Saturday, October 31, 2015

"የነፍስ ወይንስ ከስጋ ፈውስ?"


(ያሬድ ሹመቴ)
 

(አንድ አድርገን ጥቅምት 20 2008 ዓ.ም)፡- ሰሞኑን በመምህር ግርማ መታሰር ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮችን ስመለከት 20 ዓመታት ወደ ኃላ ተጉዤ አንድን ክስተስ እንዳስታውስ ምክንያት ሆነኝ። መምህር ግርማ በተከሰሱበት ወንጀን ነፃ መሆን አለመሆን ጉዳይ ምንም አይነት አስተያየት የሌለኝ ሲሆን እግዚአብሔር ሲፈቅድ እውነታውን ማወቅ እንደሚቻል በማመን ለሱ ትቼዋለሁ።

ወደ 20 ዓመት ትውስታዬ ልመለስ፡-
ባህታዊ / መስቀልን የማያውቅ የኔ ወይንም የቀደመኝ ትውልድ ይኖራል ብዬ አላስብም። የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በመናገሻ /ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የዲቁና ተማሪ ሆኜ አገለግል ነበር። በወቅቱ ታዲያ ባህታዊ /መስቀል በርካታ ተከታይ የነበራቸው ብዙ "ተዓምራት እና ፈውስ" ያደርጋሉ የሚባሉ አባት ነበሩ። እንዲያውም የሞተ ሰው አስነስተዋል ተብሎ ይነገርላቸው ነበር።

 ቅ/ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከጠቅላይ /ክህነት በደረሰው መመሪያ መሰረት እኚህ አባት በቅጥር ጊቢው ተገኝተው እንዳይሰብኩ በመከልከሉ ሶስቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ በሮች በሰንሰለት ተቆለፉ። በእሳት አደጋው በኩል በሚገኘው ማርገጃ ክፍት ቦታ ላይ ባህታዊ /መስቀል ስፍር ቁጥር ከሌለው ምዕመን ጋር ሱባኤ ተያያዙ። ወቅቱ የአብይ ፆም ወቅት እንደነበር አስታውሳለሁ። በተቆለፈው ቤተ ክርስርስቲያን ውስጥ ግን ቅዳሴ አልተቋረጠም።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በአቤቶ እያሱ ልጅ አዛውንቱ ልጅ መስፍን እያሱ (ጫማቸውን እግራቸው ውስጥ ለማስገባት እንዴት እስከሚያልበኝ እታገል እንደነበር አስታውሳለሁ) የተቆለፈውን በር ሰንሰለት በመጋዝ ቆርጠው "የአያቴን ቤት ማንም አይዘጋውም ግቡ" ብለው አዘዙ። ውጭ ያለው ምዕመን እየጎረፈ ወደ ውስጥ በእልልታ እና በሆታ ገባ። በመሀል ሾልከው የገቡ ማንነታቸው የማይታወቅ አጥፊዎች የቤተ ክርስቲያኑን መስኮት በድንጋይ ሲሰብሩ አንድ አንዶቹ ደግሞ ቁሳቁሶችን ሰርቀው ተሰውረዋል። ፖሊስ ቦታውን ከግርግሩ ነፃ ለማውጣት ብዙ ጊዜ ፈጅቶበታል።

ግርግሩ እና ወከባው እስከ ምሽት ድረስ ቆይቶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። ባህታዊ /መስቀልም ታሰሩ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዝርፊያውና የተሰባበሩ መስኮቶች ብቻ በምሽቱ ዜና እወጃ ላይ በመታየታቸው ባህታዊ /መስቀልን "የሚከተሉ" ምዕመናንን በእጅጉ አበሳጭቶ ነበር። እንዲያውም ይህንን ያደረገው እራሱ መንግስት ነው እስከማለት ደርሰው እንደ ነበር አስታውሳለሁ።

ባህታዊ /መስቀል ከእስር ከወጡ በኋላ ቀጨኔ መድሀኒያለም በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው (ከሰው በስጦታ ያገኙት ይመስለኛል) በመወሰን ስብከት እና "የፈውስ" አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጠሉ።
ከረዥም ርቀት ተጉዘው የሚመጡ ምዕመናን ቀጨኔ መድሐኔአለም ቤተ ክርስቲያንን ሳይሳለሙ ባህታዊ /መስቀል ቤት አምሽተው ይመለሳሉ። የቃል ኪዳን ታቦቱ ያለበት ቤተ ክርስቲያን ተረስቶ የባህታዊ /መስቀል ግቢ እና መንደር በምዕመናን ተጥለቀለቀ።

አንዲት መኪና ደግሞ እንደነበረቻቸው አስታውሳለሁ። ድምጽ ማጉያ ሁል ጊዜ የተተከለባት በየሄዱበት ቦታ ከመኪናቸው ሳይወርዱ የሚሰብኩባት። ምዕመኑ መንገዱን ዘግቶ ስብከታቸውን ይሰማል። አብዛኛው ሰው ደግሞ መኪናዋን በእጁ ለመዳበስ እና "ለመፈወስ" እየጓጓ ሲጋፋ አስታውሳለሁ። ተመልከቱ እንግዲህ መኪናዋ "ቅዱስ" ናቸው የተባሉትን ሰው ስለያዘች ነው።

ሁሉ ጊዜ አልፎ ዛሬ ባህታዊ /መስቀል ሚስት አግብተው ወልደው ሲኖሩ ሁሉም አይንህን ለአፈር ብሏቸዋል።
ስጋ የተሸከመን ማመን እና መከተል መጨረሻው ይህ ነው። የእምነት መሸርሸር የሚያመጣ መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለስጋ ህመም ፈውስ የሚሰጥን ሰው በመከተል ብቻ ነፍስን ነፃ ማውጣት አይቻልም። በዙ ተአምራት ዛሬ በበርካታ የእምነት ድርጅቶች ውስጥ አለ። ወደ እግዚአብሔር ቤት የምንሄደው ነፍሳችንን ለማዳን ቢሆን ስጋችንም አብሮ ይፈወሳል።
 
በስጋ ፈውስ ምክንያት ሰውን ተከትሎ ከቤተ ክርስቲያን መውጣት እግዚአብሔርን መከተል ሳይሆን ሰውን መከተል ነው። ስጋ ተሸካሚ ሰውን ማመን ደግሞ ውጤቱ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው። የእግዚአብሔርን አሰራር በምድር ስሌት አንጠብቅ። ምንም ቢሆን ምንም እስካሁን ፀንታ ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን ነች። ብዙዎች አልፈዋል። አሁንም ያልፋሉ። ቤተ ክርስቲያናችን ግን እስካሁን ድረስ አለች። ወደ ፊትም ትኖራለች!!
የስጋ ፈውስ ፍለጋ የመንፈስን መዳን አያረጋግጥምና ምክንያታችን የስጋ ፈውስ ብቻ አይሁን።
 
"እንደ ስጋ ፍቃድ የሚኖሩ የስጋን ፍቃድ ያስባለና፥ እንደ መንፈስ ፍቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።
ስለ ስጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ህይወትና ሰላም ነው" እንዲል ሮሜ 85-6 

ልዑል እግዚአብሔር የነፍሳችንን ድህነት የምንሻ ያድርገን!!


2 comments:

  1. እውነት ነው ወንድሜ መልእክትህን ተቀብዬዋለሁ፡፡ የሚገርምህ እኝህን ባህታዊ ገ/መስቀል የሚባሉትን እኔም ልጅም ብሆን በጣም አስታውሳለሁኝ፡፡ ሰንበት ት/ቤት ተማሪ ነበርኩኝና የሰንበት ት/ቤት መምህራችን አበክሮ ይመክረን ስለነበረ እኝህን ሰው እኔም አላውቃቸውም አይቻቸው አላውቅም፡፡ እኛ ደብር መጥተው ተብሎ ታናሽ እህቴ ሁሉ ሄደው ሲያያዋችው እኔ አልሄድኩኝም ጭራሽ አልቀበልም፡፡ የሚገርምህ ክርስቶስ በሚያውቀው መልካቸውን እራሱ እኔ አሁን አንዳንድ መጽሐፋቸው ላይ ሰው ይዘው አየሁ ልበል አላውቅም፡፡ አሁን ባያቸው አላውቃቸውም፡፡ መምህርን ግርማ የሚባሉትን ያወኳቸው በዚህ ዓመት ከሶስት ወር በፊት በኢንተርኔት ራዲየ አቢሲኒያ የሚባል ድረ-ገጽ ላይ ነው እንደአጋጣሚ አግኝቻቸው ትምህርታቸውን ስከታተል ያወኩቸው ፡፡ ትምህርታቸውን በጣም ወደድኩት፡፡ ገርሞኝ ሰው ጠየኩኝ፣እኔ ሰፈሬ ቂርቆስ ነው ጎረቤቶቼ እስጢፋኖስ አንድ አባት እያሉ በተደጋጋሚ ሲነግሩኝ ግን ሰንበት ት/ቤት ያስተምረን የነበረው ወንድማችን በጣም ይመክረን ስለነበረ አልተቀበልኩትም ማንንም መከተል አይመቸኝም፡፡ በዘመኔ መምህርና የታወቀ ጸበል ተብሎ የሚሯሯጡበት መንገድ መሄድ አይመቸኝም፡፡ እኔ በጣም የሚያመኝ፣ በሕይወቴ በስጋ ሕመም የምንገላታ ሰው ቢጠራ አንዷ እኔ ነኝ፡፡ መንፈስ ቢባል እንደእኔ የሚፈትነው የለም፡፡የሚገርምህ አይደለም እሷቸውን ፀበል የእንጦጦ ኪዳነ ምህርት የታወቀች ናት አይደል፡፡እጅግ በጣም ታምሜ እራሴን ሁሉ ባላወኩበት ጊዜ እንኳን ፀበል የሄድኩት በአካባቢዬ በሚገኘው ፀበል ነው ስጠመቅ የነበረው፡፡ እኔ ግን አንድ ቀን ሄጀ አላውቅም አይደለም የሰው ስም ተጠርቶ ቀርቶ፡፡ እኚህን ሰው ጎረቤቶቼን ስጠይቃቸው እኛ እስጢፋኖስ የምንከታተላቸው ያን ጊዜ ስንነግርሽ የነበሩት ናቸው ብለው ነገሩኝ፡፡ እኔ ስለእሳቸው የሰማሁት ከዚህ በፊት በአካል ባላውቃቸውም ስማቸውንም በትክክል ባላውቅም ጠንቋይ ናቸው ነው ሲባል የሰማሁትና እንዴት እንደዚህ ዓይነት የወንጌል ትምህርት ያስተምራሉ፤ ብዬ ግራ ተጋባሁኝ ስለዚህ መመርመር አለብኝ ሰው የሚለውን ከመስማት አይቶ መመርመር መልካም ነው ብዬ ሙሉ 9ዐ ፓርት ሙሉውን ባይሆን 9ዐፐርሰንቱን አዳመጥኩኝ፤ ሁለቱንም መጽሐፋቸውን አነበብኩት፡፡ መጽሐፋቸው የጠላትን መረጃ በደንብ ይገልፃል እንዴት አወቁ የሚለውን ነገር ባስብም በትክክልም ግን የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚከሰተውን ነገር በትክክል አስቀምጠውታል፡፡ እኔ ይቅርታና እኔ በራሴ የሰይጣን አሰራር ነው ብዬ ያልተገነዘብኩትን ሁሉ በእውነት ለመናገር አውቄያለሁኝ፡፡ እኚህን ሰው በአካል ጎባኤያቸው ተገኝቼ መመልከት እንዳለብኝ አሰብኩኝ፣ የት እንዳሉ መረጃ ወሰድኩኝ በእርግጥ ቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ ባይሆን እኔ እንደማልሄድ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስላሴ እንደሆኑ ሰማሁኝ ሄድኩኝ፡፡ ቤተክርስቲያን አውደምህረት ላይ ስለሆነና ከቅድስት ስላሴ ስም የቀረበ ፀበል ስለሆን እንደፀበልነቱ ተቀብዬ ተጠምቄ መጣሁኝ፤ በድጋሚ ጀሞ ኡራኤል ሄድኩኝ እንደዚሁ ፀበሉን ተጠመኩኝ፡፡ ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጻፋቸውን ጽሁፎች ሳነብ የእሱ ጽሁፎች ስለአሳመኑኝና ከዚህ በፊት ያስተማረን የሰንበት ት/ቤት ወንድምም ትምህርቱ ስለነበረኝ የበለጠ እንድረዳ አድርጎኛል፡፡ የፈውሱን ኘሮግራም ሙሉን ነው የተመለከትኩት በኢንተርኔት ማለት ነው፡፡ በተጨባጭ እኔን እኝህን ሰው እንዳልቀበል ያደረገኝ አምስት ነገሮች አሉ፤
    1ኛ ከአጋንንት ጋር ረጅም ሰዓት ማውራት
    2ኛ አጋንንት እሷቸውን ሲያወድሳቸው እየተቀበሉ ማበረታታቸው
    3ኛ የአባቶችን መቁጠሪያና ቅባ ቅዱስን ማንም ተራ ሰው እንዲጠቀምበት ማድረጋቸው፡፡
    4ኛ ተከታይ እንዲኖራቸው እንጂ በትክክል የቤተክርስቲያን ልጆች ሆነው እንዲቀሩ የሚያደርግ አካሄድ አይደለም እያደረጉ ያሉት፡፡ ይህንን ያልኩበት ምክንያት አንድ ሰው ከተፈወሰ በኋላ ለምንድን ነው የእሷቸውን እግር እየተከተለ የሚሯሯጠው? የተፈወሱት ሰዎች አንድ ጊዜ ምስክርነት ሰጡ፡፡ ከዚያ በኋላ በእሷቸው ጉባኤ እየተገኘ እሷቸውን የሚያወድስበት መድረክ ማን ነው የፈቀደለት? አሁን አሁን ያሉት ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነት ደግሞ የአባታችን በረከት ሁሉ እየተባለ እሷቸው እንደ አንድ ቅዱስ ሰው አድርጎ መናገር ምን ማለት ነው? በቤተክርስቲያንናችን ስርአት አንድ ሰው ቅዱስ ተብሎ ለመጠራት የራሱ የሆነ ህግና ስርአት አለው፡፡ በሕይወት ያሉትን ሰዎች ቅዱስ ብለን እንኳን መጥራት ካለብን ክህነታቸውን ተመልከተን በድንግልና ጸንተው ለእግዚአብሔር ተለይተው የሚኖሩትን ጰጰሳትንና ፓትሪያርክን እንጂ ቤተክርስቲያናችን በሕይወት ያለን ተራ ሰው ቅዱስ ብላ የሚጠራ ስርአት የላትም እኮ? አንድ ሰው ቅዱስ ለመባል አንድ ይህንን ዓለም ማለፍ አለባቸው? ሁለት ቢያንስ 1ዐዐ ዓመት ያሳለፉ መሆን አለባቸው ሶስተኛ. እኛ አይደለንም ደግሞ አንድ ሰው ቅዱስ ብለን መጥራት ያለብን እግዚአብሔር እራሱ ነው ማስነሳት ያለበት እንጂ እኛ ያውም ቤተክርስቲያን ያልተቀበለችውን ክህነት ለምን እንቀበላለን ሲጀመር? የቅድስት አርሴማን ታሪክ መገንዘብ በቂ ነው፡፡ የሌሎችንም ቅዱሳን ገድላቸው የተፃፈላቸው አባቶችንም ብንመለከት ይህንን የተመለከተ እንጂ የትኛውም ትውልድ አንስቶ ተራን ሰው ቅዱስ ያለበት ዘመን የለም፡፡ ስለዚህ መምህር ግርማ ትምህርታቸው ጥሩ ነበረ፡፡ ነገር ግን ተከታየቻቸው ሲያወድሳቸው አሜን ብሎ መቀበላቸው እኔ እሷቸውን እንዳልቀበላቸው አድርጎኛል፡፡ ደግሞም አፍሬያለሁኝ፡፡ ይህ የተፈጠረበት ምክንያት አስተምሯቸው ህዝቡ እንዲከተላቸው እንጂ የክርስቶስ ሆነው እንዲቀሩ አላደረገም፡፡ በየፊስ ቡክ የሚለጠፈው ሁሉ ትክክል አይደለም፡፡ መመረቅ፣ መጸለይ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከዚያ አልፎ በረከታቸው ይደርብን፣ እየተባለ መወደስ አይገባም፤ የጌታንና የእመቤታችንን ስነስእል በልባችን እንዳላደረግን ዛሬ የእሳቸውን ፎቶ በደረት እየለጠፉ በየፊስ ቡክ መለጠፍ ከየት የተማርነው አስተምሮ ነው ብዬ ሳስበው እሳቸው የዘሩትን ነው ያጨዱት፡፡ ይህ ደግሞ መሆን የለበትም፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምሮ አይደለም፡፡
    5ኛ አስተምሯቸው ላይ አንዳንድ ጊዜ ስለራሳቸው ሲናገሩ አስረግጠው የሚናገሩት እሷቸው የሚፈውሱት ከሰማይ በተሰጣቸው ፀጋ እንጂ በትክክል የእግዚአብሔር ስም እንደሚፈውስ አድርገው ማስተማርና መግለጽን አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ በጣም ስህተትና የቤተክርስቲያናችን የስብከት ዘዴም አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያናችን የስብከት ዘዴ ስለራስ የሚነገርበት መድረክ እንዳይሆን አበክሮ ያስተምራል፡፡ አንድም ቦታ ላይ እሳቸው ኃጢያተኛና የስጋ ድካም እንዳለባቸው በስህተት እራሳቸውን በገለጹበት ጊዜ ሁሉ የትህትናን አስተምሮ አያስተምሩም፡፡ ስለዚህ ከላይ በገለጹኩት መሰረት እኔ እኝህን መምህር ግርማ እራሴ በተጨባጭ በመረመሩኩት መሰረት እንዳልቀበላቸው አድርጎኛል፡፡ የተከሰሱበትን የክስ ሁኔታ ግን ፖሊስ ያቀረበውን መረጃ ብሎ የተናገረው ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ሲሆን ነገር ግን ወደፊት የሚያቀርባቸውን ምርመራዎችን ተመልክቼ ደግሞ የተመለከትኩትን አስተያየቴን እሰጣለሁኝ፡፡

    ReplyDelete
  2. አንድ ያድርገን ገጽህን በጣም ነው የወደድኩትና በርታ እግዚአብሔር ያበርታህ፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልን፡፡

    ReplyDelete