ቤቱ የእያንዳንዱን እምነት ሥርዓት ያከብራል። ፍላጎቱ ከሌለ በስተቀር ማንም በማንም ላይ እጁን አንስቶ ይጫን የሚል ሕግ የለውም። ስለዚህ በአዳራሽ ቢያከናውንም ሁሉም የየራሱን ይጸልያል እንጂ እኔ ባንተ ላይ ልጸልይ አንተ በእኔ ላይ ጸልይ ማለት አይቻልም።
ቤተ መቅደስ ውስጥ ጸሎቱ ይካሄድ ተብሎ መርሐ ግብሩ ከተዘጋጀ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በራሷ መንገድ ስለ ውሃ የምትፀልየውን ጸሎት(በእንተ ማያተ አፍላግ) እንድትጸልይ፣ እርሷ መሪነቱን እንድትይዝ እና እነእርሱ ተመልካች ብቻ እንዲሆኑ ሊደረግ ይገባ ነበር። ይህ ቢሆን ሥርዓቱም ሳይናጋ ቤተ መቅደሱም ሳይደፈር በሰላም ይጠናቀቃል። ችግሩ እዚህ ላይ ነው።
ጸሎቱ በእኛ አባቶች እንደማይመራ እየታወቀ፣ ጸሎቱን የሚመሩት ሌሎች እንደሆኑ እና በቤተ መቅደስ ውስጥ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ፓስተር ሊጸልይ እንደሆነ እየታወቀ ቤተ መቅደስ ይዞ መግባት ምን ይባላል? ደጋግመው ያነበቡት መርሐ ግብር መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን ስለ ቤተ መቅደሱ መደፈር አልተጨነቁም። ከዚህ ይልቅ ሕዝቡ አይቶ እንዳይቆጣ በማሰብ ሕዝቡን ከደጅ መለሱት። 
 
መርሐ ግብሩ በጥንቃቄ በተመረጡት እንግዶች አማካኝነት ሊካሄድ ሁሉም ቦታቸውን ያዙ። ቅዱስ ፓትርያርኩም ዘግየት ብለው ደረሱ። ቅዱስነታቸው መርሐ ግብሩን በተመለከተ መረጃ የላቸውም እንዳይባል / አባ ኃይለ ማርያምን የወከሉት እርሳቸው እንደመሆናቸው ጉዳዩ በትክክል በሪፖርት መልክ ይደርሳቸዋል። ቦታው መመረጡን መርሐ ግብሩም ምን እንደሚመስል አስቀድሞ ሳይነገራቸው በደፈናው ይገኙልን አይባልም። በርግጥ የምክር ቤቱ ተወካይ እዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ቅዱስ ፓትርያርኩ «ከአባ ኃይለ ማርያም በየጊዜው ሪፖርት አልተደረገላቸውም ስለዚህ ስለጉዳዩ ብዙም መረጃ የላቸውም» የሚል ነው። ይህ ደግሞ ግልጽ የሆነ የአሠራር ድክመት እንዳለ ያሳያል። እንዲህ ያለውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ እያዘጋጁ በየጊዜው ሪፖርት አለማቅረብ በጉዳዩ ላይም ሐሣብ አለመለዋወጥ ትልቅ የአሠራር ድክመት ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ አሁንም እንደ ምክር ቤቱ ተወካይ ገለጻ ጸሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ደረሱ፤ መቀባባቱም ላይም እርሳቸው አልነበሩም።
እዚህ ላይ / አባ ኃይለ ማርያም ፓትርያርኩ ሳያውቁ በራሳቸው መንገድ ከፓስተሮቹ ጋር ጸልየዋል ወይም ቅዱስነታቸው ጉዳዩን እያወቁ አባ ኃይለ ማርያምን ከፊት አስቀድመው ራሳቸውን ከጨዋታ አግልለዋል። ጉዳዩን እግዚአብሔር ይመርምረው። በየትኛውም መንገድ ቢሆንም ግን አባ ኃይለ ማርያም ከተጠያቂነት አላመለጡም። ቅዱስ ፓትርያርኩ «ቀድሞም ሪፖርት አላደረገልኝም ሲቀባቡም አልነበርኩም» ካሉ መቼስ ምን ይደረጋል። የአሠራር ክፍተቱን ከመውቀስ ባለፈው መናገር አይቻልም። በሌላ በኩል ግን ፓትርያርኩ «በወቅቱ አልነበርኩም፣ አልሰማሁም አላየሁም» ቢሉን «ከሰሙ በኋላ ምን ርምጃ ወሰዱ? የድርጊቱ ተቃዋሚ ቢሆኑ ፈጣን የሆነ አስተዳደራዊ ርምጃ ወስደው በተመለከትን ነበር» ማለታችን የማይቀር ነው።
ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር "ስሜ ለዘለዓለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም። ዓይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናል" (2ዜና 7÷14) ተብሎ የተናገረለት ቤተ መቅደስ ነው። የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ታቦተ ሕጉ ያለበት ቤተ መቅደስ ነው። በመዓልትና በሌሊት ቅዱሳን መላእክት ተግተው የሚጠብቁት ቤተ መቅደስ ነው። ፓስተሮቹ በዚህ በከበረ ሥፍራ ቆመው ለመፀለይ ሲዘጋጁ ውሃ አምጡልን ሲሉ የሚናገር የሚያስቆማቸው እንዴት ይጠፋል? እንደ ምክር ቤቱ ተወካይ ገለጻ ከሆነ ስህተት መሆኑን የሚጠቁም ማንም ሰው ቢኖር ተወካዮቹ በድፍረት ይህን ድርጊት አይፈጽሙም ነበር። ትንፍሽ ያለ፣ ተዉ እባካችሁ ቤተ መቅደሱን አታርክሱብን ያለ ግን አልነበረም።
ፓስተር ኦላቭ (Rev.Dr Olav Fyske የኖርዌይ ሉተራን እምነት ፓስተር፣ የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ) በራሱ መንገድ ጸሎት አድርጌያለሁ ብሎ ሲፈጽም እየተጠራሩ መቀባባት ተጀመረ። የእኛዋ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ / አባ /ማርያምም ቀርበው ተቀቡ:: እርሳቸው ደግሞ ፓስተር ዮናስ ይገዙን (በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የመካነ ኢየሱስ ፕሬዘዳንት) በአደባባይ ቀቡ። (ተሐድሶን አዝምተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ሌት እና ቀን እንቅልፍ አጥተው የሚሠሩ ፕሮቴስታንቶች መሪ በቤተ መቅደሳችን ተቀባ (ፎቶ ግራፉ ላይ እንዳየነው ማለት ነው) በዚህም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከልማት እና በሰላም ጉዳይ አብሮ ከመሥራት አልፎ የእምነት አንድነት የተፈጠረ ይመስል የሚገርም ድራማ ሠርተው አሳዩን። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን ከፕሮቴስታንት ፓስተር ጋር በቤተ መቅደስ አብሮ ጸለየ ቅባትም ተቀባባ።
ለመሆኑ ፕሮቴስታንቶቹ ኢኩሚኒዝም ምን እንደሆን ያውቃሉ? አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ ተከባብሮ መኖር ምን እንደሆነ መቼ ያውቃሉ። እምነታቸውን የሸጡ ባንዳዎችን ሰብስበው የሚያዘልሉብን እነ እርሱ አይደሉ እንዴ? ወደየገዳማቱ፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን እና መንፈሳዊ ኮሌጆቻችንን ቅጥረኛ የተሐድሶ አራማጆችን በመላክ ሁከትና ብጥብጥ እየፈጠሩ በጎን ስለሰላም ይወያያሉ። በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፀንተን የመኖር መብታችንን ለመግፈፍ ጉድጒድ እየቆፈሩ፣ ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጨዋ መስለው ይታያሉ። እንደውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚሰሩትን ፖለቲካ ቀመስ የማፍያ ሥራ በመረጃ ይዛ ለምክር ቤቱ ልትከሳቸው ሲገባ(ለነገሩ መናፍቃኑ በተመለከተ ፍርዱን የምንጠብቀው ከአንድ አምላክ ነው) እነርሱን ጎትቶ ቤተ መቅደስ ይዞ መግባት፣ ቅባት መቀባባት ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው። በአጭር ቃል ለመግለጥ መነኩሴው በሰሞኑ ድርጊታቸው በማንነታቸው ላይ ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል።
በየትኛወም መልኩ ቢሆን ከሌሎቹ እምነት ድርጅት መሪዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። እነርሱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልናና ክብር ዘንግተው ወይም ሆን ብለው አብረን እንፀልይ፣ ቅብዓ ሜሮን እንቀባባ፣ ቀድሰን እንቆራረብ ሌላም ሌላ የሚል ሀሳብ በድፍረት ሊያነሱ ይችላሉ። የእኛ መልስ ግን ጠንካራ መሆን ይጠበቅበት ነበር። ቀዩን መስመር ሲያልፉ ከዚህ አትለፉ ብለን ማስቆም ይጠበቅብናል። «እዚህ ላይ አቁሙ» ብሎ ለማስቆም ድፍረት ያልነበራቸው ከምክር ቤቱ የሚሰጥ ርዳታ ስለነበረ ያንን ላለማጣት ነው የሚሉ አስተሳሰቦችም ሲንፀባረቁ ነበር።
በመሠረቱ ይህ ዓለም አቀፍ ምክር ቤት የዘንድሮው ስብሰባው ከርዳታ ጋር የተገናኘ አልነበረም። ድርጅቱ ርዳታ ሰጪም አይደለም። ሁሉም እምነቶች በፈቃደኝነት የሚሳተፉበት እንደመሆኑ አስገድዶ የሚሰራው ሥራም የለም። ርዳታ ቢኖር እንኳን በማስገደድ ሊያደርገ የሚችለው አንድም ነገር እንደሌለ ተወካዩ ይገልፃሉ። ስለዚህ በርዳታ ስም ተገደው አደረጉት የሚለው መረጃ የተሳሳተ ነው። ቤተ መቅደሳችን ውስጥ ይህ ድርጊት አይፈፀምም ቢሉ የሚቀርባቸው ምንም ነገር የለም። የሚያስገድዳቸውም አንዳችም ነገር አልነበረም። ይሄኔ ነው መጠየቅ ምክር ቤቱ እኔ አላስገድድም ካለን አባ ኃይለ ማርያም ይህን አሳዛኝ ድርጊት የፈፀሙት ማንን ለማስደሰት ነው?
ማጠቃለያ
ሰዓሊተ ምሕረት ላይ የተፈጸመው የስህተት ድርጊት በፎቶ ግራፍ ወደ ሚድያ ከወጣ በኋላ የፈጠራቸው ብዙ ነገሮች አሉ። 
1-
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አሠራር ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ላለፉት 70 አመታት አብሮ ሠርቷል። (ቤተ ክርስቲያናችንም የምክር ቤቱ መሥራችና አንጋፋ አባል ነች።) እንደ ዘንድሮው ያለ ሕዝብን የሚያሳዝን ድርጊት ግን ተፈጽሞ አያውቅም። ምክር ቤቱ በመከባበር ላይ የተመሰረተውን ግልጽ የሆነውን ዓላማውን መሥራች ከሆኑት ሀገሮች አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና ካህናት እንዲጠራጠሩት ሆኗል። ጥርጣሬው ደግሞ እንዲሁ የተፈጠረ ሳይሆን በአደባባይ በተፈፀመው አሳዛኝ ድርጊት ምክንያት ነው። 
ኢኩሚኒዝም በልማት በሰላም ጉዳይ አብሮ ተባብሮ መሥራትን የሚያንፀባርቅ ሲሆን ይህ አብሮ የመሥራት ጉዳይ ግን ቀይ መስመሩን ካለፈ እምነትን፣ ቀኖናን፣ ትውፊትን፣ ወደ መደበላለቅ ከተጓዘ ግን በራሱ የቃሉን መሠረታዊ ዓላማ ያዛባል። ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በኢኩሚኒዝም ዙሪያ በጻፉት ጽሁፋቸው ይህንኑ አባባል በግልጽ ሁኔታ ሲያስረዱን እንዲህ ብለዋል። 
 "
ኢኩሚኒዝም ማለት በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ጥላቻና ክፉ አስተሳሰብ ለማስወገድና አብሮ ለመሥራት የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች ንቅናቄ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን "የኢኩሚኒዝም" መንፈስ በትክክለኛ ዓላማው ትቀበለዋለች። ማለትም በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ጥላቻና አልይህ አልይህ መባባልን አርቆ ሁሉም የየራሱን ጠብቆና አክብሮ የሌላውንም መብት ጠብቆ መኖር "የኢኩሚኒዝም" ዓላማ ነው። "ኢኩሚኒዝም" ስም ለገንዘብ ብሎ ራስን መቸርቸር ወይም የሌላውን ትውፊት ከራስ ጋር ማዳበል ግን በታሪክ እና በትውፊት ላይ ማመጽ ነው" (አባ ጎርጎርዮስ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ 10 ምዕራፍ፤ ገጽ )
/ ንጉሡ ከዚህ መሠረታዊ ሃሣብ ተነሥተው ምክር ቤቱ በእምነት ጉዳይ የማንንም መብት አይደፍርም ይላሉ። ታዲያ / አባ ኃይለ ማርያም ማንን ለማስደሰት ቤተ መቅደሱን ያስደፈሩት? በፈጸሙት ትልቅ ስህተት ምክንያት ምክር ቤቱን ሆነ ቤተ ክህነትን ከሕዝብ አቃቅረዋል። ስለዚህ ሙሉ ኃላፊነት ወስደው ለጥፋታቸው ይቅርታ መጠየቅ ያለባቸው እርሳቸው ናቸው።
2-በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ኃላፊዎች ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጥር አድርጓል
ካህናት እና ምእመናን በጠቅላይ ቤተ ክህነት አሰራር ላይ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው ከተደረገ መዋቅሩን ጠብቆ የሚሠራበት ሰንሰለታዊ አሠራር አደጋ ላይ ይወድቃል። በኃላፊነት ላይ የተቀመጡ አባቶች ተዓማኒነታቸውን አስጠብቀው በመጓዝ ከታች ያለው ካህንና ሕዝብ እምነቱን በእነርሱ ላይ እንዲጥል ማድረግ አለባቸው። ይህ ዓይነቱ ድርጊት ያውም በእምነት ጉዳይ ኃላፊነትን ሳይወጡ መገኘት ሕዝቡን በቤተ ክህነት አሠራር ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው ያደርጋል። እረኞች ናቸው፣ የመምሪያ ኃላፊዎች ናቸው፣ ያላቸው አበው ከፕሮቴስታንት እምነት መሪዎች ጋር በአደባባይ ቆመው ሲፀልዩ ካየ ሰማዩ ይደፋበታል። ነገሮችን በሙሉ እንዲጠራጠር ያደርገዋል።
ቤተ ክህነት የምትመራው በቅዱስ ሲኖዶስ ነው። አባቶቻችን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ደግሞ በተሐድሶ መናፍቃን ላይ ያላቸው አቋም ጠንካራ መሆኑን ማንም የሚመሰክረው ሃቅ ነው። እነርሱ ከላይ ባይበረቱ እስከአሁን ተሐድሶ አራማጅ ጳጳስ ከአንድም ሁለት ሶስት እያለ ሲቀላቀል ማየታችን የማይቀር ነበር። አባቶች ትናንት እንደበረቱት አሁንም በሕዝቡና በቤተ ክህነቱ መካከል ያለውን ክፍተት ለማስተካከል የእርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። / አባ /ማርያምም ሆነ በዙሪያቸው የነበሩ የቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ የተድበሰበሰ ሳይሆን ግልጽ የሆነ መልስ እንዲሰጡ መደረግ አለበት። 
 
ይቅርታ መጠየቅ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት የሚገባቸውን ቀኖና መቀበል ይኖርባቸዋል። ከዚያም አልፎ እንዲህ በተፋፋመ ወቅት / አባ /ማርያምን ወደ ጵጵስና ሹመት ማቅረቡ ክፍተቱን የበለጠ እንደሚያሰፋ ተረድቶ ለጊዜው የዶክተሩን ሹመት ማዘግየት ይገባል። /ይህን ለማለት ሙሉ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሆነ ግልጽ ነው። እኛም የልጅነታችንን ድርሻችን ለመወጣት የሰነዘርነው መሆኑ ይሰመርበት/
3-ተመሳሳይ ጥፋቶች እንዲፈፀሙ በር ይከፍታል

ይህ ስህተት ዛሬ በቀኖና ካልተስተካከለ (ያጠፋን አካል ቀኖናው በሚያዘው መሠረት እንዲቀጣ)ካልተደረገ ነገ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእምነት መሪዎች ጋር አብሮ የሚቀድስ ካህን ቢነሳ ለማስተካከል እንዳይቻል ያደርጋል። ፕሮቴስታንቶቹ በተለይ የኢትዮጵያ ፕሮቴስታንቶች መሪዎች በተሐድሶ ስም አስርገው ያስገቧቸው መናፍቃን አንድ ነን እያሉ ሕዝቡን እንዲያሳስቱ በር ይከፍታል። በየሥፍራው ሾልከው እየገቡ ለሚያጠፉት ጥፋት መንገድ ይሆናቸዋል። «ሃይማኖት አያድንም "ጌታን"መቀበል ብቻ ይበቃል። "ጌታን" ከተቀበልህ አንድ ነንና ከመካነ ኢየሱስ ጋር መፀለይ ይቻላል» የሚለውን የጥፋት ስብከት ያጠናክራል። 
ስብሐት ለእግዚአብሔር 
ወለወላዲቱ ድንግል
(
ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን)
(
ኮለምበስ ኦሀዮ)

1 comment: