የጎርባቾቭ ማስታወሻ
(አንድ አድርገን ጥቅምት 06 ቀን 2008 ዓ-ም)፡- ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የሆን ሁላችን ልንቃወማቸውና ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ልናስወጣቸው፣ ከዐውደ ምህረታችን ልናወርዳቸው የሚገቡን የተዋህዶ እሾህ ናቸው ፡፡ ሀራጥቃዎች!!
በምግባረ ንስሃ ተጸጽተው፣ በትሁት ስብዕና ተማርከው፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልብተው " ቤተ ክርስቲያንን እናድስ " ቢሉን እንኳ፤ እንደቀደሙት አበው ጉባኤ ጠርተን፥ ወንበር ዘርግተን ፥ መጽሐፍ ገልጠን እንከራከራቸው ነበር፡፡
እኝህ ግን የጸጸት ልብ የሌላቸው ፣ በትዕቢትና በድፍረት የተካኑ፣ ያለዐዋቂነትን የተሞሉ ትምክህተኞች ናቸው፡፡ በገዛ ቤታችን እንዳሻቸው ሲሆኑ፤ ስለ እነሱ ጊዜ አጠፋን፡፡ የዋሃን የሆኑ ምዕመናንን ለኑፋቄያቸው ሰጠን፡፡ የእውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን አገልግሎት ከንቱ አደረግን፡፡ ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያን ከልማትና ከወንጌል ሥራ ይልቅ በእነሱ ጉዳይ ላይ እንድትደክም ሆነ፡፡
በእርግጥ ይህ ለእነሱ ድል ነው፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት ተራምደዋል፡፡ በክህደታቸው አባታቸው አርዮስን፣ በግብራቸውም ተረፈ አይሁድን መስለዋል፡፡ አካሄዳቸው ሁሉ የመናፍቃንን መንገድ የተከተለና የፕሮቴስታንት ምንደኞችና ቅጥረኞች ሆነው ተሰግስገዋል፡፡
እነሱ መምሰል የሚገባቸውን መሰሉ፡፡ በዚህም ከዚህ ዓለም የሆነ ጥቅማቸውን አገኙ፡፡ ..... ጥያቄው ግን ይህ አይደለም፡፡ ከእኛ ወገን ሆነው እኛን ካልመሰሉ ፦ ከቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ምን ይሠራሉ ነው? በዐውደ ምህረታችን ለምን ይቆማሉ ነው? በተዋሕዶ ስም ለምን ይነግዳሉ ነው?
ታድያ እኛ ምን ሠራን? እነሱ፦ መምሰል የሚገባቸውን ከመሰሉ ፤ መሆን የሚገባቸውን ከሆኑ ፤ ታድያ እኛ ምን አደረግን?
በየዋህነት አንታለል፡፡ ሰውን አንከተል፡፡ በሥራቸው እንለያቸው፡፡ በሰውነታቸው እንውደዳቸው፡፡ ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶአቸውን ግን አምርረን እንጥላ፡፡ በይቅርታ ለመመለስ እስካልፈቀዱ ድረስ ግን አንሸከማቸውም፡፡ ከቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዐውድ አውጥተን ልንጥላቸው ግን ግድ የሚሆንበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡
ይህ የገንዘብ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚስት የባል የወላጅና ልጅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ የጥቅምና የድንበር ወይም የዘር ጉዳይ አይደለም፡፡
ገንዘብ ካልከኝ፥ ማንም እንዲሰርቀኝም ሆነ እንዲያጎድልብኝ የማልሻው ገንዘቤ ሃይማኖቴ ናት፡፡ ሚስት፣ ባል፣ ወላጅና ልጅ ካልከኝ፥ የጥምቀት ልጅነት፣ የቤተ ክርስቲያን አካልነት፣ የክርስቶስ ቤተሰብነት ጉዳይ ነው እምነቴ፡፡ ወደ ሰማያዊው መንገድ የምትመራኝ ጥቅሜ ናት ተዋሕዶ፡፡ ርስቴ ወሰን ድንበሬ፣ ምርጥ ዘሬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህም ጉዳይ ነው ሀራጥቃዎችን የምታገለው፡፡
ይህ የአንድ ማኅበረ አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኀበር አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ አጀንዳው የእነ መምህር ዘመድኩን ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የጋራ ነው፡፡
በአንፃሩም የእነ አቶ በጋሻው ደሳለኝ እና ጀሌዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እነሱ ፊታውራሪ ሆነው የሚያገለግሉ የእናት ጡት ነካሾች ሲሆኑ ፤ ከጀርባቸው የተደራጁ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ የሚደግፉ ፣ ስልትና ዕቅድ የሚነድፉ፣ ግለሰቦች እና ድርጀቶች አሉ፡፡
ስለሆነም ጉዳዩ የእምነታችን፤ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው እኛን የሚያገባን፡፡ የፀረ ተሀድሶውን ዘመቻ መቀላቀል የሚኖርብንም ለዚህ ነው፡፡ ልዩነታችንን ወደጎን ትተን ፥ ኩርፊያችንን አውልቀን ጥለን ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ኅልውና በአንድነት እንቁም፡፡ በተለያዩ ምክንያት ከአገልግሎት የራቅን ሁሉ የመመለሻው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ከዚህ የሚበልጥስ ምን አለ?!
በመሠረቱ አጀንዳውን መምራት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ሲቀጥል የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ መሆን ነበረበት፡፡ አሁን ግን ከፈረሱ ጋሪው ቀድሟል፡፡ ከጌታው ይልቅ ሎሌው ተሰልፏል፡፡ " እግር ራስን አይክም፥ ልጅ አባትን አይመክርም " የሚለው ተረት ቦታው ለሀራጥቃዎቹ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከታች ወደላይ አጀንዳውን ማንሳታችን ስህተት የለውም፡፡ መንጋውን እንዲጠብቁ ለተሾሙት ማሳሰባችን ነውር የለውም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከፊት ፥ ሰዎች ከኋላ ሊከተሉ ግድ ነው፡፡ " ተመልከት ዓላማህን ፥ ተከተል አለቃህን " ነው ነገሩ፡፡ ዓላማችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አለቃችንም መሠረቷ ጉልላቷ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ " አትንገሩን አዲስ ጌታ የለም! " እንዳለው ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ፡፡
ይህን ድምጽ ለኁሉም ኦርቶዶክሳዊያን ሊደርሰ ይገባል፡፡ አብረን እንነሳ፡፡ ሀራጥቃ ከዐውደ ምህረታችን ይውረድ፡፡ ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ ቤተ ክርስቲያንን አይወክላትም፡፡ የሚታደስ ዶግማና ቀኖና ለስንዱዋ እመቤት የላትም፡፡ ሙሰኛና ጉበኛ፣ ፖለቲከኛና ዘረኛ ከሆኑት የአስተዳደር ሰዎች ጨምሮ ሀራጥቃዎች እናንተው ታደሱ፡፡ ከግቢያችንም ውጡ፡፡ እውነት እውነት እንላችኋለን አንተዋችሁም፡፡
የሚታደስ ዶግማና ቀኖና ለስንዱዋ እመቤት ላልኅው ገድል ና ድርሳናት ን ሁሉን አንባሃል? ከወንጌል ጋር የሚጋጩትን አይታሃል ? ጽሁፍ ሰውን ወደ አመጽ የሚመራ አንድ የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ የለውም ተሀድሶች ለማጥፋት ጉልበት ሳይሆን ወንጌል ስበክ
ReplyDeleteአሁንም ካንተው ጋር ነኝጥቅሱስ የሚለው አባቶቻችሁን፣ዋኖቻችሁን ምሰሉአቸው የእምነታችውን ፍሬ እየመለከታችሁ ተከተሉአቸው ተብለናል።ገድሉ እኮ ለዲያብሎስና ለቡችሎቹ ገደል ነው።ለእኛ ግን አዲስ ክርስትያኖች እንዳንሆን መንገድ ጠቖምያችን ነው።በፈተና ማዕበል ያለፉትን የእናት አባቶቻንን ቅዱሳን ሕይወት አሳይቶን እንማርበታለን።አሁን ትንሽ በራልህ።ኩበት ነህ !
Deleteእናንተ ወራዶች፡- አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት ተብሎ የተጻፈውን አታስተውሉም? እስኪ የቱ ነው የሚታደሰው? በኒቂያ፣ በኤፌሶንና በቁስጥንጥንያ የተወገዙትን የክህደት ትምህርቶች ከመቃብር እያወጣችሁና ስታችሁ ለማሳት ደፋ ቀና እያላችሁ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የተለየ ትምህርት የሚያመጣ ሁሉ አስቀድሞ በተጠቀሱት ታላላቅ ጉባኤያት የተወገዘ ነው፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶሳውያን በሙሉ ሃይማኖታቸው፣ ሥርዓታቸው፣ ትውፊታቸውና ታሪካቸው እንዲበረዝና እንዲከለስ ከቶ አይፈቅዱም ፡፡ በሌላ አነጋገር ሁላችንም የጸረተሐድሶ እንቅስቃሴ ደጋፊ ነን፡፡ የጸረተሐድሶ እንቅስቃሴ የማኅበረቅዱሳን ድርሻ ብቻ ሳይሆን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤ/ክ የሁሉም ሕዝበክርስቲያን ተልዕኮ ነው፡፡
ReplyDeleteዲያብሎስና ልጆቹ ክህደትና ጥፋትን ከማስፋፋት የተቆጠቡበት ቀን የለም፡፡ ይሄም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የፈተነ ሰይጣን በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን እኛን ከመፈተን ወደ ኋላ አይልም፡፡ ዳሩ ግን አስቀድሞ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተሸነፈ አንፈራም-የአሸናፊው የእግዚአብሔር ልጆች ነንና፡፡
እኔን የሚገርመኝ የሚደንቀኝ እዉነት አንተ ወ አንቺ ቅዱስ ወንጌልን አንብበህ ታዉቃለህን? የቱ ጋ ነዉ ስለእመቤታችንና ሰለቅዱሳን ስበኩ የሚለዉ? እኛስ የተሰቀለዉን ክርስቶስን እንሰብካለን ከሚል በስተቀር እኔ አላየሁም፡፡ ደግሞም በሱ መስቀል እኛ ነፃ መሆናችንን ደግሞ በሱ ካመንን የመንግሰቱ ወራሾች መሆናችንን ያበሰረዉን ወንጌል መቀበል አንድ ሲሆን ወንጌሉ ልክ አይደለም ማለት ደግሞ ሌላ ነዉ፡፡ በጭፍን መሳደቡ ለምን ይሆን አልገባኝም፡፡ ቤተክርስቲያናችንስ ጌታን የሚያስቀኑ የአምልኮ ስርዓቶች ከሉተር መሰል መነኩሴ ነዉ ያመጣችዉ? የቀደምት አባቶች እዉን በኒቂያና በቁስጥንጢንያ ጉባኤያት ያነሱት ስለእመቤታችንና ስለቅዱሳን አምልኮ ነዉ? የቤተክርስቲያንን ታሪክ አንብብ እንጂ የዋሃንን አታሳስት፡፡ በየጊዜዉ እያሰረጋችሁ የምታስገቡት ጣዖቶች ምንድርናቸዉ? ሰሞኑን ደግሞ ቅድስት አርሴማን ከፍ ከፍ ማለት ቀጥላችሁዋል፡፡ ይህ ከንግድ ሰንሰለትና ከሆድ ጋር የተያያዘ ነዉ፡፡ ከስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ጀምሮ እስከ ሰንበቴ ጸበል ጸዲቅ ገበያ የሚደራዉ እንዲህ የምታመልኩት የሚነካና የሚዳሰስ የእጅ ጥበብ ስታባዙ ስለሆነ ወንጌሉን ለፕሮቴስታንት ብቻ ሰጥታችሁ እርፍ አላችሁ፡፡ ጌታችን በደጅ ነዉ፡፡ ሳይፈርድባችሁ ንስሐ ግቡ፡፡ ይህችን ቤተክርስቲያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚቻለዉ ከናንተ ኑፋቄና ክህደት ነፃ ስትሆን ነዉ፡፡ ወንጌል በየሞባይሉ በየኢንተርኔቱ የሚያነበዉ ትዉልድ ከእንግዲህ የአባቴ የአና ሃይማኖት ብሎ ኑፋቄን አያሞካሽም፡፡ኢየሱስ ጌታችን እሱ ብቻዉን በቂ ነዉ፡፡ ደግሞም የአሸናፊዎች አሸናፊ ነዉና ድል ያደርጋል፡፡
ReplyDeleteእናም ወንድሜ አንድ ፊደል ላይ ብቻ ቆመህ እራስህን አትግደል፡፡ ቃል ስጋ ሆነ እንጂ የተባልከው ቃል ፊደል ሆነ አይደለም የተባልከው፡፡ ስጋ ደግሞ ማለት የሰው ልጅ ማለት ነው፡፡ አንተ ጣኦት ስትል ይህን ሁሉ እያልክ እንደሆነ እንኳን የተረዳህ አይመስለኝም፡፡
ReplyDeleteአንድ አድርገን ያስተላለፈው መልእክት እውነት ነው፡፡ ልንታገላቸውና ልንቃወማቸው ይገባል፡፡ ከአውደምህረታችን ይውረዱልን፤ የመናፍቃን ዳንኪራ በእየአዳራሹ በየሰፈሩ የሚጩሁብን አነሰና በቤተክርስቲያናችን የምህረት አደባባይ ላይ ልናያቸው አይገባም፡፡ራሷ ክርስቶስ የሆነችው ቤተክርስቲያን ሲያመን የምንፈወስባት፣ የሀጢያት ሸክማችንን የምናራግፍባት፣ ሲጨንቀን የምናርፋባት ናት፡፡ ፡፡ ስለዚህ አሁንም ተግተን እንጸልያለን እስከምንችለው በጉልበት ሳይሆን እውነቱን በመግለጽ ከአዳባባያችን፣ የኑፋቄ ትምህርታቸውን ልናስወግድ ይገባል፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
ReplyDelete