Wednesday, October 7, 2015

ቀዳዳ ያላጡት የዘመናችን የአርዮሳውያን



(አንድ አድርገን መስከረም 26 2008 ዓ.ም)፡- 

 ኦልማን የተባለ የታሪክ ፀሃፊ 379 በቁስጥንጥንያ የነበረውን የሃይማኖት ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆታል፡፡ 


ሃይማኖታዊ ጉዳይ እንደማንኛውም ተራ ወሬ ስራ መፍቻና የቀልድና የመዝናኛ ጉዳይ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡ ቲያትር ቤት ውስጥ የነበረው ሁኔታ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጣ የቤተክርስቲያን ብቸኛ ሃብት ተደርጎ ይታይ የነበረው ጉዳይ ወደ ቲያትር ቤት አዳራሽ ተወሰደ በአንድ ወቅት የተሻለ ክርስቲያናዊ ትርጉም ይሰጠው የነበረና ወደ ቀልድ መድረኮች የማይመጣው የቤተክርስቲያን ምስጢር በአደባባይ የብዙወች መዘባበቻ ከንፈር መምጠጫ ሆነ፡፡ 


በቁስጥንጥንያ መንበር ላይ የተቀመጡት አርዮሳውያን መሪወች ይህ እንዲሆን የሚያበረታቱ ሃይማኖትም ጉዳይ ደንታ ቢሶች ነበሩ፡፡ የቤተክርስቲያን የነበረውን ህዝብ ታላቅ ከበሬታ ይሰጠው የነበረውን ጉባኤ አቃለሉት ናቁት ነዋሪዋቹም እውነተኛ የነበረውን ነገር እርቃኑን አስቀሩት ቅዱስ የነበረው አለማዊ በሆኑ ሰዋች ከንፈር ተቃለለ ከዚህ ሁሉ በጣም የከፋው ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት ቤተክርስቲያንን ማቃለልና መዘባበቻ ማድረግ ሰዋቹን ደስታ የሚሰጣቸው ነገር ሆነ ደስታ ብለው በቆጠሩት ነገር ላይ ጊዜያቸውን ማባከን ተያያዙት ቤተክርስቲያንን ወደ ቲያትር መድረክነት ሰባኪወቻቸውንም ወደ አክተርነት ለወጧቸው፡ ሕዝቡንም ከቤተክርስቲያን አውጥተው በአዳራሽ እንዲሰበሰብና የቀደመ ማንነቱን ቀስ በቀስ እንዲረሳ አደረጉት ተሳካላቸውም፡፡ 

ሰባኪው ሕዝቡን ያስደስታል ብሎ ካመነ እንደምርጫቸው እራሱን ለመለወጥ ችግር አልነበረበትም፡፡ እንደወደዱም አድርጎ ያዝናናቸዋል ያስቃቸዋል ደስታ ከተባለም እንዲሁ ያስደስታቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር የሚደረገው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ለጆሯቸው ደስ የሚላቸውን ነገር እንጂ ከእግዚአብሄር የሆነው ነገር ይነገራል ተብሎ ፈፅሞ አይታሰብም፡፡ አቀራረቡም ቲያትር ቤት ውስጥ እንደሚያዩት ውዝዋዜና ዳንስ ነገርም የተቀላቀለበት አይነት ዝላይ የሚመስል አደገኛ ጨዋታ ነበር፡፡ኮሜድያኑ ወደ መድረክ አደባባይ እንደሚወጣ ሁሉ በቤተክርስቲያን አደባባይ ሲወጣ ልክ በቲያትር ቤቶቻቸው እንደለመዱት ቅልጥ ባለ ጭብጨባ ታጅቦ ነበር የሚወጣው ያሳዝናል የሰባኪወቹም ቁጥር ደግሞ በሕዝቡ ቁጥር ልክ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሰባኪወቹም ይህንን አድናቆት ነፍሳቸው ይወደው ነበር ወደ መድረክ ሲወጡ እንዲጨበጨብላቸው የራሳቸው ቲፎዞወች በየጉባኤው የተለያየ ቦታ ያስቀምጡ ነበር፡፡ የቤተክርስቲያን የአምልኮት መፈፀሚያ እቃወችም ነገስታቱና መኳንንቱ ከቅምጦቻቸው ጋር ይገለገሉባቸው ነበር፡፡ የተቀደሰውና ሰወቹን ሁሉ የሚመራው የእግዚአብሄር ቃል የወንጌል ህግ ተረስቶ ማንኛውም ሰው ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ከሚለምነው ለማኝ እስከ ንጉሱ ድረስ ለድህነት የሚጠቅመውን የሕይወት ኑሮ መኖር ሳይሆን ጥቅስ መወራወርን ኑሮየ ብለው የተያያዙበት ጊዜ ነበር፡፡በየጎዳናው በየገበያው በየበረንዳው ከሕፃኑ እስከ አዛውንቱ ከአብና ከወልድ ማን ይበልጣል የሚል ተግዳሮት ሲነጋገሩ መስማት የተለመደ ነበር፡፡ አርዮሳውያን የቁስጥንጥንያን ቤተክርስቲያን 325 – 379 ያወረሷት ሃብት ይሄ ነበር፡፡



ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት ስንዱ እመቤት ሆና ሳለ በአሁኑ ሰዓት ለግል ጥቅማቸው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችና  ማኅበራት በተለያየ መልኩ ምእመናንን በማደናገር እያወኳት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አካላት ባልሆኑ አስተማሪዎቻቸው የተሰጣቸውን ተልእኮ በመያዝ ‹‹መልካም የሆነው ትምህርት እንዳይኖር አብዝተው ይተጋሉ› እንዳለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የወንበዴዎች ዋሻ ለማድረግ ሌት ተቀን ከውጭ እየገፉ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ለሆዳቸው ባደሩ አጋዦቻቸው አማካይነት እየተደገፉ ስልታቸውን በመቀያየር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሳያውቁ ለዘመናት የኖረችው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በተገቢ ሁኔታ እንዳትወጣ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹የሲኦል ደጆች አይችሏትም›› እንዳለው በዘመኑ በገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ የሆኑ ጠባቂዎቿን ያሥነሳላታል፣ በድልም ያረማምዳታል፡፡


በእኛም ዘመን የተነሱብን ሰዎች ቀስ በቀስ ምዕመኑ ለሃይማኖቱ ደንታቢስ እንዲሆን የሚሰሩ ፤  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እውቅና ያልሰጠቻቸው አካላት ዘመኑን በመምሰል ምዕመናን በቀላሉ ቤታቸው ሆነው በሚከታተሉት የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ለዘመናት ስትገነባቸው የቆየቻቸውን ስርዓት ፤ ትውፊት ፤ ቀኖና እና ዶግማዋን  በጥቂት ሰዓታት የቴሌቪዥን ስርጭት የማጠልሸት  ፤ የመበረዝ ፤ የማዳቀልና የማዛባት ሥራ የሚሰሩ ፤  የከበረውን የእግዚአብሔር አውደ ምህረት ወደ ተራ መድረክነት ለመለወጥ የሚሰሩ ፤ ለመርሐ ግብር ድምቀት ምዕመኑን ከቅጽሩ በማስወጣት በአዳራሽ በመሰብሰብ ለፕሮግራም ማድመቂያ የሚያደርጉ ፤ ስለ ዛሬ ዝናቸውና ቆሞ መሄዳቸው ብቻ እንጂ በማር የተለወሰ ትምህርታቸው ስለ ሳቱት ነፍሳት ግድ የማይሰጣቸው  ሰዎች ናቸው  ከፊታችን ቆመው የሚገኙት፡፡ 


በአሁኑ ሰዓት ያለን ምዕመናን ለቤተክርስቲያንና አንዲት ተዋህዶ እምነታችን እንደ አባቶቻችን ጤዛ ልሰን ድንጋይ ተንተርሰን ድምጸ አራዊትን ታግሰን ስለ ሃገርና ስለ ቤተክርስቲያን መጸለይ ቢያቅተን ፤ አለት ጠርበት ሕንጻ ቤተክርስቲያ ሰርን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላፍ  ባንችል እንኳን አሁን ያላትን ሕጓን እና ስርዓቷን ጠብቀንና አስጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ በቀጣይ ወር አባቶች በሚያደርጉት ጉባኤ የቤተክርስቲያን የወቅቱ ጉዳይ የብዙዎች ከንፈር መምጠጫ እና የጥቂቶች መዘባበቻ ሆኖ እንዳይቀጥል የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ ከማቅረብ በተጨማሪ ወደፊት በቴሌቪዥን ስለሚተላለፉት መርሐ ግብሮች በሲኖዶስ እውቅና የተሰጣቸው ወይም የሚሰጣቸው ማኅበራት በምን መልኩ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ማካሄድ እንዳለባቸው የሚያሳይ መንገድ ያመላክታሉ የሚል እምነት አለን፡፡


No comments:

Post a Comment