Friday, February 3, 2012

የአዲሱ ሚካኤል ምዕመን አስተዳሪውን አገዱ


  • አቡነ ጳውሎስና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቃላቸውን አልጠበቁም

(አንድ አድርገን ጥር 25 2004ዓ.ም )፡- የደብረ መዊዕ ቅ/ሚካኤል ካቴድራል ካህናት እና ምዕመናን የካቴድራሉን ንብረት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ፤ ከተባባሪዎቻቸው ጋር በመመሳጠር በብዙ ሺህ የሚቆጠር የካቴድራሉን ገንዘብ አጉለዋል፤ በካቴድራሉ አስተዳደር እና በሀገረ ስብከቱ የማይታወቁ ተገቢ ያልሆኑ ቅጥሮችንና ዝውውሮችን ፈፅመዋል፡፡ ገቢዎችን በተደጋጋሚ ዘርፈዋ ያላቸውን አስተዳዳሪ ከሀላፊነታቸው አገደ፡፡

ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት በጉዳዩ ላይ ተሰብስበው በመምከር ከ10ሺህ  በላይ የምዕመናንን አቤቱታ ፊርማ ከአስፈላጊ ማስረጃዎች ጋር በማጠናከር ለአዲስ አበባ አገረ ስብከት እና ለፓትርያርኩ ልዩ ፅ/ቤት በግንባር አቅርበዋል፡፡
የካህናቱ እና ምዕመኑ ዋና ጥያቄ ላለፉት ሁለት ዓመታት የደብሩን አስተዳደር ክፉኛ በመበደል የቆዩት ሊቀ ሊቃውንት ተ/ጊዮርጊስ ከሀላፊነታቸው ተነስተው ካቴድራሉን የሚመጥን አባት በአስቸኳይ እንዲመደብላቸው ጥቅምት 20/2004 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ ተወካዮች በተገኙበት በቃለ አዋዲው ድንጋጌ መሰረት የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ የተስተጓጎላን ካቴድራሉ ልማት የሚቀጥልበትን መንገድ እንዲመቻችላቸው ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም መልስ ሳያገኙ ወራትን ለማስቆጠር ችለዋል፡፡


ታህሳስ 5 2004 በስድስት ትላልቅ የህዝብ መጫኛ አውቶቢሶች ምእመኑ አቤቱታውን ለማሰማት በጠቅላይ ቤተክህነት ለፓትርያርክ ተጠሪ ፊት ቀርበው ጉዳዩን ባረዱበት ወቅት ፤ ተጠሪው በሶስት ቀናት ውስጥ ጉዳዩ ተጣርቶ ለችግሩ እልባት እንደሚሰጥ ቃል ተገብቶላቸው ነበር ፤ ተጠሪው ቃላቸውን መጠበቅ ቢያቅታቸው ለተግባራዊነቱ ምንም ያህል እርምጃ ባይራመዱም እንኳን ነገሩን አለዝበው መሸኝት ችለው ነበር ፤ ከህዳር ወር ጀምሮ ርቀው የቆዩት አስተዳዳሪው ጥር 20 /2004 ዓ.ም ቀን በውስጥ ባቀመጧቸው ሰዎች በመጠቀም ለሚያደርሱት ቀጥተኛ ያልሆነ ተፅህኖ ፤ እያደረሱ ያሉት የገንዘብ ብክነት ፤ በስማቸው የሚንቀሳቀስ ምንም ሂሳብ እንዳይኖር በማሰብ በተደረገው ስብሰባ ጉባኤው አስተዳዳሪው አግዷል ፤ 5 ያህል  ልኡካንን በመምረጥ የቤተክርስያኗ አገልግሎት በማይስተጓጎልበት እና በሚቀጥልበት መንገድ ተወያይተው ስራ ጀምረዋል፡፡ልኡካኑ እንዳሉት ከፓትርያርኩ ምንም ምላሽ ካላገኙ እጃቸው ላይ ባላቸው  መረጃ መሰረት ወደ ፍርድ ቤት ፍትህን ፍለጋ እደሚሄዱም አስጠንቅቀዋል ፤ እኝው አስተዳዳሪ ከወራት በፊት የቤተክርስያኗን ሙዳይ ምፅዋት ገልብጠው ሲሄዱ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን ከዚህ በፊት ገልፀን ነበር፡፡

መንግስት በቅርቡ በአዋጅ የመሰረተው መስሪያ ቤት በባንኮች አካባቢ  ስራቸው እና ገቢያቸው የማይመጣጠኑ ሰዎች ላይ ጥናት በማድረግ የሰበሰቡት ገንዘብ ያከማቹት ሀብት በህገወጥ መንገድ የተሰበሰበ ከሆነ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን መስሪያ ቤትና ፤ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ጥናት በማድረግ ሰዎችን በህግ አግባብ የሚጠይቅበትን አሰራር በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፀድቆ ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም እስካሁን ምንም ስራ ሲሰራ መመልከት አልቻልንም ፤ ነገር ግን ነገ ; ከነገ ወዲያ ህጉ ወደ ስራ በሚገባበት ሰዓት እኛም በቤተክርስትያናችን ላይ ለሚደረጉ የገንዘብ ምዝበራዎች መረጃ በመሰብሰብ ቤተክህነት ሳይሆን ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሄደን የምናመለክትበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ፤ እስከ አሁን ለተዘረፉት የቤተክርስትያን ገንዘብ ማንም በህግ አግባብ ቆሞ ጥፋተኛ ያልተባለበት አካሄድ ስለሆነ ያለው ፤ መልሰን ውሀ ወቀጣ ውስጥ መግባት አንፈልግም ፤ ከወራት በፊት የ2500 ብር ደመወዝተኛ በቤተክህነት ውስጥ የሚሰራ አንድ የክፍል ሀላፊ ከ1.5 ሚሊየን የሚቆጠር ብር ቤቱን ሰርቶ ሲያስመርቅ ፓትርያርኩ በግብዣው ላይ እንደተገኙ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ (20 ዓመት ሙሉ እንኳን ሳይበላ ሳይጠጣ ቢያጠራቅም 1.5 ሚሊየን ብር ሊሰበስብ አይችልም ፤ ታዲያ ብሩ ከየት መጣ ?) ፤ የ3000 ብር የማይሞላ የወር ደመወዝተኛ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ቤት በሳሪስ አካባቢ በጥቂት አመታት መግዛቱንም እናውቃለን ፤ ከአሁን በኋላ ህገወጥ አሰራር ፤ የገንዘብ ምዝበራ ተመልክተን ቤተክህነቱ ወይም ፓትርያርኩ መፍትሄ እንዲያመጡ የምንጠብቅበት ጊዜያት አይኖሩም ፤ እናውቃለን ብለንም መረጃው ምስጥ እንዲበላው አፈር ውስጥ አንደብቅ ፤ የቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ የጀርባ ታሪክም ከዚህ የዘለለነና የተለየ ታሪክ የሌላቸው ሰው ናቸው ፡፡


መረጃ ለሰዎች ማድረስ ዋናው አላማችን ቢሆንም ፤ መረጃ ብቻውን ግን መፍትሄ ሲያመጣ ለማየት አልቻልንም ፤ ስለዚህ ከቤተክርስትያን ጀርባ ለሚካሄደው የገንዘብ ምዝበራ ምግባር ፤ ከአስፈላጊ ማስረጃዎች ጋር በማጠናከር መረጃዎችን ለፖሊስና ለፀረ ሙስና ኮሚሽን በማቅረብ ለቤተክርስትያኗ የመፍትሄ ሰዎች ለመሆን እንሰራለን፡፡

‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስትያናችንን ይጠብቅ››

ቤተክርስትያናችንን የመጠበቅ ኋላፊነት የሁላችንም መሆኑን አውቀን ፤ ስርዓት ሲጣስ እያየን ዝም ልንል አይገባም ፤ 

1 comment:

  1. Egziabher Yirdachihu...We are all with you...

    ReplyDelete