Thursday, March 16, 2017

የይሓ ቤተ መቅደስ ጥገና ተደርጎለት ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

ከክርስቶስ ልደት በፊት 800  ዓመተ አለም  እንደተገነባ የሚነገርለት ጥንታዊው የይሓ ቤተ መቅደስ ጥገና ተደርጎለት ዛሬ ለጎብኚዎች  ክፍት ሆነ። ቤተ መቅደሱን መጠገን ያስፈለገው በዕድሜ ብዛት የመሰንጠቅና ሌላም ጉዳት ስለደረሰበት መሆኑን በአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የአርኪዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ አላይ  ገብረስላሴ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ከአደዋ ከተማ 32ኪሎ ሜትር  ርቀት ላይ የሚገኘው  የይሓ ቤተ መቅደስ ጥገናው የተደረገለት ባለፉት   ስምንት ዓመታት በጀርመናዊያን  ባለሙያዎች እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ባለሙያው እንዳሉት ቤተ መቅደሱ ጥንታዊ ይዘቱ  ሳይለቅ የተሰነጠቁ  ድንጋዮችን መሙላት፣  የበሰበሱ ድንጋዮችን ደግሞ በሌላ የመተካት ስራው በጥንቃቄ ተከናውኗል፡፡
የቤተ መቅደሱን  የጥገና  ስራ መጠናቀቁን ይፋ በማድረግ  መርቀው ለጎብኚዎች ክፍት ያደረጉት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  አቶ ዮናስ ደስታ እና  የትግራይ ክልል  ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሃይሌ ናቸው፡፡
 ምንጭ ፡- http://www.ena.gov.et
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ይሓ የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራ 

(ከምሕረተሥላሴ መኰንን)
 ከአክሱም ከተማ በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 56 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጥንታዊቷ ይሓ ከተማ ትገኛለች፡፡ የይሓ ከተማ መግቢያ ላይ ከተማዋ የምትታወቅባቸው ሁለት ታላላቅ ሕንጻዎች ይገኛሉ፡፡ አንደኛው ግራት በዓል ግብሪ በሚባለው ቦታ የነበረው ቤተ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ሥፍራ አሁን የአርኪዮሎጂ ስፍራ (ሳይት) ሲሆን፣ በተመራማሪዎች ተከልሎ ይታያል፡፡ የጀርመን አርኪዮሎጂካል ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች በሚያደርጉት ቁፋሮ ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ 8ኛውና 9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚጠጉ ግኝቶች ይፋ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች በአካባቢው ቁፋሮ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም በደርግ ወቅት ተቋርጦ 1985 .. ዳግም መጀመሩን ያሳያሉ፡፡ ኢትዮጵያን ኢንስቲትዩት ኦፍ አርኪዮሎጂና የፈረንሳይ የአርኪዮሎጂ ቡድንን ጨምሮ የብዙ ተመራማሪዎች መዳረሻ ነው፡፡


ከክርስቶስ ልደት በፊት 8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታነፀው የይሓ ምኩራብ (ቤተ መቅደስ) ሌላው ነው፡፡ ግንቡ ውስጥ መስዋዕት የሚቀርብበት፣ ጸሎት የሚደረግበትና የእረፍት ቦታዎች አሉ፡፡

የይሓ ግንብ እንደ ዛሬው ሲሚንቶና አሸዋ በመጠቀም ሳይሆን ረዣዥምና ግዙፍ ድንጋዮችን በማነባበር የተሠራ ነው፡፡ ግንቡ 18 15 ሜትር ስፋትና 13 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ መቅደሱ 12 ዐምዶች እንደነበሩት የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ የይሓ ግንብ በወርቅ የተለበጠ እንደነበርም ይነገራል፡፡

ተመራማሪዎች ዘመናት ስለተሻገረው የግንቡ ጥንካሬ የተለያዩ መላ ምቶች ያስቀምጣሉ፡፡ የግንቡ ካቦች ያላቸው የተስተካከለና ወጥ ቅርፅ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ በጽሑፍና በቪዲዮም በተደጋጋሚ የሚወሳው ይህ ግንብ በእውን ሲታይ አግራሞትን ይጨምራል፡፡ ግንቡ ከውጪ ሲታይም ይሁን ውስጡ ሲገቡ ልዩ ግርማ ሞገስ አለው፡፡

ይሓ የሚለው ቃል በሳብኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ማለት እንደሆነና የከተማዋን ቀደምትነት እንደሚያመላክት ይነገራል፡፡ ይሓ 8ኛው እስከ 3ኛው ክፍለ ዘመን የቆየው የጥንታዊው የደአማት መንግሥት መቀመጫ የነበረች ሲሆን፣ በወቅቱ ከተማዋ የንግድ፣ የሥነ ጥበብ፣ የአስተዳደር እንዲሁም የእርሻ ማዕከል ነበረች፡፡ የከተማዋን ልቀትና ጥንታዊነት የሚያሳዩ አሻራዎችን አሁንም ድረስ ይታያሉ፡፡

ወደ 200 ሜትር በሚጠጋ ልዩነት የሚገኙት ምኩራቡና ቤተ መንግሥቱ ከፍ ባለ ሥፍራ የተገነቡ ናቸው፡፡ የይሓ ምኩራብ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ክርስትና ከተስፋፋ በኋላ ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት አቡነ አፍፄ ወደ ቤተ ክርስቲያንነት እንደተቀየረ ይነገራል፡፡ አጠገቡም ቤተ ክርስቲያን ተገንብቶ ይገኛል፡፡ በባለሁለት ሕንፃው የአቡነ አፍፄ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎችና የድንጋይ ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡

በአራት ማዕዘን ቅርፅ የተገነባው የይሓ ግንብ ጣሪያ የለውም፡፡ የጥንታዊ ሥልጣኔ ህያው ምስክር የሆነው ግንቡ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ተፅዕኖዎችን ተቋቁሞ ዘመናት መሻገሩ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ ዛሬ ላይ ግንቡን ለመጠበቅ በአራቱም ማዕዘን የቆሙ የብረት ድጋፎች ተደርገውለታል፡፡ የግንቡ አንዳንድ ክፍሎች የፈረሱ ሲሆን፣ በደረሰበት የእሳት አደጋ ነው የሚል መላምት አለ፡፡

በአካባቢው 1960ዎቹ ወዲህ በተካሄዱ የአርኪዮሎጂ ጥናቶች ከአለት የተሠሩ 17 የሚጠጉ መቃብሮች፣ የሳባውያን ጽሑፍ የያዙ ጥርብ ድንጋዮችና እጣን ማጨሻ፣ ከመዳብ የተሠሩ ማህተሞች እንዲሁም የእርሻና የሕንፃ መሣሪያዎች ተገኝተዋል፡፡ የአንበሳ ቅርፅ ያለው የሊባኖስ ተራራ ለአካባቢው ውበት ጨምሮለታል፡፡  
የይሓ ግንብ በታሪክ፣ በአርኪዮሎጂና ኪነ ሕንፃ ጥበብ ያለው ትልቅ ቦታ ዝነኛ እንዲሆን ካስቻሉት እውነታዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከቅድመ አክሱማይት ሥልጣኔ አስቀድሞ የነበረው የደአማት መንግሥት ሥልጣኔ ቅሪቶች አንዱ ከመሆኑም በላይ ከሰሀራ በታች አፍሪካ ዕድሜ ጠገብ የሥልጣኔ ምልክት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ ከግንቡ ወደ መሬት ሲቆፈር ሌሎች ሕንፃዎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡

ይሓ ከተማ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻና የአገሪቱም ቀደምት መዲና ናት፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመስፋፋቱ አስቀድሞ የነበረውን አምልኮ የሚያሳዩ ቅሪቶችና በአባ አፍፄ የተገነባው ቤተክርስቲያን የማኅበረሰቡን የእምነት ሥርዓት በንጽጽር የሚያሳዩ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ የሶሪያው አባ አፍፄ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ኢትዮጵያ ብዙ ገዳማት መመሥረታቸው ይነገራል፡፡

በትግራይ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያ በርካታ ጎብኚ ካላቸው አካባቢዎች ይሓ ይጠቀሳል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ ቀደምትና ማራኪ ታሪካዊ ቦታዎች አንዱ መሆኑን የሚመሰክሩ ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች አሉ፡፡ ከቀደምት ዓለም አቀፍ አሳሾች አንስቶ ቦታው እንደሚጎበኝ የሚያሳይ መረጃ ከትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይገኛል፡፡ ወደ ይሓ ከተጓዙ አሳሾች መካከል 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ይሓን የጎበኘው ፍራንሲስኮ አልቫሪስ እንዲሁም ጄምስ ብሩስ፣ ሄነሪ ሶልችና ቴኦዶር ቤንት ይጠቀሳሉ፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የይሓ ግንብ ከጥንታዊ ሰሜናዊ አረቢያ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ . ክሪስ ሒርብቶ የተባሉ አርኪዮሎጂስት በሠሩት ጥናት ከቅድመ አክሱማዊ ሥልጣኔ አስቀድሞ ከሰሜን አረቢያ ጋር የነበረውን ትስስር ከሚያሳዩ መረጃዎች መካከል በአካባቢው የተገኙ የዓረብኛ ጽሑፍ የሰፈረባቸው የድንጋይ ግኝቶች ይጠቅሳሉ፡፡ ተመሳሳይ ግኝቶች ከኢትዮጵያ ውጪ በኤርትራም እንደሚገኙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአካባቢው የተገኙ መረጃዎችን መነሻ በማድረግና የኪነ ሕንፃ ጥበቡን ተመሳሳይነት በማጣቀስ ከይሓ የተቀዳ ሥልጣኔ ስለመኖሩ መላ ምት የሚያስቀምጡ ተመራማሪዎች አሉ፡፡

ስለቀደምት አክሱማዊ ሥልጣኔ ጥናት የሠሩት ሮዶልፎ ፋቶቪች በይሓ የተለያየ ወቅትን የሚያመለክቱ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ይፋ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው በአካባቢው ያሉ ሕንጻዎች ከመገንባታቸው አስቀድሞ ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ግራት በአል ግብሪ ቤተ መንግሥት የተገነባበት ወቅት፣ ሦስተኛው ደግሞ የቤተ መንግሥቱ እድሳት የተካሄደበት ነው፡፡ በአካባቢው የተገኙ መካነ መቃብሮች ለዚህ ማስረጃ እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡

በአስፋወሰን አስራት የተሠራ ጥናት የይሓ ግንብ ከተሠራበት ግብዓት አንስቶ አካባቢው የተመረጠበትን ምክንያት በጥልቀት የሚያስረዳ ነው፡፡ ግንቡ የተሠራባቸው የድንጋይ ጡቦች ከየት እንደተጓጓዙ በትክክል ባይገለጽም የዒዲግራት ሳንድ ስቶንና የተከዜ ሳንድ ስቶን ካላቸው ቅርበት አንፃር መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡

ብዙ ተመራማሪዎች ይሓ ለዋና ከተማነት ተመራጭ የሆነችው ለም አፈር ያለው ቦታ ስለሆነ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ይሓ ለኤርትራ ቅርብ መሆኑ በቀይ ባሕር ለመነገድ መመቸቱ ከተመረጠበት ምክንያት መካከል መሆኑን የሚገልጹም መረጃዎች አሉ፡፡ በአካባቢው ዝሆንና ዋልያ መገኘታቸውም ተመራጭ እንዳደረገው ይገልጻል፡፡ በይሓ ግንብ የዋልያና ዝሆን ምስሎች ተቀርፀው መገኘታቸው እንስሳቱ ይሰጣቸው የነበረውን ቦታ ያመላክታሉ፡፡

ግንቡ ለዘመናት ተጠብቆ ለመቆየቱ እንደምክንያት ከሚነሱት አንዱ በአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን መገንባቱን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ መገኘቱ ከሰው ሠራሽ ችግሮች ቢጠብቀውም፣ ግንቡ የተሠራባቸው ግብዓቶች በአየር ንብረት መለዋወጥና በመሰል ተፅዕኖዎች እንዳይጎዳ የሚያስችሉ መሆናቸው ያለው ጠቀሜታ ተመልክቷል፡፡

ትግራይ አካባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች የይሓ ግንብን የኪነ ሕንፃ ጥበብ የተከተሉ እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የይሓን ሥልጣኔ የወረሱት አክሱማውያንም ይህንኑ ተከትለው ነበር፡፡ በቅድመ አክሱማዊ ሥልጣኔ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚጠቀሱት ሐውልቲ መላዞ፣ አዲስ ግላማ፣ ቶኮንዶ፣ ይሓና ኮአይቶ ሲሆኑ፣ ይሓ ከሁሉም ዕድሜ ጠገቡ ነው፡፡

በአካባቢው የመጀመሪያ ሰፋሪዎች የነበሩት ሳባውያን ለአክሱማይት መንግሥት መሠረት ጥለዋል፡፡ በአክሱማዊ መንግሥት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ኢዛና ቀዳሚነት በመንግሥት ደረጃ ኢትዮጵያ ክርስትናን ተቀበለች፡፡ የወቅቱ መገበያያ ሳንቲሞች የመስቀል ምልክት ያለባቸው ሲሆን፣ እንደ ይሓ ባሉ ቅድመ አክሱማዊ መንግሥት ሥፍራዎች ጨረቃና ሌሎችም ምስሎች መገበያያ ላይ ይከተሉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

 ከሦስት ምዕት ዓመት በላይ የሚሆን ታሪክን በጉያዋ የያዘችው ይሓ፣ አሁን ላይ ይፋ ከሆኑትም በላይ ለወደፊት በርካታ ቅርሶች እንደሚገኙባት የተመራማሪዎች እምነት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግራት በዓል ግብሪ ቤተ መንግሥት፣ የአቡነ አፍፄ ቤተ ክርስቲያንና የይሓ ግንብ በስፋት እየተጎበኙ ይገኛሉ፡፡

No comments:

Post a Comment