ማለዳ ተነሥቶ ነጠላን አጣፍቶ በቤቱ መገኘት
የቤተክርስቲያን ደጅ ዝቅ ብሎ መሳም በእምነት ማሻሸት
ሰዓታት ኪዳኑን በጥዑመ ዜማ በካህናት መስማት
#ይናፍቃል_ለካ ተቀብሎ ማዜም በአንድነት በኅብረት።
አሐዱ አብ ተብሎ ቅዳሴን ማስቀደስ
በፍቅር በኅብረት ተሰጥዖን መመለስ
በዕጣኑ መዐዛ በመስቀል መቀደስ
ደጀ ሰላም ገብቶ ፀበል ጸዲቅ መቅመስ
#ይናፍቃል_ለካ በካህኑ መስቀል በእጆቹ መዳሰስ።
እያወክ በድፍረት ሳታውቅም በስህተት
እግዚአብሔር ይፍታህ ለሠራኸው ኃጢአት
መባል በካህኑ ከእሥራት መፈታት
#ይናፍቃል_ለካ የአባቶች ድምጽ መስማት።
የሕጻናት ድምጽ መስማት ለቁርባን መሰለፍ
ሁሉ ነጭ ለብሶ ከቤቱ መሳተፍ
ቅዱስ ወንጌል መሳም ታምሯንም መስማት
የሰንበትን መዝሙር በኅብረት መዘመር
ትምህርተ ወንጌልን መማር በመምህር
ተሰልፎ መውሰድ የቅዳሴን ፀበል
# ይናፍቃል_ለካ ሰላም ግቡ መባል።
አቅለን ያየነው በሳምንት አንድ እሑድ በቤትህ መገኘት
ተኝተን አርፍደን ባላሰብነው ሰዓት መጣብን ይህ መዓት
አዎ አምላካችን ናፍቆናል ይህ ሁሉ በዚች አጭር ቀናት
መሐሪው ጌታችን ይቅር በለን እና መልሰን ወደቤት
ሕመምህን እያሰብን በሰሙነ ሕማማት
በደጅህ ሰብስበን በትንሣኤህ ዕለት።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
# በምስጢረ_ድግሴ
No comments:
Post a Comment