Wednesday, October 7, 2015

‹‹እስልምና ጉዳዮች››ን የመሰለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር


  • ‹‹ ወደ ተቋሙ ጠንካራ ሰው እንዲመጣ አይፈለግም::›› ቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ መሐመድ ጋአስ



(አንድ አድርገን መስከረም 28 2008 ዓ.ም)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2008 .. የአገሪቱ ጠቅላይ ሆነው በድጋሚ በተመረጡ በማግሥቱ፣ 30 አባላትን የያዘ ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ አፀድቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካፀደቁት 30 አባላትን የያዘ ካቢኔ ውስጥ 12 ብቻ በቀድሞው ካቢኔ ውስጥ ያልነበሩ ሲሆኑ፣ የቀሩት 15 በነበሩበት ሥልጣን የቀጠሉ የቀድሞ ካቢኔ አባላት ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመጥናሉ ካሏቸው ግለሰቦች ውስጥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩን አቶ አሚን አብደልቃድርን የተኳቸው ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ሙሳ ይገኛሉ፡፡ 

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ፋይዳ የለውም ያለውን ሴክተር ዳግም ለአጋር አካላት  ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት መሀሙድ ድሪል ይህን ተቋም አስተዳድረዋል ፡፡ አቶ መሀሙድ ድሪል ባላቸው የቋንቋ(ከአምስት እስከ ስድስት ቋንቋ ተናጋሪ)  እና የተለያየ ስብእና የተላበሰ ሰው መሆን ቦታው የሚገባቸው ሰው ሆነው ቢገኙ ላይገርም ይችል ይሆናል፡፡

ነገር ግን ይህን ሚኒስትር መስሪያ ቤት በእምነታቸው ሙስሊም የሆኑ ሰዎች ብቻ በተደጋጋሚ ለምን እንመሩት ይደረጋል?  እውን ከእነሱ ውጪ የመምራት አቅም ያለው ሰው ጠፍቶ ነውን? ይህ ሀገሪቱ አለኝ የምትለው የባህልና የታሪክ አሻራን ለቀጣይ ትውልድ የሚያስተላልፍ ግዙፍ ተቋም ለመምራት ለምን የገዥው ፓርቲ ተመራጭ መሆን አስፈለገ?  መንግሥት የሚያስቀምጠው ፖሊሲ እና ስትራቴጄካዊ አቅጣጫዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚችል ሰው እውን ጠፍቶ ይሆን ? እጅግ የካበተ እውቀት ያላቸው ሥማቸው እጅግ የተከበሩ ብዙ ሰዎች ያሏት ሀገር እንዴት ይህን ያህል የግለሰብ ፤ የማሕበረሰብ ፤ የእምነት ተቋማት እና የሀገርን ታሪክና ትውፊት  ያለውን አጉልቶ ፤ የሌለውን አውጥቶ ለዓለም ማሕበረሰብ የማስተዋወቅ ተልዕኮ ያለውን ተቋም እንዲህው አንዷን ኢንጂነር አንስቶ ሚኒስትር እንዴት ይደረጋል? ኮንስትራክሽን ሚኒስትርን በአቶ መኩሪያ ኃይሌ አንዲመራ እያደረጉ ባህልና ቱሪዝምን እንዴት በኢንጂነር ሙያ ያለው ሰው ይመራዋል? ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ሙሳ በሙያቸው ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት የመሰሉ ተቋማት ላይ ቢመደቡ ውጤታማ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል ፤ ነገር ግን ባሕልና ቱሪዝም ባለቤት የሌለው ቤት ይመስል የሀገሪቱን ባሕል ፤ ቱሪዝም ፤ ትውፊት ፤ እና የሀገር ገጽታን በሚመለከት ትልቅ ተልዕኮ ያለውን ተቋም በገዥው ፓርቲ ሥር ያሉትን ድርጅቶች የሚኒስትርነት ቦታ ስብጥሩን ለማስተካከል ሲባል እንዴት መሰረታዊ መስፈርቶች ሳይሟሉ አንድን ሰው በሚኒስትርነት ደረጃ ይመደባል? 




የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዋጅ ቁጥር 471/98 የባህልና ቱሪዝም በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ሦስት ሚኒስትሮችን አስተናግዷል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፤ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወ/ሮ ፈቲያ ዩሱፍ የሚመራ ሲሆን የቀድሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአሁኑ በግብጽ የኢትዮጵያ ኢምባሲ አምባሳደር መሐመድ ድሪር እና  የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንትና ሚኒስትር ዴኤታ መሐመድ ጋአስ ይመራ ነበር፡፡ በባለፈው አምስት ዓመት አምባሳደር መሐመድ ድሪልን አቶ አሚን አብደልቃድር ተክተዋቸዋል፡፡ አሁን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩን አቶ አሚን አብደልቃድርን የተኳቸው ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ሙሳ ሲሆኑ በአፋር ክልል የተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ በትምህርታቸው በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ በተቋማዊ አመራር የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም አብዛኛውን ጊዜ ከእነዚህ በግንባር ድርጅቶች ከማይመሩ ተቋማት አንዱ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህው ከኢህአዴግ አጋር ድርጅት አንዱ አፋር ተነስቶ አፋር ተሹሟል፡፡ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ የአፋር ክልል አደጋ መከላከልን ይመሩ የነበሩ ሴት አመራር ናቸው፡፡ በእርግጥ ኢንጅነር የባህልና ቱሪዝም ሴክተር መሪ ሲሆኑ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆን ይሆናል፡፡ ሊያውም ኮንስትራክሽንን በአቶ ስታስመራ የኖረች ሀገር፡፡ ችግሩ ግን ይህ አይደለም፡፡  ከእሳቸው በፊት የነበሩት አቶ አሚን አብዱልቃድር ምንም እንኳን ሙስሊም ቢሆኑም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተቀራርቦ በመስራት በኩል ባለፉት ዓመታት ብዙም ችግር አልተስተዋለባቸውም፡፡ ያም ሆኖ እስከአሁን ባለው ሂደት 75 በመቶ በላይ እሴቶቿ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ጉልህ ሚና እየተጫወተ ባለ ሀገር ላይ እሷን ሊወክል የሚችል ሹመኛ አለመኖሩ ሆን ተብሎ ይሆን እስኪያስብል ችግር ሆኖ መዝለቁ ቀጥሎዋል፡፡  ሴት የማይገቡባቸው ገዳማት መስህቦቿ የሆኑ፤ ሴት የማይረግጥባቸው በርካታ ኢስላማዊ መዳረሻዎችን ሀብቴ ናቸው የምትል ሀገር ይህንን ሀብት እንዲመሩ ሴት ሾማለች፡፡ ኢትዮጵያ ቢቻል የሚያስፈልጋት ሴኩላር የሆነ የሴክተሩ መሪ ነበር፡፡ ይህ የትኛውንም ወገን አያሸማቅቀውምና፡፡ ምናልባት ቀጣዩ የዴኤታዎች ሹመት ካላስታረቀው በስተቀር፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዚህ ቀደምም በቀድሞ ሚኒስትር አምባሳደር መሐመድ ድሪር እና በቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ መሐመድ ጋአስ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ መቆየቱ ይታወሳል። የሁለቱ ሚኒስትሮች ውዝግብ ተከትሎ ስለተፈጠረው ችግር ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ዳውድ በወቅቱከዜጋም ከጋዜጣም የሚደበቅ ነገር ስለሌለ እኔም ከመናገር ወደ ኋላ የምልበትና የሚያስፈራኝ ነገር የለምብለው ነበር፡፡ ጨምረውም ‹‹ ዋናው የሚያጣላንም ጉዳይ የሰው ኃይል ምደባ የመሆኑም ሚስጢር ይሄው ነው። ወደ ተቋሙ ጠንካራ ሰው እንዲመጣ አይፈለግም። በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ስር ያሉ የተቋማት ኃላፊዎች ማለትም ብሔራዊ ቴአትር፣ ቤተ መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት፣ የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ቅርስና የዱር እንስሳት ጥበቃ አሉ። እነዚህን ተቋማት የሚመሩት ጠንካራ ሰዎች አይደሉም›› ብለዋል። አቶ ዳውድ በጊዜው ተቋሙን አስመልክተው እንደተናገሩት  ‹‹በጨለማ ተደብቀው የመሾም ተግባር ነው ያለው። ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮች አሉ። ተቋማቱን የሚመሩ ኃላፊዎች መሾም ያለባቸው በአቅምና ሕግ በሚጠይቀው መመዘኛ እና በሙያም በፖለቲካም ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው›› ብለው ነበር ።

ይህን ተቋም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ታሪክ፣ባህላዊ ቅርሶች እና ቋንቋዎች ጠናታቸውንና ጽሁፎቻቸው መዳበራቸውን፤ በባህላዊ ተጽእኖ ሳቢያ ማህበራዊ እድገቶችን የሚያጓትቱ አመለካከቶችን እምነቶችንና ልማዳዊ አሰራሮችን የመለወጥ ስራ መሰራቱን እንዲሁም የባህል ዘርፉ ልማታዊ አስተዋጽኦ መስፋፋቱን፣  የመገናኛ ብዙሃን ለሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ሠላምና ልማት የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ መሆናቸው፣  ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ የሚተላለፉበት መንገድ መቀየሱንና ተግባራዊ መሆኑን፣ ለአገሪቱ የቱሪዝም ምንጭነት የሚያገለግሉ አስፈላጊ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን እና የቱሪዝም መስህቦችና መልካም ገፅታዎች መተዋወቃቸውን፣   የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ቦርዶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባበቡ  መወጣታቸውን፣ ሚኒስትሩ  የሚከታተላቸውና የሚቆጣጠራቸው መ/ቤቶችን ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣  ስትራቴጂዎች እና ዕቅዶች በአግባቡ በሥራ ላይ መዋላቸውን፣ ተቋሙ እንዲከታተላቸው እና እንዲቆጣጠራቸው ለተመደቡ መ/ቤቶች በህግ የተሠጡ ስልጣንና ተግባር በትክክል እየተተገበሩ መሆኑን፤ የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡና በውጤታማነት በስራ ላይ ማዋላቸውን እና ሴክተር ዘላል ለሆኑ ስራዎች ተገቢውን ትኩረት ሠጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን፣ መከታተልና መቆጣጠር ነው፡፡

1 comment: