Saturday, January 24, 2015

‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ውለታ ፈላጊ ባትሆንም ለሀገር ባህልና ለቅርስ ጥበቃ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከሚነገረው በላይ ነው፡፡›› ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል

አንድ አድርገን ጥር 17 2007 ዓ.ም
  • ከ80 እና ከ90 በላይ በሀገሪቱ የሚጎበኙ ቅርሶች ታሪካዊ ቦታዎች የቤተ ክርስቲያኒቷ ናቸው፡ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኗ  ሃይማኖትን ከሀገር ፍቅር ጋር  አያይዛ ስትሰራ መቆየቷንና  አሁንም እየሰራች እንደሆነ ያመላክታል፡፡
  • አንድ ሰባኪ መጀመሪያ መስበክ ያለበት ራሱን ነው፡፡ እኛ ሱፍ ለብሰን ለምን የሀበሻ ልብስ አትለብስም ማለት ይህ ማደናገር እንጂ ማስተማር አይደለም፡፡ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስናስተምር እኛ ራሳችን በዚያ ውስጥ ማለፍ መቻል አለብን፡፡ ራሱን ያልሰበከና ሕይወት የሌለው ሰባኪ አደናጋሪ ነው እንጂ ሰባኪ አይደለም፡፡
  • ሃይማኖታዊ በዓላትን ከሌላ ነገር ጋር ቀላቅሎ ማቅረቡ እና ከእምነቱ ጋር አብሮ የማይሄዱ ነገሮችን አጫፍሮና አገናኝቶ  ማቅረቡ ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን ያለው አካሄድ ግን‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› ዓይነት ነው፡፡
  • ትውፊት ተጠብቂ የሚቆየው በሀገር ውስጥም በውጭም የሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ሥርዓቷ ሳይፋለስ ወጥ ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡
  •  የመስቀል በዓል ነው ካልን ሌላ ቅልቅል አያስፈልገውም፡፡የመስቀል በዓል የቤተ ክርስቲያናችን በዓል እንጂ የባህል በዓል አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የመስቀል በዓልን የምታከብረው በሃይማኖት በዓልነቱ ነው፡፡ ዩኔስኮም ሲመዘግበው የሃይማኖት በዓልነቱ እንጂ የባህል ብሎ አይደለም፡፡ ከነበረው ይዘት የሚለቅ ከሆነ ዩኔስኮም ከመዝገብ ይፍቀዋል፡፡
  • ማንኛውም የውጭ ሀገር ጎብኚ የሚመጣው  ጥምቀትን ለማየት ነው እንጂ የካርኒቫል በዓል አለ ብሎ አይመጣም፡፡ እነዚህ ፍልስፍናዎች የሴኩላሪዝ ተጽህኖዎች ናቸው፡፡ አላማው ሃይማኖትን ማዳከም ነው፡፡

ምንጭ ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ

በአደባባይና በአውደ ምህረት ስለሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት ሃይማኖታዊ ይሁኑ እንጂ ከመንፈሳዊ በዓላቱ ጋር ተያይዘው የሚከናወኑ ባህላዊ እና ሌሎች ኹነቶች ኢትዮጵያዊማንነትን የሚገልጹ ናቸው፡፡ እነዚህን በዓለም አቀፍ መዝገብ ተመዝግበው የምናከብራቸው እና በብሔራዊ ደረጃ የሚከበሩ በዓላት አሁን ላይ እክብካቤ እና ጥበቃ የማይደረግላቸው ከሆነ ወደፊት በሌሎች የእነት ተቋማት የባለቤትነት ሽሚያው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም፡፡ ቀድሞ ጥምቀትንና መስቀልን የመሰሉ በዓላትን የማያከብሩ የእምነት ተቋማት በአሁኑ ሰዓት እያከበሩ ይገኛሉ ፤ ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠችላቸው ቀመር ‹‹ደብረዘይት›› ፤ ‹‹ሆሳህና›› እና ‹‹ስቅለት›› ማለት ጀምረዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊትም ኅዳር 6 የምናከብረውን የእመቤታችንን በዓል እኛም ይመለከተናል በማለት ደብረብርሃን የሚገኝው የካቶሊክ እምነት ተቋም እንደ አዲስ አንድ ብለው በ2002 ዓ.ም ማክበር ጀምረዋል፡፡ እየዋለ ሲያድር የባለቤትነት ጥያቄውም ቢሆን በሌሎች እየተነሳ ሊሄድ ይችላል፡፡ እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮችን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከአቡነ ሳሙኤል ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡ እነሆ…

ስምዐ ጽድቅ ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታከብራቸው መንፈሳዊ በዓላት ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር ያላቸው ጠቀሜታ እንዴት ይታያል?

ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ፡- መንፈሳዊ በዓላት ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር ብዙ ነገር ጠቃሚ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ በዓላት አከባብ እምነታችን ፤ ሥርዓታችን ፤ ባህላችንና ቋንቋችን ይገለጻል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን  በመንፈሳዊያት በዓላቷ አማካይነት  በተለይ ከራሷ ይልቅ ለሀገር ብዙ ጠቅማለች፡፡ ጥንትም አሁንም እየጠቀመች ያለችው ሀገርን ነው፡፡ በየዓመቱ የቱሪዝም ፍሰቱ  ሲጨምር ታያለህ፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ሆቴሎችና አስጎብኚዎች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡በዚህም መንግሥት ተጠቃሚ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ውለታ ፈላጊ ባትሆንም ለሀገር ባህልና ለቅርስ ጥበቃ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከሚነገረው በላይ ነው፡፡ በየበዓሉ ቤተ ክርስቲያኗ ማንነቷን ፤ እምነቷን ፤ ሌላን ስርዓቷን  ጠብቃ እንደቀደሙት አባቶቻችን  እስከዛሬ ድረስ ማክበሯ ትልቁ ጠቀሜታ  ነው፡፡ ገዳሞቻችን ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን ፤ መንፈሳዊ ቅርሶቻችን ይጎበኛሉ ፤ ተጠቃሚዋ ግን ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን ሌላው አካል ነው፡፡ ከ80 እና ከ90 በላይ በሀገሪቱ የሚጎበኙ ቅርሶች ታሪካዊ ቦታዎች የቤተ ክርስቲያኒቷ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኗ  ሃይማኖትን ከሀገር ፍቅር ጋር  አያይዛ ስትሰራ መቆየቷንና  አሁንም እየሰራች እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ከዚህ ውጪ ቤተ ክርስቲያኗ ከቀደምት አባቶቻችን የተቀበልነውን ሃይማኖታዊ መንሳዊ በዓላት ይዘት ፤ ሥርዓትና አከባበር ሳይፋለስ ተጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ መቻሏ ሊያስመስግናት ይገባል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ ደረጃ የሚከበሩ የቤ ተክርስቲያናችን መንፈሳዊ በዓላት በሥርዓት ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ምን ይደረግ ይላሉ?

ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ፡- መንፈሳዊ በዓላት በሥርዓት ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ሳይለቅ በሥርዓት ፤ በአለባበስ እና በመሳሰሉት ማስጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ትልቁ የቤተ ክርስቲያናችን አንጋፋነትም ፤ አማኞቿም ሌላውም እንዲወድዷትና  እንዲናፍቋት የሚያደርጋቸው ይኽ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በየትም ሀገር ብትሔድ ሃይማኖቱንና ማንነቱን አይቀይርም፡፡ ትውፊት ተጠብቂ የሚቆየው በሀገር ውስጥም በውጭም የሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ሥርዓቷ ሳይፋለስ ወጥ ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ እስከታች ያለው ምእመን የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ መታወቅ ያለበት ግን ለዓለም አቀፍ ገጽታ ብለን የምናከብረው መንፈሳዊ በዓላት የሌሉን መሆኑን ነው፡፡ በተለይ የምዕራባውያን የባህል ተጽህኖ እንዳይስፋፋ በየመድረኩ ትምህርት መሰጠቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተሰብ ላይ ስራ መስራት አለብን፡፡ ቤተሰቦች ደግሞ ልጆቻቸው ማስተማር ይችላሉ፡፡ ሃይማኖታዊ በዓላት ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ሥርዓታቸውን እንዲጠብቁ በየሰንበት ትምህርት ቤቶች ፤ በካህናት ማሰልጠኛ ተቋማት በየአብነት ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ አባቶች ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ማድረግ ካልተቻለ ወደፊት የትኛው የኔ ነው? የሚል የባለቤትነት ጥያቄ ይገጥመናል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት በሁሉም ዘርፍ ማስተማርና መመካከር ይገባል፡፡
 ስምዐ ጽድቅ፡-  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶች በመንፈሳዊ በዓላት እየሰጡት ያለው አገልግሎት እጅግ አስደሳችና አኩሪ ድርጊት እየሆነ መጥቷል፡፡ ምን አልባት እነዚህ ወጣቶች ከበዓላት በኋላ መሰባሰባቸውን እንዳይተዉ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት? ከወጣቶችን ምን ይጠበቃል?

ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ፡- ወጣቶች በበዓላት ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን እየሰጡት ያለው አገልግሎት በእጅጉ ያስደስታል፡፡ ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሃይማኖታቸው ሲሉ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ እንደ አሁኑ አይሁን እንጂ ቀደም ሲል ስለ ሃይማኖታቸውና ስለ ሃገር ፍቅር ሲሉ ገና በለጋ እድሜአቸው የእናት አባታቸውን ቤት ትተው ወደ አብነት ትምህርት ቤት የሚሄዱት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ዛሬም ወጣቶች  በሚችሉት ሁሉ በመንፈሳዊ በዓላት ላይ  እያሳዩት ያለው እንቅስቃሴ ከቤተ ክርስቲያን እቅፍ እንዳልወጡ ያሳየናል፡፡ እነዚህ ወጣቶች የሚይዛቸውና የሚደግፋቸው ቢያገኙ ከዚህም በላይ መስራት ይችላሉ ባይነኝ፡፡

በመንፈሳዊ በዓላትጊዜ የሚታየው የወጣቶች አገልግሎት በዚህ ብቻ ነው ወይ መገደብ ያለበት ስንል ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት  በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ መሥራት እንዳለብን ሁኔታዎች ያመለካታሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች በመንፈሳዊ መዝሙርና አገልግሎት ተወስነው እንዲቀሩ ማድረግ የለብንም፡፡ ይህን ስብስባቸውን ወደ አንድ በማምጣት የተሻለ ነገር እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ አገልግሎታቸው የበለጠ እንዲያሳድጉት ሃይማኖታቸውን ፤ ታሪካቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው በሥርዓት እንዲሄዱ በየአጥቢያቸው በሰንበት ትምህርተ ቤት ሥር እንዲታቀፉ ማድረግ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል በሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን በሥጋዊ ኑሯቸውም ላይ ተጽህኖ እንዳይገጥማቸው ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ወጣቶች የኢኮኖሚ ችግር አለባቸው፡፡ በዚህም አብዛኞቹ ወጣቶች የቤተሰብ ጫና ሆነው ይታያሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ በአረቡ ዓለም ያሉ ወጣቶች የዚህ ቤተ ክርስቲያን አባላት የነበሩና በቤተ ክርስቲያን አጸድ ውስጥ ያደጉ ናቸው፡፡ በማያውቁት ሀገር እምነትና ቋንቋ  ሥር ወድቀዋል፡፡ እንዲህ እንዳይሆን ከዚህ ስራ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ አጫጭር ስልጠናዎችን  በመስጠት እዚሁ አገራቸው በራሳቸው ቋንቋ እና እምነት  መሥራት እንዲችሉ ብናደርጋቸው እነሱም አይጎዱም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በአገልግሎቷ ትረካለች፡፡ ኢኮኖሚ ተጽኖ ያለበት ወጣት  የእምነት መሸርሸርና የአእምሮ ድካም ይታይበታል፡፡

እነዚህ ወጣቶች ከእነዚህ ተጽዕኖዎች ማምለጥ እንዲችሉ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን በመዳሰስ ራሳቸውን  የሚመሩበት መንገድ ካመቻቸን ለበለጠ አገልግሎት እንዲዘጋጁ ማድረግ እንችላለን፡፡ ከላይ ከቤተክህነት ጀምሮ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ፤ በየሰንበት ትምህር ቤቶች ፤ በየሀገረ ስብከቱ የወጣቶችን ፍላጎትና ልምድ እያጠኑ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግራዊ ማድረጊያ ገንዘብ በማፈላለግ ሥራ  መፍጠር አንዱ መንገድ ነው፡፡ ወጣቶችን በዚህ መንገድ መያዝ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣቶች ራሳቸው ፍቃደኛ መሆን መቻል አለባቸው፡፡ በበዓላት ጊዜ እንደሚሰባሰቡት ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወታቸውንም እያጎለበቱ ወደ ልማት ለመሰማራት ነገ ዛሬ ሳይሉ ዝግጅቶች ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት ላይ የቤተ ክርስቲያናችንና የሃገራችን ማንነት ከፍ ብሎ እንዲታወቅ ቤተ ክርስቲያን መድረኩን እንዴት ነው መጠቀም ያለባት? የትኛውን ነው አጉልታ መናገር ያለባት?

ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ፡-  በዓለም አቀፍ ድርጅቶች  የተመዘገቡ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ በዓላት ለቤተ ክርስቲያን ፤ ለሀገርም ብዙ ጥቅሞችን እያስገኙ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ በቅርቡ በዓለም  አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የመስቀል በዓል ማንሳት ይቻላል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ አይተናል፡፡ ከሃይማኖታዊ በዓሉ ይልቅ ሌላው ኹነት ትኩረት ሲሰጠው ተመልክተናል፡፡ በዓሉ የመስቀል በዓል ነው ካልን ሌላ ቅልቅል አያስፈልገውም፡፡ የመስቀል በዓል የቤተ ክርስቲያናችን በዓል ነው፡፡ እንዳንዶቹ ገብቷቸውም ይሁን ሳይገባቸው የመስቀል በዓል የባህል በዓል ነው ሲሉ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን የመስቀል በዓል የባህል በዓል አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የመስቀል በዓልን የምታከብረው በሃይማኖት በዓልነቱ ነው፡፡ ዩኔስኮም ሲመዘግበው የሃይማኖት በዓልነቱ እንጂ የባህል ወይም የቱሪዝም ቀን ብሎ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከነበረው ይዘት የሚለቅ ከሆነ ዩኔስኮም ከመዝገብ ይፍቀዋል፡፡ የቱሪዝም ቀን ሌላ ጊዜ ሊደረግ ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት አካሄዶች በተደጋጋሚ ይታያሉ፡፡  ይህ ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት ስታከብረው  የነበረ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ በዓል ነው፡፡ የገና ፤ የጥምቀት የመሳሰሉት ፍጹም ሃይማኖታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በዓላት ናቸው፡፡ እነዚያንም መቀየር አይቻልም፡፡ እንዲህ አይነት መንፈሳዊ በዓላት ሲከበሩ ቤተ ክርስቲያኗ የበዓሉ ባለቤት ናትና በዕለቱ መድረኩን መጠቀም ያለባት ራሷ ናት፡፡ ከሁሉም በላይ በመድረኩ ላይ በመድረኩ መነገር ያለበትም ስለ ሃይማኖታዊ በዓሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ጎንደር ላይ የጥምቀትን በዓል የካርኒቫል ስም ለመስጠት ተሞክሮ  ነበር፡፡ ይህ አሁን እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ወደፊትም ቢሆን ከእምነቱ ጋር አብሮ የማይሄዱ ነገሮችን አጫፍሮና አገናኝቶ  ማቅረቡ ተገቢ አይደለም፡፡

ማንኛውም የውጭ ሀገር ጎብኚ የሚመጣው  ጥምቀትን ለማየት ነው እንጂ የካርኒቫል በዓል አለ ብሎ አይመጣም፡፡ እነዚህ ፍልስፍናዎች የሴኩላሪዝ ተጽህኖዎች ናቸው፡፡ አላማው ሃይማኖትን ማዳከም ነው፡፡ ቱሪስት ሆኖ ዘፈን ለመስማት የሚመጣ የለም ፤ ያሬዳዊ ዜማ ለመስማት ነው የሚመጣው፡፡ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን አለባበስ  እና የቤተ ክርስቲያንን ንዋየ ቅድሳት ለማየት ነው የሚመጡት፡፡  ስለዚህ ሃይማኖታዊ በዓላትን ከሌላ ነገር ጋር ቀላቅሎ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም፡፡ ከልማቱ ጋር ማገናኝቱ ፤ ከሰላም ጋር ማገናኝቱ ጥሩ ነው፡፡ ተጠቃሚው ሕዝቡ ነውና፡፡

 እነዚህ ብሔራዊ በዓላት ቤተ ክርስቲያኗ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ስታከብራቸው ያቆየቻቸውን መንፈሳዊ በዓላት መልካቸውንና ገጽቸውን እንዲለውጥ ማድረግ አግባብ አይደለም፡፡ ይህን የመጠበቅ ሓላፊነት ያለባት ቤተ ክርስቲያኗ ናት፡፡ አሁን ያለው አካሄድ ግን‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› ዓይነት ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡-  በአጠቃላይ በአውደ ምሕረትም ሆነ ሕዝብ በተሰበሰበበት የሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት በሙሉ ባለቤትነታቸው የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በተለይ ጎልተው የሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት ሽሚያ በሚመስል ሁኔታ አንዳንድ መሳሪያዎችን ሳይቀር እየተጠቀሙ በዓሉን ለመጋራት የሚጥሩ ወገኖች አሉ፡፡ አንዳንዶችም አብረው ማክበር ጀምረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያኗ መብቷን እንዴት ነው ማስከበር የምትችለው?

ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል፡-  የሚገርመው የዛሬ ስምንት ዓመት ይመስለኛል አንተ ከላይ ባነሳህው ጥያቄ ዙሪያ እኔ ራሴ ለሲኖዶስ ‹‹ የአእምሮ ንብረት ባለቤት›› የሚል አንድ ጥናት አቅርቤ  በሲኖዶስ ውሳኔ አግኝቷል፡፡ ይህን የማስጠበቅ ሓላፊነት የቤተ ክርስቲያኗ ነው፡፡ ያሬዳዊ ዜማን ሌሎች ሲጠቀሙበት እንመለከታለን ይህ ስህተት ነው፡፡ ያሬዳዊ ዜማን ማንም ሊጠቀምበት አይችልም ፤ የራሳችን ንብረት እና ሀብት ነው፡፡ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ( ከበሮው ፤ ጽናጽሉ ፤መቋሚያው ፤ ቅዳሴው ፤ ልብሰ ተክሊሉና ሻሹ ሳይቀር) ማንም ሊዘምርበት አይገባም፡፡ 14ቱ ቅዳሴያት የእኛ ናቸው፡፡ አሐዱ አብ ቅዱስ ብሎ መቀደስ በራሱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  የሚፈጸም ሃይማኖታዊ ጸሎት ነው ፤ ይህ የማንም አይደለም፡፡

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀድሞ የማያውቁትን ፤ ለመደባቸውን የእነሱ ያልሆነውን ምእመናኑን ለማደናገር እንዲያመቻቸው መንፈሳዊ በዓላትንና የቤተ ክርስቲያኗ ንብረት የሆኑትን አንዳንድ መሣሪያዎችን  ሳይቀር ሲጠቀሙ እናያለን፡፡ ይኼ እንዲስተካከልና ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ብሎ ወስኗል፡፡ ችግሩ ያለው አስፈጻሚው አካል ላይ ነው፡፡ የቤቱ አቅም ማነስ ካልሆነ በስተቀር ማንም አካል የቤተ ክርስቲያኗን የኔ ብሎ መጠቀም አይችልም፡፡ ይህን ማስከበር ካልተቻለ የቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

በአንጻሩ የመስቀልን በዓል ስናከብር ሌሎች የእነሱ ያልሆነውን እናከብራለን ካሉ ፤ መቼ ነው የጀመሩት ? ለምን ጀመሩት ? እምነታቸውስ ይፈቅዳል ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ እና ሌሎች ነገሮችን ሥር ሳይሰዱ ከወዲሁ መፍትሄ ቢያገኙ  መልካም ይመስለኛል፡፡  ያለበለዚያ ግን  አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች  በጣም አሳፋሪ አደናጋሪም ናቸው፡፡

በመሠረቱ ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያኒቷን መለያየት አይቻልም፡፡ ለዚህም የሀገሪቱ የታሪክ ሂደት መስካሪ ነውና፡፡ ስለዚህ የሌሎች ተቋማት ከየት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚያ አካባቢ እንዲህ ያለ ቀኖና እና አገልግሎት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹ ከአውሮፓ እና ከምስራቁ ዓለም የመጡ ናቸው፡፡ እኛ እና እነርሱ ምን እና ምን እንደሆንን ዓለም ያውቀዋል፡፡ ብዙ ምዕመናን ኪዳን ሲያደርሱ ሲያይዋቸው ሊታለሉ ይችላሉ ፤ አንዱን ቅዳሴ ለአራት ከፍለው ግማሽ ቅዳሴ ሲቀድሱ ለካስ ከዚህም አሐዱ አብ ብለው ይቀድሳሉ ፤ ለካስ ተንሥኡ ለጸሎትና እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ይባላል በሚል ግራ መጋባት የለባቸውም፡፡ ስለዚህ የራሳችንን የሆኑትን ምእመናን በዚሁ ጉዳይ ላይ ትምህርት መስጠት አለብን፡፡
 ስምዐ ጽድቅ ፡- ካህናት አባቶች ፤ ወጣቶች ፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ፤ ማኅበራት የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ በዓላት ተጠብቀው እንዲሔዱ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አካላት ድርሻቸው ምንድነው?

ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ፡ እነዚህ አካላት የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ በዓላት ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ሕግና ሥርዓት ጠብቀው ማስጠበቅ የሚችሉ ወይም ቀጥተኛ ተዋናኝ የሚሆኑ ናቸው፡፡ የመንፈሳዊ በዓላቱ ይዘትና ቀኖናዊ ሥርዓት እንዳይለቅ አንዱ ለሌላው ማስተማር ላይ ትኩረት ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ምዕመናኑ ስለ መንፈሳዊ በዓላት ሥርዓት መጠበቅ ያላቸው ግንዛቤ ማደግ አለበት፡፡ ወደፊት አንድ ምዕመን  ወይም ወጣት ስለሚያከብረው መንፈሳዊ በዓል ከአለባበስ ጀምሮ የራሱን እምነትና ማነነት መግለጽ ካልቻለ ሥርዓቱን ሊጠብቅ አይችልም፡፡

ሰናስተምር ግን መጀመሪያ እና ራቻስን መማር አለብን፡፡ አንድ ካህን ወይም ሰባኪ መጀመሪያ መስበክ ያለበት ራሱን ነው፡፡ እኛ ሱፍ ለብሰን ለምን የሀበሻ ልብስ አትለብስም ማለት ይህ ማደናገር እንጂ ማስተማር አይደለም፡፡ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስናስተምር እኛ ራሳችን በዚያ ውስጥ ማለፍ መቻል አለብን፡፡ ራሱን ያልሰበከና ሕይወት የሌለው ሰባኪ አደናጋሪ ነው እንጂ ሰባኪ አይደለም፡፡ ራሱን አስገዝቶ ከሆነ ግን ሌሎች ሃይማኖቱንና እንዲወድዱ ፤ ሥርዓቱንና ቀኖናውን እንዲያከብሩ ለማድረግ ያን ጊዜ ምቹ ይሆናል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶቹም በመንፈሳዊ በዓላት እስከ ዛሬ ሲያደርጉት እንደነበረው ጠበቅ አድርገው መቀጠል አለባቸው፡፡ እነርሱ ሕጉንና ሥርዓቱን የሚያከብሩ ከሆነ ሌሎችን እንዴት መሳብ እችላለሁ ብሎ መነሳት ይቻላል፡፡ አሁን ግ እነርሱ ለሥርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ፤ በመንፈሳዊ በዓላት ጊዜ ማንም ሳይሰበስባቸው ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ያሉ ወጣቶች አባል ማድረግ እና መደገፍ ይጠበቅባችዋል፡፡
ማኅበራትን በተመለከተ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት ደስ ይላል፡፡ አንድ ወይም ሁለት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጎልተው መውጣት መቻል አለባቸው፡፡በተለይ  በየዓመቱ የምናከብራቸው መንፈሳዊ በዓላት ጊዜ የእኛ የሆነውን ሥርዓት ለዓለም ለማሳየት በዝተውና ደምቀው መታየት አለባቸው፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፡-  ስለሰጡን ቃለ ምልልስ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡
ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ፡-  እኔም አመሰግናለሁ




3 comments:

  1. Abatache bsw abn saml egezabher amlak regim edma yestlen aman!!

    ReplyDelete
  2. t 11:21 AM

    Abatache bsw abn saml egezabher amlak regim edma yestlen aman!!

    ReplyDelete
  3. ለቤተክርስቲያን የሚያሰቡ አባቶችን አምላክ ያብዛልን.....

    ReplyDelete