Monday, February 6, 2012

ስለ ብርሃን እንዲመሰክር ስለ ተላከው መብራት


 (የዮሐንስ ወንጌል የሦስተኛው ሳምንት ጥናት)!

ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክርዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛውብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።ዮሐ.16-9

 አካላዊ ቃል ከአባቱ ዕሪና ሳይለይ ሰው ሆኖ ተገልጧልና ስለዚሁ ድንቅ ነገር ይመሰክር ዘንድ መልአክ ሳይሆን ዮሐንስ የሚባል ሰው ተላከ /አውግስጢኖስ/፡፡ ሌሎች ነብያት ክርስቶስይወርዳል ይወለዳልብለው ትንቢት ቢናገሩም ክርስቶስን ሊያዩት ወደዱ እንጂ አላዩትም /ማቴ.1316-17/ ሐዋርያትምወረደ ተወለደብለው አስተማሩ እንጂከእኛ በኋላ ይመጣልአላሉም /ሐዋ.42/፡፡ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከእርሱ የሚበልጥ የሌለ መጥምቁ ዮሐንስ ግን እንደ ነብይከእኔ በኋላ ይመጣል እንደ ሐዋርያምይመጣል ያልኳችሁ እርሱ ነውእያለ ያስተምር ነበር /ዮሐ.11530 ሄሬኔዎስ/፡፡ ወንጌላዊው ስለ አካላዊ ቃል ቀዳማዊነት እየመሰከረልን ቆይቶ አሁን ደግሞ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ጨምሮ የሚነግረን ምስክርነት በሁለት ወይም በሦስት ስለሚጸና ነው /ዘዳ.19:15 .ቄርሎስ/፡፡

 መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የመሰከረው ምስክርነት እውነተኛው ብርሃን የሰው ምስክርነት አስፈልጐት ሳይሆን ሰዎች ስለ ብርሃን በሚረዱትና እነርሱን በሚመስል አገልጋይ (ዕሩቅ ብእሲ) ሲነገራቸው አምነው እንዲድኑ ስለተፈለገ ብቻ ነው /ዮሐ.534 .ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም ዮሐንስ ሲመሰክርለት የነበረው ብርሃን ዓለም (የሰው ልጅ) በመላ አጥቶት የነበረ ብርሃን ነው /ኢሳ.92 አርጌንስ/፡፡ አዎ! ዮሐንስ ከአማናዊው ብርሃን የተነሣ የሚያበራ መብራት ነበር እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም /ዮሐ.535/ አማናዊው ብርሃንስ በመስቀል ላይ የዓለምን ጨለማ ያስወገደው የእግዚአብሔር በግ ነው /ኤፌ.213-17 አውግስጢኖስ/፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያውዓለምን የፈጠረ እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ሥጋ ለብሶ መጣ፤ ተገለጠ፤ ረቂቅ ሲሆን ገዝፎ ታየ፤ ዳሰስነውምያለን /1ዮሐ.11-2 .አትናቴዎስ/፡፡ በእውነቱ ለዚህ አንክሮ ይገባል! እርሱ የማይደፈር ግሩም ነው፣ በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፡፡ እርሱ የማይመረመር ልዑል ነው፣ በእኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብር ሥጋን ተዋሐደ፡፡ እርሱ የማይያዝ የማይዳሰስ እሳት ነው፣ እኛ ግን ያዝነው ዳሰስነውም /አባ ሕርያቆስ/፡፡

 ነገር ግን እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ቢመጣም ሆን ብለው ዓይነ ልቡናቸውን ለጨፈኑ አላበራም፤ አያበራምም /ማቴ.1314-15/፡፡ እነዚህ ዓይነ ስዉራን (ልበ ስሑታን) የእግዚአብሔር ነገር ሲነገራቸውም እንደ ሞኝነት ይቆጥሩታል /1ቆሮ.214 .ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ እኛም ብንሆን ልቡናችን በኃጢአት ጨለማ ከተጋረደ ብርሃኑን ማየት አንችልም፤ ኃጢአትን ከእኛ ስናርቅ ግን ወደ እውነተኛው ብርሃን እየቀረብን እንሄዳለን /ማቴ.58 .ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ/፡፡ ይህንን ብርሃን ለማየት ዓይነ ልቦናችን የተከፈተ ሲሆን በብርሃኑ እንመላለሳለን /.ቄርሎስ/፡፡ በእርግጥም በጽድቅ ጐዳና የሚሄድ ሰው መላ ዘመኑ የብርሃን ሕይወት ነው /ዓይነ ስወሩ ዲዲሞስ/፡፡

በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱምከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።ዮሐ.110-13

 እንዴት ያለ ድንቅ ቸርነት ነው?! አካላዊ ቃል በዓለም የነበረ ቢሆንም ከዓለም ጋር እኩል ዕድሜ አልነበረውም /መዝ.902/፡፡ አመጣጡም እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በዓለሙ የሌለ ሁኖ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወንጌላዊው እንዲህ እንዳናስብዓለሙም በእርሱ ተፈጠረብሎ ይቀጥላልና፡፡ በዚሁ ቃል መሠረት ማንም ሰው ይመንም አይመንም የወልድ ቅድመ ዓለም መኖር አያስቀረውም፡፡ የቃልን እግዚአብሔርነት አያጐድለውም፡፡ በዚህ ዓለም ጥበብ የሚመላለስ ሰውስ ይህ ምሥጢር እንዴት ሊገባው ይችላል /1ቆሮ.214/?! የሚገርመው ደግሞ ዓለም ያላወቀችው ወልድን ብቻ ሳይሆን አባቱንም ጭምር መሆኑን ነው /ዮሐ.1725 .ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡

ሰው ወዳጅ የሆነው አምላካችን እኛ በፈቃዳችን የማይበላውን በልተን ብንቆሽሽም እንደ ቆሸሽን እንቀር ዘንድ አልወደደም፡፡ ስለዚህ እርሱ ራሱ በደሙ ካልወለወለን በስተቀር መልአክም ይሁን ሰው ሊያስታርቀን ስላልቻለ ፍቅሩ አስገድዶት የእኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ መጣ/.አትናቴዎስ/፡፡ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት- የሰው ፍቅር ወልድን ከዙፋኑ ስቦ ጎትቶ አወረደው፤ እስከ ሞት ድረስም አደረሰው /አባ ሕርያቆስ/፡፡ አንድ ዐይነ ስውር ሰው ፀሐይን ባያይ ፀሐይዋ ስለሌለች ሳይሆን እርሱ ሊያያት ስላልቻለ ነው፡፡ ይህንን የክርስቶስ ፍቀር ያላወቁ ሰዎችም እንዲህ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፡- “የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ (ዲያብሎስ) የማያምኑትን አሳብ አሳወረእንዲል /2ቆሮ.44 .ቄርሎስ/ የሰው ልጅ በሙሉ ለእግዚአብሔር በእግዚአብሔር ቢፈጠርም የዚህ ዓለም ገዢ የተባለው ዲያብሎስ ግን እስራኤል ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሕግ በማስተው፣ አሕዛብን ደግሞ በአምኮተ ጣዖት በማሳወር ፈጣሪያቸውን እንዳያውቁት አደረገ /ኢሳ.12-4/፡፡ መዝሙረኛው ይህ ነገር ቢያስደንቀውአእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለአለ /መዝ.4920 .ቄርሎስ/፡፡

 ተወዳጆች ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር እንዴት እንደወደደን ታስተውሉ ዘንድ እንማልዳችኋለን /1ዮሐ.31/፡፡ ወልድ እኛን ወንድሞቹ ያደረገን ብቻውን ስለሆነ አልነበረም ፡፡ ወንድሞቹ ያደረገን ፍቅሩ ብቻ ነው፤ ወንድሞቹ ያደረገን የዘላለምን ሕይወት እንድንወርስ ስለወደደ ብቻ ነው፤ እርሱ ከእኛ ይጠቀም ዘንድ አላዳነንም /ዮሐ.316/፡፡ እርሱ የመጣው ለተቀበልነው ሁሉ በጸጋው የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ሥልጣን ሊሰጠን ነው /ዮሐ.112/፡፡ ታድያ እርሱ ሊያነሣን ወዶ ሳለ እኛ አንነሣም የምንለው ለምንድነው? ልጅነትን አንቀበልም ብለንስ ወድቀን እንቀር ዘንድ ለምን እንመርጣለን? /አውግስጢኖስ/፡፡ እርሱአማልክት ዘበጸጋ ናችሁብሎ የልዑል ልጆች ሊያደርገን ፈልጐ ሰው ሲሆንልን እኛ እንደ ዲያብሎስ ለምን ወድቀን እንቀራለን? /መዝ.816-7 ቴዎዶር ዘስይርጥ/፡፡ ስለዚህ ከተዋሕዶ ብርሃን ርቃችሁና ክርስቶስን ባለማወቅ ጨለማ ውስጥ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ ሥልጣንን እንድታገኙ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ /ማቴ.2819 .ባስልዮስ/፡፡ በክርስቶስ ስታምኑና መዳናችሁን ወደምትፈጽሙበት ልምምድ ስትገቡ ከወንድና ከሴት ፈቃድ ሳይሆን ከሥላሴ ፈቃድ ዳግመኛ ትወለዳላችሁ /ዮሐ.113/፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ይወዳችኋል፤ ይጠራችኋልም፡፡ ሰማይና ምድር የማይወስኑት አምላካችሁ በጠባብ ደረትና በአጭር ቁመት ከሴት የተወለደው እናንተ ከእርሱ ትወለዱ ዘንድ ነው፡፡ የሞተላችሁም እናንተ ሞት ይቀርላችሁ ዘንድ ነው /አውግስጢኖስ/፡፡

 የሥላሴን ልጅነት አግኝታችሁና ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለተጋባችሁ ለእናንተም  ወንጌላዊው ሲናገርየእግዚአብሔርን ልጅነት ሰጣቸውሳይሆንየእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸውእንዳለ አስተውሉ፡፡ ምክንያቱም በጥምቀት የተከፈተልንን መዳን የምንፈጽመውና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ሙላት የምንደርሰው ልጅነታችንን እስከ መጨረሻ ያለነቀፋ ስንይዝ ብቻ ነው /ማቴ.1022/፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችንን ከእኛ ንዝህላልነት ካልሆነ በስተቀር ማንም መልሶ ሊወስዳት አይችልምና /ማቴ.251-13 .ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ አዎ! ይህን ስናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ወዳጆች ነን እንጂ ባሮች አይደለንም፤ ልጆችም ከሆንን ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ነን /ሮሜ.817 ገላ.47 .ዮሐንስ ዘደማስቆ/፡፡

 ስለዚህ ሁላችንም የመዳናችን ቀንድ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እንመለስ፡፡ እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ተቀምጠን ለነበርን ለሁላችን ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን ያወርሰን ዘንድ የመጣ እውነተኛ ብርሃን ነው /ሉቃ.179 2ቆሮ.29/፡፡ እንግዲያስ ሰው ብቻ መሆን ይብቃን፤ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆንም ልጅነትን እንቀበል፡፡ ከተቀበልን በኋላም ሁል ጊዜ እንደ መላእክት ክብሩን እናይ ዘንድ ልበ ንጹሐን እንሁን /ማቴ.58 አውግስጢኖስ/፡፡

 መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ እኛ ሥራ ሠርተን አንበቃምና ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ብዛት መንግሥቱን ያድለን፡፡ አሜን /.ዮሐንስ አፈወርቅ/!!
  ሰላም ወሰናይ! (ወውእቱ ቃል ሥጋ ኮነሳምንት ይቀጥላል!)

by Gebregziabher Kide on Sunday, December 11, 2011  From facebook address

5 comments:

  1. yiketil tiru new, Amlake kidusan ke enante gar yihun

    ReplyDelete
  2. Abune fanuel done great job , for reason he appointed very real lekawonet as leke kahinat. Others mk elememts please find job that close match to ur profile. You guys no idea about to manage and to serve thechurch just leave ourchurch now. Bc you mk come wrong, place to find job go to employment agency I hope you can be hire not in eotc.

    ReplyDelete
  3. if any thing happen to abune fanuel it should be the last age of mk to burried forever.

    ReplyDelete
    Replies
    1. Are you from the protests whether you believe it or not Luter who the one sow protestantism was completely forget what he did and get an excuse from God. You are running for just for life which will end up in this stupid world. Do not forget u are real protestant. see your self nothing will be done by force. thing Eyobe. If you raise your hands to whom they are from God you will COMPLETELY BURIED ON hail. may God help you.

      Delete
  4. 10000 % i am sure you will be the who will be buried. If you are not to the right God will say you bye like YEHUDA! you are the same to that

    ReplyDelete